አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ሶማሌ ከሚሊኒየሙ ወዲህ

10 Sep 2017
3136 times

መሐመድ ዓሊ (ኢዜአ)

ሰላም ሁሉም ነገር ነው ፡፡ ሀገር የሚለማውና የሚያድገው በሰላም ወጥቶ መግባትና ሲቻልና የተረጋጋ አካባቢ ሲኖር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከሚሊንየሙ መከበር በፊት የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ከሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች በተለየ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር የሚታይበት ነበር፡፡ በክልሉ መረጋጋት ስላልነበረም ለልማት ስራዎች በሚፈለገው መጠን ትኩረት መስጠት አልተቻለም ነበር፡፡

ከዓመታት በፊት በክልሉ በአብዛኛው አካባቢ የህዝብ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር። በተለይም ከቀብሪ በያህ ወደ ደገሃቡር፣ ከደገሃቡር ቀብሪ ደሃር፣ ከቀብሪ ደሃር ጎዴ፣ ከባቢሌ ፊቅ እና ከቀብሪ ደሃር ዋርዴር ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከ15 ቀናት እስከ አንድ ወር ጊዜ የሚፈጅና በእጀባ ብቻ የሚከናወን ነበር።

ቦምቦች በዋናነት በጅግጅጋ ከተማ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንደ ሆቴሎችና ስታዲየም ያሉ ስፍራዎች ላይ ይወረወራሉ። በተደጋጋሚ የንፁሃን ዜጎች ህይወት እንደዘበት የሚያልፍበት ወቅት እንደነብር ይታወሳል። በወቅቱ የነበሩት የክልሉ መንግስት ፕሬዜዳንት ለከፍተኛ ጉዳት ታዳርገው ነበር። ይህ ሁሉ የሰላም እጦት ውጤት ነበር ማለት ይቻላል።

በደገሀቡር ወረዳ ኦበሌ ቀበሌ በነዳጅ ፍለጋ ስራ ተሰማርተው የነበሩ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን ላይ አሸባሪዎች የፈጸሙት የግፍ ጭፍጨፋም ዓለም የሚያስታውሰው ነው። ተጨማሪ ትውስታዎችን ማቅረብ ይቻላል። ነገርግን የተጠቀሱት ማስረጃዎች ስለሰላም እጦት ለጊዜው በቂ ይሆናሉ።

በክልሉ የድህነት ቅነሳና ዘላቂ ልማት ፕሮግራም ለመተግበር ፣ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ለማስፋፋትና የስርጭቱን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ፣ በሀብት ግንባታ ላይ ለማተኮርና ሌሎች ተግባራት ለማከናወን ሰላም በእጅጉ የሚናፈቅበት ወቅት ነበር ።

ህዝቡ የራሱን ሠላም ለማረጋገጥ በሚሊኒየሙ መግቢያ እነዚህ ጠንቆች በጉያው ይዞ መቀጠል አልቻለም። ሽብር ለክልሉም ሆነ ለአካባቢው እንደማይጠቅም በመረዳት በስፋት መከረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰላም ጠንቅን ለማጥፋት በገባው ቃል መሰረት ተንቀሳቀሰ። ለዓመታት ሲናፍቀው የነበረውን ሠላም በራሱና በመንግስት ጥረት ማረጋገጥ ቻለ፡፡

ከአስር ዓመታት በፊት በክልሉ አንድም የሚድያ ተቋም አልነበረም። በዚህም የተነሳ ህዝቡ በአካባቢው ጉዳዮች የሚመካከርበትና የሌላ አካባቢ መልካም ልምድ የሚጋራበት ተቋም አልነበረውም፡፡ ይህንን በመገንዘብ የክልሉ መንግስት በ2003 ዓ.ም የጅግጅጋ 99.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮና የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋም ማሕበረሰቡ ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝና አካባባውን እንዲጠብቅ አስችሎታል፡፡

የክልሉ መንግስት ባለፉት 10 አመታት ብዛትና ጥራት ያላቸውና በክልሉ ቋንቋ የሚሰራጩ በርካታ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አውተሮች እንዲገነቡ በማድረግ ህዝቡ በክልሉም ሆነ በአገሪቱ እየተከናወኑ ያሉትን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተደደር ሥራዎች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ ኢስማኤል ይናገራሉ፡፡

የክልሉ ፀጥታና ፍትህ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲራህማን አብዱላሂ ደግሞ የክልሉ መንግስት ለፀጥታ ጉዳዮች በሰጠው ልዩ ትኩረት በክልሉ እየተከናነ ያለው የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ስራዎች ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል ባይ ናቸው።

በተለይም በክልሉ የተሰማራው የልዩ ፖሊስ ኃይል ደሙን በማፍሰስና የህይወቱን መስዋእት ጭምር በመክፈል በህዝብ ላይ ይፈፀሙ የነበሩ የግድያ፣ የአፈና፣ የዝርፍያና ሌሎች ፀያፍ ድርጊቶች ማስቆም ችሏል ።

ፖሊስ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩ ፀረ-ሰላም ሀይሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ ደረጃ መጠበቅና ማስከበር ከመቻሉም ባለፈ የክልሉን ህዝብ ወደ ፈጣን ልማት ለማሸጋገር አስችሏል፡፡

የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል የአሸባሪውን ኦብነግ ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ ፀጥታና ሰላም ካሰፈነ በኋላ ሕዝቡ በአካባቢው ልማትና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በሰፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የክልሉ ልዩ ኃይል አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በትምህርትና በጤና ልማት ስራዎች በበጎፍቃደኝነት በያለበት እያገለገለ መሆኑንም አቶ ኢብራሂም ይገልጻሉ፡፡

የልዩ ፖሊስ ኃይል ከድርቅ ጋር ተያይዞ በቅርቡ በተከሰቱ የአጣዳፊ ተቅማጥና የምግብና የውሃ እጥረት ለመቅረፍ አስቸኳይ እርዳታ ከማድረጉም ባሻገር በክልሉ እየተካሄዱ ያሉትን ዘርፈ-ብዙ የልማት አውታሮች ላይ በግንባታ ስራ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ለአብንት አንስተዋል፡፡

ከአስር ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ ከአሁኑ ጋር የሚያነጻጽሩት የሀገር ሽማግሌውት አቶ አብዲከሪም ቀሊንሌ በአሁኑ ወቅት ክልሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም አጠቃለይ የእድገት ችግሮችን ቀርፎ ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር መሰረት ይዟል ይላሉ፡፡

ከአስር አመታት በፊት ጅግጅጋ ከተማን ጨምሮ በየአከባቢው የጎላ የሰላም ማጣትና መደፍረስ ችግር የክልሉ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ አብዲከሪም በሚሊኒየም መባቻ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በመሆን በገባው ቃል መሰረት ከአሸባሪዎች ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ በማካሄዱ ዛሬ በየቦታው አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል ።

አሁን ያለው ጠላት ድህነት ብቻ በመሆኑ ህዝቡ ከመንግሰት ጎን ተሰልፎ በልማት ስራዎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበትም ይመክራሉ ።

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፣ ዴሞክራሲ እንዲያብብና መልካም አስተዳደር እንዲነግስ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው በየደረጃው ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስትና ህዝብ የጀመሩትን ጥረት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊገፉበት ይገባል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን