አርዕስተ ዜና

ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ- የብዝሃነታችን የግጭት አፈታት ዘዴ ትሩፋት

06 Oct 2017
2580 times

ሀብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)

 አባቴ አሁን እየኖረበት የሚገኘው ይዞታው ሁሉ ነገሩ ነው። እንዳሻው ቦርቆበት፣ ውሃ ተራጭቶበት፣ ያሻውን የቤት እንስሳ አርብቶበት፣ የጓሮ ጎመን ጎርሶበት ብቻ ምን አለፋችሁ የፈለገውን ሆኖበት ያደገበትም ጭምር ነው። ከዚያም ልጅነቱ የፈጠረለትን የውርስ ዕድል ያገኘበት፣ ትዳር የያዘበት፣ ልጆች ያፈራበት እናም የልጆቹን ወግ ማዕረግ ያየበት ማንነቱም ነው መሬቱ። ሆኖም ከጊዜ በኋላ አንድ የአባቴ ድንበርተኛ ከአባቴ ይዞታ የተወሰነው ክፍል የእኔ ነው ሲል ጥያቄ አነሳ፣ ጥያቄው በተገቢው ቢቀርብ መልካም ነበር፤ ድንበርተኛው ግን አባቴ በሚውልባቸው በመዋል አላስቆም አላስቀምጥ ይለዋል።

ይዞታው ሁሉ ነገሩ ለሆነው አባቴ ነገሩ እንዲሁ በዝምታ የሚታለፍ ጉዳይ አልነበረም፤ አባቴ ሰውዬውን አይሆኑ እንደሚያደርገው ይዝታል፤ ሰውዬውም ልብ አርጉልኝ በማለት የሰዎችን እገዛ በሚፈልግ ሁኔታ አቤቱታውን በየጊዜው ያቀርባል። የሁኔታው መካረር ያላማራቸው ጎረቤቶች ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ፤ በዚህም ለሽምግልና የሚሆኑ ሰዎችን መርጠው ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ሁለቱም ማለትም አባቴም ሆነ ጎረቤቱ እንዲወያዩ በማድረግ በይዞታው ላይ ያላቸውን መረጃ እንዲያቀርቡ አዘዙ፤ በትዕዛዙ መሰረትም አባቴ በንጉሱ ጊዜ ከመሬቱ ባለይዞታዎች ጋር የተዋዋለበትን በእጅ ጽሁፍ የተፃፈበት በጊዜ ብዛት የነተበና ያረጀ የወረቀት ማስረጃውን አቀረበ።

የአባቴ ጎረቤት ግን መረጃ ሊያቀርብ አልቻለም። እንደውም አባቴ ባቀረበው መረጃ ላይ፣ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳው የአባቴ ጎረቤት ለአባቴ፣ ጥያቄ የተነሳበትን የመሬት ይዞታ እንደሸጠለት በተሞነጫጨረ የእጅ ፅሁፍ መቀመጡን ሽማግሌዎቹ ይመለከታሉ። በዚህ ጊዜ የአባቴ ጎረቤት ፊት ላይ የግርምት ሁኔታ ይስተዋልበትም ነበር፤ ለዚህም ምክንያቱ መረጃው እስካሁን በአባቴ እጅ ላይ መገኘቱ ነው። ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩት ሽማግሌዎችም በማስረጃው መሰረት ፍርዱን ለአባቴ ሊሰጡት ችለዋል። ሆኖም ጉዳዩን የያዙት ሽማግሌዎች ነገሩን በዚህ ለመቋጨት አልፈለጉም። ነገሩ ዳግም እንዳይነሳና የአባቴና የጎረቤቱ ግንኙነትም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ የማስታረቅ ስራ ሰርተው፣ እንዲሁም ‘የውሾን ነገር ያነሳ…’ የሚያስብል የቅጣት ውሳኔ ሀሳብ በማቅረብ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊፈቱት ችለዋል።

የአመለካከት፣ የባህል፣ የፍላጎት፣ የስልጣን፣ የእውነታና ፍላጎት አለመጣጣም ልዩነቶች ለግጭት መንስኤ ከሚሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ስለሆነም እንደ ሃገራችን ያሉ የብዙ ባህሎችና የአኗኗር ዘይቤዎች የሚንፀባረቁባቸው ሃገራት በየማህበረሰቦቻቸው በየጊዜውና በተለያየ ምክንያት የሚነሱ ግጭቶችን በራሳቸው መላ ሲፈቱ ይስተዋላል። ከላይ በአብነት እንደቀረበው ታሪክ በሃገራችንም በተመሳሳይ መልኩ ግጭቶች ሲከሰቱ በማህበረሰቡ ባህል መሰረት እየተፈቱ አሁን እስካለንበት ደርሰናል። በአብዛኛው ጊዜም ቢሆን ግጭቱ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መፍትሄ እየተበጀለት የቆየ ቢሆንም በቅርብ ጊዜ በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የተፈጠረው ግጭት በጊዜው ሳይደረስለት ቀርቶም በርካታ ጥፋቶችንም አስከትለው፣ ጥቁር ጠባሳው እንዲተርፈን አድርገው ያለፉ ችግሮችም አይታጡም።  

እንግዲህ ግጭት በግለሰብና በግለሰብ፣ በቡድንና በቡድን አልፎ ተርፎም ወደ ብሄርና ጎሳ በማደግ ሊከሰት ይችላል። ከላይ በአባቴና በጎረቤቱ መካከል እንደተፈጠረው አይነት ግጭቶችንም ሆነ ሌሎች ሰፋ ያሉትን ከመነሻቸው ጉዳት ሳያደርሱ በእንጭጩ እንዲቀሩ ለማድረግ በየማህበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት ሲሰራባቸው የቆዩ የግጭት አፈታት መላዎችን መጠቀም ችላ ሊባል አይገባውም። ‘ውሃን ከጥሩ ነገርን ከስሩ’ ነውና ብሂሉ የየማህረሰቦቹ የግጭት አፈታት ዘዴዎች የግጭቱን መነሻ እስከ መድረሻው የማጥራት ብቃትም አላቸው። እንዲህ እንደኛ የሁለት ግለሰቦች ፀብ በፍጥነት አድገው የብሄረሰብ አጀንዳ ሆነው በሃገር ላይ የከፋ ጉዳት እስከማድረስ ሲዘልቁ ለሚስተዋልባት ሃገር የየማህበረሰቡ የግጭት አፈታት መላ ‘ማን ልበል’ የሚያሰኝ ምላሽ ሊሰጠው አይገባም።

መንግስት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል በአዋኝ አከባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች እገዛ እንዲገኙ እንዲሁም በአካባቢው ግጭት ዳግም እንዳያገረሽ እያደረገ ከሚገኘው ጥረት ባሻገር የየማህበረሰቦቹ የግጭት አፈታት ዘዴን ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። ከዚህ ቀደምም የኦሮሚያ ክልል ከጋምቤላና ከቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግስታት ጋር የአስተዳደር ወሰን ማካለልን አስመልክቶ የደረሷቸው ስምምነቶችም በተሞክሮነት ቀርበው ሰላማዊ መላዎች ሊመቱ ይገባል። የየማህበረሰቦቹ የግጭት አፈታት ዘዴ ሳይዘነጋ ማለት ነው።

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች ለተነሳው ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትም በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚመሩ ህዝባዊ ጉባዔዎች በቅርቡ እንደሚካሄዱ ጠቅላይ በሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት የተመራ የውይይት መድረክ ላይ መገለፁም በመንግስት በኩልም ችግሩ በመነጋገርና በመግባባት እንዲፈታ ጥረት መኖሩን የሚያሳይ  ነው። በውይይት መድረኩም ላይ የሁለቱ ክልሎች አመራር አባላትና የፀጥታ አካላት ተሳትፎ አድርገውበት እንደነበር መሰማቱም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ ላይ ጠንካራ ተስፋን ያጭራል።

በተለይ የውይይት መድረኮቹን የሁለቱ ክልሎች የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደሚመሩት መታሰቡ ለግጭት አፈታት ሂደቱ ይበል የሚያሰኝ መፍትሄን ሊያመጣ እንደሚችል እሙን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት የውይይት መድረክ ላይ ለችግሩ ፈጣንና ዘላቂ እልባት ለመስጠት የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለኢዜአ ተናግረዋል። ታዲያ በቅርቡ የተባለውን ውይይት ቶሎ በማፋጠን መድረኮቹን አመቻችቶ መፍትሄ መሻቱ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።

በተለያዩ ምክንያቶች ለሚፈጠሩ ግጭቶች ህገ መንግስቱ የራሱ መፍትሄ አለውና የተጠቀሱ ህግጋትን ተግባራዊ በማድረግ ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየትና አጥፊዎችንም ለህግ በማቅረብ ለችግሩ እልባት መስጠቱ ሊዘገይ አይገባም። የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን መብት ያስከበረ አንቀፆችን በውስጡ የያዘ ህገ መንግስትም የግጭት አፈታት መላዎችንም በውስጡ የያዘ ከመሆኑ አንፃር የማህበረሰቦቹን የግጭት አፈታት ዘዴ በማጣመር ውጤታማ ተግባርን መፈፀም ይቻላል።   

‘አበራሽን ያየ…’ ነውና ሌሎች የአህጉራችን ሃገራት ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንደ ተሞክሮ በመውሰድ በሰከነ ሁኔታ ለግጭቶች መፍተሄ ማበጀት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እየሆነ ነው። በአህጉሪቱ ምስራቅ በተባለ አንድ አይነት አቅጣጫ ላይ ከምትገኘው ሃገረ ሩዋንዳ ትምህርት ሊሆነን የሚችል ጉዳይን ወስደን ማየቱ ተገቢ ነው።

መገናኛ ብዙሃኑም ግጭቶችን ለማርገብ እንጂ እንዲባባስ ከሚያደርጉ ዘገባዎች ከምን ጊዜውም በተለየ መታቀብ ይጠበቅባቸዋል። ከውጭ መረጃ የሚሰጡ መገናኛ ብዙሃንም ሃላፊነት የጎደላቸውን ዘገባዎች ከማሰራጨት የሚቆጠቡበትና ሰከን ብለው የሚያስቡበት እንዲሆንም ወቅቱ ይፈልጋል።

የሴጣን ጆሮ ይደፈንና አሁን ላይ አባቴና ጎረቤቱ እንደወትሮው ሁሉ አዲስ አመትና የመስቀል በአላትን በአንድ ላይ ቅርጫ ተካፍለው በመብላት፣ ቡና አፍልተው በአንድ ላይ በመጠጣት በሰላምና በደስታ አክብረው አሳልፈዋል። ከዚህም በዘለለ በችግር ጊዜ የሚረዳዱ፣ ሲጠራሩ በፍጥነት አቤት የሚባባሉ ጎረቤታሞች ብቻ ሳይሆን ዘመዳሞች ሆነዋል። ‘ያገሩን በሬ ባገሩ ሰርዶ’ እንዲሉ አበው መንግስትም በየቦታው የተነሱ ግጭቶችን ለመፍታት የተናጠል ጥረት ከማድረጉ በፊት ለማህበረሰቡ የግጭት አፈታት መላዎች ቦታ ሊሰጥ ይገባዋል። ለግጭቶቹ ፈጣን መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ የሚያስችል አቅም በየባህሎቻችን ውስጥ መኖራቸውን የሚመለከተው አካል ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋው አይገባም፤ መልዕክታችን ነው።  

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን