አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ፈሳሹ ወርቅ

07 Aug 2017
3651 times

ተካ ጕግሳ -ከኢዜአ

በአፍሪካ በወተት ምርት ቀዳሚዋ አገር ደቡብ አፍሪካ እንደሆነች ጥናቶች ያመለክታሉ። በአማካይ በአንድ የቤተሰብ መሪ 357 የወተት ላሞች ይገኛሉ። ባለፉት 10 ዓመታት የወተት ላሞችን በእጥፍ ያሳደገችው ደቡብ አፍሪካ ከዚሁ ዘርፍ የምታገኘው ምርት ከአህጉሩ ቀዳሚ እንድትሆን የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ኬኒያ፣ሱዳንና ግብፅ ተከታዩን ደረጃዎች ይይዛሉ ።

ጥናቱ አገራችን ያለችበት ደረጃ ባያሳይም ዜጎችዋ የሚያደርጉት ጥረትና አገራችን ከዘርፉ የሚታገኘው ምርት ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን እየተደረጉ ካሉት እንቅስቃሴዎች መረዳት ይቻላል።

ወጣት ሳምራዊት ድምፁ ትባላለች። የ27 ዓመት ወጣት ስትሆን ተወልዳ ያደገችው በመቀሌ ከተማ ነው ።በ2003 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ሙያ ከመቐለ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች ። ስራ ለመያዝም ጊዜ አልፈጀባትም።

በ2004ዓ.ም በድምፂ ወያነ ትግራይ ተቀጥራ የወር ደመዝተኛ ሆና ነበር። በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁና በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገኙ ወጣቶች እያነጋገረች ለአድማጮችዋ ፕሮግራም ሰርታም ታሰራጭ ነበር ።

የወጣቶቹ መለወጥ ቀድሞ ወደ ውስጧ የገባው ሳምራዊት ከተቀጣሪነት ይልቅ በግል ወይም በማህበር ተደራጅቶ መስራት አዋጪ መሆኑን በስራ አጋጣሚዎች በተግባር አይታዋለች ።ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ስራ ለመጀመር ምክንያት እንደሆናትም ትናገራለች ።

ሆኖም መደበኛ ስራዋን ፈጥና ለመልቀቅ አልፈለገችም። ነገር ግን በውስጥዋ ያለው ስሜት ማስታገስ ትፈልጋለች።ባጠራቀመችው ትንሽ ገንዘብ መነሻነት በትርፍ ጊዜዋ የራስዋ ስራ ለመስራት ወሰነች ። በመሆኑም በወላጆቸዋ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ 3ሺህ 200 ብር በመያዝ 20 ደሮዎች ገዝታ ማራባት መጀመርዋን ገልፃለች።

ከዶሮዎቹ የምታገኘው ጥቅም እያደገ በመምጣቱ በአንድ አመት ውስጥ ወደ አምስት መቶ ብታደርሳቸውም በተለያዩ ምክንያቶች ለኪሳራ በመዳረግዋ ስራውን ለማቆም ተገደደች  ። የረጅም ጊዜ ህልሟ ግን ለጊዜው ተዳፈነ እንጂ አልጠፋም ።

የጋዜጠኝነት ስራዋን ለማከናወን በአንድ ወቅት ወደ ውቅሮ ስትሄድ ከአመት በላይ ተዳፍኖ የቆየው ህልሟ መነቃቃት ጀመረ።በዚሁ ከተማ በወተት እርባታ ተሰማርቶ ያገኘችው ወጣት ያሳለፋቸው ውጣ ውረዶችና የደረሰበት ደረጃ ስትረዳ ራሷም በወተት ሃብት ለመሰማራት የሚያዳግታት አለመሆኑን በመገንዘብ ስራውን ለመጀመር ውሳኔ ላይ ደርሳለች።

“አንድ ጊዜ ለስራ ወደ ውቅሮ ሄድን አንድ በጣም የተቀየረ ወጣት ነበረ። ወጣቱ ደግሞ ላም ገዝቶ የተቀየረ ነበር ። እኔም የሱን ተሞክሮ አይቼ መጋቢት  ወር 2006 ዓ.ም አካባቢ የመጀመሪያ ላሜን ‘ሸዊትን’ ገዛሁ ። በ27 ሺህ ብር  ነበር የተገዛችው ። ሸዊት መጀመሪያ ስራ የጀመርኩባት የወተት ላም ስም ነው ። የስያሜው ትርጉም ደግሞ እሸት ማለት ነው “ ትላለች።

በሶስት ዓመታት ውስጥ የላሞችዋ ቁጥር ወደ 17 በማድረስ ስራውን አጠናክራ እያስኬደችው የምትገኘው ሳምራዊት በአሁኑ ወቅት ከ700ሺህ ብር በላይ ካፒታል እንዳላት ታስረዳለች ። በቀጣይም የራስዋ የሆነ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም እቅድ እንዳላት ትናገራለች ።

 “በአሁኑ ወቅት ህዝብና መንግስት በሚያደርጉት ጥረት አገራችን በጥሩ ጎዳና ላይ ናት ።ይህ በቀላሉ የተገኘ አይደለም። አሁንም አገራችንን ይበልጥ የምታድገው በዜጎችዋ ነው ። በተለይም በእኛ ወጣቶች ነው። ስለዚህ ለመለወጥ መስራት ያስፈልጋል ። የኔ አይነቱ ስራ ደግሞ የበለጠ አዋጪ ፣ አስተማሪና በጣም ፍቅር ነው “ትላለች።

አዎን ! ስራው ለወጣት ሳምራዊት ፍቅር ነው ። ከላሞቿ ጋር ማውራት ያስደስታታል ። አስራ ሰባቱ ላሞቿ እንደ ሰው ስም አውጥታ ፣ መጠሪያ ሰጥታ ታዋራቸዋለች ። ላሞቹም ድምፅዋን ሲሰሙ በሰውኛ ቋንቋ መልስ መስጠት ባይችሉም ዞር እያሉ ይመለከትዋቷል ። ፍቅር በፍቅር ናቸው ።

“ ሸዊት፣ ምነው ዛሬ አኮረፍሽኝ? ስራ ስለበዛብኝ ነው የዘገየሁት። ቀድሜ ሰላም ስላላልኩሽ ነው አይደል ያኮረፍሽው ?  አይዞሽ መጥቻለሁ ----- “  እያለች ለላሞቿ ያላትን ፍቅር ትገልጣለች።

አልፎ አልፎ ወደ ገጠር እየሄደች ዘመዶችዋን የመጠየቅ ልምድ ቢኖራትም ትውልዷንና እድገቷን ከተማ ውስጥ የሆነችው ወጣት አሁን ላይ ከማንም አርሶ አደር በማያንስ መልኩ በዘመናዊ የወተት ላሞች እንክብካቤ ላይ ተሰማርታ ውጤታማ ሆናለች ።

ሌላዋ ወጣት ሚሚ ገብሩ ደግሞ  በ2002 ዓ.ም በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛ ስራ አጥታ መቆየትዋን ታስረዳለች።

በአረብ አገራት የተሻለ ስራ አለ ስለተባለች ለሁለት አመታት ከሶስት ወር የስደት ኑሮውን ሞክራው ተመልሳለች ። ያተረፈችው ነገር ግን አልነበረም ። ከስደት መልስ በቤተሰብ ድጎማ በ20 ሺህ ብር አንዲት  የወተት ላም ገዝታ ስራ መጀመርዋን ትናገራለች።

በወተት ሃብት ልማት ስራ የሁለት አመት ቆይታዋ 470 ሺህ ብር ካፒታል ማፍራት እንደቻለች የምትናገረው ሚሚ ገብሩ ስራ ካልተናቀና ችግርን ተቋቁሞ የማለፍ ፅናት ካለ በአገር ሰርቶ መለወጥና በአሸናፊነት መወጣት ይቻላል ትላለች።

 “ልምዱም ሆነ እውቀቱ  አልነበረኝም ። ቤተሰቦቼም ቢሆኑ በዚሁ ስራ ያለፉ አይደሉም ። 20 በ80 የሚባል ብድር ስጠይቅ ለግብርና ስራ ነው የሚፈቀደው ሲሉኝ አማራጭ አልነበረኝምና በድፍረት ገባሁበት “ በማለት ታስረዳለች።

 “ 80 ሺህ ብር ተበድሬ ሶስት ላሞች ገዛሁኝ ። ሶስት ጥጃዎችም  ወለዱልኝ ። ትንሽ ሳይቆዩ ግን ሁሉም ሞቱ ። ተስፋ ሳልቆርጥ እቁብ ገብቼ እንደገና ላሞች ገዝቼ ስራውን አስቀጠልኩት” ትላለች ።

ወጣቶች ወደ አረብ አገራት ከመሄድ በአገራቸው ያለው ሰፊና ምቹ የልማት እድል ተጠቅመው ስራ ሳይንቁ ከሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ የራስዋን ተሞክሮ አብነት በማድረግ ታስረዳለች።

በመቐለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሌላዋ የቤት እመቤት ወ/ሮ መድህን ወልዱ በ2008ዓ.ም አንዲት የወተት ላም በመግዛት ስራውን መጀመራቸው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሶስት ላሞችና ሁለት ጥጃዎች ያሉዋቸው ሲሆን በየቀኑ 400 ብር ገቢ እንደሚያስገኙላቸው ተናግረዋል ። አራት ባጃጅ ተሽከርካሪዎች በቀን ከሚያመጡት ገቢ ጋር የሚመጣጠን መሆኑ ነው ።

ስራው በቀላል ወጪ የሚሰራና ብዙ ድካም የማይጠይቅ ነው ያሉት ወ/ሮ መድህን ያላቸውን የቦታ ጥበት ለመቅረፍ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄአቅርበው ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸው ገልፀዋል።

በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የእንስሳትና አሳ ሃብት የቴክኖሎጂ ሽግግር ንኡስ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተስፋማሪያም አሰፋ በክልሉ በዓመት እስከ 800 ሚሊዮን ሊትር  ድረስ የሚገኝበት አቅም ቢኖርም በህብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ግን 559 ሚሊዮን ሊትር ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል ።

ቢሮው በክልሉ ያለው የወተት ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ካለፈው አመት ጀምሮ የተሻሻሉ የወተት ዝሪያዎች ወደ ህብረተሰቡ በማዳረስ የተጠቃሚውን ቁጥር ለማሳደግ

እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ሴቶች ወደዚሁ ስራ ለመግባት ከወተት ላሞች ይልቅ በበግና ፍየል ማድለብ፣ በዶሮና በንብ እርባታ ለመሰማራት ይመርጡ እንደነበር የገለጡት አቶ ተስፋማሪያም ካለፈው ዓመት ወዲህ ግን በወተትና የወተት ተዋፅኦ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ታዲያ!  እኛም ይህንኑ ጅምር ስራ ከዚህ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል የሚለው መልእክታችን በዚሁ ዘርፍ እንደነ ሳምራዊት ዓይነት ብዙ  ስኬታማ ወጣቶች የምናይበት ዘርፍ እንደሚሆን አንጠራጠርም።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን