አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ስደተኛው ኢንዱስትሪ

08 Aug 2017
3175 times

                                መብራህቱ  ይበልህ (መቀሌ ኢዜአ)

ብዙዎቹ  ስደተኛው  ኢንዱስትሪ  ይሉታል። ከአገር አገር፣ ከአህጉር አህጉር ስለሚንከራተት ነበር ስደተኛው የሚል መጠሪያ  የተሰጠው ። የመንከራተቱ ሚስጢር ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ የሰው ጉልበትና እውቀት ለማግኘት ነው።

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ከሌላው የማምረቻ ዘርፍ በተለየ መንገድ ከርታታ መሆኑ ይነገርለታል ። ቋሚ ወዳጅ የለውም። ከወቅቱ ጋር አብሮ የሚሄድ ወዳጅን ፍለጋ ባህር አቋርጦ  ምድርን  ሰንጥቆ  የሰው ሀይል ያለህ እያለ የሚንከራተት ዘርፍ መሆኑ ነው።

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስቱሪ ዓመታዊ ግብይቱ በትሪሊዮን  የአሜሪካን ዶላር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ። በዘርፉ የሚንቀሳቀሰው የሰው ሀይልም ከሌላው የማምረቻ ዘርፍ በብዙ እጥፍ ብልጫ ይወስዳል።

በአለማችን በርካታ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ባለቤት ከሆኑ አገሮች መካከል የህንድን ዓመታዊ ግብይት ብንመለከት ዘርፉ ምን ያህል አዋጪና ሰፊ ምጣኔ ሀብት እንደሚንቀሳቀስበት እንገነዘባለን ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ህንድ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በዓመት 150 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለገበያ እንደምታቀርብ ያሳያል። ከዚሁ ውስጥ 40 ቢሊዮን ዶላሩ ወደ ውጭ በመላክ  የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ መሆኑን ያሳያል።

አገሪቱ ካላት የህዝብ ብዛት አንፃርም  ኢንዱስትሪው በእጅጉ የሚያዋጣት ሆኖ ተገኝቷል። 51ሚሊዮን ህዝቧ በጨርቃ ጨርቅና አልበሳት ስራ  ቧሰማራቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ህንድ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገቢ  15 በመቶ ያህሉን ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት  ኢንዱስትሪ ታገኘዋለች። ከአጠቃላይ አመታዊ ምርቷም  የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉ ድርሻ አራት ከመቶ ይሸፍናል።

በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ደግሞ አመታዊ ግብይቷ  ወደ 230 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ለማድረግ እየኳተነች እንደምትገኝ ድረ ገፆች ያሳያሉ።

አገራችን በዓለም ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ፣ በርካታ ገዢ ኩባንያዎች፣ ብዙ ሚሊዮን የሰው ሀይል ወደ ሚንቀሳቀስበት  የማምረቻ ዘርፍ  ለመቀላቀል  ወገቧን ጠበቅ መንቀሳቀስ ጀምራለች።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከተመረቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የመታጨቱን ብስራት ሰምተናል።

በምረቃው ስነ ስርአት ላይ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ እቁባይ የማምረቻ ዘርፉን ዋና የኢኮኖሚው ምሰሶ ለማድረግ ስራው እንደተጀመረ አብስረዋል።

ዘርፉን ለመቀላቀል ግን በርካታ እድሎችና ፈተናዎች ጎን ለጎን መቀመጣቸውም ተገልጿል። ከፈተናዎቹ መካከል በብዙ ትሪሊዮን ዶላር የሚንቀሳቅሰውን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ገበያ ሰብሮ ለመግባት መንገዱ አልጋ በአልጋ  አለመሆኑን ዶ/ር አርከበ እቁባይ ያስረዳሉ።

ከተሰራበት፣ከተለፋበትና ወገብን ጠበቅ ተደርጎ ከተገባ ግን ወደ ውድድሩ ለመግባት በርካታ  ፀጋዎችና እድሎች እንዳሉም ዶ/ር አርከበ እቁባይ አስረድተዋል።

በዙሪያው ተመሳሳይና ተመጋጋቢ  ኢንዱስቱሪዎች ማበባቸው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክን መፃኢ ጊዜ ብሩህ ያደርገዋል።

በውጭ ባለሀብቶች ተገንብተው ወደ ማምረት ምእራፍ እየተሸጋገሩ የሚገኙት የህንድ ኩባንያ  ቮሎሲቲ፣የባንግላድሽ ኩባንያ ዲቢኤል፣አንድ የጣልያን ኩባንያና ቀደም ብሎ የተገነባ ማጋርመንት መቐለ አካባቢ መከተማቸው ፓርኩን እድለኛ ያደርገዋል።

እርሻ ብቻ ሳይሆን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፎችም በኩታ ገጠምና በመደዳ  እየከተሙ በመሆናቸው በርካታ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይነገራል።

ከአዋሽ ሃራ ገበያ መቐለ በመገንባት ላይ ያለው የባቡር ሀዲድም ዘርፉ የሚያመርተውን ምርት በፍጥነት ወደ ወደብ ለማንሳትና ከውጭ የሚመጡ ግብአቶችን በብዛትና በፍጥነት ለማጓጓዝ አመቺ ያደርገዋል ።

መቐለ ከጅቡቱ ወደብ በ600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አመቺ ያደርገዋል ።  

ዶክተር አርከበ እቁባይ እንዲህ ይላሉ፣ “እርዳታ መለመንና ወደ ሰው አገር ተሰዶ ጉልበትን በርካሽ ዋጋ መሸጥን የመሰለ አሳፋሪ ስራ የለም ። ኢንቨስትመንትን መሳብ ግን የድህነት መገለጫ ሳይሆን ለልማት የቆረጠ መንግስት ማሳያ ነው።”

ሰፊ ኢንቨስትመንትን መሳብ ቀጣዩና ከባዱ የቤት ስራ መሆኑንም  ያስረዳሉ። በተለይም የዳበረ ቴክኖሎጂ ፣ልምድና ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን ማስመጣት የውድድር ብልህነትን ይጠይቃል ባይ ናቸው።

ከመቐለ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ የሚገኙ ከተሞችም  የኢንዱስቱሪ ማእከል የመሆን እድላቸው ሰፊ መሆኑን ይናገራሉ ።ይህንኑ ለማድረግም  ክልሉና የፌደራል መንግስት ዝግጁ መሆናቸውን በመጠቆም።

በዘርፉ የሚሰማራውን የሰው ሃይል የኢንዱስትሪ አስተሳሰብና ቅኝት ያለው ፣ በእውቀትና በክህሎት እራሱን ያዘጋጀ ለማድረግ ውስብስብና ከባድ ፈተና በመሆኑ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባልም ነው ያሉት ዶክተር አርከበ ።

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።

የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስገዶም ለኢዜአ እንደገለፁት የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ  በልዩ ሀኔታ የተገነቡ 15 ሼዶች አሉት። ወደ ስራ ሲገቡ  20 ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች  የስራ እድል ይፈጥራሉ ። ሌላ ከተማ መቆርቆር ማለት ነው።

ፓርኩ ውስጥ የህክምና፣የፖሊስ፣የአንድ መስኮት አገልግሎት ማእከል ፣የጉምሩክ፣ንግድና የሌሎች አገልግሎቶች መስጫ ማእከላትና ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎችን ያካተተ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በኢፌዴሪ የኢንቨስትመንት ኢጀንሲ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑ አቶ አበበ  አበባየሁ ፓርኩን በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም በዓለማችን የሚታወቁ ሶስት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ለመግባት የሚያስችላቸውን ድርድር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ሲመረጥ ያለ ምክንያት አይደለም ያሉት አቶ አበበ ለዘርፉ የሚመች የሰው ሀይል መኖሩን በጥናት ተረጋግጧል ይላሉ።

በዙሪያው በዘርፉ ሊሰራ የሚችል ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ የሰው ሀይል መኖሩ እንደተረጋገጠም ያስረዳሉ።

ይህም በመቐለ ዙሪያ እየከተሙ ያሉትን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች የሚመግብ የሰው ሀይል በመኖሩ ከርታታው ወይም ስደተኛው ፋብሪካ ማረፊያ እንዲያገኝ እስችሎታል።

ፓርኩ በፍጥነት ስራ እንዲጀምር የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ምክትል ርእስ መስተዳድሩ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ ናቸው።

ፓርኩን ሊያውኩ የሚችሉ የውሃና የኤሌክትሪክ እጥረት  በፍጥነት እንዲፈታም የፌደራል መንግስቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል።

አብዛኛው የክልሉ ህዝብ ኑሮው ግብርና ላይ የተመሰረተ ቢሆንም 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከተማ ውስጥ ይኖራል።

ፈጣን የሚባል የአዳዲስ ከተሞች መቆርቆርና መስፋፋት ከሚታይባቸው የአገራችን ክልሎች መካከል ትግራይ ግንባር ቀደም ደረጃ እንደያዘችም ይጠቀሳል።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በፓርኩ ምረቃ ላይ ’’ የትግራይ ክልል ከሌሎች የአገራችን ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ከግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ባለፈ ህዝቡም ሆነ የክልሉ መንግስት በአማራጭ የኑሮ መሰረቶች ላይ ትኩረት ሲያደርግ ቆይቷል።በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መፃኢ እድሉ ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር የተቆራኘ እንደሚሆንም ህዝቡ የተረዳው እጅግ ቀደም ብሎ ነው’’ ያሉት ።

የህዝቦች ወደ ከተማ መሰብሰብ ማህበራዊ መሰረተ ልማቶችን ከማቅረብ ባለፈ ለኢንዱስቱሪ ልማት መስፋፋትም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት ።

ስደተኛው ኢንዱስትሪ ማረፊያውን መቐለ ኢንዱስትሪ  ፓርክ ለማድረግ ተቃርቧል ። የአካባቢው ወጣቶችም በናፍቆት እየጠበቁት ነው ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን