አርዕስተ ዜና

'መሬ ዮ... መሬ ዮ' - ኢሬቻ

06 Oct 2017
4999 times

በአሸናፊ አራርሳ (ኢዜአ)

የገላን ኮረብታዎች፣ የዝቋላ ከፍታዎች፣ የየረር ሰንሰለታማ ተራሮች ቁልቁል ቢሾፍቱን እያዩ ሐሴት የሚያደርጉበት ቀን ነው ''የኢሬቻ በዓል ዕለት''። የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝቦች ዘንድ ፈጣሪ አምላክ /ዋቃን/ ለማመስገንና ምልጃ ለመጠየቅ የሚከናወን ጥንታዊ ሥርዓት ነው።

በቢሾፍቱ የከተሙ ሪዞርቶች፣ ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀኑን ለማክበር በስፍራው የሚገኙትን ለማስተናገድ ከተማዋን አስውበዋታል። የኢሬቻ ባህላዊ ክንዋኔና እሴቱ በህዝብ ዘንድ የጎላ ቦታ ይሰጠዋል።

የኢሬቻ ሥርዓት /እሬፈና/ በተለያዩ ቦታዎችና ልዩ ልዩ መልኮች ይከናወናል። በጥቅሉ ሲታይ ግን በሁለት ቦታና ወቅቶች ተከፍሎ ነው የሚከበረው። ከሥርዓቶቹ አንዱ በተራራ ላይ የሚከናወነው የኢሬፈና ሥርዓት ሲሆን፤ ሌላው ቢሾፍቱ የምታስተናግደው በጅረትና ኃይቆች ዙሪያ የሚፈፀመው ሥርዓት ነው። ኢሬቻ ቱሉ (በተራራ ላይ የሚፈፀም) በተራራ ላይ የበጋ ወራት አልፈው በበልግ ወቅት መግቢያ ላይ የሚከበር ነው።

ታኅሳስ ጥርና የካቲት ከፍተኛ ፀሐይ የሚታይባቸውና የውሃ እጥረት የሚከሰትባቸው ወራት ሲሆኑ፤ በእነዚህ ወራት ሰውም ሆነ እንስሳት በውሃ እጦት በእጅጉ የሚጎዱባቸው በመሆኑ ፈጣሪ /ዋቃን/ ያንን ወቅት በሠላም አሻግሯቸው ለዝናቡ ወቅት ስላደረሳቸው የሚያመሰግኑበትና ለከብቶቻቸውና ለራሳቸው ውሃ ያገኙ ዘንድ ዝናብ የሚለምኑበት የኢሬፈና ሥርዓት ነው። ሥርዓቱ የሚፈጸምበት ቦታ የደመና መገናኛና እርጥበት በተቸረው ተራራ ጫፍ ሲሆን፤ የፀሎትና ምልጃ ልመናን በባህሉ መሠረት ለዋቃ ያቀርባሉ።

ቢሾፍቱ በመልካ ጅረቶች ላይ የሚደረገውን የኢሬቻ በዓላት መካከከል አንዱና ትልቁ የሚባለውን አስተናግዳለች። የክረምቱ ወራት አብቅቷል፤ መስከረም ተገባዷል።ጨለማ አልፎ ብርሃን ሆኗል።

በቢሾፍቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በአንድ ቦታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው የሚያከናውኑት ሥነ-ሥርዓት ነው። ኢሬቻ የፀደይ ወቅት በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሐይቆች ሃብታም የሆነችው የቢሾፍቱ ከተማ ቅንጡ ሆቴሎቿ ሳይቀር ቄጤማ የሚጎዘጎዙበት፣ አርቲ አርቲ የሚሸቱበት ቀን ነው። አየሩ በአርቲ ሽታ የሚታወድበት፤ ፈረሶችና በቅሎዎች በጌጣጌጥ ተንቆጥቁጠው ከጌቶቻቸው ጋር ወደ ሆራ አርሰዲ የሚወርዱበት ልዩ ቀን ነው።

አርሶና አርብቶ አደሮች ተስፋ ያደረጉት አዲስ ወር በመሆኑም ለዚህ ቀን በመድረስ ከደስታና ለዋቃ ከሚቀርብ ምስጋና በቀር ሌላ የሚስተካከለው ስጦታ የለምና ቢሾፍቱ በምስጋናው ቀን በባህላዊ ዝማሬ ደምቃለች። "ውሃ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው" የሚለው የኦሮሞ ቀደምት ፍልስፍና ፈጣሪን ስለ ግሩም ሥራው ለማመስገን በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ኃይቅ ዙሪያ የሚከናወን የምስጋና ቀን ክንዋኔ ነው።

በዚህ ወቅት ወዳጅ ዘመድ ከወንዙ ማዶ ተጠራርቶ የባህል ልብስ በመልበስ እርጥብ ሣር እና አደይ አበባ በመያዝ "ያንን የወንዝ ሙላት ቀንሶ በሠላም ስላገናኛቸውና ወደ ተናፋቂው የፀደይ ወቅት ስላሸጋገራቸው ለማመስገን ሲሉ ዓመቱ ዞሮ በሠላም ደረሰ እንደማለት ''መሬ ዮ….መሬ ዮ..."  የሚል ዜማ እያዜሙ፣ ክረምቱ በሠላም ተገባዶ፤ ፀደይ አብቦ፤ ወዳጅ ዘመድ በሠላም በመገናኘቱ፣ ለፈጣሪ ምስጋና እያቀረቡ ወደ ወንዝ ወርደው ሙላቱ የቀነሰውን ወንዝ በእርጥብ ሣሩና በአደዩ እየነከሩ በክረምት ዝናብ ጎርፍ የደፈረሰው ወንዝ ውሃው መጥራቱን የፀደይ መገለጫ መሆኑን እያሳዩ፣ ቀጣዩ ወቅት የሠላም፣ የጤና፣ የአንድነት፣ የብልጽግና እንዲሆን ፈጣሪን እየተማጸኑ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ።

በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ሆራ አርሰዲም ከጥንት ጀምሮ ኦሮሞዎች ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች፣ ሌሎችም የአገር ውሰጥና የውጭ ጎብኚዎችም ሳይቀሩ በዓሉን በጋራ ይታደሙታል።

 ኦሮሞና በዓላት

በጥንቱ የኦሮሞ የዋቄፈና እምነት መሠረት ብዙዎቹ በዓላት ወርሃዊ ናቸው። እነዚህ ወርሃዊ በዓላት የሚከበሩት በየአጥቢያው ባሉት መልካዎች፣ በኦዳ (ዋርካ) ዛፍ ስር እና "ገልመ ቃሉ" በሚባለው ቤተ እምነት ነው። ሴቶች በየዓመቱ ወረሃ መስከረም ላይ በየአከባቢያቸው ተሰብስበው በዜማና ግጥም ፈጣሪያቸውን የሚያመስግኑበት እንዲሁም በየትኛውም ጊዜ ቢሆን በአከባቢያቸው ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ፍለጋ የሚሰባሰቡበት ''አቴቴ'' የተሰኘ በዓል፣ የገዳ ሥርዓት ካሉ አበይት በዓላት መካከል ኢሬቻ አንዱና አብዛኛው ኦሮሞዎች ከየአቅጣጫው በመሰብሰብ ለአምላካቸው (ዋቃ) በጋራ ምስጋና የሚያቀርቡበት በዓል ነው።

ኦሮሞ ለሰው ልጆችና ለከብቶቹ በእጅጉ ይጨነቃል፤ በመሆኑም እንደ ኢሬቻ ያሉ ታላላቅ በዓላት በወንዝ ዳርቻ ሲከበር ውሃ ሕይወት ላለው ሁሉ ማስፈለጉን ያመላክታል።

ኢሬቻ ለምን ይከበራል?

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ማኅበር ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቱ ጥያቄውን ሲመልሱ፤ “ኢሬቻ ማለት ሠላም ነው፤ ክረምት ዘንበህ፤ ለሰው ልጅ እህል አብቅለህ፤ ለከብቶች ሣር አብቅለህ፤ ወንዞች ከሙላቱ ጎድለው ዘመድ አዝማድ በዓይነ ሥጋ እንዲገናኙ ስለረዳኸን "እግዚአብሔር ምስጋና እናቀርብልሃለን" በማለት ለፈጣሪ (ለዋቃ) ምስጋና ለማቅረብ ነው” ይላሉ።

“ዋቃ ክረምቱን በሠላም ስላሳለፈልንና ከሰማይ ባዘነበው ውሃ መልካም ፍሬ ስለሰጠን ያለ ክፍያ በቸርነቱ ለሚንከባከበን አምላክ ምስጋና ማቅረብ የተገባ በመሆኑ ነው” የሚሉት ደግሞ የበቾ አባ ገዳ ተሾመ በቀለ ናቸው። “ዋቃ” ፍጥረተ ዓለምን ያስገኘውና ሂደቱንም የሚያስተገብረው አንድ አምላክ ማለት ነው። ኦሮሞ ችግር ሲገጥመው አቤቱታውን የሚያቀርበው “ለዋቃ” ነው። በደስታ ጊዜም ተሰብስቦ “ዋቃ”ን ያመሰግናል። ኢሬቻ ደግሞ የዚህ ዓይነቱ የምስጋና ማቅረቢያ በዓል መሆኑን አባ ገዳ በየነ ይገልጻሉ።

ኢሬቻ በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተለያይተው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው። በመሆኑም በበዓሉ ላይ የተገኙት ሁሉ ይቅር እንደሚባባሉ የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ወለጋ የጅማ አርጆ አባ ገዳ ኢፋ ናቸው። በዓሉ የሚከበርበት ቀን የዓመቱ መጀመሪያ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ዓመቱ የደስታና የብልጽግና ይሆን ዘንድ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ይጎርፋሉ። የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪ የሆነው “ቃሉ” ለሕዝቡና ለአገሩ “ኤባ” (ምርቃት) ያደርጋል። ታዲያ ማንኛውም ሰው ወደ በዓሉ ስፍራ ሲሄድ አለባበሱን ማሳመር ይጠበቅበታል። በእጁም የወይራ ቀንበጥ፣ እርጥብ ሳር አሊያም የአደይ አበባን ይይዛል።

የኢሬቻ በዓል ጥቅሙ

የኢሬቻ በዓል የሁሉም ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚያከብረው፣ ማኅበራዊ አንድነቱ  የላቀ ከመሆኑም ባለፈ የውጭ ቱሪስቶችን በመሳብ የገቢ ምንጭ መሆኑን የሚናገሩት የምስራቅ ሐረርጌ አባ ገዳዎች ምክትል ኃላፊ አባ ገዳ ቱኬ አንያ ናቸው።

አባ ገዳ በየነ፤ በዓሉ ሠላምና የእርቅ በመሆኑ የተጣላው ካልታረቀ በአባ ገዳዎች ይረገማል፤ በመሆኑም እርግማኑን ከመፍራት የተነሳ “ይቅር” በመባባል ዕርቅ፣ ሠላም አንድነት የሚንጸባረቅበት ሥርዓት ነው ስሉ ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ኢንዱስትሪ ዳይሬክተር አቶ ዲማ አበራ በበኩላቸው “ኢሬቻን ለማክበር የሚመጣው ኦሮሞ ብቻ አይደለም፣ ክርስቲያን ወይም ሙስሊም ብቻም አይደለም፣ ከተለያዩ ሃይማኖትና አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች የሚሳተፉበት በመሆኑ በዓሉ ለሕዝቡ አንድነት የጎላ አስተዋጽኦ አለው” ብለዋል።

ባህላዊ እሴቱ ጎልቶ የሚታይበትና የሕዝቡን ፍቅር የሚያዳብር መሆኑንም ነው አጽንኦት የሰጡት።

    የኢሬቻ በዓል ምንነት 

ኢሬቻ በኦሮሞ ባህል ለተለያዩ ትላልቅ ስርዓትና በዓላት ላይ በእጅ የሚያዝ እርጥብ ሳር ማለት ነው። ለጋብቻ ጥያቄ በራሱ (ኢሬቻ) እርጥብ ሣር አገልግል ውስጥ ተጨምሮ ነው የሚላከው። ድሮ ሰዎች መልዕክተኛ ሲልኩ እርጥብ ሣር ቆርጠው በመስጠት፣ "አደራህን በፈጣሪ ስም ይህን መልዕክት አድርስልኝ" ነበር። የኢሬቻ በዓል ላይ እሬፈና የሚባል ስርዓትም ሲከወን እርጥብ ሳር ውሃ ውስጥ እየተነከረ ነው ለዋቃ ምስጋና የሚቀርበው።

ሕዝቡ በዓሉን ሲያከብር ኢሬቻ (እርጥብ ሣር) ይዞ፣ በእለቱ የሚዘመሩ መዝሙሮች እየዘመረ ወደ “መልካ” (ወንዝ) ይሄዳል። እዚያም ሲደርሱ “በክረምት ወቅት ያሉትን ችግሮች አሣልፈህ ለዚህ ላደረስከን በጣም እናመሠግናለን” ይላሉ።

በዚያው ቀንም ግለሰቦች ኢሬቻውን ይዘው የጐደለባቸውን ለፈጣሪያቸው በፀሎት እየነገሩ መለመን ይችላሉ። መልካው (ወንዙ) ምልክትነቱ ከዚህ በኋላ "በጋ ሆኗል፣ ወንዙም ጐድሏል፤ ዘመድ ከዘመድ ወንዝ እየተሻገረ መጠያየቅ ይችላል" የሚል ነው። በዕለቱ ሽማግሌዎች ሃይማኖታዊ ንግግሮች ያደርጉና በድሮው ባህል እርድ ይኖራል፣ የቀረበው ይበላ ይጠጣና ፈጣሪን በተለያዩ መንገዶች እያመሰገኑ ወደ መጡበት ይመለሣሉ ማለት ነው።

የኢሬቻ በዓልን ማክበር የተጀመረው ከገዳ ሥርዓት አጀማመር ወዲህ መሆኑን አባ ገዳዎቹ ይገልጻሉ። በበዓሉ አማካኝነት ሰፊ አገልግሎቶች ያሉት ሲሆን፤ አባ ገዳዎች በኦሮሞ ዘንድ ጎጂና በማኅበረሰቡ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ባህሎችን የሚያወግዙበት፣ አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት፣ በሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች ላይ ተፅዕኖ እንዳይደርሱ የሚመክሩበት ሥርዓትም አላቸው።

በዚህም ዓመት በዓሉ ከመከበሩ በፊት አባ ገዳዎች፣ ስለ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭትና መከላከል፣ ስለ ሴት ልጆች ግርዛት ጉዳት እንዲሁም ለሴቶች መብት እንቅፋት በሆኑ እንደ ያለ አቻና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ላይ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አባ ገዳ በየነ ሰንበቱ ለአብነት አንሰተዋል።

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን