አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የዓለም ሻምፒዮና የእስከአሁኑ ውጤትና የህዝቡ ስሜት

11 Aug 2017
3315 times

ይሁኔ ይስማው-ኢዜአ

በእንግሊዝ ለንደን በመካሔድ ላይ በሚገኘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ባለፉት ሰባት ቀናት ከተደረጉ ውድድሮች 24ቱ አሸናፊዎቻቸው ታውቀዋል።

ኢትዮጵያም  ከተጠናቀቁት 24  የስፖርት አይነቶች ውስጥ በሰባቱ ተካፍላ ሶስት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። የቀሩት አምስት ውድድሮች በቀጣዮቹ  ሶስት ቀናት ፍጻሜአቸውን እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ከተካፈለችባቸው 13 የስፖርት አይነቶች መካከል 3 ሺህ መሰናክል ወንዶች፣ 800 ሜትር ወንዶችና 1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ውድድር አሸናፊዎች ተለይተዋል።በሁለቱም ጾታ የተካሔዱት የ10 ሺህ ሜትርና የማራቶን ፍልሚያ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።

አገራችን ከተሳተፈችባቸው ርቀቶች መካከል  በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች አንድ ወርቅና አንድ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በወንዶች ማራቶን  አንድ የብር ሜዳሊያ ማግኘት ተችሏል።

በሴቶች 10 ሺህ ሜትር አትሌት አልማዝ አያና ወርቅ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ የብር ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስገኝተዋል።

ፍጻሜአቸውን ካገኙት ውድድሮች መካከል በወንዶች 10 ሺህ ሜትር እንግሊዝን የወከለው ሙሀመድ ፋራህ ፉክክሩን በበላይነት ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በርቀቱ ሜዳሊያ ማጥለቅ አልቻሉም።

በተመሳሳይ በወንዶች 3 ሺህ መሰናክልና  800 ሜትር እንዲሁም በሴቶች ማራቶን የተሳተፉት አትሌቶች አጥጋቢ ውጤት አላስመዘገቡም።

አገራችን ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ ቅድሚያ ግምት የተሰጠውና ብዙዎችን ያስቆጨ ውጤት የተመዘገበበት የሴቶች የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ነው።

በርቀቱ ኢትዮጵያን ወክለው ከተወዳደሩት መካከል አትሌት ጉዳፍ ፀጋይና በሱ ሳዶ ማጣሪውን ማለፍ ሲያቅታቸው ትልቅ ተስፋ የተጣለባት አትሌት ገንዘቤ ዲባባም በፍጻሜው ድል ሳይቀናት ቀርቷል።

በዚህ ርቀት ኢትዮጵያ ሜዳሊያ በማጣቷ በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የተለያዩ አሉታዊ አስተያየቶች ተደምጠዋል።በተለይ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚነሱት ሐሳቦች ሚዛን የማያነሱ መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

አትሌት ገንዘቤ ባለፉት ዓመታት ሀገሯን ወክላ በተሳተፈችባቸው ርቀቶች  ስምንት ወርቅ ፣ ሁለት ብርና አንድ ነሀስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን ለሀገሯ አስገኝታለች።

አትሌቷ ካለችበት እድሜ አኳያ  በቀጣይ በኦሎምፒክና በአለም ሻምፒዮና ውድድሮች በመካፈል  ለሀገሯ ብዙ ታሪኮችን እንደምትሰራም ይጠበቃል።

ለአትሌቶች ድክመታቸውን የሚያስተካክሉበትና  ጠንካራ ጎናቸውን የሚያጎለብቱበት  አስተያየት መስጠት የሚያበረታታ ሲሆን በስሜት የተሞሉ ስዎች የሚያቀርቡት ስድብ አዘል ትችት ግን ከባድ የስነልቦና ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል በቅድሚያ ሊታሰብበት ይገባል።

አንድ ሳምንት ያስቆጠረው 16ኛው የዓለም ሻምፒዮና  ከሶስት ቀናት  በኋላ የሚጠናቀቅ ሲሆን ኢትዮጵያም በቀጣይ ከምትወዳደርባቸው ስድስት የስፖርት አይነቶች በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ተወዳዳሪዎቹ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻሉም።በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀሩት የውድድር አይነቶች ሜዳሊያ ለማግኘት ተሳትፎዋን ትቀጥላለች።

በ1 ሺ 500 ሜትር ወንዶች ተካፋይ ከነበሩት  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አማን ወጤ በጉዳት፣ተሬሳ ቶሎሳ ውድድሩን በጡንቻ ህመም ምክንያት በማቋረጡና ሳሙኤል ተፈራ ደግሞ ስምንተኛ በመውጣት ከፍጻሜው ውድድር ውጭ ሆነዋል።

 በዚህ የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ከ 25 በሚካሄደው የ3 ሺህ መሰናከል የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌት እቴነሽ ዲሮና ብርቱካን ፈንቴ ትወከላለች።

ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ ተስፋ ከተደረገባቸው ርቀቶች የወንዶች 5 ሺህ ሜትር  አንዱ ሲሆን በርቀቱ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ፣ሰለሞን ባረጋና ሙክታር እንድሪስ ከእንግሊዛዊ አትሌት ሙሀመድ  ፋራህ እና ከኬንያውያን ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።

እሁድ በሚከናወነው 16ኛው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ማጠናቀቂያ ላይ ኢትዮጵያን በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር የሚወክሉት አልማዝ አያና፣ሰንበሬ ተፈሪና ለተሰንበት ግደይ  ከኬኒያዊቷ ሄለን ኦብሬ ጋር የሚያደረጉት ትንቅንቅ መላው የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪ በጉጉት የሚጠብቀው ነው።

 በውድድሩ መዝጊያ ቀን ኢትዮጵያ በሴቶች የ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ፍጻሜ ትካፈላለች።

አትሌት ሀብታም ዓለሙ ዛሬ የሚደረገውን የ800 የሴቶች ግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ማለፍ ከቻለች በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ እለት ለፍጻሜ የምትወዳደር ይሆናል።

በአለም አትሌቲክሰ ውድድር አንደኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ  አትሌቶች 1 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛ ለሚወጣ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም እስከ ስምንተኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የተለያየ የገንዘብ ሽልማት ይሰጣቸዋል።

ከዚያ ውጭ አትሌቶች በአለም አቀፍ ውድድሮች ሲያሸንፉ በግላቸው ስፖንሰር ካደረጓቸው የስፖርት ትጥቅ አምራቾችና ኩባንያዎች  ሽልማት የሚያገኙ በመሆኑ ጊዚያዊ የውጤት ቀውሱን ከገንዘብ ጋር ማያያዝ ተገቢ አለመሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መንግስትም የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ላውለበለቡ አትሌቶች የሚሰጠው የራሱ የማበረታቻ ሽልማትም አለው።

መንግስት ከሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት ባለፈ ለአሸናፊ አትሌቶች እውቅናና ምስጋና ያቀርባል፡፡ ባለድሎቹ ከሀገራቸው ህዝብም ከፍተኛ ክብርና ፍቅር የሚያገኙ መሆኑን ካለፉት ዘመን አይሽሬ አትሌቶች ስለሚገነዘቡ ምክንያቱን ከሰሙ በኋላ አሰተያየት መስጠት ብልህነት ስለሆነ ቀድመን ለወቀሳ አንቸኩል፤አበቃሁ፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን