አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የውሳኔ ዓመት ይሁንላችሁ !

09 Sep 2017
2060 times

 መኳንንት ካሳ  (አሶሳ ኢዜአ)

አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው፡፡ አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ በመቀበል የአመቱ መቀየር በእድሜያችን ላይ ብቻ ሳይሆን በኑሯችን ላይም ለውጥ እንዲያመጣ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው፡፡

በዚህ የዘመን መስፈሪያ ዓመት  ሲቀየር አብረው የተሻገሩ ሰዎች መልካም ምኞታቸውን የሚለዋወጡበት ነው፡፡ የተዘራው እንዲያፈራ፣ ውጥናቸው እንዲሳካ በአጠቃላይ ዓመቱ በመልካም እንዲያልፍ ምኞታቸውን የሚገልጹበት ነው፡፡

አብዛኛው ሰው በአዲስ ዓመት በኑሮውና በስራው አንድ እርምጃ ወደ ፊት ለመራመድ የሚያቅድበት ነው፡፡ በህይወት አዲስ ነገር ለመጨመር አሊያም የማይፈልጉት ግን ከራስ ጋር የተጣላ ነገርን እዛው ከአሮጌው ዓመት ጋር ትቶ አዲሱን ዓመት በአዲስ ማንነት ለመጀመር ብዙዎች ቃል የሚገቡበት ይሆናል ፡፡  

እኔም 2009 ዓመተ ምህረትን በመሸኘት የ 2010 አዲስ ዓመትን ለመቀበል ጫፍ ላይ ባለንበት በዚህ ወቅት ይህን ጽሁፍ እንዳዘጋጅ ያነሳሳኝ ጉዳይ ስላለ ነው፡፡ ይኸውም አዲስ ዓመት ሲመጣ ብዙውን ጊዜ በዓመቱ የተለያዩ ነገሮችን ለማሳካት እቅድ የሚያዝበት መሆኑ ነው፡፡

 በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንወያይ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ጊዜ ማቀዱን ግን ደግሞ ሊሳካለት አለመቻሉን ነገረኝ፡፡ ሊቀበለው ባለው አዲስ ዓመት ዋዜማ በህይወቱ ሊያመጣው ያሰበውን ለውጥ ሳይኖረው ዓመቱ ተጠናቆ እንደገና ሌላ አዲስ ዓመት ሲመጣ አሁንም ያንኑ እቅዱን በዛ ዓመት ለማሳካት ልቡ እንደሚከጅል አጫወተኝ፡፡

 አዲስ አመት በህይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር በዓል መሆኑን እንደሚያምን ያጫወተኝ ይህ ወዳጄ በአዲስ ዓመት ከተነገሩ የመልካም ምኞት መልእክቶች አንድ ወቅት ሲነገር የሰማው መቼም ከውስጡ እንደማይጠፋ ነገረኝ፡፡ የመልካም ምኞት መግለጫውን ማን እንደተናገረው ባያስታውስም ‹‹የውሳኔ ዓመት ይሁንላችሁ›› የሚል እንደሆነ ነግሮኛል፡፡

 ለአዲስ ዓመት ማቀዱ ላይ ሳይሆን ችግሩ አዲስ ዓመት ሲመጣ በተፈጠረው የመነቃቃት መንፈስ የታቀደውን ለማሳካት የሚያስፈልገውን እርምጃ ሁሉ ለመውሰድ ዝግጁ የሆነ የውሳኔ ሰው የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ ዓመት አብዛኛው ሰው በህይወቱ ለውጥ ለማምጣት የሚያቅድበት በመሆኑ ለእቅዱ ስኬት ‹‹የውሳኔ ዓመት ይሁንላችሁ›› የሚለውን የመልካም ምኞት መግለጫ እንደወደደው አጫውቶኛል፡፡

 በዚህ ሃሳብ መነሻነት ያነጋገርኳቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች የገለፁልኝ በአዲስ ዓመት በኑሯቸው ለውጥ ለማምጣት እንደሚያቅዱ ነው፡፡ ያቀዱትን ከመፈፀም አንፃር ግን አንዱ ከሌላው ይለያልና ልምዳቸውን ለማካፈል ወደድኩ፡፡

 በህግ የተወሰነበትን የአስር ወራት የእስር ቅጣት አጠናቆ ከአሶሳ ማረሚያ ቤት ሲወጣ ያገኘሁት ወጣት አንዋር ኢሳ ከማረሚያ ቤት በአዲስ አመት ዋዜማ በመውጣቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ወጣት አንዋር ከዚህ ቀደም አዲስ ዓመት ሲመጣ በተለየ ሁኔታ በህይወቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት አቅዶ እንደማያውቅ ነግሮኛል፡፡

 በተለያዩ ሱሶች ተጠምዶ እለታዊ ስለሆነው ነገር ብቻ ከማሰብ ባለፈ የተለየ አላማ እንዳልነበረው በመግለፅ በማረሚያ ቤት ቆይታው በህይወቱ የተለየ ልምድ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡ በማረሚያ ቤት ቆይታው ስለ ህግ ያለው ግንዛቤ ማደጉንና የባህሪ ለውጥ ማምጣቱን ተናግሯል፡፡

 በአላማ መኖር እንደሚገባ መገንዘቡን የሚናገረው አንዋር በአዲሱ አመት ከፍቅር ጓደኛው ጋር ትዳር ለመመስረት ማቀዳቸውን እንዲሁም የአሽከርካሪነት ስራ እያከናወነ ጎን ለጎን የአሽከርካሪነት ፍቃዱን ለማሳደግ ማቀዱን ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በማረሚያ ቤት ቆይታው ማህበረሰቡን በታማኝነት ለማገልገልና ዳግም ወደ ጫትና ሲጋራ ሱስ ላለመመለስ የወሰነውን  ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሏል፡፡

 በአዲሱ ዓመት ስራ ለመጀመር ማቀዱን ያካፈለኝ ደግሞ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን በመጀመሪያ ድግሪ የተመረቀው ወጣት በቃና አድማሱ ነው፡፡ የ2009 አዲስ ዓመት በተከበረበት ወቅት እቅዱ የነበረው በትምህርቱ ላይ ያሉበትን ጉድለቶች በማስተካከል ውጤታማ ሆኖ ማጠናቀቅ የነበረ ሲሆን እቅዱን ማሳካቱን ተናግሯል፡፡

 በአዲሱ ዓመት ዋናው እቅዱ በሙያው ለመስራት ቢሆንም ይህ ካልተሳካ ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ ወደ ስራ ለመግባት አቅጃለሁ ብሏል፡፡ እቅድ ሲታቀድ ሙሉ ለሙሉ የታቀደው እቅድ ይሳካል በሚል ሳይሆን ሌሎች አማራጮችንም በማስቀመጥ ሊሆን እንደሚገባ ገልጿል፡፡

 አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ የሚጀመር በመሆኑ በአዲስ ዓመት ማቀድ በዓመቱ ስለሚኖር አኗኗር የሚታሰብበት በመሆኑ እቅድ ማውጣት መልካም መሆኑን ወጣት በቃና ተናግሯል፡፡ አቅምን መሰረት ያደረገ እቅድ በማቀድ በይቻላል መንፈስና በራስ መተማመን መስራት ከተቻለ እቅድን ማሳካት ይቻላል ብሏል፡፡

 የሊስትሮ ስራ ከጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው መሃመድ ሆራ የ2009 አዲስ ዓመት እቅዱ ስራውን በማሳደግ የጫማ ማደሻ ሱቅ መክፈት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን እቅዱን ማሳካት እንዳልቻለና ለእቅዱ አለመሳካት ምክንያት ያላቸውን ነገሮች በመለየት ለአሁኑ አዲስ አመት ትምህርት መውሰዱን ገልጿል፡፡

 ያለፈው ዓመት ለእቅዱ አለመሳካት ምክንያት የሆነው አለአግባብ ገንዘብ ማባከኑ በመሆኑ በዚህ አዲስ አመት የጫማ ማደሻ ሱቅ ለመክፈት ቁጠባውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡ እቅድን ለማሳካት ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቅድሚያ መስጠት ወሳኝ ነው ብሏል፡፡

 በአዲስ ዓመት የማቀድ ልምዱ ጥሩ ቢሆንም ከዛ በኋላ የታቀደው እቅድ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በየጊዜው የመከለስ ልምድም ሊኖር እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ በቀለ ወርዶፋ ናቸው፡፡

 ባለፈው ዓመት ይሰሩበት ከነበረው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያገኙትን እድገት በመጠቀም ወደ ሌላ አካባቢ ተዘዋውረው ሲሰሩ ከቤተሰብና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ሳያስተካክሉ በመወሰናቸው እቅዳቸው እንዳልተሳካ አጫውተውኛል፡፡

 በ 2010 አዲስ ዓመት የግል ስራ ለመጀመር ማቀዳቸውንና ለዚህም በቂ ጥናት አድርገው ወደ ስራ ለመግባት ማሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ 

 ያነጋገርኳቸው ሰዎች ሁሉ በአዲሱ ዓመት በኑሮና በስራ አዲስ ነገር ለመጀመር አቅደዋል፡፡ በርግጥም በአዲስ ዓመት ያሰቡት እንዲሳካ ጽሁፉን ስጀምር ወዳጄ ነገረኝ ነው ባልኩት የመልካም ምኞት መግለጫ ለመቋጨት ወደድኩ፡፡ የውሳኔ ዓመት ይሁንላችሁ ! ፡፡ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ከፍታ ነውና የከፍታው ተሳታፊም ተጠቃሚም እንሁን !።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን