አርዕስተ ዜና

ሐብትን መጠቀም እስከ ምን ድረስ?

12 Nov 2017
5043 times

 በነፃነት አብርሐም /ኢዜአ/

የሰው ልጆች ከእፅዋት ጋር ያላቸው ቁርኝት እጅግ ጥብቅ ነው። የእያንዳዱ ሰው የመኖር ህልውና በእስትንፋሱ ላይ አንደመመስረቱ፤ ያለ እፅዋት ምድራችን ለሰው ልጆች መኖሪያ ልትሆን አትችልም። ከህመማችን ለመፈወስ የምንጠቀማቸው መድሃኒቶች፣ የቤት ውሰጥ መገልገያዎች መዋቢያዎች ወ.ዘ.ተ. ሁሉም ምንጫቸው እፅዋት ነው። አብዛኛውን ጊዜ የእፅዋት ስም ሲጠራ ቶሎ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው እንጨት ወይም ቅጠል ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ስንቶቻችን ስለ ጎማ ዛፍ እና ተያያዥ ጥቅሞቹ እናውቃለን?

የጎማ ዛፍ ጎማን ለማምረት የሚረዳ "ላቴክስ" የሚባል ፈሳሽ የያዘ ሲሆን፤ ይህ ፈሳሽም በኢንዱስትሪ ተቀነባበሮ በሚፈለገው ቅርፅ የጎማ ቁሳቁስ ይመረትበታል። ላቴክስን በሌላ ጥሬ ዕቃ የመተካት አማራጭ ውስን በመሆኑ ዋጋው በዓለም አቀፍ ገበያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እንዲል አድርጎታል። የጎማ ዛፍ ከተተከለ በኋላ ለምርት እስከሚደርስ ስድስት አመት የሚወስድ ሲሆን፤ተክሉ ለምርት ደርሶ ለ30 ዓመታት አገልግሎት ከስጠ በኋላ ግንዱ የቤትና የቢሮ ዕቃዎችን ለመስራት ያገለግላል።

በዓለም አቀፍ የጎማ ዛፍ ገበያ  ቬትናም ፣ ታይላንድ፣ ኢንዶኔዥያ ፣ ሕንድ እና ማሌዥያ ቀዳሚ ሲሆኑ፤ ከአህጉረ አፍሪካም ኮትዲቯር፣ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያና ካሜሮን ተጠቃሾች ናቸው።

በየዓመቱ ከውጭ አገራት እስከ 6ሺህ ቶን ጎማ ወይም ከ2 ቢሊዮን በላይ ብር ለጎማ ግዢ ወጪ የምታደርገው ኢትዮጵያ በምድር ወገብ ቀጠና በመገኘቷና ተክሉ በኢትዮጵያ እንደሚገኝ ከተረጋገጠ ከመቶ ዓመት በላይ ቢሆንም፤ ምርቱን በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ የማዋሉ ጉዳይ ግን የተሰራው ስራ ዝቅተኛ ነው።

አገሪቷ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አንጻር የተከሰተውን የጎማ  ፍላጎት ለሟሟላት ምርቱን ከውጭ ማስገባት ላይ ጥገኛ ናት።በተለይ ወደ አገሪቱ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ጋር ተያይዞ የጎማ አቅርቦትን በውስጥ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረትም በበቂ ደረጃ ምላሽ አላገኘም።

በኢትዮጵያ ለጎማ ዛፍ ልማት ምቹ  የሆነ  መሬት እንዳለ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች ማረጋገጥ ቢቻልም፤ ዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሚደግፍ መልኩ እየተሰራበት አለመሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ይገልጻል።

ለዘርፉ በጀት አለመኖር፤ በዘመናዊ መንገድ ምርቱን ለማልማት፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ በቂ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመኖር ለዘርፉ  አለማደግ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

በኢንስቲትዩቱ የደን ሃብት አጠቃቀም ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አበጀ እሸቴ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የጎማ ዛፍን ማልማት የሚያስችል 90 ሺህ ሄክታር መሬት ያለ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው 4 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው።

"ዘርፉ ከሌሎች የደን ሴክተሮች የተሻለ አትራፊ ቢሆንም  በመስኩ የተሰማሩ የባለሃብቶችና የአርሶ አደሮች ቁጥር ግን አናሳ ነው" ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ለምርቱ ምቹ በሆኑ እንደ ቴፒና በበቃ ያሉ ሞቃታማና እርጥበታማ አካባቢዎች በ3 ሺህ 848 ሄክታር በለማ የጎማ ዛፍ በዓመት አስከ 243 ሜትሪክ ቶን ላቴክስ እየተመረተ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ወደ 10 ሺህ ቶን ለማሳደግ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

"ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች ምርቱን በማልማት ሂደት አንዲሳተፉ እድሎችን ከማመቻቸት አንጻር ሰፊ ክፍተት አለ" ያሉት ዶክተር አበጀ፤ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመረዳት ሁሉም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ምርቱን ለማሳደግ የተሻለ የዛፍ ዝርያዎችን በማቅረብ አቅም ያላቸው አርሶ አደሮችንና ቦታዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግዋል።

ዘርፉን በምርምር ለመደገፍ የተሰሩ ስራዎችም እጅግ ውስን ናቸው። ባላቸው ውስን መሬት የጎማ ዛፍን የኢኮኖሚ ዋልታቸው ካደረጉ  አገራት ጀርባ ያለው ዋነኛ ሚስጥር ዘርፉን በምርምር መደገፋ መቻላቸው ነው። በመሆኑም በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ የቤት ስራ ይጠበቃል።

የጎማ ዛፍ ልማትን በአገር ውስጥ ማስፋፋት ቢቻል የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱም በላይ  ለስራ እድል ፈጠራ እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።ከዚህ በተጨማሪ ለአካባቢ እንክብካቤና አረንጓዴ ልማት የጎላ ፋይዳ አለው አለው።

ወደ ጎማ ልማት ለሚሰማሩ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች ክትትልና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። እነዚህ አልሚዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ “ላቴክስ” አቀነባብሮ ወደ ምርት የሚቀይር ፋብሪካ ማቋቋም ቅድሚያ ተሰጥቶት መሰራት አለበት፤ ይህን በማድረግ በኩል መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ ስለማይኖር የግሉ ዘርፍን ተሳታፊ የሚያደርጉ በሮች መከፈት አለባቸው።

በተለይ ዘርፉ ትዕግስት የሚጠይቅ ኢንቨስትመንት በመሆኑ የተለያዩ የማበረታቻ ማዕቀፎችን ማበጀት መልካም ነው።የሌሎች አገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህን ነው።የጎማ ዛፍን የማለማት ሂደት ዘመናዊ አሰራርን ተከትሎ አዋጭ ዘርፍ እንዲሆን በምርቱ የካበተ ልምድ ያላቸው አገራትን ተሞክሮ በመቀመር በአገር ውስጥ ማስፋት ይገባል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን