አርዕስተ ዜና

የህዳሴው ጉዞ ሌላው ማሳያ

20 Nov 2017
5412 times

 ተካ ጉግሳ ከኢዜአ

በአገራችን ያለው የልማት እንቅስቃሴ ከዜጎቹ አልፎ የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ መሳብ ከጀመረ ሰነባብቷል።

እያደገ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አገራችን ለያዘችው የኢንዱስትሪ ልማት መፋጠን የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አያጠራጥርም።

ራእይ ያለው መንግስትና ምቹ የልማት ፖሊሲዎች ፣ የተረጋጋ ሰላም፣ሰፊ የሰው ጉልበትና ምቹ መልክአ ምድር አገራችን ይበልጥ እንድትመረጥ እያደረጋት ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ከተለያዩ የአገራችን ክልሎችና ከፌዴራል የተውጣጡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሙያዎች መቐለ ላይ ተገናኝተው የምክክር መድረክ አካሂደዋል።

በምክክር መድረኩ በአገራችን ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና የውጭ ፍሰት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንቅስቃሴና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮቸ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሔደዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ገብረየሱስ እንደገለጹት የጋራ ምክክር መድረኩ በአገራችን የተጀመረውን የተቀናጀ ኢንቨስትመት ለማሳደግ  ያግዛል ብለዋል።

በአገራችን ያለው ልማታዊ መንግስት ያወጣቸው ፖሊሲዎች ለኢንቨስትመንት እድገቱ ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው ሲሉም  ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ።

አያይዘውም “በአገሪቱ ያሉት ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችና ሌሎች ማበረታቻዎች ለእድገቱ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።’’

በምክክር መድረኩ ላይ የመወያያ ርእስ የነበረው የአገራችን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ያደገበትና ከሁለት ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲታይ ያመጣው ለውጥ ምን እንደሚመስል በአሃዝ የተደገፈ መረጃ ቀርቧል።

በኮሚሽኑ የእቅድና  ስትራቴጂክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ ጉርሙ ባቀረቡት ፅሁፍ ለአመታት ሞዛምቢክና ታንዛኒያ ይመሩት የነበረው የምስራቅ አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፍሰት ካለፈው አመት ጀምሮ እየተቀየረ በመምጣት መሪነቱን ለአገራችን ማስረከቡን ገልጠዋል።

እስከ 2008 ዓም ድረስ 3 ነጥብ 27 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ አገራችን ይገባ የነበረው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በ2009ዓም ወደ 4 ነጥብ 17 ቢሊዮን ዶላር ማደጉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በአገራችን የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ካላቸው አገራት መካከል ቻይና፣ ህንድና ኔዘርላንድ  ቀዳሚዎቹ  ናቸው።

እየታየ ላለው የኢንቨስትመንት እድገት መንግስት ከኢንዱስተሪ ፓርኮች ግንባታ ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች በመውሰዱ የተገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።

እስከ አሁን ድረስ በተገነቡት ስምንት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 17 የውጭ ባለሃብቶች  ወደ ስራ መግባታቸው ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

እነዚሁ ባለሃብቶች 1ነጥብ 48 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍሰት ይዘው ወደ አገራችን መግባታቸው የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጠናከርን ያሳያል ተብሏል።

በተለያዩ የአለም አገራት በሚካሄዱ ፎሮሞች በአገራችን ያሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች የማስተዋወቅ ስራ በመሰራቱ  ውጤቱ እንደተገኘም በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

ከየክልሉ የመጡት ተሳታፊዎችም በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሚታዩት ችግሮችና መሻሻል በሚገባቸው አሰራሮችና ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር ስላለው ግኑኝነት አስመክተው የጋራ ውይይት አካሂደዋል።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቅርንጫፍ ፕሮጀክቶች ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ታዬ እንደገለጹት የውጭ ባለሃብቶቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መግባት አገራችንን በተለያዩ አገራት ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

በዋነኛነትም ሰፊ የገበያ ትስስር በመፍጠር ፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ጠቀሜታው  የጎላ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግስት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መላኩ አለበል በአገራችን እያደገ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለህዳሴአችን ጉዞ የማንቂያ ደወል ነው።

የውጭ ባለሃብቶች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በማሳደግ የአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚያጎለብትና የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ባይ ናቸው።

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፈቃድና ፑል አስተዳደር የስራ ሂደት መሪ አቶ ሙላቱ ዱጎ በበኩላቸው የውጭ ባለሃብቶቹ ይዘዋቸው የሚመጡት ቴክኖሎጂዎችና የስራ አማራጮች ለአገራችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

በትግራይ ክልል አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ታረቀ ከስድስት ወራት በፊት ግንባታው የተጠናቀቀውና 15 ሼዶች ያሉት የመቐለ ኢንዱስተሪ ፓርክ እስከ አሁን ድረስ 80 በመቶ የሚሆነው በውጭ ባለሃብቶች ተይዟል ብለዋል።

ቀሪው 20 በመቶ የሚሆነው በአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲያዝ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንና ወደ ፓርኩ ለሚገባ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ሊያሟሉዋቸው በሚገቡት ቅድመ ሁኔታዎች  በፌዴራል መንግስት ማሻሻያ  እንዲካሄድባቸው እየተሰራ ነው ይላሉ።

ወደ ፓርኩ የሚገቡት ባለሃብቶችን የመለየትና ግንዛቤ የማስጨበጭ ስራ እየተካሄደ መሆኑንም  አቶ ጥላሁን ይናገራሉ።

እስከ አሁን ባለው  ጊዜ ውስጥ  15 የሚሆኑ አቅም ያላቸው ባለሃብቶች የተለዩ ሲሆን ከአንዳንዶቹም ጋር ውይይቶች በመካሄድ ላይ ሲሆኑ በጎ ምላሽ የሰጡም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ከፀሃፊነት ጀምረው በተለያዩ ቦታዎች ሰርተዋል። አገራችን የያዘችውን የልማት አቅጣጫም በሚገባ የተረዱት መሆናቸው ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ወደዚሁ ስራ ለመግባት አቅም ስለፈጠሩም ጥያቄው ሲቀርብላቸው ለአፍታም አላቅማሙም - ወይዘሮ ብዕዱላ ገብረጊዮርጊስ።

ወደ ኢንዱስተሪ ፓርክ ገብተው ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ባለሃብቷ ተናገረው በመንግስት የተዘጋጀውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም አቅም ያለውን የአገር ውስጥ ባለሃብት መፈጠር  እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል።

እኛም በኢንቨስትመንት ዘርፉ እየታየ ያለውን እድገት ሌላው የህዳሴአችን ማሳያ በመሆኑ ባለሃብቶች የተመቻቸላቸውን እድል ተጠቅመው ራሳቸውንና አገራቸውን ለመጥቀም መነሳሳት አለባቸው መልእክታችን ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን