አርዕስተ ዜና

ቴክኖሎጂ - እንዲህ ነው እንጂ !

08 Nov 2017
4741 times

                           ሰለሞን ደሳለኝ (ኢዜአ)

 ወይዘሮ አማከለች መረሳ በትግራይ ደቡባዊ ዞን እንዳመሆኒ ወረዳ የሚኖሩ ሴት አርሶአደር ናቸው።ሶስት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት የግብርና ስራን በማከናወን ነው።መተዳደሪያቸው ሰብልን በማልማት ቢሆንም የሚያገኙት ምርት የቤተሰብ የዓመት ቀለብ ከመሸፈን ያልዘለለ ነው - ከእጅ ወደ አፍ እንደሚሉት ዓይነት ።

 በተለይ በየጊዜው በሚገጥመው የዝናብ  እጥረትና የሰብል በሽታ ምክንያት የተሰማሩበት የእርሻ ስራ ከድህነት ኑሮ ሊታደጋቸው አልቻለም ነበር።  እናም ከእርሻ የሚገኘው የሰብል ምርት ለምግብ ፍጆታነት ብቻ ቢውል ነው። እንዲያውም ለሰብል ልማት ሲሉ የተበድሩትን የማዳበሪያ ዕዳ ለመክፈል የተንዳገዱበት ጊዜም ነበር ።

 አሁን  ግን የወይዘሮ አማከለች ኑሮ ከመሰረቱ ተለውጧል። ከጥቂት አመታት ወዲህ ከምርምር ተቋማት የተደረገላቸው ድጋፍ ለአሁኑ ህይወታቸው መሻሻል ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለይ በአፍሪካ ራይዚንግ የትግራይ ፕሮጀክት በየጊዜው ምርጥ የሰብል ዘር ወስደው በማልማት ምርታቸው እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ።

 ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጥ የድንች ዘር አልምተው ያገኙት ከ100 ኩንታል በላይ ምርት ለኑራቸው መለወጥ  ምክንያት ሆናል። ከምርቱ ሽያጭ ዕዳቸውን ከፍለው የቀራቸው 10 ሺህ ብር አምስት በጎችን ገዝተው በማርባት ስራ እንዲሰማሩ በር ከፍቶላቸዋል።

 ከዚያም የምስርና የአተር ምርጥ ዘር የማልማቱን ስራ ተያያዙት። በአካባቢው የምስርና የአተር ምርት ዋጋ ጥሩ በመሆኑ ለኑሯቸው መሻሻል ተጨማሪ ምክንያት ሆኖላቸዋል።

በቤታቸው አካባቢ ያለሙት  የእንስሳት መኖ ዛፍ ደግሞ  የእርባታውን ስራ እንደልብ ለማካሄድ ጠቅሟቸዋል።

 የምስርና አተር ተረፈ ምርቱ  ሳይባክን ለመጠቀም የሚረዳ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚም ናቸው ። ይህም በቂ መኖ  እንዲይዙ ስለረዳቸው የእርባታውን ስራ ያለችግር ያከናውናሉ።

 ከደለቡ የበጎች ሽያጭ ካገኙት ገቢ ውስጥም ስምንት ሺህ ብር በቁጠባ አስቀምጠዋል።የእንስሳቱ ቁጥርም 12 ደርሰውላቸዋል።

 ሴት አርሶአደሯ ተጨማሪ ገንዘብ ሲያሻቸውም በጎች እየሸጡ በሚያገኙት ገቢ ድህነትን ለመሰናበት እንደበቁ አስተያየታቸን የሰጡት ሰሞኑን በአካባቢያው በተካሄደው የመስክ ጉብኝት ላይ ነው።

 የወይዘሮ አማከለችን ሃሳብ ተጋርተው ልምዳቸውን ያካፈሉት ደግሞ የፕሮጀክቱ ድጋፍ ተጠቃሚና የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ አረጋ ናቸው።

 ፕሮጀክቱ ያቀረበላቸውን የሰብል ተረፈ ምርት ማስቀመጫና መመገቢያ ቴክኖሎጂ መጠቀም ከጀመሩ አራት አመታት ሆኗቸዋል ። ይህም ካሁን በፊት በአያያዝ ጉድለት የሚደርሰውን የሰብል ተረፈ ምርት ብክነት በማስቀረት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ፡፡

 ቀደም ሲል ከምርት በኋላ ሳያነሱት ማሳ ላይ ተበትኖ ይቀር የነበረውን የባቄላና የምስር ተረፈ ምርት በአግባቡ ሰብስበው ከብቶችን እያደለቡ መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት፡፡ በቅርቡ አድልበው ለገበያ ካቀረቧቸው  አምስት ከብቶች ሽያጭ ብቻ 27 ሺህ ብር ትርፍ ግኝተዋል። የእንሰሳት ማድለብ ስራው አዋጪ በመሆኑ በጎችንም ጭምር ማድለብ ጀምረዋል፡፡

 በአጭር ጊዜ ለምርት የሚደርሱ የአትክልትና አዝርዕት ምርጥ ዘሮችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሰብል ምርምር ስራ የተሳተፉት የአምባላጌ ወረዳ አርሶአደር ወይዘሮ ሐርፈያ ካህሳይ አንዷ ናቸው።

 በመኸሩ የነበረው ዝናብ አነስተኛ በመሆኑ ዘር ለመዝራት ሲወጡ ጎረቤቶቻቸው ዘሩን ከሚያባክኑት ለፍጆታ እንዲያውሉት መክረዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

 እርሳቸው ግን ዘሩን ለፍጆታ ከማዋል ብለው አርሰው ላለሰለሱት መሬት በአደራ የሰጡት ስንዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምርት ደርሶ እስከ 17 ኩንታል ምርት እየጠበቁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

 ካሁን በፊት በባህላዊ መንገድ የእርሻ ስራቸውን ያከናውኑ ስለነበር  ብዙ ጊዜ ሰብላቸው ማሳ ላይ እየቀረ ሲቸገሩ እንደነበር የሚገልፁት ደግሞ ሌላው የምርምር ተሳታፊና የእንዳመሆኒ ወረዳ አርሶአደር ተካ አበራ ናቸው።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርጥ ዘርን ጨምረው ሌሎች ግብአቶችን ተጠቅመው በመስመር ከሚያለሙት ሰብል በየዓመቱ እስከ 20 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 ከአላማጣ እርሻ ምርምር ማዕከል ያገኙትን ‘‘ቦሰት‘‘ የተባለ የጤፍ ምርጥ ዘር በመስመር በመዝራት ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚናገሩት የወረዳው አርሶአደር ንጉስ ሽፈራው ናቸው ።

 "የጤፍ ምርጥ ዘሩን የዘራሁት በመስመር ነው ። ማዳበሪያም ተጠቅሚያለሁ ። አሁን የሰብሉ አቋም ሲታይ ቀደም ሲል ከማለማቸው የአካባቢው የጤፍ ዝርያዎች ጋር ሲነፃፀር  ብልጫ አለው ። ምክንያቱም በትንሽ የዝናብ ውሃ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለምርት ደርሷል" ብለዋል።

 በልምድ ልውውጡ የአለም አቀፍ እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የእንስሳት መኖና የአዝርዕት ምርጥ ዘር ቴክኖሎጂዎችን በማዳረስ ከ6 ሺህ 550 በላይ የአካባቢውን ገበሬዎችች ተጠቃሚ አድርጓል።

 በኢንስቲትዩቱ የአፍሪካ ራይዚንግ የትግራይ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መሃመድ ኢብራሂም እንዳሉት በዞኑ የሚታየውን  የእንስሳት መኖ እጥረት ለማስወገድ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የሰብል ተረፈ ምርት አያያዝና አጠቃቀም ማሻሻል አንዱ ነው።

 የገለባ ማስቀመጫ ቴክኖሎጂዎችን ለገበሬው በማዳረስ ቀደም ሲል በፀሃይ ፣ በንፋስና በዝናብ ይደርስ የነበረውን ከ25 በመቶ በላይ የገለባ ብክነትን ለማስቀረት አስችላል።

 እንደ ምስር፣ባቄላና አተር የመሳሰሉትን የደጋ ጥራጥሬ ምርቶችን ለእንስሳት መኖ ለማዋል የሚረዳ ቴክኖሎጂ በማቅረብም አርሶአደሩን ተጠቃሚ አድርጓል።ቴክኖሎጂው የአርሶአደሩ የጥራጥሬ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ለእንስሳት መኖ በመጠቀም ካሁን በፊት ይደርስ  የነበረውን የ25 በመቶ ብክነት ጭምር አስቀርቷል።

 ሌላው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ለምርት የሚደርሱ አራት አይነት አዳዲስ የመኖ ምርጥ ዘሮችን  ለአርሶአደሩ በማዳረስ  ተጠቃሚ እያደረገ ነው። ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል በፕሮቲንና ሃይል ሰጪ ንጥረ ነገር የበለፀጉ ኦት ቬት ሚክስቸር ፣ ትሪሉሰርና ስዊት ሉውፒን የተባሉ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝርያዎች  ዋነኞቹ ናቸው።

 ዘሮቹ ከእንስሳት በተለይ ከከብቶች የሚገኝ የወተት ምርት በ50 በመቶ የሚጨምር ሲሆን እንስሳትን በአጭር ጊዜ በማድለብ አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑም የሚያስችል ነው።

 ከዚሁ ጎን ለጎን የዝናብ እጥረትንና ልዩ ልዩ በሽታዎችን በመቋቋም ለምርት የሚደርሱ 12 አይነት አዳዲስ የሰብል ምርጥ ዘሮችን ለአካባቢው አርሶአደር የማዳረስ ተግባርም ሌላኛው የፕሮጀክቱ ትኩረት እንደሆነም ነው ያስረዱት አቶ መሓመድ።

 በሄክታር ከ80 እስከ 90 ኩንታል ምርት የሚሰጡ መቀሌ 4 እና ህዳሴ የተባሉ  የዳቦ ስንዴ ምርጥ ዝርያዎችና  ከ60 እስከ 70 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ‘‘ዩቱባና ማንኩዳ‘‘ የተሰኙ የማኮሮኒ ስንዴ ዝርያዎች በአርሶአደሩ ዘንድ ተፈላጊነታቸው እየጨመሩ ከመጡ ቴክኖሎጂዎች ይጠቀሳሉ።

 ‘‘ደራሽና አለማያ ‘‘ የተባሉ የምስር ምርጥ ዝርያዎችን  ጨምሮ በሄክታር ከ40 እስከ 60 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የባቄላና የአተር ምርጥ ዘሮችም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ ሆነው ተገኝተዋል ።

 በተለይ በሄክታር እስከ 70 ኩንታል ምርት የሚያስገኘው ኤች ቢ 1307 የተባለ የምግብ ገብስ ዝርያ በአነስተኛ የዝናብ ውሃ በቀላሉ ለምርት የሚደርስ በመሆኑ በስፋት የማልማቱ ስራ እየተከናወነ ነው ።

 ምርጥ ዘሮቹ የዝናብ እጥረትንና በሽታን ተቋቁመው ለምርት በመድረስ ተመራጭ ሆነው ስለተገኙ የማስፋፋቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲሚቀጥል የሚገልፁት ደግሞ የደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ተወካይ አቶ አታክልቲ ተከስተ ናቸው።

 የአላማጣ እርሻ ምርምር ማዕከል በበኩሉ ማዕከሉ የአትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ 52 የስንዴ፣ የገብስ፣ የባቄላ፣ የማሽላና የደቆቆ ምርጥ ዘሮችን የማላመድ ስራ እያከናወነ መሆኑን ነው ያስታወቀው።

 ከእነዚህ መካከል በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጡ ‘‘ሐሸንጌና ዋልቂ‘‘ የተሰኙ የባቄላ ምርጥ ዘሮች እንደሚገኙባቸው የተናገሩት በማዕከሉ የአዝርዕት ምርምር ስራ ሂደት አስተባባሪ አዳነ ናቸው ።

 የባቄላ ምርጥ ዘሮቹ የአቀንጭራ አረምን በመቋቋም ከአሁን በፊት በአረሙ ሳቢያ ከምርት ውጪ ለሆኑ አካባቢዎች ተስማሚ በመሆናቸው በስፋት የማሰራጨት ስራ እንደሚካሄድ ነው አቶ አዳነ ያስታወቁት።

 በስንዴ አብቃይ አካባቢዎች የቢጫ ዋግ በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው የመቀሌ 3 እና መቀሌ 4 የስንዴ ምርጥ ዘሮችም ለአርሶአደሩ በስፋት እንደሚሰራጭ ነው አቶ አዳነ ያስታወቁት።

 የስንዴ ምርጥ ዘሮቹ የዝናብ ውሃ እጥረት ባለበት በሶስት ወራት ለምርት በመድረስ እስከ 50 ኩንታል ምርት የሚሰጡ በመሆኑ በአካባቢው ገበሬዎች ዘንድ ተፈላጊ ሆነዋል ነበር ያሉት ።

 የመቀሌ ዩኒቨርስቲ በበኩሉ፣በትግራይ ክልል 13 ወረዳዎች ውስጥ የተሻሻሉ የአትክልትና የሰብል ምርጥ ዘር ቴክኖሎጂዎች የሙከራ ልማትና የማስፋፋት ፕሮጀክት እያከናወነ መሆኑን ነው ።

 በዚሁ ፕሮጀክት ከ13 ሺህ በላይ አርሶአሮችን በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የተናገሩት በዩኒቨርሲቲው የግብርና ልማት ተመራማሪ አቶ የማነ ገብረመስቀል ናቸው።

 የቴክኖሎጂ ልማቱም በዋናነት ለደጋማውና ለቆላማ አካባቢዎች ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የስንዴ፤ የገብስ፤የአተር፤ የድንች፤የነጭ ሽንኩርትና የፓፓያ ምርጥ ዘሮች እንደሚገኙባቸው ነው ያስታወቁት።

 በተለይ የሰብል ምርጥ ዘሮቹ የዝናብ እጥረትንና ቢጫ ዋግ የተባለው የስንዴ በሽታን በመቋቋም በሄክታር ከ60 እስከ 70 ኩንታል ምርት የሚሰጡ በመሆናቸው በአርሶአደሩ ዘንድ ተፈላጊ ሆነዋል ።

 በአካባቢው የሚሰጠው የቴክኖሎጂ አቅርቦት፤የማስፋፋትና የአቅም ግንባታ ድጋፍ  የአርሶ አደሩን የሰብል ምርታማነት በ30 በመቶ የማሳደግ አቅም አለው ።

 በተለይ በፕሮጀክቱ  ድጋፍ ከሚደረግላቸው  የክልሉ አርሶአደሮች ውስጥ የሴት ገበሬዎችን ተሳትፎ ወደ 45 በመቶ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ።

 አዎን ! በክልሉ በነበረውና አሁን ድረስ በሚታየው ኋላ ቀር የግብርና ልማት፤የዝናብ እጥረትና የእፅዋት በሸታ ምክንያት የአካባቢው ገበሬ ከዘርፉ ልማት ተጠቃሚ ሳይሆን አመታትን ተሻግሯል።በዚህ መንገድ መጓዝ ግን ከእንግዲህ የሚሆን አይደለም።

 ስለሆነም የግብርና ቴክኖሊጂዎችን ከመጠቀም ውጪ ምርታማነትን ማሰብ የሚቻል አይሆንም።ከዚህ አኳያ የአርሶአደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተጀመሩ የቴክኖሊጂ ሽግግር ስራዎች ውጤታማ ሆነዋልና  ተገቢነታቸው አያጠያይቅም።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን