አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ብአዴን ምን አለ ?

28 Sep 2017
7199 times

                                           እንግዳው ከፍያለው (ኢዜአ)

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ ብአዴን/ ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በባህርዳር ከተማ ሰሞኑን ማካሄዱ ይታወቃል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በ2009 በጀት ዓመት መደበኛ የልማትና የፖለቲካ ስራዎች፣ በድርጅቱ ወጭና ገቢ ሁኔታ፣ በበጀት ዓመቱ እቅድና በሌሎች ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ መክሯል፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ማዕከላዊ ኮሚቴው የመከረባቸውን  አበይት ጉዳዮች በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎችም እንዲሁ፡፡

አቶ ደመቀ እንዳብራሩት ማዕከላዊ ኮሚቴው የ15 ዓመት የተሃድሶ ጉዞውንና የ2009 በጀት ዓመትን የተሃድሶ ንቅናቄ ገምግሞ ችግሮችን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለመፍታት ርብርብ ያደረገበት ዓመት እንደነበር አረጋግጧል፡፡

ከድርጅቱ የበላይ አመራር እስከ ተራ አባልና ማህበረሰቡ ድረስ የወረደው የተሃድሶ ንቅናቄ የደረሰበት ደረጃ፣ የተመዘገቡ ስኬቶችና የተስተዋሉ ችግሮች ላይ በመምከር የድርጅቱና በየደረጃው  ያለው አመራር የነበረው ሚና ተተንትኗል። በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁለንተናዊ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ማዕከላዊ ኮሚቴው በግምገማው ተገንዝቧል፡፡

በተለይም ወደ ተሃድሶ ሲገባ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች ዋናዎቹ የአስተሳሰብ ግልጽነትና የአመለካከት ዝንፈቶችን ማረም፣ የወጣቶችና የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ፣ ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም አዝማሚያን ማቆምና የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን ለመናድ የተደረጉ ጥረቶች ቀጣይ ስራ የሚጠይቁ ቢሆንም በትክክለኛውና በሚፈለገው መስመር እየተጓዙ መሆኑን  ድርጅቱ መገምገሙን አስረድተዋል።

ህበረተሰቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሙስናና ብልሹ አሰራርና ሌሎች የመልካም አስታደደር ችግሮች ለይቶ በተግባር የመፍታት ሂደቱ ስኬት የተገኘበትና ለቀጣይ ስራም ተሞክሮው መስፋት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ያለፉት 15 ዓመታት የህዳሴ ጉዞ በጥልቀት መገምገሙ በቀጣይ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስራዎች ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ፈጥኖ ለማረምና ሀገሪቱ ልትደርስ ያሰበችበትን መካከለኛ ኢኮኖሚ ለማሳካት የሚያስችል ልምድ ተገኝቶበታል፡፡

“የጠራ አስተሳሰብና ግልጽ አቅጣጫ ይዘው በተቀየሱ ፖሊሲዎችና ስትራተጅዎች ላይ መረባረብ ማለት ተግባርን በአስተሳሰብ መምራት ማለት ነው” ያሉት አቶ ደመቀ  ከዚህ አንጻር ድርጅቱ የልማት ስራዎችንም ሆነ በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የአመራሩ ቁርጠኝነት የት ላይ እንደነበር መፈተሹንም ነው ያብራሩት።

“በብአዴን ደረጃ ከበላይ አመራሩ እስከ ታችኛው አባል ድረስ የተስተዋለውን የትምክህት አስተሳሰብና ተግባር”ከማጥራት ጋር በተያያዘ ስራው ቀጣይነትን የሚጠይቅ ቢሆንም እስካሁን የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑንም ማዕከላዊ ኮሚቴው በግምገማው ማንሳቱን አቶ ደመቀ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ በመንግሥት መዋቅሮች ምሁራንን በአመራር ደረጃ መመደቡ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በእቅቀትና በሳይንሳዊ መንገድ ለመፈጸም በማስቻሉ በስራ እድል ፈጠራ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና የህዝብ ጥያቄዎችን በመፍታት ረገድ ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አቶ ደመቀ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አብራርተዋል፡፡

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት፣ ሁከትና ብጥብጥ በማስወገድ ህዝብና መንግስት የጋራ ጠላት በሆነው ድህነት  ላይ ብቻ አተኩረው ርብርብ ማድረግ የቻሉበትና ቀላል የማይባል ውጤት የተመዘገበበት ዓመት እንደነበር ማዕከላዊ ኮሚቴው መገምገሙንም ነው የገለጹት፡፡

የድርጅቱ ሊቀ መንበር እንዳብራሩት የተካሄደው የተሃድሶ ንቅናቄ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በመናድ በልማታዊነት አስተሳሰብ የመተካት ዓላማ የነበረው ሲሆን በዚህም አብዛኛውን አመራርና አባላት በልማታዊ አስተሳሰብ ማሰለፍ ተችሏል። በትግል ሂደቱ ህዝቡን ተሳታፊ ማድረግና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶታል።

አመራሩ፣ አባላትና የመንግስት መወቃቅሩ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል፣ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮች እንዲዳብሩ በማድረግ የነበሩ ችግሮችን በማረምና ለህዝቡ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ያደረጉት ጥረትና የተገኘው ውጤት አመርቂ እንደነበርም ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል።

በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ባለፈው ዓመት የተገኙ ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ችግሮችን ፈጥኖ በማረም በዘላቂነት ህዝባዊ እርካታ ለመፍጠር የሚደረገው እንቅስቃሴ በ2010 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  አቅጣጫ አስቀምጧል።

በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነትና ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ትግሉ በአንድ ጊዜ ተካሂዶ የሚቆም ሳይሆን መንግስት በለያቸው የከተማ መሬት አስተዳደር፣ የመንግስት ግዥ፣ የንግድ ስርዓት፣ ገቢና ሌሎች ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጡ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ በየጊዜው ከየወቅቱ ሁኔታ ጋር የተጣጣመና ተጠናክልሮ የሚቀጥል ትግል ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑ ተሰምሮበታል።

ከቅማንት ህዝበ ውሳኔ፣ ከጠገዴና ጸገዴ የወሰን ጉዳይ፣ ሰሜን ጎንደርን መልሶ ከማደራጀቱ አስፈላጊነትና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎችም የብአዴን ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እንደ አቶ ደመቀ ማብራሪያ  በአማራ ክልል ጠገዴና በትግራይ ክልል ጸገዴ ወረዳዎች  ሲነሳ የነበረው የወሰን ጥያቄ ምንም ይሁን ምን ከዚህ በላይ ጊዜ ሊወስድ አይገባም።  በሁለቱ ወረዳዎች መካከል ለዓመታት ሲንከባለል የቆየው የወሰን ችግር መፈታቱ በህዝቡ ዘንድ ያለውን በጋራ የመልማት ፍላጎት እንደሚያረጋግጥ “ብአዴን ሙሉ እምነት አለው” ሲሉ ገልጸዋል።

ችግሩ ሲንከባለል የቆየው  አመራሩና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ካለመስጠት እንጂ ችግሩ ከህዝቡ የመነጨ አለመሆኑን አብራርተው   “ህዝቡ ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አብሮ የኖረና የሚኖር፣ የጋራ ታሪክ ያለውና ታሪኩን ለማስቀጠል የሚሰራ፣  የጋራ ተጋድሎ ያደረገና የሚያደርግ፣ ለዘመናት የዘለቀውን ኢኮኖሚያዊና ማህብራዊ ትስስር በማስቀጠልና አብሮ የመልማትና የማደግ ፍላጎት ያለው ነው” ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ክልሎች መንግስታት የአካባቢውን ነዋሪዎች በማሳተፍ የወሰኑን ችግር መፍታታቸውን ህዝቡ አወንታዊ በሆነ መልኩ የተቀበለው ለዚህ መሆኑንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡

ችግሩ እልባት ማግኘቱ ህብረተሰቡ ናፍቆት የኖረውን  በአካባቢው ዘላቂ ሰላም የመገንባትና፣ የሁለቱን አጎራባች ህዝቦች ወንድማማችነታቸውን የማጠናከር ፍላጎት ለማሟላት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የብአዴን ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ ያወሱት።

የጋራ እቅድ በማቀድና የልማት ፕሮጀክቶችን በጋራ በመተግበር በአዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አስምረውበታል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ከሶስት የተከፈለበት ምክንያት ዞኑ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት ፣ አስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው በመሆኑና ከህዝብ ብዛት አንጻር ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ በተካሄደ ጥናት በመጀመሪያ የማያሻማ አሰፋፈር ያለባቸው  ቀበሌዎች ተለይተው የራስ አስተዳደር መመስረት እንዲችሉ ክልሉ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ የሁለቱንም ህዝቦች ጥቅም በማይጋፋ፣ መከባበርንና መፈቃቀርን በሚያረጋግጥ መልኩ መፈጸም እንደሚገባው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።

ጥያቄ የተነሳባቸው ቀበሌዎች  ጉዳይም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ   በምርጫ ቦርድ አማካኝነት በህዝብ ድምጽ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተደርጓል።

 መሪ ድርጅቱ ብአዴንና የክልሉ መንግስት በህዝብ ፍላጎት የሚሰጠውን ውሳኔ በማስከበርና  ፈጣን አደረጃጀት በመፍጠር  ወደ ልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ትግበራ እንዲሸጋገር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ  ሊቀመንበሩ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ደመቀ እንዳመለከቱት አደረጃጀቱን ፈጥኖ ወደ ተግባር ማስገባት የአካባቢው ኢኮኖሚ እንዲጠናከርና እንዲጎለብት ያደርገዋል ። ይህም በመንግስት ላይ የበጀት ጫና መፍጠሩ የማይቀር ቢሆንም  መሪ ድርጅቱና መንግስት በሚሰጡት አቅጣጫ  ይሳካል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን