አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የአንበሳውን ድርሻ.....

11 Sep 2017
5761 times

ሚስባህ አወል/ኢዜአ/

አገራችን ያላት የተለያዩ አግሮኢኮሎጂ እና የአየር ፀባይ ዞኖች የተለያየ ጣዕምና ሽታ ያላቸው እጅግ ተፈላጊ የሆኑ በርካታ የቡና ዓይነቶችን ለዓለም ገበያ እንድታበረክት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላታል፡፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ 600 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በቡና የተሸፈነ ሲሆን በዓመት እስክ 400 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቡና ይመረታል። ከዚህ ምርት ውስጥም ግማሽ  ያህሉ  ለውጭ ገበያ  ይቀርባል፡፡

በሀገሪቱ ካለው የህዝብ ቁጥር  85 በመቶ ከሚሆነው አርሶ አደር መካከል  ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጋው  በቡና አምራችነት የሚታወቅ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ በርካታ ጣዕም ያላቸው የቡና ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ከነዚህ መካከል የይርጋጨፌ፣ የሀረር ፣ የሲዳማ ና የጂማ ቡና ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በዓለማቀፍ ደረጃ በቡና ምርት በአንደኝነት የምትታወቀው ብራዚል ስትሆን ኢትዮጵያም አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የዓለም አቀፉ ቡና ድርጅት አሳውቋል ኢትዮጵያም ይህን ደረጃዋን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝም ይታወቃል፡፡

አንድ ወቅት በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ወደ ምትገኘው ይርጋጨፌ ወረዳ በቡና ምርት ዙሪያ ዘገባ ለመሥራት ሄጄ ነበር።

ይርጋጨፌ በቡና ምርቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትታወቃለች፡፡ ዱመርሶ  ቀበሌ ደግሞ በዚህችው ወረዳ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ቡና አምራች አካባቢ ናት። ወይዘሮ አየለች ዱማሮ ያኔ በዱመርሶ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ሞዴል የሚል ቅጥያ ስም አፍርተዋል።

ወይዘሮ አየለች ሞዴል የተባሉት  በቀለም ትምህርትም አልነበረም። ይልቁንስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳን እንዳላጠናቀቁ የሚናገሩ ሴት አርሶ አደር ናቸው፡፡

ታዲያ ሞዴልነታቸው በምን ሲባል ታታሪዋ አርሶ-አደር በቡና ልማት ቀበሌያቸውን ያስጠሩ ጎበዝ ሴት በመሆናቸው ነው።

''የጤና ና የግብርና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች የሚሰጡኝን ምክርና ድጋፍ በአግባቡ ጥቅም ላይ አውላለሁ'' ይላሉ ወይዘሮዋ፡፡

የአርሶ አደሯ የመኖሪያ ጊቢ  መስመራቸውን ይዘው በተደረደሩ የቡና ችግኞች ያማረ ውበትና ግርማ ሞገስ ያለው መሆኑን  ለተመለከተ እውነትም የኤክስቴንሽን ባለሙያዎቹ ትምህርትና ምክር ተቀባይነት ያገኘ ብቻ ሳይሆን  በተግባር የታየ ውጤት ነው ያሰኛል።

የታታሪዋን አርሶ አደር ጥረትና ትጋት ለሌሎች በተሞክሮ እንድታይ ነበር በተዋበው ቅጥር ጊቢ ውስጥ የአንድ ጋዜጠኞች ቡድን መገኘት አስፈላጊ የነበረው።

በአርሶ-አደሯ በዘመናዊ አኗኗር፣ በትጋታቸውና በስኬታቸው ሁሉም ጋዜጠኛ በመደነቁ  በሚያያቸው ስኬት ምስጥሩ ምን እንደ ሆነ ለማወቅ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡

አርሶአደርዋ ታድያ በአካባቢዋ ላለው የቡና ኢንዱስትሪ በምታቀርበው የቡና ምርት በዓመት እስከ ሰማንያ ሺህ ብር የምታገኝ ከመሆኑም ባሻገር በጊቢዋና በጓሮዋ በሚያምር ሁኔታ ከተከለቻቸው የቡና ችግኞች እስከ አስር ሺህ ብር እንደምታገን አጫውታኝ ነበር፡፡

ሀገራችን በ2002 በጀት ዓመት ሁለት ቢሊዮን የሸቀጦች የውጭ ንግድ ገቢ ማግኘቷን በወቅቱ የወጡ ሰነዶች ይጠቁማሉ። በ2007 መጨረሻ ደግሞ ወደ 6.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እንቅስቃሴ ተደርጓል።

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዓመታት ከሸቀጦች የውጭ ንግድ በየዓመቱ በአማካይ 3.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

የወጭ ንግድ ከሚገኝባችው ምርቶች ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ አበባ ፣ አትክክትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቁም ከብትና ስጋ ውጤቶች ይገኙበታል፡፡

ለዛሬ ጽሑፋችን  ከወጭ ንግድ ገቢው የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል የተባለለትን የቡና ምርት ላይ ያተኩራል።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከቡና የወጭ ንግድ በየዓመቱ በአማካይ የ783.3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ተጠቁሟል፡፡

በእቅድ ዘመኑ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ የቀረበው  የቡና ምርት 200 ሺህ ቶን ሆኖ በከፍተኛ ደረጃ ቢመዘገብም ከተያዘው እቅድ ጋር ስነፃፀር ግን ከሲሶ  የማያልፍ ነው።

አርሶ አደሩ ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ወዳላቸው የሰብል ምርቶች ሽግግር እንዲያደርግ በተሰሩ ስራዎች በአነስተኛ አርሶ አደሮች የሚመረት የቡና ምርት መጠንን  በ2007 በጀት ዓመት 420 ሺህ ቶን ማድረስ ተችሏል፡፡

በ2007 ተመዝግቦ የነበረውን በሄክታር 7.48 ኩንታል የተገኘውን ምርት በ2012 በጀት ዓመት ወደ 11 ኩንታል  ለማድረስ እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል።

ይህም በ2007 በጀት ዓመት የተደረሰበትን 420 ሺህ ቶን በ2012 መጨረሻ ወደ 1045.05 ሺህ ቶን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነድ ላይ  ተብራርቷል።፡፡

ለዚህ ጹሁፋችን ዋቢ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን  ጎራ ብለን  የባለስልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳኒሶን የቡና ግብይቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ጠይቀናቸዋል። 

ላቀረብንላቸው ጥያቄም በ2000 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ የቀረበበት እንደነበር ነገሩን፡፡ በበጀት ዓመቱ ወደ 171 ሺህ ቶን  ቡና  ለውጭ ገበያ ቀርቦ 524 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱንም ገልፀዋል።  

በቀጣዩ ዓመት ማለትም 2001 ዓመተ ምህረት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት በመቀነሱ ተመሳሳይ ውጤት  አልተገኘም።  

ከ2001 ዓመተ ምህረት በኋዋላ ግን ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት ጭማሪ እያሳየ በመምጣቱ በ2008 ዓመተ ምህረት 198 ሺህ 621 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ 722 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው  አቶ ዳ ሳያስረዱት፡፡

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ225 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ አቅርባ 881 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝታለች። ይህ የተጠቀሰው ገቢ በ2000 ዓመተ ምህረት ከነበረው ገቢ ጋር ስነፃፀር በግማሽ ያህል እድገት ማሳየቱንም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

በበጀት ዓመቱ ወደ ዓለም ገበያ የተላኩ ቡናዎች መጠን እና ገቢ  ለጀርመን ወደ 40 ሺህ 292 ቶን ቀርቦ 140 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ገቢ በማስገኘት የመጀመሪያ ደረጃን  ስትይዝ ለሳውዲ አረቢያ ወደ  36 ሺህ 551 ቶን የሚጠጋ ቡና ቀርቦ 133 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  ገቢ በማስገኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ለአሜሪካ ደግሞ ወደ 20 ሺህ 297 ቶን ቡና ቀርቦላት  117 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ገቢ በማስገኘት 3ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢ  ከአራት እስከ አስር ያሉትን ሀገራት እንደ ቅደም ተከተላቸው ስንዘረዝራቸው፡ጃፓን፣ ቤልጂየም፣ ደቡብ ኮርያ፣ ጣልያን፣ ኢንግላንድ፣ ፈረንሳይ እና ሱዳንን እናገኛለን፡፡

ከ1 እስከ 10 ያሉት በአጠቃላይ በመጠን 86.07%  እና  በገቢ  84.61%  የሚሆነውን  እንደሚሸፍንም  አብራርተዋል፡፡

የቡና ግብይቱንና ጥራቱን ለማስጠበቅ የሚያግዝ የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር  አዋጅ በሰኔ ወር 2009 ዓመተ ምህረት ወጥቶ ስራ ላይ መዋሉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ጥራቱን ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ ከመደረጉም ባሻገር ሀገሪቱ በቡና ግብይት ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመለየትና ችግሩን ለማስወገድ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ ነች፡፡

ቡና መገኛው እዚሁ ሀገራችን በእረኛው ካሊድ  መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን? ታድያ የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በቡና ከወጪ ንግድ መጠቀም ያለባትን ጥቅም ልታገኝ ከሆነ የበለጠ ጠንክራ መሥራት አይገባም ይላሉ? ’’መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ የሚረጋገጥበት ነው’’።                                          

                                                                                                                                                                                                                       መልካም ዓመት!!

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን