አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ህዳሴ ለምን ?

11 Oct 2017
7771 times

ገብረህይወት ካሕሳይ  ኢዜአ

ህዳሴ ግድብ፣ ህዳሴ ቴሌኮም፣  ህዳሴ ካፌ ፣ ህዳሴ ሞባይል ……. ህዳሴ ! ይህ ህዳሴ ተራ ስያሜ ወይስ የጠለቀ ትርጉም ይኖረው ይሆን ? አብረን እንየው። ሌሎች ህዳሴዎች ይቆዩና የኢትዮዽያን ህዳሴ እንመልከት።

የቀደምት ስልጣኔ አውራ፣ የገናና ታሪክ ባለቤት፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ ቡናን ለዓለም ያበረከተች፣ የጤፍ ምንጭና የነፃነት ተምሳሌት - ኢትዮዽያ።

እውን ኢትዮዽያችን መታደስ ያስፈልጋት ይሆን? የአክሱም ሀውልቶችንና የላሊበላ ውቅር አቢያተክርስቲያናትን የቀየሱ ጭንቅላቶችና የገነቡ እጆች፣ በጎራዴ መድፍን ያንበረከከ ወኔ የማን ሆነና እኛ እንታደስ?

ህዳሴ (Renaissance) በፊት የነበረውን መመለስ ማለት ነው። ዳግም መወለድ ወይም እንደገና ህይወት መዝራት (Rebirth or Revival) ብለንም ልንወስደው እንችላለን። እንታደሳለን ስንል ድህነትን በልማት ኋላቀርነትን ደግሞ በዴሞክራሲ እናሸንፈዋለን ማለታችን ነው።

ለመታደሳችን ምክንያቱ ዝቅጠት ነው። የችግሩ ምንጮች ቀደምት መሪዎቻችን ቢሆኑም የዝቅጠት ሰለባ የሆንነው ግን እኛው ህዝቦቿና አገራችን ኢትዮዽያ ናት። የዝቅጠት ውጤት ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነት ነው። ድህነትና ኋላቀርነት መገለጫችን ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

ዘመናዊ ኢኮኖሚና ጠንካራ ዴሞክራሲ የገነቡ የአውሮፓ አገራትም ቢሆኑ  በህዳሴ ውስጥ ያለፉ ናቸው። በግሪክና ሮማ ስልጣኔ ዘመን ገናና ታሪክ የነበራቸው አገራት እንደ ኢትዮዽያ ሁሉ በአንድ ወቅት ካጋጠማቸው ውድቀት ለማንሰራራት “ህዳሴ“ የሚል ቃል ተጠቅመዋል።

 እ.ኤ.አ ከ1050 እስከ 1300 በአውሮፓ የተሻለ ስልጣኔ የታየበት ጊዜ ሲሆን ከ1300 እስከ 1450 ደግሞ ረሀብ፣ በሽታና ጦርነትን ጨምሮ በርካታ ቀውሶች የተከሰቱበት ወቅት ነበር።

ግሪክና ሮማ ከስልጣኔ ወደ ኋላ በመቅረታቸው ምክንያት ከ14ኛው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው ጊዜ ውስጥ የፍልስፍና፣ የስነፅሁፍና የባህል ንቅናቄ ፈጥረው እንደገና ማንሰራራት ችለዋል ።

የኢትዮዽያ ህዝቦችም በአንድ ወቅት በዓለም የሰለጠኑ ተብለው ከሚጠሩ አገራት ጋር የሚመጣጠን ስልጣኔ ገንብተው እንደነበር ይታወቃል። በሒደት ግን አኩሪ ስልጣኔያችን ከስሞ አገራችን የድህነት፣ የረሃብ፣ የጦርነትና የብጥብጥ ተምሳሌት ተደርጋ እስከመወሰድ ደረጃ ደርሳ ነበር።  

የኢትዮዽያ ህዳሴ የተጀመረዉ ከአዲሱ ሚሊኒየም ወዲህ ነው። ዘመኑ የኢትዮዽያ ህዳሴ የሚጀመርበት ነው ብለን ተስፋ የሰነቅንበት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ብለን ፈጣን አገራዊ እድገት ማስመዝገብ ከመጀመራችን ጋር ተያይዞ የብዙሃንን ተስፋ ያጫረ ጉዳይ ስለነበረ ነው።

የኢትዮዽያን ህዳሴ የማረጋገጥ ግብ መላው የአገራችንን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ለማንቀሳቀስ የሚችልና የረጅም ጊዜ የትግል መሳሪያ ሆኖ የማገልገል አቅም ያለው በመሆኑ ህዳሴው በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።

አገራችን በስልጣኔ ወደ ኋላ ልትቀር የቻለችው በውስጧ ያቀፈችውን ብዝሃነት ማስተናገድ ስለተሳናት፣ ይህንኑ ተከትሎ በማያባራ ቀውስና ግጭት ስትናጥ በመኖሯ ፣ በተመረጠና ውጤታማ መንገድ የሚከተል ልማታዊ መንግስት መመስረትና ማስቀጠል ባለመቿላ ነው።

በሌላ አነጋገር የአገራችን ህዳሴ እውን ሊሆን የሚችለው የንቅዘቷ መሰረታዊ ምክንያት  የሆኑትን ድህነትንና ኋላቀርነትን በብቃት የሚያስወግድ ልማታዊነትን ከዴሞክራሲያዊነት ጋር ያጣመረ መንግስት መመስረት ስትችል ብቻ መሆኑ ነው።

የኢትዮዽያ የህዳሴ ጉዞ ያለፉት ዓመታትን ጨምሮ ከ40 እስከ 45 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።ኮሪያና ታይዋን እኛ አሁን ካለንበት የእድገት ደረጃ ከሚመሳሰል ሁኔታ ተነስተው 50 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከበለፀጉ አገራት ተርታ መሰለፍ ችለዋል።

እኛም ኮሪያና ታይዋን ያሳኩትን ግብ ለማሳካት የነደፍነውን የጉዞ መስመር ነው የኢትዮዽያ ህዳሴ ብለን የምንጠራው ።

 በፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካይዳኪ ገዛኽኝ ኮሪያና ታይዋን ያሳኩትን የኢኮኖሚ እድገት ኢትዮጵያ የማታሳካበት ምክንያት አይኖርም ባይ ናቸው ።

የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ በሶስት ዋናዋና ምእራፎች ተከፋፍሎ የተቀመጠ ነው ይላሉ ። አንደኛው አገሮች ከድህነት አዙሪት መውጣት የሚጀምሩበትና ወደ ዝቅተኛው መካከለኛ ገቢ (Lower middle income) መሸጋገሪያ ምእራፍ ነው። እኛም ጉዞውን ጀምረነዋል።

በዚህ ምእራፍ የነፍሰ ወከፍ ገቢ ከ100 የአሜሪካ ዶላር ወደ አንድ ሺህ ዶላር አካባቢ ማድረስ ሲሆን አሁን እያስመዘገብነው ባለው እድገት መቀጠል ከተቻለ በ2017ዓ.ም ማሳካት እንደምንችል መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አቶ ካይዳኪ እንደሚሉት ከሆነ የአገራችን ነፍስ ወከፍ ገቢ በ1983 ዓ.ም ከ100 ዶላር በታች ነበረ። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎሜሽን እቅድ በ2002 ዓ.ም ሲጀመር 377 ዶላር ብቻ ነበር። እቅዱ በ2007 ዓ.ም ሲጠናቀቅ ደግሞ ወደ 691 ዶላር  ከፍ ማለቱን ያስረዳሉ።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጀመሪያ ዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢያችንን 794 ዶላር ማድረስ ተችሏል። የ2009 ዓ.ም ሃገራዊ እድገታችንም የሚበረታታ ነበር። ዘንድሮም ከ11 በመቶ በላይ እድገት ለማስመዝገብ ታቅዷል። በዚሁ ፍጥነት ከተጓዝን ከ2017 ዓ.ም በፊት ተልእኳችንን ማሳካት እንችላለን የሚል እምነት አላቸው።

ሁለተኛው ምእራፍ ወደ ከፍተኛው መካከለኛ ገቢ (Upper middle income) የምንሸጋገርበት ጊዜ ሲሆን ከ2017 ዓ.ም በኋላ ከ15 እስከ 20 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚፈፀም ነው። የነፍስ ወከፍ ገቢያችንንም ከአንድ ሺህ ዶላር ወደ 5 ሺህ ዶላር የምናደርስበት ይሆናል።

የመጨረሻው ምእራፍ ከፍተኛ ገቢ (upper income or high income) ካላቸው ሃገራት ተርታ የምንሰለፍበት ይሆናል። የነፍስ ወከፍ ገቢያችንን ከ5 ሺህ ወደ 10 ሺህ ዶላር ለማሳደግ በጣም ፈታኝ ጉዞ የሚደረግበት ምእራፍ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ ምእራፍ ተጨማሪ 15 ዓመታትን የሚጠይቅ ሲሆን በአጠቃላይ ሶስቱን ምእራፎች በፍጥነት መጓዝ ከቻልን እንደ ኮሪያና ታይዋን ከ40 እስከ 45 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ልንደርስበት እንችላለን በማለትም ያስረዳሉ። ፈጣን እድገቱ ሲቀጥልና ፍጥነቱ ያልተቆራረጠ ከሆነ አዎን! ህዳሴው እውን ይሆናል።

የህዳሴው ጉዞአችን ሊሳካ የሚችለው ኪራይ ሰብሳቢነት ሲወገድ ብቻ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል መጀመሪያ ከጥበትና ከትምክህት መላቀቅን ይጠይቃል። በግብር፣ በመሬት፣ በንግድ ስርዓት፣ በግዥና ኮንትራት አስተዳደር የሚታዩ የሙስና ችግሮችን በማፅዳትና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይጠይቃል።

ለኢትዮጵያ ህዳሴ ቆመናል ስንል ለእንደዚህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ጉዞ ታጥቀን ተነስተናል ማለት መሆኑን በጥብቅ መገንዘብ ያስፈልጋል። ለአንድ ረጅም የማራቶን ሩጫ የሚደረግ ሳይሆን በዱላ ቅብብሎሽ መልክ ለሚከናወኑ በርካታ የማራቶን ሩጫዎች ተሰልፈናል ማለት ነው።

በሌላ አነጋገር በረዥም የለውጥና የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ሒደት ውስጥ የልማታዊ ዴሞክራሲ ቀጣይነትን ማረጋገጥ መሆኑ ነው።ይህንኑ ለማረጋገጥ ደግሞ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሰላም፣ የአንድነትና የልማት መስመሩን ቀጣይነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስምረውበታል።

ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ምእራፎች የሚያስተሳስሩ፣ ደረጃ በደረጃ እያደጉና እየጎለበቱ የሚሄዱ አራት አቅጣጫዎችን ወይም ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይላል። ቀዳሚው የልማታዊ መንግስትን ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው። ሁለተኛው የቴክኖሎጂ እድገትን ቀጣይነት መረጋገጥ ይሆናል። ሶስተኛው የመሰረተ ልማት እድገት ቀጣይነት ማረጋገጥ ሲሆን አራተኛው ለቀጣይ ለውጥ የሚያመች ሁኔታ መፍጠር ነው።

 በህዳሴው ጉዞ የመጀመሪያው ምእራፍ ለማሳካት የተነደፉት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች በእስከ አሁኑ ሂደት አመርቂ በሚባለው መልኩ በመተግበር ላይ ናቸው። አሁን በውስጣችን የተጫረው ተስፋና አንፀባራቂ ውጤቱ በፅናት ከሰራን ካሰብነው መድረስ እንደምንችል አመላካች ናቸው።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የክትትልና ግምገማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ዋለልኝ  እንደሚሉት ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በጋራ ርብርብ ይሳካል።

በእቅዱ የመጀመሪያው የትግበራ ዓመት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተውን ከባድ ድርቅ በኢኮኖሚው ላይ ተፅእኖ አሳድሮ ማለፉን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ መንግስትና ህዝብ በጋራ ባደረጉት ርብርብ የአንድ ሰው ህይወት እንዳይጠፋ ማድረግ ችለዋል። ይህም ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የፈጠረው አቅም ነው።

ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በየዓመቱ በአማካይ 11 በመቶ አገራዊ እድገት የማስመዝገብ ግብ ያስቀመጠ ቢሆንም ያጋጠመውን ከባድ ድርቅ በመቋቋም በ2008 ዓም 8 በመቶ እድገት መመዝገቡ ትልቅ እመርታ መሆኑን ያስረዳሉ።

በእቅዱ ሁለተኛው የትግበራ ዓመት ማለትም በ2009 ዓም የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት ደግሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቅርቡ ይፋ እንዳደረጉት 10 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ዘንድሮም 11 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የህዳሴው መስመር በርካታ መሰረታዊ መስኮችን ታሳቢ አድርጎ የሚራመድ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት የሚጓዝ ስለመሆኑም ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው። በአንድ በኩል የዜጎችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነተ ማረጋገጥ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማስፈን ስራ ጎን ለጎን እየተሰራ ነው ።

ለአብነት ያክል ጥቂቶችን እንግለፅ ከተባለ እንኳን የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም፣ የገጠር የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም፣ለአቅመ ደካማ አረጋዊያንና የአካል ጉዳተኞች የቀጥታ ድጋፍ ፕሮግራም ፣ የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራምና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ፕሮግራም ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ ፕሮግራሞች ዜጎችን የልማቱና የእድገቱ ተጠቃሚዎች ከማድረጋቸውም በላይ አገራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከማሳደግ አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ።

ለማሳያነት ይረዳን ዘንድ የየፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ እንደገለፁት በ2009 ዓም ብቻ  በመደበኛ የስራ እድል ፈጠራና በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በዘንድሮው ዓመትም 1ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዷል።

ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተነደፈው ፕሮግራም በሙከራ ደረጃ በ11 ዋና ዋና ከተሞች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በሂደት 972 የአገራችን ከተሞችን ያካትታል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስመላሽ በዛብህ እንዳሉት በተጠናቀቀው ዓመት ብቻ 159 ሺህ ዜጎች በአካባቢ ልማት በማሳተፍ ተጠቃሚዎች ማድረግ ተችሏል።

መስራት የማይችሉ 30 ሺህ 400 አቅመ ደካማ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ደግሞ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። እነዚህ ተግባራት ብዙ ነገሮችን የሚጠቁሙ ናቸው።ከሁሉም በላይ ግን ከእድገቱና ከልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ተነጥሎ የሚቀር የህብረተሰብ ክፍል አይኖርም።

የህዳሴ ጉዞው ሁላችንንም የሚያነቃቃ የረዥም ርቀት መዘውር ነው ስንል ድህነትን በልማት ኋላ ቀርነትን በዴሞክራሲ የማሸነፍ አጀንዳ የሁላችንም በመሆኑ ነው። የህዳሴው መስመር በሒደት ከበለፀጉ ሀገራት ጎራ የሚያሰልፈን ብቸኛው መንገድ እስከ ሆነ ድረስ መታደስ ማን ይጠላል?  እንታደሳለን እንጂ !።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን