አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ስኬት የተንጸባረቀባቸው መድረኮች

28 Sep 2017
3026 times

ጌታቸው ሰናይ-ኢዜአ

የዓለም አገሮች መሪዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 72ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔን በኒውዮርክ አካሂደዋል።  በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ "ልዩ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል" ያሉትን ጉዳይ አንስተው መክረዋል።

የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ  አንቶኒዮ ጉተረስ ወደ ድርጅቱ ሲመጡ 'ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ያሉትን ድርጅቱን የማደስ ሀሳብ አቅርበዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተቋሙ አቋም ዓለም የደረሰችበትን ስልጣኔ ስለማይመጥን ድርጅቱ መታደስና በአዲስ የአሰራር መንፈስ ውስጥ መግባት ያስፈልገዋል። ይህ ሀሳብ በአባል አገሮቹም ተስተጋብቷል።

የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንፕን ጨምሮ የሌሎች አገሮች መሪዎችም ድርጅቱ አሁን ባለበት አቋሙ ብዙ መራመድ እንደማይችልና መታደስም እንደሚያስፈልገው እምነታቸው በመግለጽ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ለዓለም ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን አገሮች ባመሰገኑበት፣ በአስጊነት ለጠቀሷቸው ደግሞ ማስጠንቀቂያ ባስተላለፉበት ንግግራቸው "ተሃድሶው እውን መደረግ አለበት" የሚለውን አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹት፤ የመንግስታቱ ድርጅት በዋናው ተልዕኮው ላይ አተኩሮ ለመስራት ተሃድሶ የማድረጉ አስፈላጊነት አያጠያይቅም።

በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ጎታች የአሰራር ሂደቶችና ውስብስብ ቢሮክራሲዎች እንዲወገዱም ነው ያሳሰቡት። አዲሱ ዋና ጸሀፊ ጉተረስ ሙሉ ስልጣናቸውን በመጠቀምና ቀጥተኛ ውሳኔ በማስተላለፍ ተሃድሶውን እውን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ነው በመልዕክታቸው ጠንከር አድርገው የገለጹት።

በተለይ ልማት፣ ሠላምና ደህንነት ከማረጋገጥና ወጥ አስተዳደራዊ ሥርዓት ከማስፈን አኳያ ተመድ የሚጠበቅበትን ያህል  "አልሰራም" ሲል የትራንፕ አስተዳደር ይወቅሳል።

የተራቡትን መመገብ፣ አደጋ ሲከሰት ድጋፍ ማድረግና ለሰው ልጆች ክብር መስጠት የመሳሰሉ ተግባራቱም ቢሆኑ በውስብስብ ቢሮክራሲና በአስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻለም ነው የተናገሩት።

አሜሪካ ተመድ ከዕለት ተዕለት የስራ ሂደት ይልቅ ውጤት በሚያስመዘግብ ተግባራት ላይ ማተኮር አለበት የሚል አቋም አላት። ስለዚህ ተሀድሶው አስፈላጊ ነው።

የድርጅቱን ተሀድሶ ኢትዮጵያም የምትፈልገው መሆኑን በተግባር አሳይታለች። በተለይ ደግሞ የፀጥታው ምክር ቤት የሰላም ማስከበር ሰነድን አሻሽላ በማቅረብ የነበራት የመሪነት ሚና ቁርጠኝነቷን ያሳየችበት፤ ለተሃድሶው በአንድ እርምጃ የቀደመችበትም ነው።

መድረኩ ኢትዮጵያ ውጤታማ ስራ ያከናወነችበትና ጎልታ የታየችበት ነው። በተጓዳኝ በተካሄዱ ስብሰባዎችና የተለያዩ ተግባራት ቀዳሚ መሆኑዋን ያስመሰከረችበትም ነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ አሁን "የተመድ ሰላም አስከባሪዎች የሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ያለው ሁኔታ የሰላም አስከባሪዎቹ ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ ባለመታጠቃቸው ሰላምን ለማረጋገጥ እና ሰዎችንና ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል እያቃታቸው መጥቷል" ብለዋል። ይህም ሆኖ ግን ከኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ተግባር የተሰማሩ ሰራዊቶቿ ውጤታማነት በተጨባጭ የሚታይ እውነት ነው።

"ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ባላት ጠቃሚ ሚና ትኮራለች" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁንም ይሄንን ተግባሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ያረጋገጡት። 

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት  የሰላም ማስከበር አሰራር እንዲሻሻል የጸና ፍላጎቷን በተግባር ማሳየቷን ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያ ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት በተወዳደረችበት ወቅት ልትተገብራቸው ቃል ከገባቻቸው ጉዳዮች አንዱ ጉዳይም ይሄው ነበር።

አገሪቷ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1967 እስከ 1968 በኋላም ከ1989 እስከ 1990 የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በሆነችባቸው ጊዜያትም በርካታ ተግባራትን በማከናወን ለዓለም ሰላምና ደህንነት ያላትን ቀናኢነት በተግባር አሳይታለች። ዛሬም ይህን ተግባሯን አጠናክራ መቀጠሏን ነው በተጨባጭ ያስመሰከረችው።

በተለዋጭ አባልነት ስትመረጥ በነበረበት ወቅት በአደባባይ ከተመሰከረላትና ከተወሱት ታሪኮች አንዱ በ50 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ ከ49 ሺ በላይ የሠላም አስከባሪ ሠራዊት ማሰማራቷ ነው። ይህ ደግሞ በሰላም ማስከበር በኩል ግንባር ቀደም አገር እንዳደረጋት ነው ታሪክ የሚያሳው።

በርግጥም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ ለዓመታት መስራቷ በታሪክ የተመዘገበ እውነት ነው። በኮንጎ፣ በኮርያ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና ሌሎች አገሮች የነበራት የሰላም ማስከበር ተግባራት ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ኮንጎ ነጻ ከወጣችበት ማግስት ጀምሮ አገሪቷን የማረጋጋት ተግባር ላይ ተሰማርቶ ነበር። በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋና በላይቤሪያ ከርስ በርስ ግጭት በኋላ የሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፤ በዚህም ታሪክ ይዘክራታል።

ለዚህ ድንበር የለሽ አስተዋጽኦዋም ዓለም በተደጋጋሚ አመስግኗታል። የፀጥታው ምክር ቤት መስራች አባል መሆኑዋና በተለዋጭ አባልነት ማገልገሏ ሲታይ ለዓለም ሰላም ያላት አቋም የማይናወጥና ቀጥተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

በሰላም ማስከበር ተግባር ላይ የነበሩትና ያሉት ኢትዮጵያውያንም ስለህዝብ አገልጋይነታቸውና ተቆርቋሪነታቸው ምስክርነት ተሰጥቷቸዋል፤ በተሰማሩበት አካባቢ ሁሉ መልካም ስምና ዝናም ተጎናጽፈዋል። ሰላም አጥተው በችግር ውስጥ ያሉትን ሰላማቸውንና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ከማድረግ ባሻገር በአካባቢ ልማትም የተሳተፉበት ሁኔታ ከዓለም ማህበረሰብ አድናቆት እንዲቸራቸው ምክንያት ሆኗል።

ከመንግስታቱ ድርጅት 72ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደ ስብሰባ ላይ "የሰላም አስከባሪ ሠራዊታችን በሚያሳየው ብቁ አፈጻጸም እንኮራለን" የሚል መልዕክት ያዘለው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ንግግርም አገሪቷ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የምታሰማራው ሠራዊት ለህግና ለወታደራዊ ስነ ምግባር የሚገዛ፣ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት የሚፈጽም መሆኑን ያንጸባረቀ ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ከስምንት ሺ በላይ የሰላም አስከባሪ ሃይል አሰማርታለች። በተባበሩት መንግስታት ጥላ ስር በመሆን በዳርፉር፣ አብዬና ደቡብ ሱዳን የሚገኙ የሰላም ማስከበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ለብዙዎች የመኖር ተስፋን የጫሩ፣ በየተሰማሩበት አካባቢ የየአገሮቹ ዜጎች ወጥቶ ለመግባት ያለባቸውን ስጋት የቀነሱ፣ ጥላ ከለላ መሆን የቻሉ ናቸው ።

ኢትዮጵያ ካላት ተሞክሮ በመነሳት ነበር በ15ቱም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ተቀባይነት ያገኘላትን የሠላም ማስከበር ተግባርን የሚያሻሽል ሰነድ ያዘጋጀችው።ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል፤ በተለይ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሆነችበት ወቅት መፅደቁ እጅግ ልዩ ያደርገዋል።

የፀጥታውን ምክር ቤት ስብሰባን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የሰላም ማስከበር ማሻሻያ ሀሳብ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በሙሉ ድምጽ በማጽደቃቸው አመስግነዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጻ፤ አገሮቹ ያደረጉት ድጋፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚከናወነውን ሰላም የማስጠበቅ ተግባር ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን ያላቸውን ዝግጁነትም ያመላክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ኢትዮጵያ የሠላም ማስከበር ተግባርን ለማሻሻል ካላት ተሞክሮ በመነሳት ያዘጋጀችው ሰነድ በሁሉም አባል አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁ "ለኢትዮጵያ ትላቅ ስኬት ነው" ብለውታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ”ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሷን በስኬት አረጋግጣለች” ሲሉ የገለጹትም የምክር ቤቱን ጉዳይ በአብነት አንስተው ነው።

በተለይ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሆነችበት ወቅት የጸደቀው የማሻሻያ ሀሳብ መልካም አጋጣሚ ነበር። ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም የቆመች መሆኑንም ያመላክታል።

የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ "ኢትዮጵያ  የዓለም ሰላም ሻምፕዮን ናት" ሲሉ አሞግሰዋታል።

የተለያዩ አገሮች መሪዎችና  ተወካዮች በወቅቱ ባሰሙት ንግግር ያረጋገጡትም ይሄንኑ ነበር። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሸንኮ፤ "ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር መስክ እጅግ የሚደነቅ ታሪክ አላት" ማለታቸው ለዚህ በዋቢነትይጠቀሳል።

አገሮች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሰራር መለወጥ፣ ዘመኑ በሚፈቅደው አደረጃጀት ላይ መገኘት እንዳለበት አጽንኦት በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ማሻሻያ ሀሳብ አቅርባ በሙሉ ድምጽ በማስጸደቋ አድናቆታቸውን ቸረዋታል።

የተባበሩት መንግስታት ለሚያደርገው ተቋማዊ ተሃድሶ አንድ አመላካች ነጥብ ተደርጎም ተወስዷል። የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የማሻሻያ ሀሳቡ በሙሉ ድምጽ መጽደቁን "ታላቅ ግምት የሚሰጠው ነው" ሲሉም አሞካሽተውታል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኬ በበኩላቸው፤ የሰነዱ መጽደቅ ኢትዮጵያ "ለዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ላበረከተችው ጉልህ አስተዋጽኦ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ይህ ሰነድ የብዙዎችን አዎንታ ያገኘው ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም የምታደርገውን አስተዋጽኦ በሁሉም አቅጣጫ ማጠናከሯ ግንዛቤ ውስጥ በመግባቱ ነው። የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በማሻሻል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መሆኑ ደግሞ ድጋፍ ለማግኘቱ ተጠቃሽ ነውም ተብሎለታል።

የፀደቀው ሰነድ በተባበሩት መንግስታት ጥላ ስር የሚከናወነው ሰላም የማስጠበቅ ተግባር ለማጠናከርና ተልዕኮውን በተሳካ መልኩ እንዲያከናውን የሚያስችል አሰራር ለመፍጠር እንደሚረዳም ታምኖበታል።

የተመድ የሰላም ማስከበር ተግባር አፈጻጸም ያሻሽላል፣ የሰላም አስከባሪው ሠራዊት ስራውን በብቃትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን በሚያስችል መልኩ እንዲደራጅ ለማድረግ እድል ይሰጣል የሚል እምነትም ተጥሎበታል።

የሰላም ማስከበር ኃይል ተልዕኮው እንዲሳካ የገንዘብ አቅሙን ለማጠናከር ያግዛል የተባለለት ማሻሻያው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት በተቀናጀ መልኩ ለመስራት እንደሚያስችላቸውም ታምኖበታል።

በተለይም የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ በሚያሰማራበት ወቅት ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት እንዲችል በገንዘብ የሚደገፍበትን መንገድ ያመላክታል። የተመድ የሰላም ማስከበር የማሻሻያ ውሳኔ ሃሳብ 2378/2017 ከተጨባጭ ተሞክሮ የተቀመረና አሁን ከሚስተዋለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንደሚጣጣም አገሮች እማኝነት ሰጥውታል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ ሊቀ መንበርነቷ በደቡብ ሱዳን ሠላም ለማምጣት ውይይቶች አካሂዳለች። እንደገና ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገቡ በማለት ያቀረበችው ሀሳብም ተቀባይነት አግኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ሩዋንዳ የተወጣጣው የሠላም ማስከበር ኃይል የመከላከል ስራ እንዲያከናወን በተወሰነው መሰረት ስራ መጀመሩንም አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይም ሶማሊያን ወደ ተሻለ መረጋጋት ለማምጣትና አሸባሪውን አልሸባብ ለማጥፋት የሚቻልበት ስልት ላይም ተወያይተዋል። በአልተሟላ መንግስታዊ መዋቅርና መሰረተ ልማት ጠንካራ ሶማሊያን መገንባት እንደማይቻልም መግባባት ላይ ተደርሷል። ለዚህ ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ በማድረግ “ለውጥ ማስመዝገብ ይገባል” የሚል ሀሳብም በጉልህ ተንጸባርቋል።  በፀጥታው ምክር ቤት የአሚሶም የመቆያ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ተገቢ መሆኑም ነው የታመነበት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንዳሉት፤ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሠላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም) እንዲቆይ የተሰጠውን ውሳኔ በሙሉ የፋይናንስ አቅም በመደገፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት እንዲመጣ መስራት እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።

አሚሶምን በማጠናከር አልሸባብ እንዲዳከም ማድረግ የሚያስችል ስራ በፍጥነት መሠራት እንዳለበት ስምምነት ተደርሷል። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ያደረገችው ጥረት የተሳካ ነው።

በምክክሩ ከሁሉም በላይ የሶማሊያን መንግስት የፖለቲካ ሂደት የሚያውኩ አካላትን ማስቆም እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል።

ለሶማሊያ ሠላም ማስከበር ሠራዊት ያዋጡት ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ብሩንዲና ኬንያ ያካሄዱት ስብሰባም ሶማሊያን ለማጠናከር የጋራ አቋም የተያዘበትና ስኬታማ ነበር።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት በተዘጋጁ መድረኮችም ላይም ሆነ ለጠቅላላው ጉባዔ ያላትን አቋም አንጸባርቃለች። የአየር ንብረት ለውጡ ልብ ወለድ ሳይሆን የእያንዳንዱን በር እያንኳኳ መሆኑን በቅርቡ የዓለም አገሮች ላይ የደረሱትን ክስተቶች ለአብነት በመጥቀስ ጭብጧን አስረድታለች። በአገሮች ላይ በተጨባጭ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ለማሳየት ጥራለች።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢትዮጵያ ድርቅ መከሰቱ፣ ሌሎች ደግሞ በአውሎ ንፋስና ጎርፍ መጠቃታቸው የችግሩን አሳሳቢነት እንደሚያሳይ በውይይት ወቅት ትኩረት ተሰጥቶታል።

"በየዕለቱ በአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖ ስር ወድቀን እየኖርን ነው። አሁን ስለጉዳቱ የምንከራከርበት ወቅት ሳይሆን ለለውጥ በጋራ የምንሰራበት ጊዜ መሆን አለበት" በማለት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኢትዮጵያን አቋም ያንጸባረቁት።

አውሮፓ ህብረትና አባል አገሮቹ፣ ቻይና፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ትናንሽ ደሴቶችና ሌሎችም ለፓሪሱ ስምምነት ተፈጻሚነት አጋርነታቸውን አሳውቀዋል።  በአየር ንብረት ለውጥ መድረክም ኢትዮጵያ የአፍሪካን ውክልና በመቀጠል አቋሟን አጽንታ ወጥታለች።

በእነዚህና በሌሎች መድረኮች ኢትዮጵያ ጎልታ ወጥታለች። ጉባዔውና ተጓዳኝ መድረኮች ተሰሚነቷን ያረጋገጠችባቸው ናቸው። የአፍሪካ ድምጽ አጉልታ በማሰማት ዛሬም እንደትናንቱ አቋሟ የማይናወጥ መሆኑን ያረጋገጠችበት መድረኮችን ተካፍላለች።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን