አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የተዳፈነ እሳት አለ!

20 Sep 2017
5005 times

 ገብረህይወት ካህሳይ (ኢዜአ)

የተዳፈነ እሳት አለ ! ። አዎን ! የተዳፈነ ግን ደግሞ እድል ካገኘ የሚለበልብ ሳይሆን በእጅጉ የሚፋጅ - እሳት ። በእሳቱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 70 በመቶ መቀነስ ችለናል ። ግን ደግሞ አሁንም በዓመት በአማካይ 19 ሺህ ዜጎቻችን በእሳቱ ይሞታሉ ።

ወደ እሳት ቀጠናው የሚገቡትን 90 በመቶ ቀንሰናል ። ግን አሁንም በዓመት በአማካይ 27 ሺህ ዜጎቻችን  እንደ አዲስ ወደ እሳት ቀጠናው ውስጥ እየገቡ ነው ። እንደ አገር እሳቱን የረገጡት ደግሞ 700 ሺህ ዜጎቻችን በህይወት አሉ ።

ችግሩ የምናነሳው ዓለም በመሰከረለት አስደማሚ ስኬቶች ላይ ሆነን ነው ። በታላቅ አገራዊ ርብርብ  ለስኬት ባንበቃ ኖሮማ እሳቱ ትውልድን የመፍጀትም አቅም ነበረው ።

ሰደድ እሳቱ እ.አ.አ በ1981 በዓለም አቀፍ ደረጃ መቀጣጠል ሲጀምር ወደ አገራችን የተዛመተው በ1978 ዓ.ም በሁለት ሰዎች አማካኝነት እንደሆነ ይነገራል ። 10 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን ሽፋኑን 13 በመቶ አዳረሰው ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችንም ለህልፈት ዳረጋቸው ።

የእሳቱ መስፋፋት እጅግ አደገኛ ነበርና ክፉኛ አስደነገጠን ። መንግስት ቀዳሚ አጀንዳ አደረገው ። የመገናኛ ብዙሃን ግንዛቤን የማጎልበት ስልት ቀርፀው የመከላከል ጥሪ አስተጋቡ ። ባለድርሻ አካላት ወገባቸው ጠበቅ አድርገው ተነሱ ። የዓለም ማህበረሰብም ከጎናችሁ ነን የሚል ምላሽ ሰጠ ።

እናም እሳቱን ማጥፋት ባንችልም እንዲዳፈን አደረግነው። የበርካታ ወገኖቻችን ህይወትም መታደግ ተቻለ። የስርጭት ምጣኔውም ከ13 በመቶ ወደ 1ነጥብ 18 በመቶ ዝቅ አደረግነው ። ዓለምም አጨበጨበልን። ለድንቅ ስኬት ተገቢው እውቅናም ተሰጠን።

እውቅናው ኤችአይቪ ኤድስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያደረግነው ባለዘርፈ ብዙ ምላሽ ርብርብና ላስመዘገብነው አንፀባራቂ ስኬት የተሰጠ ነበር። ስኬቱን ተከትሎ ግን መቀዛቀዝና መዘናጋት ተፈጠረና ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆን ዳግም ስጋት ተፈጠረ።

ሽፋኑን ወደ 1 ነጥብ 18 ዝቅ አደረግነው ስንል ምን ማለታችን ነው? በዓለም አቀፍ የኤችአይቪ ወረርሽኝ ፍች መሰረት የሽፋን ምጣኔው ከ1በመቶ በላይ ከሆነ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በወረርሽኝ መልክ አለ ማለት ነው። ይህ ደግሞ አሁንም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ያመላክታል።

ሌላው የስርጭት ምጣኔው 1ነጥብ 18 ነው ስንል 718 ሺህ 550 ወገኖቻችን ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል ማለት ነው። በየዓመቱ  27 ሺህ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙና 19 ሺህ በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች እያሉን እንዴት እንቅልፍ ሊወስደን ይችላል? ።

የፌዴራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበር ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ምትኩ ያቀበሉኝ መረጃ እንደሚያመላክተው 1ነጥብ 18 የስርጭት ምጣኔ ላይ እንገኛለን ሲባል በሁሉም አካባቢዎች እኩል ስርጭት ይታያል ማለት አይደለም ።

ከክልል ክልል፣ በክልል ውስጥም ከቦታ ቦታ፣ በከተማና በገጠር እንዲሁም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ይለያያል ፡፡ የደቡብ ክልል የስርጭት ምጣኔ 0.54 ብቻ ሲሆን አዲስ አበባ ደግሞ በ4.9 በመቶ የምጣኔ ሽፋን ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል  ።

ቤንሻንጉል ጉሙዝ 0.61 ፣ ኢትዮ ሶማሊ 0.75 ፣ ኦሮሚያ 0.82 ፣ አፋር 0.88 ፣ አማራ 1.5 ፣ ትግራይ 1.81 ፣ ድሬዳዋ 2.9 ፣ ሀረሪ 2.95 ፣ ጋምቤላ 4 የምጣኔ ስርጭት እንደሚታይባቸው የፅህፈት ቤቱ መረጃ ይጠቁማል።

በአማራ ክልል  የስርጭት ምጣኔው 1.5  በመቶ በመሆኑ ዝቅተኛ መስሎ ሊታየን ይችላል ። ግን አይደለም ። ከህዝቡ ብዛት አንፃር የስርጭት ምጣኔው ዝቅ ቢያደርገውም  204 ሺህ 481 ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች በክልሉ ይገኛሉ ። ከአጠቃላይ ቁጥርም 28 ነጥብ 5 በመቶ ይይዛል ።

ኦሮሚያ ክልል የስርጭት ምጣኔው 0.82 በመቶ ብቻ ነው። ነገር ግን ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ቁጥር 185 ሺህ 516 ይደርሳል። ከአገሪቱ አጠቃላይ ኤችአይቪ በደማቸው ከሚገኝ ወገኖች አንጻር ሲታይ ደግሞ የ26 በመቶ  ድርሻ ይወስዳል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 127 ሺህ 619 እና የደቡብ ክልል ክልል 68 ሺህ 971 ሲጨመርበት  አራቱ ብቻ ከአገሪቱ አጠቃላይ ኤች አይቪ በደማቸው ከሚገኝ ወገኖች ውስጥ 82 በመቶ እንደሚሸፍን መረጃው ያሳያል፡፡

በ2007 ዓ.ም የኤች አይ ቪ ግምት ትንቢያ መሠረት በ2009 ዓ.ም አዲስ በኤች አይ ቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአገር አቀፍ ደረጃ 27 ሺህ 288 ሰዎች ሲሆን  አማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ አዲስ አበባ ፣ ደቡብና ትግራይ 93 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል ።

ስርጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከተማ በሌላው አካባቢ ደግሞ በገጠር ከፍ ብሎ ይታያል። እንዲያውም በማይጠበቁና በማይገመቱ የገጠር አካባቢዎች ጎልቶ የታየበት አጋጣሚ አለ ።

በትግራይ ደጓ ተምቤን ስርጭቱ ከ3ነጥብ 5 በመቶ በላይ ነው።በአማራ ሸዋሮቢትና ምንጃር ሾንኮራ ስርጭቱ 4 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል ሲባል ያስደነግጣል። በኦሮሚያ ነገሌና ሻኪሶ ከ8 በመቶ በላይ አሻቅቧል ሲባል ራስ ምታት ነው። በጋምቤላ ጎግ ወረዳ ሳይቀር ስርጭቱ ከ6ነጥብ 6 በመቶ በላይ ዘሏል!! አሳሳቢ ነው።

አዳዲስ በሚፈጠሩ ከተሞችና በትላልቅ የልማት ተቋማት አካባቢ ስርጭቱ  ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ  መምጣቱን  መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ለማሳያ ያክል በአበባ እርሻ ስራ የተሰማሩ የገጠር ወጣት ሴቶች ከቤተሰብ ተለይተው በመኖራቸው ምክንያት ጥንቃቄ ለጎደለው የግብረስጋ ግንኙነት በመጋለጣቸው 25 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ውርጃ  መፈፀማቸውን  የየፅህፈት ቤቱ ጥናት ያመላክታል፡፡

በመተማ አካባቢ በሚሰሩ ተንቀሳቃሽ ሰራተኞች ላይ በተደረገ ጥናት ደግሞ 68 በመቶ የሚሆኑት በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ከትዳር አጋራቸው ውጪ ወሲብ ፈፅመዋል።  ከእነዚህ ውስጥም  69 በመቶ የሚሆኑት  ከአንድ በላይ የወሲብ አጋር ጋር ግንኙነት ያደረጉ ናቸው። 74 በመቶ  ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር የተፈፀመ ሲሆን 49 በመቶው የሚሆኑት  ደግሞ  ኮንዶም  እንዳልተጠቀሙ  መረጃው ያሳያል፡፡

በትምህርት ተቋማት ላይ ደግሞ ሁኔታው በእጅጉ አሳሳቢ ነው። የወጣቶችን ለኤችአይቪ ተጋላጭነት የሚያባብሱና ወዳልተፈለገ ባህሪያት የሚገፋፉ ሁኔታዎች ተበራክተዋል።

ፌስ ቡክ፣ የወሲብ ፊልሞች ፣  የጭፈራና  የአልኮል መጠጥ መሸጫ ቤቶች ፣ የጫት፤ የሺሻና የማሳጅ  ቤቶች  መስፋፋት ችግሩን እያባባሰው መጥቷል ።

አጋላጭ ባህሪያትን አስመልክቶ የተካሔደው  ጥናት እንደሚያመላክተው ችግሩ ከፍተኛ ነው።

ከጋብቻ በፊት ወሲብ የጀመሩ ወጣቶች በአጋላጭ ባህሪያት ምጣኔ ስንመለከተው ጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ 70 ነጥብ 53 በመቶ ፣ በአማራ እነማይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  67 ነጥብ 6 በመቶ ፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ 47 ነጥብ 5 በመቶ ፣ ጅማ መሰናዶ ትምህርት ቤት ደግሞ ከ42 ነጥብ 9 በመቶ ላይ ደርሷል ።

ከአንድ በላይ የወሲብ አጋር መኖር ደግሞ በአማራ እነማይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 57 በመቶ ፣በባህርዳር ከተማ የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 45 ነጥብ 3 በመቶ ፣ በጅማ መሰናዶ ትምህርት ቤት 30 በመቶ ፣ በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ከ28 በመቶ ላይ ይገኛል ።

የወሲብ ፊልም መመልከት በተመለከተ በባህርዳር ከተማ የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የአጋላጭ ባህሪያት ምጣኔ  50 በመቶ መሆኑን በጥናት ተረጋግጧል።

ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ወሲብ መፈፀም በተመለከተ ደግሞ ጅማ መሰናዶ ትምህርት ቤት 35 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 27 በመቶ ነው። ከሁሉም በላይ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ኮንዶም የመጠቀም ልማዳቸው አናሳ መሆኑ ነው።

ለምሳሌ በሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት ከ1ሺህ ተማሪዎች መካከል 65ቱ  ውርጃ ፈፅመዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የውርጃ መጠን ግን ከ1ሺህ ሴቶች  ውስጥ 23 ብቻ ነው። ይህ ማለት በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተፈፀመው ውርጃ በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥ ያሳያል::

አቶ ክፍሌ ምትኩ እንደሚሉት ስርጭቱ ሁሉንም አካባቢዎች የሚነካካ ቢሆንም ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ግን አሳሳቢነቱ በግልፅ ጎልቶ ይታያል። በሴተኛ አዳሪዎች የስርጭት ምጣኔው 25 በመቶ ላይ ደርሷል ።

በተንቀሳቃሽ ሰራተኞች 5 ነጥብ 7 በመቶ ፣ በነጋዴዎች 5 ነጥብ 4 በመቶ፣በረጅም ርቀት መኪና አሽከርካሪዎች 4ነጥብ 5 በመቶ ፣ በህግ ታራሚዎች 4 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም በግንባታ ዘርፍ በተሰማሩ ሰራተኞች 2 ነጥብ 9 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ጥናቱ ያመለክታል ።

ይህ የተዳፈነ የሚመስለው እሳት በተጠንቀቅ ቆመን ካልጠበቅነው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእያንዳንዳችን ቤት የመለብለብም ሆነ የመፍጀት አቅም አለው። የህዝብና የመንግስት ቀዳሚ አጀንዳ ካደረግነው ግን ማስቆም ይቻላል። እንደሚቻል ደግሞ ተግብረን አሳይተን  ነበር።

በተገኘው ውጤት በመኩራራት በዘርፉ ላይ መዘናጋትና መቀዛቀዝ መታየቱ ግን አሁንም ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል መታወቅ አለበት። በዓመት 19 ሺህ ወገኖቻችን እየነጠቀን ነው። 27 ሺህ ወገኖች ደግሞ በየዓመቱ በአማካይ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በአገራችን 718 ሺህ 550 ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል ተብሎ ይገመታል። መድሃኒት የሚወስዱት ግን 500 ሺህ ብቻ ናቸው። አቅርቦቱ አለ ግን ደግሞ ተጠቃሚው የሚጠበቀውን ያክል አይደለም።

እነዚህ ወገኖች እራሳቸውን ተመርምረው ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ የራሳቸውን ማህበራት በማቋቋም “ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ !“ በሚል መርህ በአደባባይ ህዝብን በማስተማር በመከላከሉ ሒደት ላይ ገንቢ ሚና ሲጫወቱ ነበር።

አሁን ግን መቀዛቀዙና መዘናጋቱ ተከትሎ ያቋቋሙዋቸው ማህበራት እየፈረሱና እየተዳከሙ መጥተዋል። የፀረ ኤች አይ ቪ  ጥምረቶች ጥምረት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እድላም ገብረስላሴ  እንደገለፁት በመላው አገሪቷ ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ወገኖች 180 ሺህ አባላት ያቀፉ 531 ማህበራት በማቋቋም በኤችአይቪ ኤድስ መከላከል ተግባር ላይ የበኩላቸውን አስተዋጥኦ ሲያበረክቱ ቆይተው ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የመከላከል ስራው እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ 54 ማህበራት በመፍረሳቸውና  348 ማህበራት በመዳከማቸው ምክንያት በትክክል ሃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙት 129 ማህበራት ብቻ ናቸው  ።

የማህበራቱ መዳከም ምክንያት ከውጭ የሚገኘው ድጋፍ መቀነሱ ፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የክልል መስተዳድሮች እኩል ትኩረት አለመስጠታቸው ፣ የበጀት መጥፋትና የፅህፈት ቤት አለመኖር ይጠቅሳሉ።

የአማራ ፣ የትግራይና የአፋር ክልላዊ መስተዳድሮች በአንፃራዊ መልኩ ከራሳቸው በጀት መድበውና ፅህፈት ቤት ሰጥተው ማህበራቱ እንዲንቀሳቀሱ ሲያደርጉ ሌሎች ግን የሚገባውን ያክል ትኩረት ሊሰጡት አልቻሉም ይላሉ።

የጥምረቱ የሀብት ማበልፀግ መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ጎንፋ በበኩላቸው ማህበራቱ “ትውልድ ይዳን” ብለው በአደባባይ ህዝባቸውን በማስተማር አገራዊና ዜግነታዊ ግዴታቸው ሲወጡ ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን  ከመንግስትና ከህዝብ ጎን  የተሰለፉ አካላት መሆናቸው ተረስቶ  መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አድርጎ የመመልከት መጥፎ ዝንባሌ መታየቱ ለመፍረሳቸውም ሆነ ለመዳከማቸው ተፅእኖ አሳድሯል።

በመከላከል ረገድ የታየው መቀዛቀዝና መዘናጋት ቫይረሱ ዳግም ስጋት ሆኖ መምጣቱን የገለፁት አቶ ጌታቸው በመቆጣጠር ሒደት ግን መድሃኒቱ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ መሆኑን ያስረዳሉ  ።

የተባበበሩት መንግስታት የኤድስ ፕሮግራም (UNAIDS) እ.አ.አ  በ2030  ኤድስን  የማቆም ራዕይ አስቀምጧል። አገሮችም ስምምነቱን ተቀብለው በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን  ራዕይ ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ግቦችን አስቀምጣ በትግበራ ላይ ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ራእይ ማሳካት ትችላለችን ? መልሱ በእጃችን ነው። መቀዛቀዙና መዘናጋቱ ከተቀለበሰ አዎን !ይሆናል። ባለንበት ከተኛን ግን መልሱ በፍፁም የሚል ነው።

የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሻሎ ዳባ ግን እንችላለን ባይ ናቸው። በየደረጃው የተፈጠረውን መቀዛቀዝ በመስበር የኤችአይቪ ስርጭትን የመግታት ጉዳይ የአመራሩና የህዝቡ አጀንዳ ማድረግ ከተቻለ አዎን ይቻላል በማለት ያሰምሩበታል።

ሀገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር ህዝቡ የተሟላ ግንዛቤ ኖሮት የእቅዱ ባለቤት እንዲሆን በማድረግ ፣ የመገናኛ ብዙሃን በስፋት በመጠቀም የመረጃ ተደራሽነት በማረጋገጥና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በማንቀሳቀስ ራእዩን ማሳካት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው ።

እ.አ.አ በ2030 ኤድስን የማቆም ራእይ ለማሳካት ደግሞ እስከ 2020 ድረስ ፅኑ መደላድሎች የሚፈጥሩ ሶስት ዘጠናዎችን የማሳካት ግቦች ተቀምጠዋል ።

ኤች አይ ቪ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ቀዳሚው ነው ።

ተመርምረው ኤችአይቪ በደማቸው መገኘቱን ካወቁት ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑትን የፀረ-ኤችአይቪ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው ግብ ነው።

ሶስተኛው ግብ ደግሞ ህክምና ከጀመሩት ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑትን ህክምናቸውን በትክክል ተከታትለው በደማቸው ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን በሚጠበቀው መጠን  ዝቅ እንዲል ማድረግ ይሆናል ።

አዎን ! ኤድስ መቆም አለበት። የሚቆመው ግን በተራ ፍላጎት አይደለም። ከተቀዛቀዝንበት መንቃት ፣ ከተዘናጋንበት መባነን ፣ ለጋራ ችግር የመፍትሔው አካል ሆነን መረባረብ አለብን።  “ ኤድስን የማቆም ስራ የአመራሩና የሁሉም አካላት አጀንዳ መሆን አለበት “ የተባለውም ለዚህ ነው።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን