አርዕስተ ዜና

ከብዛት ወደ ጥራት……

08 Sep 2017
3262 times

                                     ታምሩ ታደሰ /ኢዜአ/

ትምህርት ዜጎችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በመቅረጽ ለራሳቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለሃገራቸው ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዝ የእውቀት ማሸጋገሪያ ስልት ነው፡፡

የትምህርት ገበታ የተለያዩ ሰዎችን ባህል፣ እምነት፣ ልምድ፣ ተሞክሮ፣ ሕይወት፣ ስኬት፣ ሕልምና ምኞት…. ደባልቆ መመገቢያ ነው፡፡

እትዮጵያ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመኗ ካካተተቻቸው አበይት ተግባራት ውስጥ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና ተደራሽነቱን ማስፋት ይገኝበታል፡፡

ለመሆኑ ከ2ኛው የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ባሉት 10 ዓመታት በተለይ በመዲናዋ የትምህርት ዘርፉን ለማሳደግ የተከናወኑ አበይት ተግባራት ምንድን ናቸው? የመጡ ለውጦችስ?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ፍስሃ እንዳብራሩት በ2000 ዓ.ም  የቅድመ መደበኛ ትምህርት ጥቅል ተሳትፎው 937 የነበረ ሲሆን ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ጥቅል ተሳትፎውን ወደ አንድ ሺህ 168 መሳደግ ተችሏል፡፡ የተማሪዎች ቁጥርም ባለፉት አስር አመታት ወደ 172 ሺህ ከፍ ብሏል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የግል ባለሃብቱና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በከፈቷቸው ትምህርት ቤቶች ከፍለው መማር የማይችሉ ተማሪዎች የትምህርት እድል ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣  ከሁለተኛው የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ግን መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ከፍለው መማር የማይችሉ ተማሪዎችም የትምህርት እድሉን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አስር ዓመታት  አዲስ አበባ የነበሯት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  ቁጥር ከ655 ወደ 806 ከፍ ማለቱንና ይህም ከ510 ሽህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ማስቻሉን  ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ የግልና የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከ145 ወደ 217 ማደጉን ተከትሎ  የተማሪዎች ቁጥር 8 ሽህ 631  መድረሱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርትና  በትምህርት ቤቶች ማሻሻል  እንዲሁም በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በዚህም በ2000ዓ.ም  የነበረውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ቁጥር ከ15 ሺህ 253 በ2009 ወደ 22 ሺህ 311፣  የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ከ9-12) መምህራንን ቁጥር ደግሞ ከአራት ሺህ 471 ወደ 8 ሺህ 631 ማድረስ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቹ ደረጃቸውን በጠበቁ የመማሪያ ክፍሎችና የተሟላ የትምህርት ግብዓት በተሟላላቸው ትምህርት ቤቶች የሙሉቀን ትምህርት እንዲያገኙ በርከት ያሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የመማሪያ መጽሀፍ በጥቁርና ነጭ የታተም እንደነበርና ቁጥሩም ከተማሪዎች ቁጥር ጋር የማይመጣጠን እንደነበር አስታውሰው አሁን መጻህፍቱ በባለሙሉ ቀለም እንዲታተሙ ከመደረጉም ባሻገር የመጻህፍቱንና የተማሪዎችን ቁጥር ማመጣጠን እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

የመዲናዋን መስፋፋት ታሳቢ በማድረግ የትምህርት ተደራሽነቱንም በዚያው ልክ ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ50 እንዳይበልጥ ተደርጓል፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ቢሆን ከማስፋፊያ አካባቢዎች ውጪ አፈጻጸሙ ከሁለተኛ ደረጃው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

የግል ትምህርት ተቋማትም በተለይ 90 ከመቶ ያህሉን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ሽፋን በመያዝ  ለትምህርት ተደረራሽነትና ጥራት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ነው አቶ ኃይለስላሴ የተናገሩት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ተደራሽነቱን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከ32 ሺህ ለሚበልጡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች  የምገባ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ሰሞኑን ይፋ እንዳደረጉት ደግሞ አስተዳደሩ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራሙ ለታቀፉና የደሃ ደሃ ተብለው ለተለዩ 10 ሺህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትምህርት ቤት አልባሳትና መሰል የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት የተላበሱ መምህራንን ማፍራትና የትምህርት ደረጃቸውን መሰረት ያደረገ ድልድል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኃይለስላሴ ፍስሃ ከተማ አስተዳደሩ ከአመታት በፊት ተገቢውን የትምህርት ዝግጅት ያሟሉ  መምህራን  እጥረት እንደነበረበት ባይደብቁም  አሁን  ከ5-8ኛ ክፍል ከሚያስተምሩ መምህራን ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ አብዛኞችን የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል የመጀመሪያ ዲግሪ ባላቸው መምህራን መሸፈን የተቻለ ሲሆን አብዛኞቹ የመሰናዶ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት ተቋማት የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በመሆኑ በአጭር ጊዜ የመሰናዶ ትመህርት ሁለተኛ ዲግሪ ባላቸው አስተማሪዎች ይሸፈናል፡፡

የትምህርት ጥራትን በቴክኖሎጂ ከመደገፍ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት  በሬዲዮ የሚታገዝ ቢሆንም ጥራቱ ላይ የጎላ ውጤት ባለማምጣቱ አሁን የትምህርት በሬዲዮ ጣቢያው ራሱን ችሎ እንዲደራጅ መደረጉን ምክትል ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንም የኢንተርኔት አገልግሎትና የስኩልኔት መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ፋይናንስና ግብአት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ግብአትን በአይነትም በመጠንም አስተማማኝ በሆነ መልኩ ማቅረብ የሚችልበትን አቅም መፍጠሩን ምክትል ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራቱን ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል ያመች ዘንድም የዘርፉ ማነቆዎች ተለይተው ስድስት መርሃ ግብሮች ያሉት የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ  ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በመምህራን ዝግጅት፣ በአስተዳደርና በማትጊያ ስርአቱ፣ የመምህራንን የአኗኗር ሁኔታ ከማሻሻል፣ የትምህርት ቴክኖሎጂና ከማሳደግ፣ የስርአተ ትምህርት ማሻሻያና አጠቃላይ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ከማድረግ አኳያ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው አቶ ኃይለስላሴ ያብራሩት፡፡

ይሁን እንጂ በተሰራው ስራ ልክ የሚጠበቀው ውጤት አለመመዝገቡንም ምክትል ኃላፊው አልደበቁም፡፡ ለዚህም ምንም እንኳን ሁሉም ተማሪዎች 50ና ከ50 በመቶ በላይ  ውጤት አምጥተው ማለፍ እንዳለባቸው በፖሊሲው  ቢቀመጥም  ከግቡ ላይ ለመድረስ ግን ብዙ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡

በአዲሱ የትምህርት ዘመን ሁሉንም ተማሪዎች ለውጤት ለማብቃት የተሻለ አሰራር መዘርጋቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አቶ ኤልያስ ግደይ የወይዘሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ናቸው፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት የሚመሩትን ትምህርት ቤት ምሳሌ አድርገው በትምህርት ዘርፉ የተመዘገቡ ለውጦችን አብራርተዋል፡፡

ከዓመታት በፊት በትምህርት ቤታቸው በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 100 የሚደርሱ ተማሪዎች ይማሩ እንደነበር ገልጸው አሁን በአንድ ክፍል  ከ30-40 የሚሆኑ ተማሪዎች ብቻ እየተማሩ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

የትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ቁጥር ከ19 ወደ 43 በማደጉም ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ አስችሎታል፡፡

ርዕሰ መምህሩ የስኩልኔት፣ የፕላዝማ፣ የላብራቶሪና መሰል የትምህርት ግብቶች በሚፈለገው መልኩ መሟላታቸውን ገልጸው ለዚህ ደግሞ የትምህርትቤቱ በጀት ከ2 ሚሊዮን ወደ ስምንት ሚሊዮን ማደጉ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

የመምህራን አያያዙ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ቢሆንም በተሰራው ስራ ልክ ግን የትምህርት ጥራቱ የሚጠበቀውን ለውጥ አለማምጣቱን ርዕሰ መምህሩ አልደበቁም፡፡

በአዲሱ የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን የሚጀምረው ተማሪ ዳንኤል አያሌውም ቀደም ባሉት አመታት ይታይ የነበረው የኮምፒውተርና የተለያዩ የመማሪያ ግብአቶች እጥረት ሙሉ በሙሉ መቀረፉን ተናግሯል፡፡

በአንድ ክፍል ውስጥ አብረውት የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ30 አለመብለጡም ትምህርቱን ሳይጨናነቅ ለመከታተል እንዳስቻለው ገልጾ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ለመረዳዳት በ1ለ5 ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አስር ዓመታት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥና አስፈላጊ ግብዓቶችንም ለማሟላት የሔደበት ርቀት በግልጽ የሚታይ ቢሆንም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ግን አሁንም ድረስ ውስንነቶች ይስተዋሉበታል፡፡

የተማሪዎችንና የትምህርት ቤቶችን ቁጥር የማሳደጉ እንዲሁም የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን የማሟላቱ  እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ በዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር የመቅረፉ ስራ ግን ለነገ የሚባል ተግባር መሆን አይኖርበትም፡፡

ለዚህም መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት የትምርትን ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በሙሉ አቅማቸው ሊደግፉት ይገባል፡፡

                               መልካም የትምህርት ዘመን!

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን