አደገኛ ዕፅ የማዘዋወር ወንጀልና የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ

                                ሚስባህ አወል /ኢዜአ/

ፈጣሪ አዳምና ሄዋንን ፈጥሮ በኤደን ገነት አስቀመጣቸው ፤ በዚህ ገነት ውስጥ በደስታና በፌሽታ እንዲኖሩም ፈቀደ ፤ የፈለጉትን በፈለጉት ጊዜ እንዲጠቀሙም አደረገ ፤ ይሁንና ፈጣሪ አንድ ተክልን እንዳይጠቀሙ ከለከለ፡፡

ያቺ ተክል ታድያ ዕፀ በለስ ትባላለች፡፡

የሰው ልጅም  በደነገገው ህጉ ይህን ፍሬ አትብሉ(አትውሰዱ) ይህን ካደረጋችሁ ከራሳችሁ አልፋችሁ ሌላውንም ትጎዳላችሁና ለዚህም የተከለከለ ነገር አለ ይለናል፡፡

እሱንም አደንዛዥ ዕፅ ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡ የዛሬው ጉዳያችንም ይህንን መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡

የኢፌዲሪ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ በዚሁ በዛሬው ርዕሴ ላይ ያለውን አንቀጽ ላስቀድም!!

የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ስለአደንዛዥ ዕፅ ሲያትት ዕፁን ይዞ መገኘት ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ወይም ማምረት በህግ እንደሚያስጠይቅና በእነዚህ ተግባራት የሚሳተፍም ሆነ የሚተባበር በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቀጫ ህግ አንቀፅ ቁጥር 525 /1 መሰረት ያደረገ ቅጣት እንደሚጥል ይደነግጋል፡፡

በአንቀጽ 525 ያለህጋዊ ፈቃድ ወይም ግልፅ የሐኪም ትዕዛዝ ሳይኖረው ናርኮቲክ ወይም ሳይኮትራፒክ መርዛማ ፤ ጤናን የሚጎዳ ወይም ለጤንነት አደገኛ የሆኑ ዕፆችን ፤ ንጥረ ነገሮችን ፤ መድሃኒቶችን ወይም ምርቶችን ያበቀለ ፤ ያመረተ ፤ ያዘጋጀ ፤ የሸጠ ፤ ለሽያጭ ያቀረበ ፤ ያስረከበ ወይም የሸጠ ከ10 ዓመት ባልበለጠ የእስራት እና በ200 ሺህ ብር መቀጮ ይቀጣል ይላል፡፡

እዚህ ጋር የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ዕጽን ሲገልጸው የሚጠቀምባቸው ቃላት ራሳቸው በቁማቸው ብዙ ይናገራሉ ፤ ገላጭም ናቸው፡፡

ቃላቱ ምን ይሉ መሰላችሁ፡፡  “መርዛም” እና “የሚያፈዝ” በማለት ነው የሚገልጸው፡፡

ወደ ዛሬው ጉዳዬ ላምራችሁ?

ጉዳያችን ሰሞኑን በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታና አራዳ ምድብ ችሎቶች የተወሰኑ የቅጣት ውሳኔዎችን ለማሳየት ነው፡፡

የመጀመሪያው የምንመለከተው የቅጣት ውሳኔ መዝገብ በዚሁ በዕፅ ዙሪያ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የተላለፈውን ይሆናል፡፡ እነሆ!!

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛው ወንጀል ችሎት ነው የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው፡፡

የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ቸከውዲ ክርስቲያን ፣ አሎስዩስ አይንቼ እና አሰማይስ አይናይ በተባሉት ሶስት የናይጄሪያ ዜጎች ላይ ነው፡፡

የፌደራሉ ዓቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ መዝገብ እንደተገለጸው ከሆነ ሁለቱ ናይጄሪያዊያን ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ሲሆን ከብራዚል ሳኦፖሎ ወደ ናይጀሪያ አንጎ ሌጎስ ከተሞች በሚደርገው ጉዞ በትራንዚት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፍተሻ ሲደረግላቸው በሆዳቸውና በቦርሳቸው ውስጥ በአጠቃላይ 3ሺህ 860 ግራም ኮኬይን ይዘው በማዘዋወር ላይ በመገኘታቸው ነው፡፡

ሶስተኛዋ ናይጄሪያዊም ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ሲሆን ከብራዚል ሳኦፖሎ ተነሰቶ ወደ ኪሊማንጀሮ በምታደርገው ጉዞ በትራንዚት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፍተሻ ሲደረግላት በያዘቻቸው አምስት ቦርሳዎች ውስጥ 9 ሺህ 200 ግራም የካናቢስ ዕጽ የተገኘባት በመሆኑ ለቅጣት መብቃቷን ያትታል፡፡

በመሆኑም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰኔ 13 ቀን 2009 በዋለው ችሎት ቸከውዲ ክርስቲያንን በዘጠኝ ዓመት ፅኑ እስራት  አሎስዩስ አይንቼን ደግሞ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ አስራትና በ15 ሺህ ብር እንዲሁም አሰማይስ አይናይን በዘጠኝ ዓመት ከሁለት ወር ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ሁለተኛውንም መዝገብ ያየው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

አብረሃም ሸዋ ይባላል፡፡ ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት በግምት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 መምህራን ሰፈር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚጓዝበት ወቅት ባሳየው የተለየ ሁኔታ በአካባቢው ባሉ የፖሊስ አባላት አይን ውስጥ ይገባል፡፡

ወንጀልንና ወንጀል ነክ ጉዳዮችን የሚያነፈንፉት የፖሊስ አባላትም የአብረሀም ሁኔታ አንዳች የጥርጣሬ ስሜት ይፈጥርባቸዋል፤አላመነቱም ለደቂቃዎች በማስቆም ይፈትሹታል፤ በዚህ አጋጣሚ ነው ድርጊቱ የተያዘው፡፡

በግለሰቡ ኪስ ውስጥ ጠቅላላ ክብደቱ 277 ግራም የሆነ የካናቢስ ዕፅ ያገኛሉ፡፡

ፖሊስ ይህን አደንዛዥ ዕፅ ለማጣራትም ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የፎረንሲክ ምርመራ እንዲደረግ ይልካል፡፡

የምርመራው ውጤቱም የካናቢስ ዕፅ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ሂደቱን ያጠናቅርና ለፌደራሉ ዓቃቤ ህግ እነሆ ይለዋል፡፡

የፌደራሉ ዓቃቤ ህግም የምርመራ መዝገቡን ከበቂ ማስረጃ ጋር ለፌደራሉ  ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት በማቅረብ የክርክር ሂደቱን ይቀጥላል፡፡

ስምንተኛው ወንጀል ችሎትም የግራ ቀኙን ያዳምጥና በሚያዝያ 13 ቀን የቅጣት ውሳኔውን ይሰጣል፡፡

በቅጣት ውሳኔው ላይ አቃቤ ህግ ድርጊቱ ምን ያህል የከፋ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል በማብራራት ቅጣቱ  እንዲከብድ ይጠይቃል፡፡ ተከሳሹም የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ገና  ወጣትና መልካም ስነምግባር ያለውና ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ያልፈፀመ መሆኑን በማስረዳት ቅጣቱ እንዲቀልለት ይማጸናል፡፡

በመጨረሻም ችሎቱ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 1/ሀ/525 በመጥቀስ በሀገሪቷ ህግ እንዳይመረት እንዳይዘዋወር እንዳይጠቀም የተከለከለ መሆኑን በማብራራት በአንድ አመት ፅኑ እስራትና በ300 ብር እንዲቀጣ በመወሰን ፋይሉን ዘግቷል፡፡

ሶስተኛው መዝገብ በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛው ወንጀል ችሎት በቅርቡ የወሰነው የቅጣት ውሳኔ ነው፡፡

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ተከሳሹ መሀመድ ኢሳማ ይባላል ነዋሪነቱ ዱባይ ነው፡፡

ሚያዝያ 7 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ከምሽቱ በ2፡00 ሰዓት አካባቢ በቦሌ ኢንተርናሽናል የአውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ በሚያደርገው የጉዞ ሂደት ላይ በፍተሻ ላይ እያለ ባደረገው የውስጥ ሱሪ/ፓንት ውስጥ ደብቆ የያዘው 135 ግራም የካናቢስ ዕጽ በጉምሩክ ፈታሾች እጅ እንዲወድቅ ምክንያት ይሆናል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛው ወንጀል ችሎትም የዓቃቤ ህግን ማስረጃዎች በመመርመርና የቅጣት ማቅለያዎችን በማካተት ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት በአራት ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ይሁንና ዕፅ መርዝ ብቻ አይደለም መድሃኒት መስሪያም ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው በህጉ መጽሀፍ ወንጀለኛ መቅጫው ላይ “ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው” የምትለዋን ሀረግ የምናገኛት፡፡

ከላይ ያየናቸው ፋይሎች በዝውውር ላይ ያሉ ይሁኑ እንጂ ከታች የተጠቀሱት በሀገር ውስጥ ተመርተው በራሳችን ዜጎች ተይዘው መገኘታቸው ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዕፅ በግለሰብ በቤተሰብ እና በመላው ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ነውና ይህን በየአካባቢው በስፋት እየተለመደ የመጣን ተግባር ለማስቆም ግን በጋራ መንቀሳቀስና መከላከል ግድ ይላል፡፡

Last modified on Friday, 08 December 2017 21:12
Rate this item
(6 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን