አርዕስተ ዜና

የምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ለውጡ የመጪው ዘመን ከፍታ ማሳያ

08 Sep 2017
4428 times

ሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

በ18ኛው ክ/ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት የጀመረችው ሃገር ብሪታንያ ከአብዮቱ በፊት የህዝቧ ኑሮ የተመሰረተው በግብርና ላይ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ከተጠቀሰው ጊዜ በፊት ያመረተውን ምርት ምንም እሴት ሳይጨምር ጥቅም ላይ የሚያውለው ህዝቧ የሚመራው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ያሳሰባት እንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮት መቀስቀስ የግድ የሚላት ጊዜ ላይ እንድትደርስ አድርጓታል። በወቅቱ የግብርና ውጤቶችን ወደ ምግብነት ለመቀየር ኋላ ቀር የእጅ መሳሪያዎችን ይጠቀም የነበረውን ህዝቧን የተሻሻሉ መሳሪያዎችን እንዲጠቀም ማድረጓና ይህም ሁኔታ በብዛት ለማምረት ዕድልን በማመቻቸቱ ለኢንዱስትሪ አብዮት መጀመር መሰረቶች ነበሩ። በተበጣጠሱ የገጠር እርሻ መሬቶች ከሚያገኘው ምርት በቂ ገቢ ያልነበረው የህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ፋብሪካዎች በመቀጠር የገቢ ምንጭ ማግኘት ጀመረ። ከዚያም እንግሊዞች ከራሳቸው አልፈው ወደ ሌሎች ሃገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ አገኙ፤ ምጣኔ ሃብታቸውንም አሳደጉ። 

ከዚያም በ20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጃፓን ለ10 ተከታታይ ዓመታት ቀላል ኢንዱስትሪን በስፋት በመጠቀም ኢኮኖሚዋን በማሳደግ በምሳሌነት የምትጠቀስ ሃገር ሆነች። ቀጥሎም ታይገር ኢኮኖሚ የሚባሉት አገራት ማለትም ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ሆንግኮንግና ሲንጋፖር ለ20 ዓመታት ቀላል ኢንዱስትሪን ተጠቅመው ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ችለዋል።

ሶስተኛው ዙር ወደ ምስራቃዊ ቻይና ሲያመራ፤ አራተኛው ደግሞ በአሁኑ ወቅት ወደ ደቡብ ምስራቅ፣ ምስራቅና ደቡብ እስያ እንዲሁም አፍሪካ መጥቷል። እንግዲህ ኢትዮጵያም ለዘመናት በግብርና ላይ ተመስርቶ የነበረውን ኢኮኖሚዋን ወደ ኢንዱስትሪ በመዋቅራዊ ለውጥ ለመቀየር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

ለዚህም በዋነኝነት ማንሳት የሚቻለው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታዎችን ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹም ተመርቀው ወደ ምርት ተግባር በመግባት ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያመጡ ይገኛሉ። የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በቅርቡ ለምረቃ የበቁት የኮምቦልቻና መቀሌ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለተጠቀሰው ጉዳይ አብነቶች ናቸው። ከነዚህም ፓርኮች በተጨማሪ በአዳማና በድሬዳዋ ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ይገኛሉ። እነዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃገሪቱን የስራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ ከማድረጋቸውም ባሻገር ሃገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሚቀርፉት ይጠበቃል።

የሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሎ የተገመተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለአስር ሺዎች የስራ ዕድልን አመቻችቷል፤ ወደ ሙሉ ማምረት ሲገባ ደግሞ 60 ሺ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድልን ይፈጥራል። በቅርቡ የተመረቁት የኮምቦልቻና የመቀሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአንድ ላይ ከ25 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ያለስራ ከመቀመጥ ይታደጋሉ።      

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሃገሪቱ ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እያገኘቻቸው የሚገኙትን የምርት አቅርቦቶች እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ሰፊ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድል ያመቻቻሉ፤ እያመቻቹም ይገኛሉ።  በርካታ ስመጥር የአለማችን ታዋቂ ኩባንያዎችን ቀልብ እየሳቡ ይገኛሉ። በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ የጀመሩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ምርት ተግባር ገብተው ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ጀምረዋል። ሃገሪቷም በውጭ ባለሃብቶች ተፈላጊ ከሆኑ አገራት አንዷ ሆናለች።

ከዚህ በተጨማሪ በክልላዊ መንግስታት በኮርፖሬሽን ደረጃ የሚመሩ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታም የማከናወን እቅድ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ከእነዚህም መካከል በትግራይ ሁመራ፣ በኦሮሚያ ቡልቡላ፣ በደቡብ ይርጋለምና በአማራ ቡሬ አካባቢዎች የሚገነቡ የተቀናጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዋንኞቹ ናቸው። እነዚህ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪ ፓርኮች፣ ሀገሪቱ ሰፊ የግብርና እምቅ አቅም ያላት ከመሆኑ አንጻር፣ በግብርና ማቀነባበሪያ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር በሀገር ውስጥና በውጪ ገበያ እንዲሳተፉ ማድረግ ያስችላሉ። ቀደም ባሉት ዘመናት ለምርት ከውጭ ሀገራት ይገቡ የነበሩ ጥሬ እቃዎችን በራስ አቅም ለማምረት ከማስቻሉም በላይ መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመስራት ሀገሪቷ ብቃትን  እንድትላበስ ያደርጋታል። በተጨማሪ ሌሎችንም ኢንተርፕራይዞች በማሳደግ፣ በማስፋፋት ሀገሪቱን ወደ ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪዎች ማእከልነት በፈጠነ ሁኔታ ለማሸጋገር በትልቁ በር ይከፍታል፡፡ አንድ ሀገር ኋላ ቀር ከሆነ የግብርና ኢኮኖሚ ተነስታ ደረጃውን በጠበቀና ከግብርናው ጥሬ ምርት አቅርቦት ጋር ተመጋጋቢ የሆነ ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪዎችን አሳደገች፤ አስፋፋች፤ ማለት ቀጥተኛ ወደ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ልህቀትና እድገት ተሸጋገረች ማለት ነው፡፡ በዚህ ስር ነቀል የለውጥ ሂደት ውስጥ የግል ባለሃብቶች ሲሳተፉበት ደግሞ ጠቀሜታው እንዲጎላ ያደርገዋል።

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሚና ተኪ የለውም። ይህንኑ የተረዳው መንግስትም እየተገነቡ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ15 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች እንዲያዝ ዕድል አመቻችቷል። ለዚህም በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከገቡት በርካታ አለም አቀፍ ባለሃብቶች ጋር ስምንት ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሊያበረተክቱት የሚችለው አስተዋፅኦ የበለጠ ነው። በየኢንዱስትሪዎቹ ተቀጥረው ተግባራቸውን እየተወጡ የሚገኙ ዜጎችም በመዋቅራዊ ለውጡ ሂደት ውስጥ ሚናቸው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር በሚቀስሙት የዕውቀት ሽግግር የለውጡ ቀጣይነት በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲገነባ ያደርጋሉ።

በመላው አገሪቱ ተገንብተው የተጠናቀቁትና እየተገነቡ የሚገኙትት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችና 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ቀላል ኢንዱስትሪዎች ከሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ በኋላ ሰሞኑን የተመረቁት የኮምቦልቻና የመቀሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የቀጣዩን ሀገራዊ ኢንዱስትሪያዊ ጉዞና አቅጣጫ በፋና ወጊነት የሚያመላክቱ ሲሆኑ የፓርኮቹን ግንባታም በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ጅማሬ ማሳያዎች አድርጎ መውሰድ ይቻላል።     

ሆኖም እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሃገሪቷን ኢኮኖሚ በመዋቅራዊ ለውጥ ውስጥ እንዲገኝ ከማድረግ ያለፈም አስተዋፅኦ እንዳላቸው እሙን ነው። ከተሞች እንዲለሙ፣ ስራ አጥነት እንዲቀረፍ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲፋፋ፣ የአገር ውስጥ ምርታችን እንዲጨምር፣ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር እንዲስፋፋ፣ በአጠቃላይ የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ከማድረግ አንጻር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሚያስገኘውን ፋይዳ በመገንዘብ ለዚሁ የሚያግዙ በርካታ ዘመናዊ እና ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገነቡ ተደርገዋል፤ እየተገነቡም ይገኛሉ፡፡ የጥረቱ ፍሬም ከወዲሁ መጎምራት ጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የውጭ አገራትን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከቬትናም ቀጥላ ሁለተኛዋ ተቀዳሚ የዓለማችን አገር  ኢትዮጵያችን ሆናለች። በራሳችን የዘመን አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም. የአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን ዕቅድ በመያዝ እየተሰራ ይገኛል።

እንግዲህ ሃገሪቷ የምታደርገው ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ምጣኔ ሃብቷን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰው የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዕውቀታቸውን ጥግ ያህል ትንታኔያቸውን የሰጡበት ጉዳይ ነው። እንደ ባለሙያዎቹም በዕድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ለሃገሪቷ ምጣኔ ሃብት 40 በመቶ አስተዋፅኦ የነበረው ግብርና በመዋቅራዊ ለውጡ ምክንያትነት ኢንዱስትሪው ከነበረበት 15 በመቶ ወደ 28 በመቶ ከፍ እንዲል ሲያደርገው የማምረቻው ዘርፍን ደግሞ ካለበት አምስት በመቶ ወደ 18 በመቶ ያሳድገዋል። ቀድም ብሎ 40 በመቶውን ይዞ የቆየው ግብርና ደግሞ ወደ 32 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል።

ባለፉት አስር አመታት እየተመዘገበ የመጣው የሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ሃገሪቷን ስር ነቀል የምጣኔ ሃብት የለውጥ ምህዋር ውስጥ እንዲትገኝ አድርጓታል። በለውጡ ሂደትም ዜጎች ከዚህ ቀደም ይመሩት የነበረው ህይወት ተሻሽሎ የወደፊቱን ብሩህ ዘመን እውን በሚሆን ተስፋ ሊቀበሉ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። መዋቅራዊ ለውጡን ሰበብ ባደረጉ የልማት ስራዎች በርካቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ከዕውቀትና ከቴክኖሎጂ ሽግግሩም ብቁ ባለሙያ ሆነዋል። ለሃገራቸውም የወደፊት ተስፋዎች እየሆኑ ይገኛሉ። ሃገራቸው የሌሎች ሃገራት ምርት ማራገፊያ ብቻ እንዳትሆን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉም ናቸው።

ግብርናን ብቻ መሰረት አድርጎ የነበረውን የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት እሴት በተጨመረላቸው ምርቶች በመታጀብ በአለም አቀፉ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደሚያደርገው እምነት ተጥሎበታል። ‘‘መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ከፍታ ነው’’ ሲባልም ለአባባሉ እውንነት ስር ነቀል ለውጡ የሚኖረው ፋይዳ ከግምት ገብቶ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው።     

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን