አርዕስተ ዜና

የለውጥ አብነቶች

08 Sep 2017
2962 times

አስማረች  አያሌው /ኢዜአ/

በሃገራችን ከሚሊኒየሙ ወዲህ ባሉ አስር አመታት በርከት ላሉ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር በተደረገው እንቅስቃሴ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ለ10 ሚሊዮን 655 ሺህ 655 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን የመጀመሪያ አመት ትግበራም ለ1 ሚሊዮን 739 ሺህ 16 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

የስራ ባህልን ከማስረፅና ዜጎች የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት አኳያም በመንግስት የሚደረጉ ድጋፎች ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡

ባለፉት ዓስር ዓመታት አነስተኛና መካከለኛ ማምረቻ ተቋማት እንዲፈጠሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መነሻ አቅም  ሆነዋል፡፡

ከአነስተኛ የንግድ አንቅስቃሴ በመነሳት አምራች ሆነው ራሳቸውን በመጥቀምና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር በሃገራቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻቸውን እያበረከቱ ካሉ  የለውጥ አብነቶች ውሥጥ  የፍሬንድሽፕ አግሮ ኢንደስትሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለድርሻና የንግድ ዋና ስራ አስኪያጅ ወጣት አቤል መኮንን አንዱ ነው፡፡

የስራ መነሻ

ወጣቱ እንዳጫወተን  ከቢዝነስ አጋሮቹ ጋር የተመሰረተው ግንኙነት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይጀምራል፡፡ ግንኙነቱ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው “የጊዜና የገንዘብ ነጻነት” እስከ መሻት ደረሱ፡፡ ህልማቸውን እውን ለማድረግም የተለያዩ ዘርፎችን ማጥናታቸውን ተያያዙት፡፡

ወጣት አቤልና ሁለት ጓደኞቹ የተለያዩ አማራጮችን አውጥተው አውርደው የዶሮ እርባታን ተቀዳሚ ምርጫቸው አደረጉ፡፡ ስራውን የጀመሩትም በ18 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል እንደነበር ነው ወጣቱ ያጫወተን፡፡

ስራንውን ሲጀምሩ የገጠሟቸውን የቦታ፣ የአያያዝና የጤና ችግሮች በሳይንሳዊ መንገድ በመፍታት በተለይ ከቦታ እጥረት ጋር ተያይዞ የገጠማቸውን ችግር ለአፍሪካም ጭምር ሞዴል በሚሆን መልኩ መፍታታቸውን አብራርቶልናል፡፡

ለዚህም የገጠማቸውን የቦታ እጥረት ለመቅረፍ ባካሄዱት ጥናትና ምርምር እውን ያደረጉትን በ1.2 ካሬ ሜትር ቦታ 80 ዶሮዎችን መያዝ የሚችል የዶሮ ማርቢያ ‘ኬጅ’ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ማስመዝገብ መቻላቸውን  በአብነት ጠቅሷል፡፡

መንግስታዊ ድጋፎች

በመጀመሪያ አይን ውስጥ ሳይገቡ ብዙ ጥያቄዎችንም ገፍተው ሳይጠይቁ ስራቸውን ማስቀደማቸውን የሚናገረው ወጣቱ ከመንግሥት ድጋፍ መጠየቅ የጀመሩት ስራቸው ለውጥ ማሳየት ሲጀምር መሆኑን ነው የተናገረው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ብድር የጠየቁትም ለስራ የተነሱባቸውን 80 ዶሮዎች ወደ 2 ሺህ ሲያሳድጉ መሆኑን ያስታውሳል፡፡ ብድር የሚሰጠው አካልም ስራቸው ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተረድቶ የጠየቁትን የ45 ሺህ ብር ብድር ፈቅዶላቸዋል፡፡

ከዶሮ እርባታው ጎን ለጎን ያጋጠማቸውን የመኖ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ባደረጉት ጥረትም በመኖ ቅንብር የስራ ዘርፍ ተሰማርተው የራሳቸውን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለገበያ እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ የዶሮ መኖውን ለማቀናበር ለተከራዩት ቦታ በየወሩ የሚከፍሉት እስከ 40 ሺህ  የሚደርስ ብር ለስራቸው እንቅፋት ስለሆነባቸው ስራውን ከጀመሩ በኋላ ለመንግሥት ያቀረቡት የማምረቻ ሼድ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማግኘቱንም ነው ወጣቱ የተናገረው፡፡

ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ ያገኘውም ከመንግስት ሳይጠብቁ ስራቸውን በራሳቸው ጀምረው ውጤታማነታቸውንም አሳይተው የመንግሥትን ድጋፍ በመጠየቃቸው ነው፡፡

የተበደሩትን 45 ሺህ ብር  በወቅቱ በመመለሳቸውም አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በሁለተኛው ዙር 120 ሺህ፣ ከዚያም 300 ሺህ በመቀጠል ደግሞ  የወቅቱ የተቋሙ የብድር ጣሪያ የነበረውን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አበድሯቸዋል፡፡

ወጣት አቤል ስራውን ሲጀምሩ ይገጥማቸው የነበሩ ችግሮችን በማቃለል በኩል መንግስት   ከጎናቸው እንዳልተለየ ገልጾ አሁን በፈጠሩት አቅም እስከ 15 ሚሊዮን ብር መበደር እንደሚችሉ ተናግሯል፡፡

 በስራ ሄደት ያጋጠሙ ችግሮች

ስራውን ሲጀምሩ የህብረተሰቡም ሆነ የቤተሰቦቻቸው የተዛባ አመለካከት ፈትኗቸው እንደነበር ወጣቱ ስራ ፈጣሪ አጫውቶናል፡፡

የሚከፈለውን ጥሩ ደመወዝና ያገኘውን የውጭ ሀገር የትምህርት እድል እርግፍ አድርጎ ትቶ የግል ስራውን ሲመርጥ ከባለቤቱ ውጭ ቤተሰቡ ሃሳቡን ለመቀበል ተቸግረው እንደነበርና  የራቁት ሰዎች እንደነበሩም ወጣቱ አይዘነጋውም፡

ሌላው ቀርቶ ስራቸውን ሊጎበኙ የሚመጡ የአበዳሪው ተቋም ሰራተኞች ሳይቀሩ “ዶሮ እርባታ አያዋጣችሁም፤ ሌላ ስራ ቀይሩ” የሚሉ አስተያየቶችን ይሰነዝሩ አንደነበር ገልጾ በኋላ ለውጡን ሲመለከቱ ሃሳበቸውን መቀየራቸውን አብራርቷል፡፡

ስራውን ሲጀምሩ ለኪራይ በሚያወጡት ገንዘብ ምክንያት የፋይናንስ እጥረት ቢገጥማቸውም አሁን ግን በሊዝ ባገኙት 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ  ምርታቸውን ያመርታሉ፤ 1 ሺህ 50 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ህንጻ ባለቤትም ሆነዋል፡፡

በአንድ ወቅት ‘ማሬክስ’ የተሰኘ የዶሮ በሽታ ከነበሯቸው 10 ሺህ ዶሮዎች ውስጥ 9ሺህ 600ዎቹን ፈጅቶባቸው አንድ ሚሊዮን ገደማ ብር መክሰራቸው ሌላው ፈተና ነበር፡፡

የዶሮ በሽታን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ መድሃኒቶችን ከውጭ ለማስገባት ቢሞክሩም ለውጭ ምንዛሬ ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ መድሃኒቶችን ከአትራፊዎች በእጥፍ ዋጋ ለመግዛት ተገደዋል፡፡

ከስራው  የተገኘ ልምድና ስኬት

ወጣት አቤል ከስራው ባገኘው ልምድ የኢትዮጵያ እንስሳት መኖ ኢንደስትሪ ማህበር ላይ የቦርድ አባል፣በኢትዮጵያ፣ በማላዊ፣ ሩዋንዳ፣ ኬኒያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ ስራ ፈጣሪዎችን በሚያበረታታው  የአፍሪካ አግሪ ቢዝነስ አካዳሚ በዶሮ እርባታ ዘርፍ የዴስክ መሪ እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ኤክስኪዩቲቭ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ላይ አማካሪ በመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጾልናል፡፡

ከመነሻቸው አኳያ በየጊዜው ለውጥ እያሳዩ መሆኑን የሚናገረው አቤል አሁን 80 ሰራተኞችን በስራቸው ቀጥረው ማሰራት ችለዋል፡፡ ድርጅቱ የራሱ የሆኑ መኪኖች፣ ህንጻ፣ የራሱ የእርባታና የመኖ ማምረቻ ማሽኖች እንዲሁም በጥናት የተደገፉ የአእምሮ ሃብቶች ባለቤት አስከመሆን ደርሷል፡፡

ወጣት አቤል እንዳብራራልን ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ900 ሺህ ወደ 45 ሚሊዮን  ብር አሻቅቧል፡፡ በሀገሪቱ 11 ቦታዎች ላይ ምርቶቻቸውን ያከፋፍላሉ፡፡ ለአዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች በሚሰጡት የምክርና የስልጠና አገልግሎትም በዘርፉ ሊወዳደሯቸው የሚችሉ ድርጅቶችን በማፍራት ላይ ናቸው፡፡

ለአብነትም አንድ የድርጅቱ ሰራተኛ የድርጅቱን መኖ በማከፋፈል ስራ ተሰማርታ በየወሩ እስከ 1ሺህ ኩንታል መኖ በማስረከብ “በወር ታገኝ የነበረን ደሞዟን በቀን እያገኘችው” መሆኗን ጠቅሷል፡፡

የማህበሩ የወደፊት ራዕይ

ወጣት አቤል እንዳለው የማህበሩ ግብ በምግቡ ዘርፍ መስራት ነው፡፡ ለዘህ ደግሞ በተለይ በዶሮ እርባታና በእንቁላል ዘርፍ አለመሰራቱና ከዚሁ ጋር ተያይዞም  ህብረተሰቡ “እንቁላል ሸጦ ጎመን የሚገዛ” መሆኑ ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ገፋፍቷቸዋል፡፡

የራሳቸው የስራ ውጤት የሆነውን የዶሮ እርባታ ኬጅ በማስፋፋት በተለይ የእናቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና  ልጆቻቸውንም በፕሮቲን የበለጸገ ምግብ በመመገብ የተሻለ ዜጋ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም ነው የተናገረው፡፡

በቀጣይ የሀገሪቱን ገበያ በአግባቡ ለመድረስ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ ከመንደፋቸውም በላይ  እቅዳቸውን ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ጋር አጣጥሞ ለማስቀጠል ያመች ዘንድ ከመንግሥት አካላት ጋር ምክክር ያደርጋሉ፡፡

ፈረንሳይ ሀገር ለስራ ጉብኝት በሄደበት ወቅት አንድ አነስተኛ ገበሬ እስከ 250 ሺህ ዶሮዎች እንዳሉት መመልከቱን ገልጾ ማህበራቸውም የእንቁላል ጣይ ዶሮዎቹን ቁጥር ከ16 ሺህ ወደ 100 ሺህ የማሳደግ እቅድ እንዳላቸው አብራርቷል- ከሚሊየነርነት ወደ ቢሊየነርነት የመሸጋገር ህልም እንዳላቸው በመጠቆም፡፡

ይህን ለማድረግ ግን ባንኮች መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው የሰጠውን ትኩረት ተገንዝበው አሰራራቸውን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ እንዳለባቸው ሳይገልጽ አላለፈም፡፡

ለወጣቱ ያስተላለፈው መልእክት

ወጣቱ ኃይል ከስራ ጠባቂነት መንፈስ ተላቆ ሊሞከሩ የሚችሉ የስራ ዘርፎች ላይ ጥናት እያካሄደ ስራ ፈጣሪ እንዲሆንና ችግሮችም ሲገጥሙት ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የዛሬው ትውልድ ራሱን ዝቅ አድርጎ መስራትን ካልለመደና ኃላፊነቱንም  ካልተወጣ የቀጣዩ ትውልድ እጣ ፋንታም የተሻለ እንደማይሆን ገልጾ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን በመስራት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

ሌላኛዋ የለውጥ አብነት የፋሲካ ቅመማ ቅመም ዋና ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ኤልሳ ሃብቴ ናቸው፡፡

የባልትና ውጤቶችን የማምረቱን ስራ ከአምስት እህትና ወንድሞቿ ጋር በመሆን  ከቤተሰቦቻቸው  ተረክበው  ነው የጀመሩት፡፡  ከሚያመርቱት ምርት ውስጥም  65 ከመቶውን ለውጭ ገበያ ቀሪውን ደግሞ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ያውሉታል፡፡

ሁሉንም ምርታቸውን እሴት ጨምረው ለገበያ እንደሚያውሉት የሚናገሩት ወይዘሮ ኤልሳ ይህም ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ምርትን የሚያሽጉ ኢንዱስትሪዎች  አብረው እንዲያድጉ ያስችላል ባይ ናቸው፡፡

በአነስተኛ መጠን ቤት ውስጥ ከሚዘጋጅ የባልትና ምርት ሽያጭ የተጀመረው ስራ ዛሬ 10 ሚሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ በቅቷል፡፡

ወይዘሮ ኤልሳ የህንድ ቅመማ ቅመም ፋብሪካዎችን ጎብኝተው 47 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ  የቅመማ ቅመም ሴክተር ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክትም አጥንተዋል፡፡

ወይዘሮ ኤልሳ እንዳብራሩት ስራውን የበለጠ ለማስፋፋት ለመንግስት ያቀረቡት የመስሪያ ቦታ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘቱ ለኪራይ በየወሩ 77 ሺህ ብር ለመክፈል ተገደዋል፡፡ ከሚመረቱ ምርቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ በመሆኑና ለ60 ሰራተኞችም የስራ እድል በመፍጠሩ መንግሥት ለችግራቸው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸውም ነው  የጠየቁት፡፡

ከእጅ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ የሚያጣራ፣ የሚፈጭና የሚያሽግ የሊዝ ማሽን እንዲቀርብላቸው ለልማት ባንክ  ያቀረቡት ጥያቄ ግን ተቀባይነት ማግኘቱን አልደበቁም፡፡

ወይዘሮ ኤልሳ እንደሚሉት ጥራት ያላቸውን የባልትና ምርቶች ለማምረት የሚገጥማቸው መሰናክል ከምርት አሰባሰብ ይጀምራል፡፡ አርሶ አደሩ በተለይ ከማሳው የለቀመውን በርበሬ የሚያደርቀው አፈር ላይ መሆኑ አፍላቶክሲን የተሰኘው ፈንገስ እንዲራባ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ምርቱን ከአርሶ አደሩ የሚረከበው ነጋዴም ቢሆን ሚዛን እንዲጨምርለት የሚያርከፈክፈው ውሃ ፈንገሱ እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል፡፡

ፈንገሱ እንደ ጉበት ካንሰር ያሉ አደገኛ በሽታዎችን የሚያስከትል በመሆኑ አውሮፓዎች  ከኢትዮጵያ  የበርበሬ ምርት እንዳይገባባቸው እስከመከልከል በመድረሳቸው  ለአውሮፓ ገበያ የተላከ ምርታቸው ተመልሶባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዓመታዊ ገቢያቸው ከ300 ሺህ ወደ 200 ሺህ ዶላር ማሽቆልቆሉን  ይናገራሉ።

ችግሩን በራሳቸው መንገድ ለመፍታት ገጠር ገብተው ምርቱን በጥንቃቄ በመሰብሰብና በማከማቸት ከፈንገሱ ነጻ የሆነ የበርበሬ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ቢሞክሩም ምርቱ ከፈንገሱ ነጻ መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በመሳሪያ ብልሽት የተነሳ አገልግሎቱን መስጠት አለመቻሉ ችግር ሆኖባቸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ምርቱን ወደ ኬንያ ልከው ለማስመርመር 90 ዶላር ለመክፈል መገዳደቸውን ነው የገለጹት፡፡ ምርቱ አውሮፓ ከደረሰ በኋላም ቢሆን 300 ዶላር ከሂሳባቸው ተቀንሶ የአፍላቶክሲን ምርመራ ሳይደረግለት ለገበያ እንማይቀርብ አብራርተዋል፡፡

መንግስት አርሶ አደሩ ምርቱን በጥንቃቄ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ግንዛቤውን ከማሳደግ ጀምሮ  የላብራቶሪ አገልግሎት የሚስፋፋበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም ነው ወይዘሮ ኤልሳ የጠየቁት፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት  የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ አቶ ተክኤ ብርሃኑ ማሽኑ በብልሸት ምክንያት ለጊዜው አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አምነው መሳሪያውን ወደ ስራ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በስራ ፈጠራው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን  ችግሮችና ስኬቶች ነቅሶ በማውጣት የዘርፉን ማነቆዎች ማስወገድና መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት ቀጣይ የቤት ስራዎች ናቸው፡፡

በቀጣይ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በሙሉ አቅምና ጉልበት በመደገፍ ዘርፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሚሊየነሮችን እንዲያፈራና ለሚሊዮኖችም አስተማማኝ የስራ እድል እንዲፈጥር ተግቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን