አርዕስተ ዜና

አህጉራዊ ትብብርን የሚሻ ጉዳይ...

02 Nov 2017
6451 times

አማረ ኢታይ/ ኢዜአ/

አለማችን ዛሬ ዛሬ የሚያሳስቧት በርካታ ችግሮች አሉዋት ። ችግሮቹን ለመፍታት የዓለም መንግስታትና የህዝቦቿዋ የጋራ ትብብርና ቀና አስተሳሰብን የሚጠይቁ በመሆናቸው ከባድ መስዋእትነት ይጠይቃል።

ሌሎችም በአንድ ሃገር መንግስትና ህዝብ ሊፈጸሙ የሚችሉ ቢሆኑም ተመሳሳይ የመንግስታትና የህዝብ ቁርጠኝነት፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ፍላጎትንና አቅምን የሚሹ በመሆናቸው ከባድ ይሆናሉ።

አለማችንን በእጅጉ ከሚያሳስቧት በርካታ ችግሮች መካከል የአየር ንብረት መዛባትና የተፈጥሮ ሃብት መመናመን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ችግሩ ከአንድ ውስን ህዝብና የአስተዳደር ክልል አልፎ የዓለም ህዝቦችና መንግስታት የእለት ከእለት መነጋገሪያ አጀንዳ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል። ውጤቱም እጅግ አስፈሪና አስደንጋጭ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።

አለማችን በከባድ የአየር ንብረት ግለት እንድትናወጥ፣ ባልታሰበ ከባድ ዝናብና ጎርፍ እንድትጥለቀለቅ፣ ከጫፍ ጫፍ በበካይ ጋዝ እንድትታመስና ፍጥረታት መቋቋም እንስኪያቅታቸው ድረስ የተለያዩ ተለዋዋጭ ክስተቶችን እንድታስተናግድ ተገዳለች - በአየር ንብረት መዛባትና በተፈጥሮ የደን ሃብት መመናመን ምክንያት።

ሰሞኑን አለም አቀፉ የአየር ትንበያ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው የዓለም መግስታት የአየር መዛባትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በፓሪስ ላይ የገቡትን ስምምንት ተግባራዊ ካላደረጉ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ከባድ የአየር መዛባትን ምድራችን እንደምታስተናግድ ተንቢየዋል። የመሬት ግለት እጅጉን ፍጥረታት መቋቋም እንደሚያስቸግራቸውና ቀጣይ ህልውናቸውን እንደሚፈታተንም አስጠንቅቋል።

በምስራቅ አፍሪካ ሞቃታማ አከባቢዎች ያለውን ተለዋዋጭ የአየር ንብረት መዛባትና የተፈጥሮ ደን ሃብት መመናመን ያሳሰባቸው የአፍሪካ፣ የአውሮፓ፣ የኤስያና የሌሎች አህጉራት የዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪዎችም በጉዳዩ ላይ በሚታዩ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ አካሂደው ነበር።

የኮንፈረንሱ አስተባባሪዎች የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ከኖርዌይ ዓለም አቀፍ የልማት ትበብር ጋር በመሆን ነበር። በርካታ የዘርፉ ከፍተኛ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ሳይንቲስቶች በሦስት ቀናት ቆይታቸው በርካታ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል።

ዶክተር እምሩ ብርሃኑ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የደን ተመራማሪና የአውደ ጥናቱ አስተባባሪ ናቸው ።  በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ‘‘በምስራቅ አፍሪካ ደረቃማ አካባቢዎች የደን ልማት ያለበት ገፅታ እጅግ አሳሰቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በመሆኑም ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች ተወያይተው በዘርፉ ያለውን ዕውቀት ወደየአከባቢው በመውሰድ ጥቅም ላይ እንዲውልና የመፍትሄ አካል ማድረግ‘‘ የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል ።

በዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ ላይ በኬኒያ የዓለም አቀፍ የተቀናጀ ደን ምርምር ተመራማሪ ዶክተር አስቴር ገብረክርስቶስ በበኩላቸው፣‘‘ በምስራቅ አፍሪካ እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ለውጥና የደን መጨፍጨፍ የዝናብ እጥረት እየተከሰተ ነው። የተራቆቱ ስፍራዎችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ እየሄዱ ነው‘‘ ብለዋል።

አህጉሪቱ ህዝቦች ህይወት ለመታደግና  ወደ ተሻለ ብልጽግና ለማሸጋገር የችግሮቹን መንስኤ በመለየት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚገባም ነው ተመራማሪዋ ያሳሰቡት።

እንደ ዶክተር አስቴር አባባል ከሆነ በአህጉሪቱ/ በአፍሪካ/ ላለፉት 300 ዓመታት ድርቅ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የተሻለ ፖሊሲ በማውጣትና በመተግበር አደጋውን መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው።

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉና የማይችሉ እፅዋቶችን በመለየት ድርቅና በረሃማነትን መከላከል እንደሚያስፈልግም ጭምር ተመራማሪዋ ይገልፃሉ ። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን የጀመረችው ጥረት የሚበረታታና  በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊስፋፋ እንደሚገባም ነው ያስረዱት።

በእቅድና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አሰራር በመዘርጋት ተጨማሪ ሥራዎችን ማከናወን ጊዜ ሊሰጣው የማይገባ ጉዳይ እንደሆነም ነው ዶክተር አስቴር አሳስበዋል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ደንና ምግብ ሳይንስ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሳራ ተወልደብርሃን በኮንፈረንሱ ከተሳተፉ የዘርፉ ተመራማሪዎች አንዱ ነበሩ። በአህጉሪቱ ያለውን የደን መመናመን አደጋ ለመፍታት መንግስታት ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የሚያሳስቡት።

በሀገራቱ ከፖሊሲ አውጪዎች እስከ ግብርና ልማት ሠራተኞች ድረስ ስለ ተፈጥሮ ደን ሃብቶች ያለውን መረጃ ማወቅና የችግሩ መፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባቸው ረዳት ፕሮፌሰሯ ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ከሚገኘው ጠቅላላ መሬት ውስጥ ሦስት አራተኛው በድርቅና በዝናብ እጥረት እየተጎዳ ነው ያሉት ዶ/ር ሳራ በእነዚህ አካባቢ ያሉት የተፈጥሮ ደኖች ሕብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ እንዲንከባከባቸውና እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ አዲስ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ግድ እንደሚልም ገልጸዋል።

ኢትዮጰያ ውስጥ የደን ምንጠራና መመናመን ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ከባድ ችግር እንደሆነ  የገለፁት ደግሞ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ውብአለም ታደሰ ናቸው። ችግሩ ባስከተለው ጉዳትም አፈር ተሸርሽሮ መሬታችን ሁሉ የተራቆቱ ሆኗል።የእንስሳት ዝሪያዎች እየተመናመኑ መጥተዋል በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል ። ‘‘መሬታችን የአፈር ሽፋኑ በመሳሳቱ ምክንያትም በየዓመቱ ከሁለት  ቢሊዮን ቶን በላይ ለም አፈር  በጎርፍና ነፋስ እየታጠበና እየተሸረሽረ ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች አጎራባች ሃገራት ይወጣል “ ይላሉ ።

ለኮንስትራክሽን ስራዎች ፍጆታ የሚውለው የጣውላ ውጤቶችን ከውጭ ሃገራት ለማስገባት  በየዓመቱ ከ180 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢትዮጵያን እየጠየቃት እንደሚገኝ ነው ዶክተር ሳራ ያብራሩት ። ችግሮቹን ለመፍታት የደን ሽፋኑ እንዲያገግም የሚከታተልና የሚጠብቅ የአካባቢ ደን ልማትና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር የምርምር ተቋማት መቋቋማቸውና በየክልሎችም ተመሳሳይ መዋቅሮች እንዲደራጁ እየተደረገ ያለው ጥረት በመልካምነቱ ሊጠቀስ እንደሚችልም ነው ያስታወቁት።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዷ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር  የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት መጠነ ሰፊ ርብርብ በማካሔድ ላይ ስትሆን ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራትም ጠንካራ የሆኑ ተቋማት በመፍጠር በገንዘብና በሰው ሃይል በመደገፍና በማጠናከር የደን መመናመንን ለመከላከል የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል።

"የአፍሪካና አውሮፓ አገራት በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት እየተጎዳን ነው ። ችግሩን ለመፍታትና ለመከላከል በጉዳዩ ላይ ጥልቅ እውቀት ሊኖረን ይገባል ።" ያሉት ደግሞ በኖርዌይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአየር ለውጥና የአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሲርድ ናዳ ናቸው።

ኖርዌይ በ25 የአፍሪካ ሀገራት የደን መመናመንና የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ልምዷን በማካፈል፣ በምርምርና ጥናት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ሥራ በትብብር እየሰራች መሆኗንም አመልክተዋል።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በመቀሌ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በእርሻና ደን ልማት ላይ የተሰሩ የምርምር ስራዎችና በሀገር አቀፍ ደረጃም  የተፈጥሮ ደንን ከውድመት ለመከላከል የተከናወኑ ስራዎችና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች  ቀርበዋል። በመጨረሻም መንግስታት በትብብር እንዲሰሩ የሚያሳስብ ምክረ ሃሳብ በማቅረብም ስብሰባቸውን አጠናቀዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን