አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ዲፕሎማሲው - የመጨፈንና የመግለጥ ያክል ለውጥ አለው

06 Aug 2017
2022 times

            እንዳሻው  ሹሜ

በአፍሪካና በኤስያ አገራት ላይ የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጣል ሲወጥኑ እርስ በርሳቸው መነጋገር ነበረባቸው - አውሮፓዊያኑ፤ያኔ ሽኩቻ ሳያጋጥማቸው ተነጋግሮ መቀራመት የተሻለ አማራጭ አድረገው ወስደውታል። ይህ አይነቱ ግንኙነት የዲፕሎማሲ መጀመር መንስኤ እንደሆነ ድርሳናት ይዘክራሉ። በርግጥ እንደ ዓለም የፖለቲካ መዋቅራዊ ሁናቴ ትርጉሙና ተግባሩ ይቀያየራል። የወቅቱ ዲፕሎማሲ የጦርነት ኪሳራ ለመቀነስ ያለመ እንደነበር ምሁራኑ ይናገራሉ። በአመዛኙ ቢሮክራሲያዊ፤ በሂደቱና በይዘቱ ደግሞ ምስጢራዊ ባህሪ ነበረው። የገዥዎችንና የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሃሳብ፣ ፍላጎት፣ ጥቅም፣ ሥምና ዝና ለማስከበር ያገለግል እንደነበርም እንዲሁ።

 ዲፕሎማሲ በበርካታ ምሁራን ዘንድ እንደየወቅቱ ሁኔታ በርካታ ትርጓሜ ቢሰጠውም፤ የአንድን አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና አገራዊ ጥቅም ማስፈፀሚያ መንገድ ወይም መሳሪያ የሚለው ትርጉም  ብዙዎችን የሚያስማማ ይመስላል። እንደ አገራቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ባህሪ የራሱ የሆነ መልክ አለው። በፖለቲካው ዘርፍ የወከላትን አገር ፍላጎት ማሟያ ነው። ይህ ደግሞ በማሳመን፣ በሽልማት ቃል ኪዳኖች፣ በፕሮፖጋንዳ ሲበዛም ኃይል ባዘለ ማስፈራሪያና ሌሎች ዘዴዎች ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ የሚቃኝ ነው። በዚህም ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የማጉላትና የማሳየት ተልዕኮን ያስፈጽማል፤  የቆመለት ፖሊሲ በሌሎች አገራትና ድርጅቶች ዘንድ ህጋዊ ውክልና እንዲያገኝና ጥቅምን መሰረት ያደረገ ትብብር እንዲኖር ቁልፍ መሳሪያም ነው። በሌላ አገላልጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያላት አገር ከይሁንታ ካገኘችባቸው ሌሎች አገራትና አጋር ድርጅቶች ጋር የ'እከክልኝ ልከክልህ' ትብብር የምትመሰርትበት መስተጋብር ነው። ትብብሩ ደግሞ በአገራቱ መካከል የሚያጋጥም ክፍተትና ድክመት መሸፈን፤ መረዳዳትና መጠቃቀምን ማጎልበት ነው። እናም በዲፕሎማሲ ጠንካራ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስርም ይፈጠርበታል።

 ኢትዮጵያና ዲፕሎማሲዋ

 በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀምራለች - ኢትዮጵያ። እርሱም ንጉሱ ከእንግሊዝ ጋር የጀመሩት ግንኙነት ነበር። የኋላ ኋላ “ቢፈጀኝ በማንኪያ ባይፈጀኝ በእጄ” ሆነና ነገሩ ለንጉሡ ህልፈት ምክንያት ቢሆንም ግንኙነቱ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡ አይዘነጋም።

 በአገራዊና ፖለቲካዊ ደህንነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲካሄድ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከነበረበት ጊዜ አኳያ ሲመዘን ግን ደካማ ላይባል ይችላል። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ሳይንሳዊ አልነበሩም። በንጉሱና በቅርብ ባለስልጣናት ብቻ ነበር የሚመራው። በነገስታቱ የተደረጉ ዋና ዋና የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች በርካታ ውጤቶች አምጥተዋል፤ የአውሮፓዊያኑ ስልጣኔ ወደ አገር ቤት መግባት ጀምሯል። ለአብነትም በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት የተጀመሩ የዘመናዊ ትምህርት፣ የጤና፣ የባቡር፣ የቴሌና ሌሎች አገልግሎቶችና ቴክኖሎጂዎች የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው።

 ቀጥሎም በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተደረገው ዲፕሎማሲ አገሪቱ የመንግስታቱ ማህበር/ሊግ ኦፍ ኔሽን/ አባልነት፤ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትንና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምስረታና ሌሎች ውጤቶችን አበርክቷል። በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጋጋል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ነበረች። የፋሺስት ጣሊያንን ወረራ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትም ታላቅ ጥረት አድርጋለች። በተለይ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የአፍሪካ አገራት በካዛብላንካና ሞኖሮቪያ ቡድን ለሁለት በተከፈሉበት ወቅት ልዩነቱ እንዲፈታ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አፍሪካውያን ያስታውሱታል። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሰላም ወዳድና ለአፍሪካውያን ሠላምና ሕብረት የጀርባ አጥንት መሆኗን ጭምርም ያሳየ ነበር።

 የነገስታቱ ዘመን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ብዙ ፍሬ አፍርቷል። የበርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንድትሆን አስችሏታል፤ የበርካታ አገራት የዲፕሎማሲ ማዕከልም ሆናለች። የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ አፍሪካ አንድነት ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአዲስ አበባ መከፈትም ተጠቃሽ ናቸው። እናም የነገስታቱ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አገሪቷ አሁን ላላት አለም አቀፋዊ ተሳትፎና ተሰሚነት እርሾ ሆኗል።

 የአገሪቱ ሥምና መልካም ገፅታ ግን በነገስታቱና በነበራቸው ወታደራዊ ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ ነበር፤ በወቅቱ የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአገሪቱ ሥምና ዝና ባለፈ ውስጣዊ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮችን ያስረሳ እንደነበር ይነገራል። ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ በውስጥ የነበረውን የሠላም እጦት እሳት ማጥፋት አልነበረም፤ ጭሱ ከውጭ እንዳይታይ መሸፈን እንጂ። አገር ውስጥ የነበርው ችግርና የረሃብ ድምፅ ወደ ውጭ እንዳይሰማ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር። በንጉሱም ሆነ በደርግ ስርዓተ መንግሥታት የነበሩት የተለያዩ አመፆች፣ ረሃብ፣ ውስጣዊ ሠላም ማጣትና ከርዕዮተ ዓለም መውደቅ ጋር ተያይዞ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥለው እንደነበር ማስታወስ ለውጤቱ ማሳያ ነው። በሠላም ፈላጊነቱና በአስታራቂነቱ የተከበረ ሥም ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የረሃብ ተምሳሌት ሆኖም ነበር።

 ከውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢያዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጫናም ነገሩን "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" አድርጎት ቆይቷል። ቀጣናው ከኃያላኑ አሜሪካና ሩሲያ የርዕዮተ ዓለም የሽኩቻ ሜዳ ሆኖ ነበር። በዚህም ለቀጣናው አገራት ውስጣዊ ፖለቲካና የእርስ በርስ ጦርነት እስከ አክራሪነትና አሸባሪነት ሰለባ ሆነዋል። በቀጣናው በተደጋጋሚ የተከሰተው ድርቅና ወረርሽኝም ለኢትዮጵያ መትረፉ አልቀረም።

 የቀጣናው  ወላፈንና የኢትዮጵያ ጉዞ

 በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በአለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው- ዶክተር ቦኒፌስ ከትበርት። የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ዕድገት ሲያነጻጽሩ "ኢትዮጵያ በቀጣናው የተከተለችው ስልትና የመጡት ውስጣዊና  አለም አቀፋዊ ውጤቶች ከ1990ዎቹ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የመጨፈንና የመግለጥ ያክል ልዩነት አለው” ይላሉ። ባለፉት መንግስታት ከአጎራባች አገራት ጋር የጥርጣሬና የጠላትነት ስሜት የሰፈነበት ግንኙነት እንደነበራት ያወሳሉ። ዛሬ ላይ ግን ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም አገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት መመስረቷን ያትታሉ። የሠላም ነፋስ በማይነፍስበት፤ በድርቅና እረፍት በሌለው ፖለቲካዊ ሽኩቻ  በሚንጠው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንደ ደሴት ከርቀት ጎልታ የመታየቷ ምስጢር የፍላጎት ቅደም ተከተልን የመለየት ጉዳይና የመፈፀም ጥንካሬ መሆኑን ያነሳሉ።

 በሌላ በኩል ውጫዊና ውስጣዊ ክፍተቶችና ጠንካራ ጎኖች ለማጣጣም የሚያስችሉ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አልነበሩም።ዶክተር ከትበርት ኢትዮጵያ የነበሩባትን ውስጣዊና ውጫዊ ክፍተቶች በፖሊሲና ስትራቴጂዎቿ ለይታ ማውጣቷን ያነሳሉ፤ በዚህም አለም አቀፉን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር ሚዛናዊ አድርጋ ማስቀጠል መቻሏንም እንዲሁ። በጥቅሉ ዴፕሎማሲያዊ ግስጋሴዋን ሲገልጹት “የመጨፈንና የመግለጥ ያክል ልዩነት አለው” ነው ያሉት።

 ለአገሪቱ ወቅታዊ  ለውጦች የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂው የሚይዛቸውና የሚከተላቸው ስልቶች ለአገሪቱ ህልውና ቁልፍ ለሆኑት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ቀጣይነት ላለው ሠላምና ዴሞክራሲ መረጋገጥ ቅድሚያ መስጠቷና ወደ ተግባር መግባቷ መሰረት እንደሆኗትም ይናገራሉ። “የአገሪቱን የልማትና ዴሞክራሲ ራዕይ እውን የሚያደርጉ የአገር ውስጥ ሁኔታዎች ላይ ርብርብ ሳይደረግ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲ አቅጣጫ በውጭ በሚካሄድ እንቅስቃሴ ላይ ከሆነ ትርጉም ያለው ፋይዳ አይኖረውም” የሚለውን የፖሊሲ ድንጋጌም በማሳያነት ይጠቅሳሉ። በውጭ የሚደረጉት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ውስጣዊ አጀንዳዎችን ስለመፈጸማቸው በአገር ውስጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል አጋርነትንና ትብብርን የመፍጠር፣ ድጋፍን የማስገኘት፣ ለአገር ውስጥ እንቅስቃሴ ምቹ የሆነ ውስጣዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረት ነው።

 ኢትዮጵያ በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በአገር ውስጥ ፈጣን ኢኮኖሚንና አንፃራዊ ሰላምን ከማስፈን ባለፈ በፖለቲካ ትኩሳት ለሚታመሱ አጎራባች አገራት ሰላም ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጋለች። ፖሊሲው ከአጎራባች አገራት የነበረውን የጠላትነትና የጥርጣሬ ግንኙነት እንዲጠፋ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በቀጣናው ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ ትልቅ ሚና እንድትጫወትም እንዳስቻላት ይገልጻሉ።

 በቀጣናው ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሌላው ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ ጉዳይ ነው። "በዘርፉ የረዥም ጊዜ ልምድ ያለው የሰላም አስከባሪ ኃይል መገንባቷና በተልዕኮው ላይ ያላት ቁርጠኝነት፣ ብሎም የአጎራባች አገራቱን የህዝብ አኗኗር ዘይቤ፣ ባህልና የፖለቲካ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ማወቋ በሠላም ማስከበሩ ላይ የጀርባ አጥንት እንድትሆን አድርጓታል” ነበር ያሉት። በተለይም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን እርስ በርስ ጦርነት እልባት እንዲያገኝ በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ጦር/አሚሶ/ ግንባር ቀደም ነበረች። በመንግስታቱ ፀጥታ አስከባሪ ተልዕኮ ተሳትፎም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና መጫወቷን ያብራራሉ።

 በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በሠላምና ፀጥታው ዘርፍ አበርክቶቷም አለም አቀፍ ተሰሚነቷን አሳድጋለች። በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆናም ለሶስተኛ ጊዜ ተመርጣለች። ተለዋጭ አባል ከሆነች በኋላም በአፍሪካ ከፍተኛ ለውጥ እንደምታመጣ ተስፋ የተጣለባት አገር መሆኗን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ ተስተውሏል።

 ፍሬያማው ዲፕሎማሲና ቀጣይነቱ

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስክ ከነበሩባት ችግሮች ለመውጣት ትክክለኛውን መንገድ እየተከተለች እንደሆነ ብዙዎቹ ይመሰክራሉ። ለዚህ ደግሞ የውጭ ጉዳይና የአገር ውስጥ ፖሊሲዋ ተመጋጋቢ መሆናቸውን እንዲሁም አተገባብሩ በህዝብ ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነት ላይ መመስረቱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። 'ቀጣይነቱስ?' የሚለውን ጉዳይ መፈተሽ ግን ግድ ይላል።

 የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው "የህልውናና የአገራዊ ጥቅምን የማረጋገጥ ጉዳይ የሙያተኛው ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ በመሆኑ በምልዓተ ህዝቡ ላይ አንድ የጋራ አገራዊና ብሔራዊ አመለካከት መፍጠር ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ይህ አመለካከትና እምነት ያለው ግን ፖሊሲውና ስትራቴጂው የሚጠይቀውን ጥናትና ምርምር ሊያካሂድ  የሚችል፣ ፖሊሲውና ስትራቴጂውን ለመፈፀም የሚያስችል እቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ጥልቀት ያለው ሙያ፣ እውቀትና ክህሎት ያካበተ የሰው ኃይል አስፈላጊ ነው" በሚል ያትታል።

 ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ቦኒፌስ ካርበርት "ኢትዮጵያ አሁን ያላትን አለም አቀፍ ተሰሚነት ለማስቀጠል በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ ያደረገችውን ስር ነቀል ለውጥ በተለይም አገራዊ ጥቅምንና አለም አቀፋዊ ጥቅምን አጣጥሞ ከማስቀጠል፣ የሌሎችን አገራት ሉአላዊነትና የድንበር ትስስር ከማክበርና ከማስከበር፣ በአለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የራስን አሻራ ከማስቀመጥና ከሌሎች አገራትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ በማጠናከር ረገድ ያላትን ሚና ማስቀጠል ይኖርባታል" ይላሉ። በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሁነቶችን ከአለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን አጣጥመው መራመድ የሚችሉ ፕሮፌሽናል ዲፕሎማቶች ያስፈልጓቷል። የዓለም ተለዋዋጭ ሁናቴን ዝምድና መረዳት፣ መተንተንና የክስተቶችን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ መተንበይ የሚችሉ ዲፕሎማቶች ያሻታል።

 በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃነታቸው ማግስት ጀምረው ለውጭ ግንኙነታቸው ትኩረት ሰጥተዋል። ለምሳሌ፡- ግብፅና ኬንያ ከ40 እና ከ37 ዙር በላይ የዲፕሎማት ሙያተኞችን አስመርቀዋል፤ ራሱን የቻለና የተደራጀ የውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ተቋም በማቋቋም። ከነዚህና መሰል ሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ስትወዳደር ኢትዮጵያ በጅምር ላይ መሆኗን ያሳያል። በዚህ ረገድ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ታሪክ ያስቆጠረው ዲፕሎማሲ የውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ተቋም አልነበራትም። ቅርብ ጊዜ ድረስ የውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ተቋም ከመቋቋሙ በስተቀር፤ እንዲህ አይነት ተቋም ሳይኖራት መቆየቱ  ዲፕሎማሲዋ ሳይንሳዊ ባልሆነ መንገድ ሲመራ በመቆየቱ ከዲፕሎማሲው እድሜ አኳያ ወኋላ እንዳስቀራት ይተነትናሉ።

 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት ማሰልጠኛ ተቋም በ2005 ዓ.ም.  ነው በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ስር በአዋጅ የተቋቋመው። የተቋሙ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ እንደሚሉት፤ ተቋሙ እስካሁን ሶስተኛ ዙር ሰልጣኞችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል። ተቋሙ በዩኒቨርስቲው ስር መሆኑ በራሱ አቅዶ ለመንቀሳቀስ እንዳላስቻለው ነው የተገለጸው። ይህ ደግሞ እንደማንኛውም ተቋም አቅዶ ለመንቀሳቀስና መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራትና እራሱን የበለጠ ለማደራጀት ችግር እንደሆነ ዶክተር ማርቆስ ይገልጻሉ።

 ስለአጠቃላይ የአገሪቱ ዲፕሎማሲ ሲናገሩም "ዲፕሎማሲያችን በግለሰቦች የራስ ጥረት ላይ የተንጠለጠለ ነው። በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል፣ አሁንም ቢሆን በአምስት አመት ውስጥ ብዙ አልሄድንም፣  በተፈለገው ፍጥነት እየሄድን አይደለም፣ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ተቋም ለመመስረት አሁንም ረዥም መንገድ ይጠብቀናል" ይላሉ።

 በእርሳቸው ገለጻ ማሰልጠኛ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት የራሱን ህጋዊ እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ነው። ተቋሙ እውቅናውን ካገኘ በኋላ አዳዲስ ወጣት ዲፕሎማቶችን ለማፍራት ያስችላል፤ በራሳቸው ጥረት የዲፕሎማሲ አቅማቸውን በማሳደግ በርካታ ስራን እየሰሩ ያሉ ነባር ዲፕሎማቶችም እንዲሰለጥኑ ያደርጋል። በጥቅሉ ተቋሙ በሙያተኞች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት እቅድ ይዟል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን