አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ታላቁ መሪና አረንጓዴ ኢኮኖሚ

12 Aug 2017
3266 times

                      ሰለሞን ተሰራ /ኤዜአ/

ዓለማችን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ለውጦች ተፈራርቀውባታል፡፡ ከፖለቲካዊ አብዮቶች “እምቢተኝነት” በተጨማሪ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በሳይንሱ፣ … መስክ አያሌ ዘመን ቀያሪና ሂደት ለዋጭ አብዮቶችን አስተናግዳለች፡፡

ጌታቸው አሰፋ ጥቅምት 2004 ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳብራሩት እነዚህን አብዮቶች ‘አብዮት’ ያሰኛቸው ከዚያ በፊት የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ወይም የሳይንስ … እንቅስቃሴ ወይም ስራ ስላልነበረ አይደለም።

ይልቁንም በመጠናቸውና በአይነታቸው ከተለመደውና ከነበረው አሰራርና አካሄድ ለየት ባለ መልኩ ግብርናው፣ ኢንዱስትሪው፣ ሳይንሱና የመረጃ ቴክኖሎጂው ስለተስፋፋና አገሮች ከተለመደው መንገድ ‘በእምቢታ’ ወጥተው ወደ አዲሱ መንገድ ስለገቡ እንጂ፡፡ አረንጓዴ አብዮትም ይህን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡

ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በመቀነስና በመቋቋም ረገድ ሀገራት ሊከተሏቸው ስለሚገባቸው አቅጣጫዎችና መውስድ ስለሚገባቸው እርምጃዎችም ጭምር በሳል ሀሳቦችን አንስተዋል፡፡

እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስም የሀገራቸውን የአረንጓዴ ልማት ራዕይ ለማሳካትና አቋማቸውንም ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማስገንዘብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ታግለዋል፡፡

በዴንማርኳ ኮፐንሃገን የተካሄደውን ጉባዔ ባስታወስን ቁጥር የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አሻራ በግልጽ ያረፈበት የበለጸጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጡ የጎላ አስተዋጽኦ ለማያደርጉት ግን ደግሞ ከሌሎቹ እኩል የችግሩ ገፈት ቀማሽ  ለሆኑ ደሃ ሀገራት ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚለው መከራከሪያ ሃሳብ ይታወሰናል፡፡

በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት በሚለቁት በካይ ጋዝ ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ደሀ ሀገራት ተጽእኖውን መቋቋም እንዲችሉ ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል የሚለው የመከራከሪያ አቋማቸው ሚዛን ደፍቶ ብዙዎችን አግባብቶ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

በጉባዔው ማጠቃለያም  ያደጉ አገሮች እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ለአፍሪካና ለታናናሽ ደሴቶች የሚውል ተጨማሪ 30 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃላቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

 እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ ደግሞ በየዓመቱ መቶ ቢሊዮን ዶላር ሊሰጡ መስማማታቸውም ኢትዮጵያ ለመራችው የተደራዳሪ ቡድን ትልቅ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ይሁን እንጂ ቃል የተገባውን ገንዘብ ያዋጣሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩ ሀገራት የተለያዩ ሰበቦችን እየደረደሩ ቃላቸውን በመብላታቸው ታላቁ መሪ የተሟገቱላቸው ሀገራት አሁንም ድረስ ተገቢውን ካሳ አላገኙም፡፡

በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መሪነት ከ20 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተውጣጡ 50 ባለሙያዎች ተሳትፎ የተዘጋጀው የሀገሪቱ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ፣ የሀገሪቱ ፈጣን እድገት የእርሻ መሬት መጣበብን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብት መራቆትን ሊያስከትል እንደሚችል ያትታል፡፡ የሀገሪቱ እድገት ፈታኝ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችልም በግልጽ አስቀምጧል፡፡

የሀገሪቱን ፈጣን እድገት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመጣል ያመች ዘንድ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ትኩረት የተሰጠውም ለዚህ ነው፡፡

ስትራቴጂው በተዘጋጀበት ወቅት ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለማገዶ ሲባል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ደን ይጨፈጨፋል፡፡ አረንጓዴው ኢኮኖሚ ከማገዶ እንጨት ፍላጎት ማደግ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ የደን ሀብት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀነስ ሁለት ስትራቴጂዎችን አስቀምጧል፡፡

አንደኛው አማራጭ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ጨምሮ የኤሌክትሪክ፣ የሲሊንደር፣ የባዮጋዝና መሰል የኃይል አማራጮችን  ማስፋፋት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዛፎችን መልሶ በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን በመጨመር የከባቢ አየር ለውጡን ተጽዕኖ መቋቋም ነው፡፡

የሀገሪቱ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለዓለም ኢኮኖሚም ጭምር አዋጭ ሀሳቦችን አካትቷል፡፡ አገሪቱ የምትከተለው አረንጓዴና ‹‹ያልተበከለ›› የኢኮኖሚ አማራጭ  ከምታመነጨው ዝቅተኛ የበካይ ጋዝ መጠን ጋር ተደማምሮ 80 በመቶው የሚሆነውን በካይ ጋዝ ቋጥሮ ለማስቀረት የምታወጣውን ወጪ ይቀንስላታል፡፡

ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ እየተጓዘች ያለችበት የልማትና እድገት መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንዳይሰነካከልም ግልጽ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፤ የመከላከያ ስትራቴጂዎችን በመንደፍም በተግባር አረጋግጠዋል፡፡

በፍጥነት እያንሰራራ ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና ከእድገቱ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ሁኔታዎች ለአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ እንዳይሆኑ  አዋጪው መንገድ  የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂን መተግበር ነው በሚለው አቋቸማውም ይታወሳሉ ታላቁ መሪ፡፡

ይህ አቶ መለስ ሲያራምዱት የነበረው አቋምና ቁርጠኝነት ሀገሪቱን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አረንጓዴ ልማት ከሚያራምዱ ሀገራት ውስጥ በመጀመሪያው ረድፍ እንድትሰለፍ አድርጓታል፡፡፡

መላ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታላቁ መሪ ህልፈተ ህይወት ማግስት የገቡትን  ቃል አክብረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግንባታ ራዕያቸውን  ለማሳካትና ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ህብረተሰቡ በቁጭትና በእልህ በራሱ ተነሳሽነት የታላቁን መሪ ለከባቢ አየር ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይ ለማሳካት ባደረገው ርብርብም የሀገሪቱ የደን ሽፋን እየተሻሻለ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን