አርዕስተ ዜና

ሳይቃጠል በቅጠል

06 Oct 2017
1648 times

                       ሰለሞን ደሳለኝ ( ኢዜአ)

ወይዘሮ አረጋሽ ካሳዬ ይባላሉ ። የማይጨው ከተማ ነዋሪ ናቸው ። ሶስት ጉልቻ የመሰረቱት  ከሃያ አመት በፊት ነበር።ያኔ በወጣትነት እድሜያቸው የራሳቸው ስራ ባይኖራቸውም የትዳር አጋራቸው ገቢ ደህና ስለነበር በተከታታይ ሁለት ልጆችን ወልደው ለማሳደግ እንዳልከበዳቸው ይናገራሉ ።

“የኋላ ኋላ በትዳር አጋሬ ባህሪ ላይ የምመለከተው ሁሉ እንግዳ ሆነብኝና ግራ መጋባት ጀመርኩ” የሚሉት ወይዘሮ አረጋሽ ባለቤታቸው የአልኮል መጠጥ እየጠጡና  አምሽተው እየገቡ  እንቅልፍ ይነሷቸው እንደነበር ይገልፃሉ።

“በባለቤቴ ሁኔታ ውስጤ ኩፉኛ እየተረበሸ ቢሆንም ትዳር ነውና ሁሉን ነገር ችዬ መኖር እንዳለብኝ ራሴን በማሳመን የትዳር ህይወቴን ቀጠልኩበት” ይላሉ ።

ነገር ግን የትዳር አጋራቸው  ብዙ ሳይቆዩ ጤንነታቸው  እየታወከ መጣ። በዚህም ምክንያት ከስራ ይልቅ አልጋ ላይ ተኝተው የሚያሳልፉበትን ጊዜ እየበዛ ቀናት በወራት እየተተኩ የቤተሰቡ ኑሮ መመሰቃቀል እንደጀመረ ያስረዳሉ።

“ የባለቤቴ ጤንነት ከመሻሻል ይልቅ እየጠናበት በመምጣቱ ፈውስ ፍለጋ በርካታ የፀበል ስፍራዎችን ባዳርስም ጥረቴን ሳይሳካ ቀረ “  በማለት ፊታቸውን ቅጭም አድርገው በሃሳብ ወደ ኋላ ነጎዱ ። ባለቤታቸው ከጎናቸው ተለይተዋል ። የሞቱት በ1993 ዓም ነው ።

ልባቸው በሀዘን የተጎዳው ወይዘሮ አረጋሽ ያለ አባት የቀሩ ሁለት ጨቅላ ህፃናትን የማሳደጉ   ሃላፊነት የእርሳቸው ብቻ ሆነ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ? እሳቸውም ቢሆኑ የባለቤታቸው ጦስ ሰለባ ሆነዋል።

ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሽታ ይደቋቁሳቸው ጀመር ። አንዴ አልጋ ሲይዙ ሌላ ጊዜ ቀና ብለው ከኑሮ ጋር ግብግብ ሲገጥሙ አራት ዓመታት ተቆጠሩ።

በ1998 ዓ.ም ማብቂያ  በማይጨው ሆስፒታል የደም ምርመራ መጀመሩ ተሰማ ። ወይዘሮዋ ግን   ሰው ምን ይለኛል በሚል የደም ምርመራ ለማድረግ   ለጊዜውም ቢሆን ድፍረቱን አጥተው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ዘግይተውም ቢሆን ወደ ሆስፒታሉ በማምራት የደም ምርመራ አድርገው ቫይረሱ በውስጣቸው እንደሚገኝ ተነገራቸው ። የባለቤታቸው ሞት ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ተገነዘቡ ። ነፍስ ታሳሳለችና በእጅጉ ተደናገጡ።

“ለሃጥኣን የወረደ ለጻድቃን”  እንዲሉ ወይዘሮ አረጋሽ ሙት ወቃሽ መሆን ባይፈልጉም ባለቤታቸው ካመጡት መዘዝ የተመዘዘ መጥፎ ፅዋ መጎንጨታቸው ግን ክፉኛ አሳዘናቸው።

“ከጤና ባለሞያዎች በሚሰጠኝ  ተደጋጋሚ የምክር አገልግሎት እራሴን በመጠበቅና መድሃኒቱን በስርዓቱ በመከታተል የወደፊት የህይወት ጉዞየን ቆም ብየ እንዳስብ አስችሎኛል” ነበር ያሉት ።

“ከድንጋጤ አለም ወጥቼ መረጋጋት ስጀምርም ቫይረሱ ካለባቸው አባትና እናት አብራክ የተገኙትን ልጆቼን በማስመርመር እንደ እድል ሆኖ ሁለቱም ከቫይረሱ ነፃ ለመሆን ስለቻሉ በወቅቱ የተሰማኝ ደስታ አሁን በቃላት ብቻ ከምገልፀው በላይ ነው “ በማለት ያስታውሱታል።

በግንዛቤ ማነስ ምክንያት ከአንዳንድ ሰዎች ይደርስባቸው የነበረው  መገለል እጅግ አስከፊ የነበረ ቢሆንም ከሌሎች ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ተባብረው “ትውልድ እናድን” የተሰኘ ማህበር መስርተው ዛሬም ድረስ ወገኖቻቸውን በማስተማር ላይ ናቸው፡፡

የማህበሩ ሊቀመንበር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ወይዘሮ አረጋሽ እንዳተናገሩት አሁን የማህበሩ አባላት ቁጥር 450 ደርሷል። ሁሉም አባላት ፀረ ኤድስ  መድሃኒት ይጠቀማሉ።ራሳቸውን በመጠበቅ ያለችግር ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩም ናቸው።የበሽታውን ስርጭት ለመግታትም የድርሻቸው እየተወጡ  ይገኛሉ።

“ቫይረሱ ያለበት ሰው  ከደባል ሱሶች በመራቅ ራሱን መጠበቅ እስከቻለ ድረስ እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው ያለችግር መኖር እንደሚችል ከእኛ ትምህርት መውሰድ አለበት” ሲሉም ይመክራሉ ።

የከተማው ነዋሪ  ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ  እያደገ ቢመጣም  የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ካሁን በፊት ሲካሄድ የነበረው ጥረት  መዳከሙ ግን መዘናጋት እያስከተለ ነው የሚል ስጋት አላቸው ።

ስጋቱ የወይዘሮ አረጋሽ ብቻ አይደለም ። በአገር አቀር ደረጃ በተካሄደው የተቀናጀ ርብርብ ዓለምን ያስደመመ ስኬት ማስመዝገብ ተችሎ ቢቻልም ስኬቱን ተከትሎ የመጣው መርካት፣ መዘናጋትና መቀዛቀዝ ግን ዳግም ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል።

በትግራይ ምእራባዊ ዞን  እየታየ ያለውም ይኼው ነው ። ከፌሰደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በዞኑ የቫይረሱ ስርጭት ቀላል የሚባል አይደለም። አገር አቀፍ የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ 1ነጥብ 2 በመቶ ቢሆንም በራያ አዘቦና ኮረም ግን ከ3 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ደርሷል ።

እንዲያውም ከትልልቅ ከተሞች ይልቅ በገጠር ከተሞች ስርጭቱ የባሰ ሆኖ የታየበት አጋጣሚም አለ ። ለምሳሌ በነፍሰ ጡር እናቶች ቅኝት የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ በማይጨው ሆስፒታል 6ነጥብ 6 ሲሆን በጨርጨር ጤና ጣቢያ  ግን  6ነጥብ 8 በመቶ መድረሱ ተረጋግጧል ።

የኮረም ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ለተገርግስ ተስፋይም ባለፉት አመታት በከተማው የኤች አይቪ ኤድስ የግንዛቤ ማሳደጊያ፣ የትምህርት ቤቶች የፀረ ኤድስ ክለባትና የወጣቶች አቻ ለአቻ ትምህርት፣ የደም ምርመራና የኮንዶም ስርጭት በመከናወኑ የበሽታው ስርጭት ቀንሶ አንደነበር ተናግረዋል።

በተለይ በከተማው ቫይረሱ ባለባቸው 700 የሚጠጉ ሰዎች የተመሰረቱ ሶስት ማህበራት የሚያከናወኑት የትውልድ እናድን ትምህርታዊ ስራዎች ለበሽታው መቀነስ ገንቢ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነበር ።

ይሁንና ከበሸታው ስርጭት መቀነስ ጋር ተያይዞ ቸልተኝነት ተፈጥሯል ያሉት ሃላፊዋ ይህም በአሁን ግዜ በከተማውን የበሽታው ስርጭት መጠን ወደ 1.5 በመቶ ከፍ እንዳደረገው ነው የሚናገሩት።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ በበኩሉ በሽታውን ለመከላከል ቀደም ሲል ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች መቀዛቀዛቸውን ተከትሎ መዘናጋት መፈጠሩ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ዳግም እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

በዞኑ በ2009 ዓ.ም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የጤና ምርመራ ካደረጉት 126 ሺህ ነዋሪዎች መካከል 933ቱ  ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱን ነው የሚናገሩት በመምሪያው የጤና ልማት ቡድን መሪው አቶ መሳይ አበበ።

ካለፈው አመት ጋር ሲታይ በዞኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ566 ብልጫ ማሳየቱ በአካባቢው የበሽታው ስርጭት እየተስፋፋ ለመምጣቱ በቂ ማስረጃ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መለኪያ በሽታው ወደ ወረረሽኝ አድጓል የሚባለው ከአንድ በመቶ በላይ ሲደርስ ነው ያሉት አቶ መሳይ ከዚህ አንፃር አሁን ያለው በዞኑ  በሽታው ስርጭት ሽፋን ከ1.5 በላይ በመሆኑ አካባቢው በችግሩ ውስጥ እንዳለ ያረጋግጣል ብለዋል ።

ነገር ግን አሁንም ኤች አይ ቪ ቫይረስን ለመግታት ጊዜው አልረፈደምና መዘናጋት ባስከተለው ችግር ምክንያት በዞኑ የሚታየው የበሽታው ወረርሽኝ ሳይባባስ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው ።

በዚህ አመት የዞኑን ህዝብ ንቅናቄ በመጠቀም የህብረተሰቡን  ግንዛቤ ለማሳደግ የሚረዱ ሰፊ የትምህርትና ስልጠና ስራዎች ታቅደው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እንቅስቃሴ ማድረግ   ተጀምሯል።

በቅርቡ የወጡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በትግራይ ክልል የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ 1ነጥብ 81 በመቶ ነው ። በዓመት በአማካይ  1ሺህ 899 አዳዲስ ሰዎች  በቫይረሱ ይያዛሉ። በዓመት በአማካይ ደግሞ 1 ሺህ 473 ሰዎች በበሽታው ይሞታሉ ።

መቀሌ ፣ ቃፍታ ሁመራ ፣ ደጓ ተምቤን ፣ ዓዲግራት ፣ ራያ አዘቦና ኮረም ከ3 ነጥብ 5 በመቶ በላይ የስርጭት ምጣኔ የሚታይባቸውና ልዩ ዘርፈ ብዙ ምላሽ የሚያስፈጋቸው አካባቢዎች ናቸው ።

የቫይረሱን ስርጭት ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ አምራች ሃይልና  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሃላፊነቱን የተሸከሙ ሴቶችን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ ነው ። የነገ አገር ተረካቢ ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ የሚጣልባቸው ህፃናትም ያለአሳዳጊ እንዲቀሩ የማድረግ አቅም አለው።

አሁንም ግን መፍትሄው በእጃችን ነው ። ዋናው ነገር ኤችአይቪ ኤድስን የመከላከል ጥረት የአመራሩና የህዝቡ ቀዳሚ አጀንዳ ማድረግ ነው ። የመገናኛ ብዙሃንም አስከፊነቱን በማስተማር በህዝብ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠርና የማሳደግ ስራ እንዲሰሩ ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል። አጋር ተቋማትንና የሲቪክ ማህበራትን በንቅናቄው ንቁ ተሳታፊ ማድረግም እንዲሁ።

የሶስቱ 90ዎች መርህ መተግበር ደግሞ ለስርጭቱ መከላከል ወሳኞች ናቸው ። ቀዳሚው  ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው ከሚገመቱት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው እራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው ።

ሁለተኛው ተመርምረው እራሳቸውን ካወቁ ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑትን ወዲያውኑ ፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት እንዲጀምሩ ማድረግ ይሆናል።

ሶስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ መድሃኒት መውሰድ ከጀመሩ ዜጎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት መድሃኒቱን በትክክልና በተከታታይነት ያለማቋረጥ እንዲወስዱ በማድረግ ቫይረሱን መተላለፍ በማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማዳከም ነው ።

እነዚህንና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችን አቀናጅተን መረባረብ ከቻልን ቫይረሱን መከላከል ብቻ ሳይሆን እ.ኤ.አ በ2030 ኤድስን ማስቆም ይቻላልና ሳይቃጠል በቅጠል እናድርገው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን