አርዕስተ ዜና

አወዛጋቢው ጉባኤ

12 Nov 2017
6742 times

ይሁኔ ይስማዉ

ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጠዋት ላይ የተለያዩ ክለቦች፤ አመራሮች፣ የክልሎች እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች፣ የአሰልጣኞች ተወካይ፣ የዳኞች ተወካይና ሌሎች  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ የስም ምዝገባ እየተካሄደ ነው።

በተመሳሳይ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጉባኤው በሚካሄድበት መሰብሰቢያ አዳራሽ  መግቢያ ላይ መግቢያ ባጅ እየወሰዱ ናቸው።

ከጉባኤው መጀመሪያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ጉባኤውን እንዲዘግቡ የተጋበዙ መገናኛ ብዙኃን ውስን መሆናቸው ጥሪው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንን ያገለለ ከመሆኑም በላይ ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው የክልሎች መገናኛ ብዙኃን አለመጋበዛቸው አንዱ አስገራሚ ጉዳይ ነበር።

ጉዳዩን የሰማው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፌዴሬሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ያደረገበት መንገድ አግባብነት የሌለው በመሆኑ እንዲስተካከል ለፌደሬሽኑ አሳውቋል።

የቁጥር ገደብ የተጣለባቸውም ሆነ በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው ያልተካተቱት የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ለምን አንገባም እያሉ የፌደሬሽኑን አመራሮች ቢጠይቁም ምላሽ ሳይሰጣቸው በመጉላላታቸው አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠው ወደ መጡበት ተመልሰዋል።

ብዙዎቹ ተስፋ ሳይቆርጡ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በድንገት ሁሉም እንዲገቡ በመፈቀዱ ወደ ጉባኤው አዳራሸ ገብተዋል፡፡

በትርምስ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ይጀመራል ከተባለበት 1 ሰዓት ዘግይቶ ነበር የተጀመረው።

በጠዋቱ መርሐ ግብር ከ3 ሰዓት ከ 45 ደቂቃ ጀምሮ ለ5 ደቂቃ የጉባኤውን አጀንዳ ለማጽደቅ ቀጠሮ ቢያዝለትም በሁለተኛ ቀን ጠዋት ላይ ይደረጋል ተብሎ በእቅድ የተቀመጠው አዲሱን ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ የመምረጡ ጉዳይ ሰፊ ክርክርና የውይይት ጊዜ ወስዷል።

የክርክሩ መነሻ ደግሞ የእጩዎቹ ምርጫ ይራዘም ወይስ በዚሁ ጉባኤ ላይ ይመረጥ የሚለውን ለመወሰን ሲሆን በ5 ደቂቃ ይጠናቃቃል የተባለው ጉዳይ ትልቅ መከራከሪያ ሆኖ ከ 2 ሰዓት በላይ ጊዜ ወስዷል።

የአጀንዳው መጽደቅ ሰባት ያህል ርእሰ ጉዳዮች ቢኖሩትም ከ2 ሰዓት በላይ የፈጀው ክርክር ምርጫውን በተመለከተ ብቻ ነበር።

ከጉባኤው አባላት አንዱ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የምርጫው መራዘም ለምን እንደ አማራጭ እንደቀረበ ማብራሪያ እንዲሰጥ በመጠየቃቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻና ሌሎች ስራ አስፈጻሚዎች ምላሽ ሰጥተውበታል።

የምርጫው መራዘም ክልሎች በስራ አስፈጻሚነት የሚያቀርቧቸው እጩዎች አንድ ብቻ መደረጉ ስህተት በመሆኑና አስመራጭ ኮሚቴ ከተፈለገም ያንን ለማከናወን  መሆኑን ለተሳታፊዎች አስረድተዋል።

ምላሽ ከተሰጠ በኋላም አሁንም ክርክሩ ሊቆም ባለመቻሉ 68 በ 62 በሆነ የአብላጫ ድምፅ የምርጫው ጊዜ እንዲይራዘም ተወሰነ።

ምርጫው በአብላጫ ድምጽ እንዲራዘም ሲወሰን ሌላ አዲስ ክስትት አሳይቶ አልፏል፡፡ ይህም ስራ አስፈጻሚዎቹ ሳይግባቡ የተግባቡ ለመምሰል ያደረጉት ማስመሰል እርስ በርስ መተማመመን እንደሌላቸው ያሳየ ክስተት ነበር።

በምክትል ፕሬዝዳንቱና በአንዳንድ ስራ አስፈጻሚዎች በኩል በድምጽ ብልጫ ይራዘም የሚለው ሀሳብ ትክክለኛነቱ አጠራጣሪ በመሆኑ እንደገና ይቆጠር የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።

ይሁን እንጂ የጉባኤው መሪ አቶ ጁነዲን ባሻ ቆጠራውን ያደረኩት እኔ አይደለሁም፣ቆጠራውን የተመረጡ ሰዎች በግልጽ ያከናወኑት ነው በማለት በጥቂት ስራ አስፈጻሚዎች ድጋሚ እንዲደረግ የቀረበውን ሀሳብ ውድቅ አደረጉ።

ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ተላከ በተባለው ደብዳቤ ምክንያትና ከዚያ ፊትም ባለፉት አራት ዓመታት በስራ አስፈጻሚነት የገቡት የፌዴሬሽኑ ስዎች እርስ በእርስ መስማማቶች እንደሌሉ በመገናኛ ብዙሃንና በፌደሬሽኑ ሰዎች ሲነገር የነበረው እውነት ለመሆኑ ፍንጭ ጥሎ አልፏል።

በዚህ ወቅት በስራ አስፈጻሚች መካከል ስላለው አለመግባባት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትና ምክትላቸው እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሀሳብ ሰንዝረዋል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በስራ አስፈጻሚዎች በኩል ሁሉም የራሱ  ሀሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚደረግ የሀሳብ ክርክር እንጂ ግጭት የለም ሲሉ ጠዋት ላይ ተናግረው ነበር።

ከሰዓታት ቆይታ በኋላ የፌዴሬሸኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን በሻ ደግሞ እርስ በእርስ አለመግባባቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

በሁለተኛው ቀን መርሃ ግብር የፌደሬሽኑ መተዳደሪያ የማሻሻያ ረቂቅ ደንብና የተራዘመው ምርጫ በምን መልኩ፣የት፣ መቼ መከናወን እንዳለበትና ከሁሉም በላይ ደግሞ የምርጫውን ሁኔታ የሚከተታሉ አስመራጮችን የመምረጡ ጉዳይ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚሁ መሰረት የስራ አስፈጻሚዎችና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ከ45 ቀናት በኋላ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንዲካሄድ ተወሰነ።ይሁን እንጂ የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ሳይነሳና እልባት ሳያገኝ የጉባኤው አባላት ተበትነዋል።

የአስመራጭ ኮሚቴውን ምርጫ በተመለከተ አማራ ክልልን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ ተካ አስፋው አስመራጭ ኮሚቴው የግድ መመረጥ እንደነበረበትና ገለልተኛ አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምርጫው እንዲካሄድ ካልተደረገ የቀኑ መራዘም አስፈላጊ አልነበረም ሲሉ  ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የደቡብ ክልል እጩ የሆኑት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አስመራጭ ኮሚቴ መምረጥ እንደማይቻል ተናግረዋል።"አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ አሁን እየተሰራበት ያለው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አይፈቅድም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው አስመራጭ ኮሚቴ ለምን እንዳልተመረጠ ለቀረበላቸው ጥያቄ ''የጉባኤው አባላት ጠቅላላ ጉባኤው አልቋል ሳይባል ነው የተበተኑት'' ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ የሆነው በዋናነት አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚፈልጉና የማይፈልጉ በሁለት ጎራ የተከፈሉ አስተሳቦች በመፈጠራቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት።

አቶ ጁነዲን በጉባኤው ማጠቃለያ ዕለት ከተቻለ ከሰዓት በኋላ አባላቱ እንዲሰባሰቡ በማድረግ የአስመራጭ ኮሚቴው ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል ቢሉም ጉዳዩ ሳይቋጭ የጉባኤው አባላት ተበትነዋል።

በጉባኤው ሁለተኛ ቀን ውሎ የፊፋ ተወካይ የነበሩ ሲሆን የአስመራጭ ኮሚቴውን አለመመረጥ ለፊፋ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ከ45 ቀናት በኋላ ይደረጋል የተባለው ምርጫ ቀደም ብሎ አዳዲስ ጉዳዮች ይሰሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ሀሳብና አስተያየት ለመስጠት ይደረግ የነበረውን ፉክክር ስመለከት አንደኛ ክፍል እያለሁ መምህራችን ጥያቄ ጠይቀው የማውቃት ከሆነ እድሉን አግኝቼ መልሱን ለመመለስ ከመቀመጫዬ ከፍ በማለት እጄን ዘርግቼ ላይ ታች ሳራገብ የነበረውን ሁኔታ እንዳስታውስ አድርጎኛል።

ሁለተኛው ጉዳይ  ከአንደኛ ክፍል ቆይታዬ ጋር ተያይዞ የመጣልኝ  ሀሳብ ለመናገር  የነበረኝ ድፍረት ሲሆን፤ ይኽው ድፍረት አይሉት ልጅነት በፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት በኩል ታይቷል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ ጠቅላላ ጉባኤው መጀመሪያ ሊደረግ ታስቦ ከነበረበት ቦታ በተለያዩ ሁኔታዎች የተቀየረበትን ምክንያት ሲያብራሩ የአገርን ባህልና ወግ በሚፃረር መልኩ ሐሳባቸውን የገለፁበት ሁኔታ ታይቷል።

ሶስተኛው ጉዳይ በልጅነት እድሜ የሚደረግውን አይነት ቀልድ ይሁን ቁም ነገር በማይታወቅ መልኩ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ባለፉት አራት ዓመታት የነበረው ስራ አስፈጻሚ እግር ኳሱን ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ አምጥቶታል በማለት የገለጹበት መንገድ ነው።

ጉዳዩን ያነሱት በተለይ ከእግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር ጋር አያይዘው ሲሆን በፊት በፊርማ ወቅት ይከፈል የነበረውን አሁን በወርሃዊ  ደመወዝ  እንዲለወጥ በማድረግ መንግስት ከግብር  ማግኘት ያለበትን ጥቅም በአግባቡ እንዲያገኝ አድርገናል ብለዋል።  

በእርግጥም  የተጨዋቾች ክፍያ አሁንም የቁጥጥርና የክትትል ክፍተት ያለበትና ገና ሰፊ ስራ የሚጠይቅ ቢሆንም ወርሃዊ ክፍያ መደረጉና ተጨዋቾች የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉ መደረጉ የሚያስመሰግን ነው።

የዝውውር ጉዳይ ግን አሁንም ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በደንብ ሊታይ እንደሚገባ የደደቢት እግር ኳስ ክለብን ወክለው በጉባኤው ላይ የታደሙት አቶ ሚካኤሌ አምደመስቀል አሳስበዋል።

ለደደቢት እግር ኳስ በ75 ሺህ ብር ወርሃዊ ክፍያ አልጫወትም በማለት ለሌላ ክለብ  በ23 ሺህ ብር የፈረመ ተጨዋች አለ።ይሄ የሚያሳየው በብዙ ክለቦች በኩል አሁንም ያልጠራና ትክክለኛ ያልሆነ የተጨዋቾች ዝውውር እንዳለ ነው ሲሉ ነበር አቶ ሚካኤል የተናገሩት።

በተጨዋች ዝውውር ላይ አሁንም አሰራሩን በአግባቡ ተግባራዊ የማያደርጉ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ተጨዋቾች ወርሃዊ ደሞዝ እንዲያገኙ መደረጉ ብቻውን እግር ኳሱን ፕሮፌሽናል ያደርገዋል ወይ የሚለው ዋና ሀሳብ ነው።

የአገሪቱ ክለቦች አደረጃጀት፣ አሰለጣጠን ፣የተጨዋቾች ምልመላና በእነዚህ ውሰጥ የሚካተቱ ዝርዝር ሀሳቦችና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ሳይሰሩ እግር ኳሱን ሙያዊ ስነምግባሩን በጠበቀ መንገድ እንዲመራ አድርገነዋል ማለቱ ከቀልድነት ያለፈ ቦታ አይኖረውም።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን