አርዕስተ ዜና

ሰላም - የመገናኛ ብዙኃን ትርፍ ወይስ ኪሳራ?

11 Nov 2017
7690 times

በእንግዳ መላኩ / ኢዜአ/

የዛሬ 23 ዓመት ወርሃ ህዳር መጨረሻ፡፡ መላ የሀገሪቱ ዜጎች በራሳቸው ፍላጎት ይወክሉናል ብለው የመረጧቸው ተወካዮቻቸው አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ጣሪያ ስር ተጠልለዋል፡፡ በአንድ ጣሪያ ስር ያሰባሰባቸው ጉዳይ ደግሞ መላው የሀገሪቱ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው የቀጠናውን ግዙፍ ወታደራዊ ስርዓት ከገረሰሱ በኋላ በተከፈለው መስዋዕትነት የተገኘውን ድል በሰላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ማጀብ የሚያስችላቸውን የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ ማጽደቅ ነበር፡፡

በህገ መንግሥት ጉባዔው ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የጸደቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰብ መብቶች እንዲከበሩ፣ የጾታ፣ የሃይማኖትና የባህል እኩልነቶች ያለአንዳች ልዩነት እንዲረጋገጡ፣ የጋራ ተጠቃሚነት፣ መብትና ነጻነቶች  በጋራ እንዲጎለብቱም ትልቁን  በር ከፍቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዛሬ 23 ዓመት የሰነቁትን በመላ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የማስፈን፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የማፋጠን፣ ዜጎች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነጻ ፍላጎታቸው፣ በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፍቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡  በዚህም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተመሰከረላቸው ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለአመታት በወሬ ነጋሪ ብቻ በሩቁ የሚያውቋቸውንና የሚናፍቋቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን መለማመድ ጀምረዋል፡፡ በብሔራቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው፣ በፆታና በሐይማኖት ልዩነታቸው፣… አንገታቸውን እንዲያቀረቅሩ ተገደው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለምንም ልዩነት ወግ፣ ቋንቋና  ባህላቸውን የሚያዳብሩበት፣ ከሀገሪቱ ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙበት፣ ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያንሸራሽሩበት፣ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ተዘዋውረው የመስራትና በመረጡት አካባቢ መኖር፣… መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቶላቸዋል፡፡

ምንም እንኳን በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም በወቅቱ የነበሩት መገናኛ ብዙሃን ግን ቢያምርም ቢከፋም የወቅቱን ሥርዓት ፕሮፓጋንዳ ከማስተጋባት በዘለለ የህብረተሰቡን ብሶት ነቅሰው የሚያወጡ፣ የስርዓቱ ብልሹ አሰራር እንዲስተካከል የሚጥሩ እንዲሁም ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያብብ፣ የዜጎች  እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ተግተው የሚሰሩ አልነበሩም፡፡

 

ልክ እንደ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ነጻነቶች ሁሉ የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ነጻነት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያገኘውም  በዚሁ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሶስተኛው ምዕራፉ ሽፋን ከሰጣቸው አበይት ጉዳዮች መካከል አመለካከትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ስር ባሉ ንዑሳን አንቀጾች በግልጽ እንደተቀመጠው “የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የስነ ጥበብ ፈጠራ ነጻነት” ከመረጋገጡም ባሻገር ባለፉት ሥርዓቶች በመገናኛ ብዙኃን ስራዎች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው ቅድመ ምርመራ ተከልክሏል፤ መገናኛ ብዙኃን የህዝብን ጥቅም የሚመለከቱ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበት እድልም ተረጋግጧል፡፡

ይህም ዜጎች ሃሳባቸውን እንዳያንሸራሽሩና በመገናኛ ብዙኃን  የአሰራር ነጻነት ላይ ተጋርጠው የነበሩ ተቋማዊና መዋቅራዊ መሰናክሎችን በማስወገድ በህገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች እንዲከበሩና ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ዘብ መቆም ሚችሉበትን ምህዳር ለማስፋት  ትልቁን በር ከፍቷል፡፡

ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው የመገናኛ ብዘኃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 በመገናኛ ብዙኃን የአሰራር ነጻነት ላይ ሳንካ የነበሩ ተቋማዊና መዋቅራዊ አሰራሮች እንዲስተካከሉ በማድረግ በነጻ ሃሳብን የመግለጽ ባህል እንዲጎለብት አድርጓል፡፡ መገናኛ ብዙኃን የተቋቋሙበትን መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ዓላማ ማሳካት የሚችሉትም ሆነ የሀገሪቱ ዜጎች በነጻ መረጃና  አስተያየት የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማስተላለፍ መብት የሚረጋገጠው ጤናማ የመረጃ ስርዓት ሲሰፍን በመሆኑ አዋጁ በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን እድገት ውስጥ የድርሻውን ተወጥቷል፡፡

የሀገራችንም ሆነ የሌሎች ሀገራት መገናኛ ብዙኃን ግጭቶች እንዳይከሰቱና የሰላም መሰረት እንዲሰፋ፣ በህዝቦች መካከል  ፍቅርና አንድነት እንዲጎለብት፣ የዜጎችን የስራ ባህል በማሳደግ ከድህነት ራሳቸውን አርነት እንዲያወጡ በመቀስቀስ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ እንዲሁም  የተጠያቂነት ስርዓት ስር እንዲሰድ የማድረግ አበርክቷቸው በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡

በዚያው ልክ መገናኛ ብዙኃን በህግ ጥላ ስር ሆነው ለተቋቋሙለት ዓላማ የማይሰሩ ከሆነ በአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጥላ ማጥላት የሚያስችል አቅምም አላቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁለት አስርት ዓመታት ብዙም ባልራቀ ጊዜ ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን ቀስቃሽነት በጎረቤታችን ሩዋንዳ የተከሰተውን አስከፊ ሰብአዊ እልቂት ማስታወሱ በቂ ነው፡፡

ሩዋንዳ እ.ኤ.አ ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ 1994 ባሉት 100 ያህል ቀናት ውስጥ በተካሔደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከአምስት እስከ 10 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን አጥታለች፡፡ በዚህ ዘመቻ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊ የፖለቲካ ድርጅቶች የመሰረቷቸውና በሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ሰልጥነው እስካፍንጫቸው የታጠቁትን የኢንተርሃምዌና ኢምፑዛሙጋቢ ሚሊሻዎችን፣ የፕሬዝዳንቱን የክብር ዘብና ሌሎች የጸጥታ አካላትን  ጨምሮ  በተለያዩ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሲስተጋቡ በነበሩ ፕሮፓጋንዳዎች የተነሳሱ 200 ሺህ ያህል የሁቱ ጎሳ አባላት   ተሳትፈዋል፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 6/1994 ምሽት የሩዋንዳውን ፕሬዝዳንት ሃብያርማናን እና የቡሩንዲ አቻቸውን ያሳፈረው አውሮፕላን በመዲናዋ ለማረፍ በማንዣበብ ላይ ሳለ ተመትቶ ወደቀ፡፡ ከዚህ አደጋ እንድም ሰው በህይወት አልተረፈም፡፡ ምንም እንኳን ለጥቃቱ ኃለፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም ሁቱዎች ግን ግድያው መነሻውን ከኡጋንዳ አድርጎ የሀገሪቱን መንግሥት ቁም ቅምጡን አሳጥቶት በነበረው  የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር አላከኩት፡፡

በዚያው ሌሊት ኢንተርሀምዌን ጨምሮ የፕሬዝዳንቱ የክብር ዘብና ሌሎች የጸጥታ አካላትም ጭምር በንጹሃን ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ ጭፍጨፋ ማካሔድ ጀመሩ፡፡  በቀጣዩ ቀን ደግሞ  ምንም እንኳን የሁቱ ጎሳ አባል ቢሆኑም በለዘብተኛነታቸው ምክንያት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዘጠኝ የቤልጂየም ሰላም አስከባሪ አባላት ጠባቂዎቻቸው ጋር ተገደሉ፡፡ የ800 ሺህ ገደማ ሩዋንዳውያንን ህይወት የቀጠፈውን እልቂት ያባባሱት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን መሆናቸው ደግሞ ክስተቱን ይበልጥ ታሪካዊ አድርጎታል፡፡

የኦታዋው ካርሌቶን ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ትምህርት ቤት 10ኛውን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሲዘክር ለውይይት በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደተመለከተው ለሩዋንዳው እልቂት በተለይ ታዋቂው ‘ራዲዮ ቴሌቪዥን ሊብሬ ደስ ሚለስ’ ወይም በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል (RTLM) የተሰኘ ሬዲዮ ጣቢያና በየ15 ቀኑ ሲታተም የነበረው ካንጉራ የተሰኘ ጋዜጣ ሲያራግቡት የነበረው የጥላቻ ዘገባ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡  ሬዲዮ ጣቢያው በተለይ ምንም የማያውቁ የቱትሲ ጎሳ አባላት ያለምንም ምክንያት  እንዲገደሉና እንዲሰቃዩ የሚያበረታቱ ቀስቃሽ ዘገባዎችን ሲያሰራጭ እንደነበረም ተረጋግጧል፡፡

መገናኛ ብዙኃኑ አናሳ ቁጥር ያላቸው ቱትሲዎች  በብዙሃኑ ሁቱዎች ላይ አደጋ የደቀኑ አስመስለው ሲያራግቧቸው የነበሩ የተዛቡ መረጃዎች ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ እንዲነሱ ማድረጉንም በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ምሁራን ያቀረቧቸው ሪፖርቶችና ጥናቶች ምስክሮች ናቸው፡፡

ይህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት  ካስከተለው ሰብኣዊ እልቂት ቀጥሎ አህጉራችን አፍሪካ ያስተናገደችው ሌላኛው የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ይህን መሰሉን ሰብዓዊ ቀውስ አስቀድመው መከላከልና መዋጋት ሲገባቸው በጥላቻ ዘገባዎች የሌሎችን አስተሳሰብ  ሰልበው  አንደኛው ጎሳ በሌላኛው ላይ ጦር እንዲሰብቅ ያደረጉት ቅስቀሳም ሌላኛው የአፍሪካ የሩብ ምዕት ዓመት ክስተት ነው፡፡

አብዛኞቹ መገናኛ ብዙኃን የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የእንስሳትና ዕፅዋት ህልውና ሳይቀር ያሳስባቸዋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንዲወገዱ፣ በመላ ዓለም አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣… የድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ በመወጣት ላይም ይገኛሉ፡፡

የሀገራችን መገናኛ ብዙኃንም በተለይ ባለፈው ሩብ ምዕት ዓመት ሀገሪቱ ከነበረችበት አስከፊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተመንጥቃ እንድትወጣ፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶችና ነጻነቶች እንዲረጋገጡ፣ የዜጎች ቋንቋ፣ ወግና ባህል እንዲጎለብት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ፣ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያንሰራፋ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ የዜጎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ንቃተ ህሊና እንዲዳብር፣… ተግተው ሰርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በሀገሪቱ ጨቅላ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ ችግሩ የሚስተካከልበትን መንገድ ከማመላከትና ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ መሀል ላይ ቆመው የሚዋልሉ አልፎ አልፎም ህዝባዊና ህገመንግስታዊ ሃላፊነታቸውን ዘንግተው ችግሮችን ለማባባስ ሲውተረተሩ የሚስተዋሉ ጥቂት የህዝብና የግል መገናኛ ብዙኃን መኖራቸውንም በተለያዩ ጊዜያት ተመልክተናል፡፡

የሩቁን ትተን የቅርብ ጊዜውን ብንመለከት እንኳን በሀገሪቱ አንድ አንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን አስመልክተው ጥቂት የህዝብም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን በህዝቦች መካከል አብሮ የዘለቀውን አንድነትና ወዳጅነት የሚሸረሽሩ ከዚያም አልፈው ግጭቶቹን የብሔር ግጭት መልክ ያላቸው የሚያስመስሉ  ዘገባዎችን አሰራጭተዋል፡፡ ህብረተሰቡ ለዚህ መሰሉ ዘገባ ጆሮ ከመስጠት ተቆጥቦ ችግሮቹ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መስመር መምረጡ በጀ እንጂ አዝማሚያው ወደ አልተፈለገ  አቅጣጫ ሊወስድ የሚችል እንደነበር  ለመገመት አያዳግትም፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ባለፈው አንድ አመት የግልና የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ያደረገውን ጥናት ዋቢ አድርጎ ይፋ እንዳደረገው አብዛኞቹ መገናኛ ብዙኃን ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዝምታን ይመርጣሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ግጭቶችን የማባባስ አዝማሚያ ታይቶባቸዋል፡፡ በዚህ መሰሉ ተግባር ለተሳተፉ መገናኛ ብዙኃንም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘርኣይ አስግዶም ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ዙሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለይ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ  “መገናኛ ብዙኃን  ለምን  ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ ማድረስ አልቻሉም” የሚል ጥያቄ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ማንሳታቸውም ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንዳብራሩት መገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲያዊ ስርኣት ግንባታ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የላቀ ቢሆንም በተቋማቱ ወስጥ የሚስተዋለው የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ የአመለካከትና የአቅም ክፍተት  ተቋማቱ መስራት የሚገባቸውን ያህል እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ችግሩን በማያዳግም መልኩ ለመፍታት ያመች ዘንድም የማስፈጸም አቅምን መሰረት ያደረገ የሚዲያ ሪፎርም ስራ እተሰራ መሆኑን ገልጸው በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት የማነጹን ተግባር ጠንከር አድርገው እንዲገፉበት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ለመገናኛ ብዙኃን የእለት ከእለት ስራ ወሳኙ ነገር መረጃ በመሆኑ የመንግሥት ተቋማት ትክክለኛውን መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ የሚያደርጉበትን ዘመናዊ የመረጃ ስርኣት መዘርጋትም ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለህትመትና ለኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ብቻ ሳይሆን ለማህበራዊ ሚዲያውም ተገቢውን ተኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን “በማጋጋልና በማጧጧፍ” ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም አልደበቁም፡፡ 

የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የሚያስተዳድሩ ግዙፍ ኩባንያዎችም ጭምር ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ፣ ዘረኝነትንና ጽንፈኝነትን የሚሰብኩ፣ ሽብርተኝነትን የሚደግፉ መረጃዎች ለስርጭት እንዳይበቁ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ እየሰሩ ባለበት ወቅት በኢትዮጵያም የማህበራዊ ሚዲያ አስተዳደርና አጠቃቀም ስርኣት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

መገናኛ ብዙኃኑ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት የላቀ ሚና የሚጫወቱበትን ምህዳር የማስፋቱ የቤት ስራ እንዳለ ሆኖ በተለያየ ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችን የሚያወሳስቡ መገናኛ ብዙኃንን በህጉ መሰረት “አደብ እንዲገዙ ማድረግ” እንደሚያስፈልግም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ለዚህም  በተለይ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት የሁለቱ ክልሎችና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን “ጉዳዩን ለማቀጣጠል” ሲሰሩ እንደነበር ለአብነት አንስተዋል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከመገናኛ ብዙኃን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም “የግጭቶችን መንስዔም ሆነ የተወሰደውን እርምጃ ሊያሳይ የማይችል ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ ማሰራጨት ባህልም ህጋዊ መሰረትም የሌለው” ከመሆኑም በላይ በተለይ “አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ የተነሳ አድርጎ መዘገብ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር” መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ የዜጎችን መብት የሚጻረር መረጃ በሚያሰራጩበት ጊዜ የህዝብ ጠላትነታቸውን እያረጋገጡ መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ህዝቡን ያማረሩና አደባባይም ያስወጡ የመልካም አስተዳደር እጦት ጥያቄዎች፣ ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ልማትን ሊያፋጥኑ የሚችሉ አያሌ የቤት ስራዎች፣ እዚህም እዚያም የሚስተዋል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ባሉበት ሀገር ከሰላም ይልቅ ሁከትና ብጥብጥን ማስቀደም፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን  መስበክ፣  አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ጦር እንዲሰብቅ መገፋፋት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም፡፡ ትርፍ ቢኖረውማ ኢንተርሃምዌንና አክራሪ የሁቱ ጎሳዎችን በማነሳሳት 800 ሺህ ገደማ የቱትሲ ጎሳዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ደም በአደባባይ እንዲፈስ ምክንያት  የሆኑ የሩዋንዳ መገናኛ ብዙኃን የት በደረሱ!!!

የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ተደራሹ ህብረተሰብም ሆነ መንግሥት ተቋማቱ ህገ መንግሥቱ ያጎናጸፋቸውን መብትና ነጻነት ተጠቅመው የሀገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ የሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  ግንባታ  የሚገዳደሩ ጉዳዮችን ነቅሰው በማውጣት ህዝብና መንግስት እንዲወያይባቸው ከዚያም ሲያልፍ እልባት እንዲገኝላቸው በማድረግ ህዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡  

ይሁን እንጂ አንዳንድ የሀገራችን የግልና የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ሰፊውን የመጫወቻ ሜዳ ትተው ህጉ ያስቀመጠውን ቀይ መስመር ለመርገጥ የሚያደርጉት መፍጨርጨር ትርፉ ከምኑ ላይ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ አለንልህ ከሚሉት ህዝብ በፍቅር ፋንታ ጥላቻንና ጠላትነትን ከዚያም ሲያልፍ የህግ ተጠያቂነትን እንደ ትርፍ የሚቆጥሩ መገናኛ ብዙኃን ካሉም መጨረሻቸው  ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የቅርብ ጊዜውን የሩዋንዳ እልቂት  መለስ ብሎ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

                                             ሰላም አይራቀን!!!

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን