አርዕስተ ዜና

''ሰርገኛ ጤፍ''

08 Nov 2017
6547 times

            አስራት ፈጠነ /ኢዜአ/

ኢትዮጵያ የህዝቦች ሙዚየም ናት።የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣የተለያየ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአኗኗር፣ የደስታና የሃዘን መገለጫ ባህል ያላቸው። የተለያየ ሃይማኖታዊና እምነት የሚከተሉ። ነገር ግን  በቋንቋም ሆነ በባህል የተወራረሱ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ሃገር ናት። 

 በልዩነታቸው አንድነታቸውን በአንድነታቸው ልዩነታቸውን ይዘው ድንበር ሳይገድባቸው በተለያየ ጊዜ ሃገር ለመውረር የመጣ ጠላትን ህብረት በመፍጠር  ሉአላዊነታቸውን  አስከብረው የኖሩ ህዝቦች ናቸው - ኢትዮጵያዊያን ።

 ለአንድ አላማ ቆመው በአንድ ላይ በፅናት የተዋጉ፣ በአንድ ላይ የቆሰሉ፣ በአንድ ላይ የሞቱና በአንድ ላይ የተቀበሩ መቼም ቢሆን ሊለያዩ የማይችሉ ህዝቦች ናቸው።

 ይህን ለዘመናት የዘለቀውን ግንኙነት አጠናከሮ ለማስቀጠልም ሰሞኑን በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የበለጠ ትስስር ለመፍጠር የምክክር መድረክ ሲካሄድ ሰንብቷል። በምክክር መድረኩ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ ቅኝት፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች በሚል ጥናት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ናቸው።

 የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተጀመረ ነው። ሁለቱ ህዝቦች በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶች የተዋህዱና የተወራርሱ ናቸው። አንዱ የአንዱን ልጅ ተቀብሎ ጡት እያጠባ የሚያሳድግበት የጉዲፈቻ ስርዓት እንዲዳብር ያደረጉ ህዝቦች መሆናቸውን በጥናታቸው አመላክተዋል።

 ሁለቱ ህዝቦች በየወቅቱ ብቅ ይሉ በነበሩ ገዢዎች በህዝቦች ላይ ይፈፅሙት ከነበረውን የግፍ ጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅና ሃገራቸውን ከውጭ ወራሪ ጠላት ለመመከት በጋራ ሲታገሉ የኖሩ ናቸው። ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆንም በአገሪቱ የነገሰውን የፈላጭ ቆራጭ የዘውድ አገዛዝ ስርዓት በመቃወም ታግለዋል መስዋትነት ከፍለዋል።

 የተዛባ የታሪክ አፃፃፍ፣ የህዝቡን ትክክለኛ ግንኙነት መሰረት ያላደረገ የፅንፈኛ  ፖለቲከኞች መበራከት በሁለቱ ህዝቦች ዘንድ ለዘመናት የዘለቀውን አንድነት እንዲሻክር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም ።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሃይ ባይ ባጣው ማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት  ሃላፊነት በጎደላቸው አካላት የሚሰራጨው ነውረኛና ፀያፍ ንግግሮች፣ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ የዲያስፖራ ፖለቲከኞች የሚሰነዝሩት መረን የለቀቀ ብሄር ነክ ፅሁፎች በሁለቱ ህዝቦች ማህበራዊ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረና የፅንፈኝነት አቅጣጫ እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል።

 የአማራ ህዝብ “ትምክህተኛ” የኦሮሞን ህዝብ ደግሞ  “ጠባብ” በሚል የሚሰነዘሩት ንግግሮችም በህዝቦች ግንኙነት መካከል ጫና እያሳደሩ ነው። ስለሆነም ትምክህተኛም ሆነ ጠባብነት እንደ ግለሰብ ሊኖር ይችላል እንጂ ህዝብ እንደ ህዝብ ትምክህተኛም ሆነ ጠባብ ሊሆን ስለማይችል፣ ሆኖም ስለማያውቅ ፣ ወደ ፊትም ሊሆን ስለማይችል ንግግሮቹ በፍጥነት ሊታረሙና ሊስተካከሉ እንደሚገባ ጥናቱ ጠቁሟል።

 ችግሮችን ለመፍታት በህዝቦች መካከል ቋሚ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መፍጠር፣ ሊቋረጥ የማይችል የመሰረተ ልማትና የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠርና የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ማዳበር እንደሚገባም ተመላክቷል።

 እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት የፌደራሊዝም ስርዓት መተግባር ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ያሉት ምሁሩ ፅንሰ ሃሳቡን ተረድቶ በማስገንዘብ በኩል ክፍተት አለ። የፌደራል ስርዓቱን ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት እንከን ሳይኖረው መተግበርና የህዝቦችን አንድነትና በጋራ የመኖር ባህል በህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንደገና ማጠናከር እንደሚገባም ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በጥናታቸው ላይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አሳይተዋል።

 በመድረኩ የተገኙትና ስሜት በሚነካ ንግግራቸው የታዳሚውን ቀልብ የሳቡት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊነት አንዱ ብሄር ከአንዱ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የተገነባና በቀላሉ የሚጠፋም ሆነ የሚደበዝዝ ማንነት አለመሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ጥረት የተገነባች ሃገር ናት።

 ኢትዮጵያዊነትን ማንም ተነስቶ የሚሰጥህም ሆነ የሚከለክልህ አካል የለም። በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ በፍቅር የሚኖር ማንነት ነው። በፍቅር መኖርና ለፍቅር መሞት ነው ኢትዮጵነዊነት። ለዚህም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ጉዳይ፣ በማንነቱ፣ በአንድነቱና ህብረቱ የማይደራደር ጠንካራና ግልፅ ህዝብ ነው።

  ባለፉት አመታት ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት አንደሆነ ለአብዛኞቻችን ብዥ ብሎብን ነበር ። ግን  ፍቅር ማለት ነው። “ ሱስ ” ብለውታል። በህዝቡ ዘንድ ኢትዮጵያዊነቱ ረሃቡና ጥሙም ጭምር ነው።

 ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ቀይ ጤፍ አይደለም ። ነጭ ጤፍም አይደለም ።”ሰርገኛ ጤፍ” ነው።  “ሰርገኛ ጤፍን ማንም አበጥሮ መለየት እንደማይችል ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝቦች ማንም መለየት አይቻለውም።  እንደ ሰርገኛ ጤፍ አብሮ የሚበጠር፣ አብሮ የሚፈጭ ከተቻለም አብሮ የሚበላ አንድ ህዝብ ነው። አንድ ለአንዱ ጌጡ ነው። ኩራቱ ነው። እንደ ሸማ ጋቢ አብሮ የተሰፋ ሊለያይ የማይችል ህዝብ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት እየደበዘዘ ያለ ቢመስልም በህዝቦች የልብ ማህተም የታተመና በቀላሉ የሚጠፋም ሆነ የሚጨልም ማንነት አይደለም “ሲሉ  ተናግረዋል።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትናንሽ ጉዳዮች በሚፈጠሩ አለመግባባቶች የአንድነታችን ጥንካሬ እየተፈታተኑ ይገኛሉ ባይ ናቸው ። የሚገርመው ነገር ደግሞ ይላሉ አቶ ለማ የሚፈጠሩትን ችግሮች ክስተቶች ናቸው በማለት ከችግሩ ጋር የመላመድ አደገኛ አዝማሚያ እየታየ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ አዝማሚያ ቶሎ ካልተመከተና መፍትሄም ከስር ከስሩ ካልተበጀለት ሲዳፈን ሲዳፈን ኖሮ አንድ ቀን ረመጡ ሁላችንም ያቀጥለናል ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት በአፅንኦት ተናግረዋል።

 አሁን ፍቅር ያስፈልገናል ያሉት አቶ ለማ ከአማራ ክልል ህዝብ ጋር በቅርበት ለመነጋገር ወደ ባህር ዳር ስንመጣ ለታይታ ወይም ለአንድ ወቅት ሞቅታ አይደለም። በእውነት ስለ እውነት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታችን ማጠናከር  እንደሚያስፈልገንና ስለሚያስፈልገን በማመናችን ነው። የአማራ ክልልም እንዲሁ።

 በመሆኑም በጉርብትና ፣ በወዳጅነት እንዲሁም በዝምድና ተዋህደው፣ ተፋቅረውና ተሳስበው በሚኖሩ በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ግንኙነት መካከል ምንም አይነት የሚከለክል አጥር ሊበጅ አይገባውም ሲሉ በአፅኖት ገልፀዋል።

 በየትኛውም ህዝብ ውስጥ ልዩነት አለ። ወደ ፊትም ይኖራል። ነገር ግን የሚያመሳስሉንን ጉዳዮች በማጎልበት፣ ልዩነቶችን በማጥበብና አንድነትን በማጠናከር ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማስቀጠል ከችግሩ መውጫ መንገድ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ አስረድተዋል።

 በተለይም የወጣቱን እጅግ አሳሳቢ የስራ እጥነት ችግርና የመልካም አስተዳደር መጓደሎችን መፍታትም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

 ለዚች ሃገር አንድነትና ቀጣይነት የነገ ሃገር ተረካቢ የሆነውን ወጣት በስነ ምግባር በማነፅ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ማጠናከር የግድ መሆኑን ርዕስ መስተዳደሩ ገልፀዋል።

 የሃገሪቱ ምሁራንም የሃገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ለችግሮች መፍትሄ በመጠቆም ምሁራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

 የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የዘመናት ግንኙነት ለአፍታም ቢሆን ሳይቋረጥ ተጠናከሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋርም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በቀጣይ ይደረጋል ብለዋል።

 በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀው የአብሮነትና የአንድነት ትስስር በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ጠንካራ ኢትዮጵያን የመፍጠር ዓላማ የያዘ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው።

 ኢትዮጵያዊነት በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህብረት፣ አንድነትና መከባበር የተገመደች ሃገር ናት። በህዝቦቿ የጠነከረ የእርስ በእርስ ግንኙነትም አጥንታቸውን ከስክሰውና ደማቸውን አፍስሰው  ከወራሪ ጠላት ተጠብቃና ተከብራ የኖረች ሃገር ማቆየት ችለዋል ።

 የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነትም ስር የሰደደና ለረጅም ዘመናት በወግና ባህል ተሳስረው፣ ተጋብተውና ተዋልደው፣ አንድ ቋንቋ ተናግረው እንደ አንድ የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው።

 የኦሮሞ ህዝብ ማንነቱ ፣ ቋንቋው፣ ወጉና ባህሉ በአማራ ህዝብ ዘንድ ተከብሮና ተጠብቆ እየኖረ ሲሆን የአማራ ባህል፣ ወግና ቋንቋም እንዲሁ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተከብሮ እየኖረ ነው ብለዋል ።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን አንድነትና መጠናከር የማይመቻቸው አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት ሆነ ተብሎ ቀን ከሌት በተቀነባበረ ሴራና የጥፋት ዘመቻ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል። ነገር ግን በአስተዋዮቹ  ህዝቦች እምቢተኝነት የእለት ከእለት ትንኮሳዎቻቸውን በትዕግስትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተባበረ ክንድ እየተመከተ ይገኛል። አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ ግጭቶችም የኦሮሞ ህዝብ የአማራውን ሃብትና ንብረት በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ወንድማዊ አጋርነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ ችለዋል።

 በአማራ ክልል ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች የሚኖሩ ሲሆን ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተጠብቆ ፣ ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እየተደረገ ነው።

 በኦሮሚያም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ ርእሰ መስተዳድሩ ገልፀው   በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ለዘመናት የዘለቀው ማህበራዊ  ግንኙነትና ትስስር እንደ ብረት የጠነከረ መሆኑን አስረድተዋል ።

 ወጣቱ ትውልድም ከአባቶቹ የወረሰውን የአንድነትና የመተባበር ባህል በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

 የህዝብ ለሀዝብ ትስስሩን በማጠናከርም በብሄር ብሄረሰቦችና ሀዝቦች አንድነትና እኩልነት የተገነባችውንን አዲስቷን ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ የመገንባት ሃላፊነታችን በብቃት ለመወጣት  ቆርጠን የተነሳን መሆናችን ለህዝቡ ማረጋገጥ እንፈልጋለን ሲሉ አቶ ገዱ ተናግረዋል።

 የአማራ ክልል ህዝብ ያደረገላቸው አቀባበልና አክብሮት ወገናዊነቱን እንዲሁም ለኦሮሞ ህዝብ ያላውን ጥልቅ ፍቅር ያሳየበት መሆኑን የገለፁት ደግሞ አባ ገዳ ሁሴን በዳሳ ናቸው።

 የህዝብ ለህዝብ ትስስሩም የኦሮሞና የአማራ ህዝብ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወጣቱ ትውልድ እንዲያውቀው የሚያደርግ ነው ብለዋል።

 የጎጃም አካባቢ ህዝብ የኦሮሞ ወንድሞቹን እስከ ታላቁ የአባይ ድልድይ ድረስ በመሄድ ጨፌ ጎዝጉዞ ፣ ማርና ወተት ይዞና በወንድማማችነትና በፍቅር መንፈስ ደማቅ  አቀባበል አድርጎላቸዋል።

 “አብሮነታችን ለሰላማችን ሰላማችን ለአብሮነታችን” በሚል መሪ ቃል የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች የጣና ሃይቅ ደሴቶችን፣ የቤዛዊት ቤተ መንግስትና የአማራ ሰማዕታት ሃውልትን በመጎብኘት ፕሮግራማቸውን አጠናቀዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን