አርዕስተ ዜና

ስንጋጭ የሳቁት ስንስማማ ማልቀሳቸው አይገርምም !

13 Sep 2017
2853 times

መብራህቱ ይበልህ (መቀሌ  ከኢዜአ)

 የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም የሚል ብሂል አለ ። እንዴት ያስጥል ? ባል ቢሆንም እኮ እሱም አህያ ነው ። አህያ ከመበላት የምትድነው እራሷን ከጅብ ከጠበቀች ብቻ ነው ።

 እኔን የገረመኝ ጅብ ለዘመናት አህያን ሲያሳድድ መኖሩ አይደለም - የቅርቡን የአህያና የጅብ ፍቅር እንጂ  ። በዪና ተበዪ ፣ አጥፊና ጠፊ ፣አሳዳጅና ተሳዳጅ እንዴት ተፋቀሩ ?ይገርማል ። ይባስ ብሎ ደግሞ ቀበሮና በጎች አንድ ጉረኖ ላይ ሲያድሩ አይቼ ደነቀኝ ።

 ምን ዘመን መጣብን ? እንዴት አህያና ጅብ ፣ ቀበሮና በግ ሊፋቀሩ ቻሉ ?ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው ። አይዞን! በምንም ተአምር ፍቅራቸው ዘላቂ ሊሆን አይችልም ። እርስ በርሳቸው መበላላታቸውም አይቀርም ።

 ጉዳዩ እንዲህ ነው ። አይጥና ድመት ሊፋቀሩ የሚችሉት ድመቱን እስኪርበው ድረስ ብቻ ነው ። የአህያና የጅብ የጋራ ቆይታ ደግሞ ጅቡ ወደል አህያውን ለመቦጨቅ አመቺ ጊዜና ቦታ ለመምረጥ ካልሆነ በስተቀር  መበላቱ ግን አይቀርም ።

 በቅርቡ በአማራና በትግራይ  ወሰን  አካባቢ የነበረውን መለስተኛ አለመግባባት ወደ ግጭት እንዲያመራ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም - ጠባቦችና ትምክህተኞች ።

 ግጭት በአግባቡ ማስተናገድ ከተቻለ ከጉዳት ይልቅ ዘላቂ መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ የታወቀ እውነታ ነው ። እነሱ ግን ግጭቱን አቀጣጠልነው ብለው በጋራ ስቀው ነበር ። አለመግባባቱ በሁለቱም ህዝቦች በጎ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሲፈታ ደግሞ አብረው ማላዘን ጀመሩ ።

 ህዝብን እርስ በርሱ ያባሉ መስሎአቸው ሰርግና ምላሽ ዓይነት ሽርጉድ ቢያሳዩንም አብረው እንደማይዘልቁ ግን ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው ። ታዲያ! ሰሞኑን እንዴት አብረው ተሰለፉ? መልሱ ቀላል ነው ።በሬውን ሰርቀው ስጋውን ለመቀራመት ቢሆንም በቆዳው ሽያጭ መጣላታቸው እንደማይቀር ግን እነሱም ያውቁታል ።

ከተፈጠረው አለመግባባት በስተጀርባ  ሁለት የማይጣጣሙ ሃይሎች አብረው ተሰልፈዋል ። ሁለቱም የጎሪጥ የሚተያዩ ፣ አንዱ ለሌላው የማይተኛ ፣ በእርቅና በድርድር ሊፈታ የማይችል መሰረታዊ ቅራኔ ያላቸው ሃይሎች ናቸው - ጠባቦችና ትምክህተኞች ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ይበላላሉ ።

የትምክህት ሃይሎች “ እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል” የሚል መርህ ያነገቡ ናቸው ።አንድ ቋንቋ ፣ አንድ አገር ፣ አንድ የአስተዳደር ስርዓት መኖር አለበት ብለው የሚያምኑ፣ ብዝሃነትን የማይቀበሉና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የመጨፍለቅ አባዜ የተጠናወታቸው ሃይሎች።

በሌላ በኩል የተሰለፉት ጠባብ ሃይሎች ደግሞ በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የማይቀበሉ በግልባጩ ደግሞ የመገንጠል ጥያቄን በማራገብ የህዝቦችን ሰላም ለማደፍረስ  የቆሙ የጥፋት ሃይሎች አንደሆኑ ይታወቃል ።

የአማራና የትግራይ መንታ ህዝቦች ጠገዴ አካባቢ በግጨው ቀበሌና ዙሪያው የወሰን ጥያቄ ሲነሳ በሰላም እንደሚፈቱት እርግጠኞች ነበሩ ። ሁለቱም የጥፋት ሃይሎች ግን በእሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ አለመግባቱን ወደ ግጭት እንዲያመራና ግጭቱን ያከረሩት መስሎአቸው ድዳቸው እስኪታይ ድረስ ለመሳቅ ሞክረው ነበር ። ሁለቱ መንታ ህዝቦች ግን የሚቀመሱ አልሆኑም ።

አስቀድመው በውስጣቸው መከሩበት ። ምክክራቸውን የጋራ ለማድረግ ደግሞ ባለፈው ሀምሌ ወር መቀሌ ከተማ ላይ  ህዝባዊ ኮንፈረንስ አካሄዱ ። “ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን “ በመሀከላችን ውስጥ ግጭት ምን ሲደረግ በማለትም በጋራ ለሰላም ዘብ ቆሙ ። ስለ ሰላም ዘመሩ ። ሁለቱም የሰላም ጠበቆች መሆናቸውም በአቋም መግለጫቸው አረጋገጡ  ።

የሁለቱም ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮችም በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው ለህዝብ ውሳኔ ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ቃል ገቡ ።

ስምምነቱ የሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነትን ያጠናከረ፣ ሰላምና መረጋጋትን ያሰፈነ ህዝበ ውሰኔ መሆኑን የአገር ሽማግሌዎቹ ይገልፃሉ፡፡ በስምምነቱ መሰረትም በጋራ የህዝብ ተሳትፎ ወሰናቸውን የማካለል ስራ አከናወኑና ዘመናትን ያስቆጠረው አንድነታቸው በምንም መልኩ እንደማይሸረሸር አረጋገጡ ።

ስምምነቱ የተፈፀመው ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው ። በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 48 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የክልሎች ወሰንን በሚመለከት የሚነሳ ጥያቄ  ካለ  ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈፀማል ይላል፡፡

በትግራይ ክልል ፀገዴ ወረዳና በአማራ ክልል ጠገዴ ወረዳ ወሰኑ ሳይታወቅ የቆየውን አንድ ቀበሌ ላይ ሁለቱም ክልሎች ሰሞኑን የፈፀሙት የጋራ ውሳኔም  ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው አንቀፅ 48ን መሰረት ባደረገ ነው፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 40 ንኡስ አንቀፅ 3  ላይ  መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት መሆኑ ተደንግጓል፡፡

በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት   መሬት የሁሉም ህዝቦች የጋራ  ንብረት፣ በጋራ የሚጠቀሙበት ሀብት ከመሆን ባለፈ ለየትኛውም ክልል ብቻ  የተተወ  ንብረት አይደለም ማለት ነው፡፡

የትግራይ ፀገዴና የአማራ ጠገዴ በታሪክ አጋጣሚ ግማሹ ትግርኛ ግማሹ ደግሞ አማርኛ ተናጋሪ ሆነ እንጂ  ሁለቱም የማይነጣጠሉ መንታ ህዝቦች ናቸው ። እውነታው እንዲህ ከሆነ የግጨው ቀበሌ የት ነበረ ? የትስ ይሄዳል ? ያው እዛው ነው ። መንታ ህዝቦቹ በመተሳሰብ ፣ በመፈቃቀርና በመከባበር ይጠቀሙበታል - በፍትሃዊነት  ።

ከፀገዴ ወረዳ የተወከሉ የሀገር ሽማግሌ አቶ ካሳዬ ሀፍቱ የመንታ ህዝቦቹ የዘመናት የደም ትስስርና የትውልድ ሀረግ እየመዘዙ የሚሉት አላቸው ።

በ1984 ዓ.ም ለአስተዳደር ይመች ዘንድ በ16 ቀበሌ የሚኖር ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪዎች ነን በማለት በትግራይ ክልል ፀገዴ ወረዳ ሲካለሉ፣ 12 ቀበሌዎች ደግሞ አማርኛ ተናጋሪዎች ነን በማለታቸው  በአማራ ክልል ጠገዴ ወረዳ  አስተዳደራዊ መዋቅር ስር እንዲጠቃለሉ ተደረገ ይላሉ ።

ግጨውና አከባቢው  ደግሞ  በይደር ወሰኑ ሳይካለል እስከ አሁን ድረስ መቆየቱንና የሁለቱም አጎራባች ወረዳ አርሶ አደሮች ሰጪና ከልካይ ሳይኖራቸው ለአመታት በጋራ እያረሱ ሲጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡

በትግርኛ አነጋገር “ወፍረ ዘመት” ይሉታል፡፡ ወፍረ ዘመት ማለት ባለቤት ሳይኖረው ሁሉም በየፊናው እየሄደ እያረሰ የሚጠቀምበት መሬት ማለት ነው፡፡

ወሰን ሳይኖረው የሁለቱም ክልል አጎራባች ወረዳዎች አርሶ አደሮች ሲጠቀሙበት የነበረው መሬት  ለአስተዳደርና ለአጠቃቀም  እንዲያመች  በፍጥነት ወሰኑ እንዲካለል የሁለቱም  ወረዳ አገር ሽማግሌዎች መጠየቃቸው ህገ መንግስታዊ መሰረት የያዘ ነው፡፡

በመሆኑም አንድም ወሰኑ ሳይካለል የቆየውን የግጨውና አካባቢው ቦታ ከሁለቱም ወረዳዎች እያንዳንዳቸው 50 ተወካዮችና የአገር ሽማግሌዎችን በመምረጥ አስተዳደራዊ ወሰን በማስቀመጣቸው የአገር ሽማግሌዎችና ተወካዮች ብስለትና አስተዋይነትን ከማድነቅ ይልቅ መኮነኑን ምን አመጣው?

በህገ መንግስቱ መሰረት መሬት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ሆኖ እያለ  ለእከሌ ክልል መሬት ተቆርሶ ተሰጠ፣ እከሌ ክልል ደግሞ ሰፊ የእርሻ ቦታ ወሰደ ብሎ ለቅራኔ ማነሳሳት ለጥፋት ከመጋበዝ ባለፈ ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡

ሲጀመር አስተዳደራዊ ወሰን ባልነበረበት ቦታ ከየት ወደየት እንደሄና እንደተሰጠ  የሚያሳይ ውሀ የሚቋጥር ማስረጃም መረጃም  በሌለው ሁኔታ፣ መካለሉ ኖረም አልኖረም ተጋብቶና ተዋህዶ፣ በጋራም ሰርቶ በሚኖር ወንድማማችና እህትማማች ህዝብ መካከል  አፍራሽ ሀይሎች የሚነዙት አሉባልታ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡

የፀገዴ አገር ሽማግሌ አስተባባሪ አቶ ካሳዬ ሀፍቱ  “የሁለቱም ህዝቦች ጥያቄ የእርሻ ቦታው በጋራ እንጠቀምበት እንጂ መሬት ለክቶ የመቀራመት ጉዳይ አልነበረም” ፡፡

በመሆኑም የአርሶ አደሩ ጥያቄ ከእርሻ ስራው ሳይፈናቀል ህጋዊ የመጠቀምያ እውቅና አግኝቶ በነፃነት እንዲያመርት ነበር ፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ያደረጉትም  ይህንኑ ነው ይላሉ፡፡

በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 40 ንኡስ አንቀፅ 4 ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው የተከበረ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

ውሳኔው ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ህዝቡን ደስ ያሰኘ መሆኑንም አቶ ካሰዬ ይናገራሉ፡፡

ሁለቱም ርእሰ መስተዳድሮች ለአገር ሽማግሌዎች ውሳኔ ተገዢ መሆናቸውን ስላረጋገጡላቸው አድናቆታቸውን ይገልፃሉ ።

ወሰን የማካለሉ ስራ ዳኛና ሌላ ሶስተኛ አካል ሳይጨመርበት በወንድማማች ህዝቦች መተማመንና መተዛዘን በተሞላበት መንገድ መጠናቀቁ ለጠላቶች በር የዘጋና የዞረ ድምር ሳያስቀር ለአንዴና ለመጨረሻ የተቋጨ አጀንዳ መሆኑን  አቶ ካሳዬ በልበ ሙሉነት ነበር የገለፁት ፡፡

ሌላው የፀገዴ ወረዳ የአገር ሽማግሌ መልአከ ፀሀይ ሙሉ ድረስ  “ውሳኔው ህዝባችንን ያስደሰተ ነው፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው ሰላምና አብሮነት ነው፡፡ በውሳኔው ረክተናል ። በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን  እንፈልጋለን “  ይላሉ፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ የአየገር ሽማግሌዎቹ በየቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ህዝቡን እንዳወያዩት ነው የሚናገሩት፡፡

በውሳኔው የተከፋ አርሶ አደር አላጋጠመንም ይላሉ፡፡ ሁለቱም መንታ ህዝቦች የጋራ ችግራቸውን በራሳቸው ንቁ ተሳትፎ መፍታታቸው ከማንም በላይ ያስደሰተው ለዘመናት አብሮ የዘለቀው ህዝብ ራሱ ነው ። ችግሩን ለማባባስ ከዳር ሆነው አሉባልታ የሚነዙ ሃይሎች ቢያላዝኑ አይፈረድባቸውም ። ምክንያቱ ደግሞ ለጥፋት መቆማቸው ነበር - ግን ህዝቡ ነቃባቸው ።

የእንጀራ ገመዳቸውና የህልውናቸው ማራዘሚያ ስልት አድርገው የሚያስቡት አሉባልታ ሰሚ አጣ ። ይህ ቦታ ተወሰደብን ፣ ይህ ቦታ ደግሞ ትርፍ አገኘን እያሉ ግጭት የሚፈጥሩበት እድልም ጠቧል ። ያላቸው ብቸኛ እድል ችግሩ ሲፈጠር የሳቁትን ያክል ችግሩ ሲፈታ ደግሞ እርር ድብን ብለው ማልቀስ ብቻ ነው ።

ህዝቡ ግን ከእንግዲህ በኋላ  ’’አደብ’’ ይግዙልን እያለ ነው ፡፡ የሁለቱም ክልል መንግስታትም እየተከታተሉ ልካቸውን እንዲያውቁ ያድርጉልን  ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ሁለቱም ህዝቦች እስከ አሁን መሬቱን በጋራ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ የሁለቱም  የአገር ሽማግሌዎች የተማመኑበት ዋና ቁም ነገር  አሁንም እንደወትሮው ማንም አርሶ አደር ከእርሻ ቦታው ሳይፈናቀል  የመጠቀም መብቱ እንዲከበር ማድረግ መሆኑ መልአከፀሀይ ይገልፃሉ፡፡

ወሳጅም ሰጪም የለም፡፡ አርሶ አደሩ ኬላ ሳያስፈለግው ያመረተውን ምርት በፈለገው ቦታ እንዲሸጥ የማድረግ ስራ ነው ተፈፃሚ እንዲሆን የጠየቁት፡፡

ህዝበ ውሳኔው ከሁለቱም ክልል የሚመለከታቸው አካላት በተጨማሪ የፌደራል መንግስት የአገር ሽማግሌዎችን ውሳኔ ተቀብሎ እንዲያፀድቀው ከመጠየቅ ባለፈ በህዝቡ አንዳች ግርታም የለም ብለዋል፡፡

የሁለቱም ህዝቦች ፍላጎት ሁለቱም ክልሎች በጋራ ሆነው መሰረተ ልማት እንዲስፋፋላቸው ከመጠየቅ ውጭ  የመሬት ጥያቄ የአርሶ አደሩ ጥያቄ አይደለም ያሉት ደግሞ ሌላ የፀገዴ ወረዳ የአገር ሽማግሌ ተወካይ አቶ ብረሀኑ ተሾመ ናቸው፡፡

የህዝቡ አጀንዳና ፍላጎት ልማትና አብሮነት ነው፡፡ ፀገዴና ጠገዴ የአንድ እናት ልጆች ናቸው፡፡

በመሆኑም ህዝቡ መሀል ገብቶ ሊለያያቸው የሚችል ሀይል አለመኖሩን ባለፈው ክረምት በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ግርግር በእነሱ ዘንድ አለመከሰቱ ትልቅ የመንታ ወንድማማችነት ማሳያ መሆኑን  በግልፅ አሳይተዋል፡፡

ለወደፊቱም ቢሆን በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ ለዘላቂ ልማትና አስተማማኝ ሰላም መረጋገጥ አብረው እንደሚሰሩ  የማያጠራጥር ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን