ድህነትን ያነገሱ የድህነት ባለፀጎች

19 Jun 2017
3453 times

ገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)

ዝናቡን ለማሳለፍ  ሁሉም መንገደኛ ወደቀረበው መጠለያ መሯሯጥ ይዟል። እኔም ስታዲየም አካባቢ ባለች አነስተኛ ካፌ ውስጥ ጥግ ይዤ ተቀምጫለሁ፤ ቀጠሮ የሰጠኝን ጓደኛዬን ለመጠበቅና የሚጥለውን  ዝናብ ለማሳለፍ መሆኑ ነው

ተሳክቶልኝ 15 ደቂቃ ያህል ብቀድመውም በቀጠሮ አከባበርና ንባብ ላይ ቀልድ የማያውቀው ጓደኛዬ በሰአቱ ካፌዋ ውስጥ ተገኘ።

በወርሃ ሃምሌ አብዛኞቹ የሃገራችን ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ለአመታት ያስተማሯቸውን ተማሪዎች ያስመርቃሉ። በመሆኑም ወቅቱ ለተመራቂ የሚበረከቱ ስጦታዎች ከወትሮ ዋጋቸው  ወደድ ማለቱ  የተለመደ ነው።

እኛም ከወር በፊት በተመራቂ ጓደኛችን በተደረገልን ጥሪ መሰረት ወደ ተመራቂው ቤት ከመሄዳችን በፊት ስለምንሰጠው የማስታወሻ ስጦታ መነጋገራችን አልቀረም። ስጦታው መሆን ካለበት ኪሳችንን የማይጎዳ ግን የማይረሳ መሆን እንዳለበት ስንነጋገር አጠገባችን ቆሞ ያላስተዋልነው መጽሃፍ አዟሪ ለስጦታ የሚሆኑ መጽሃፎችን እንደያዘ ቀልጠፍ ብሎ ነገረን።

የግርሃም ሃንኩክ Lords of Poverty /የድህነት ጌቶች/ የጓደኛዬን ቀልብ ሳበው፤ ስለምርጫው ያስቀመጠው ምክንያት ደግሞ ተመራቂው ጓደኛችን ከሌሎቻችን ባነሰ የመመረቂያ ነጥብ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንደያዘ ምንም የስራ ልምድ ሳይኖረው ስድስትና ሰባት አመታት የስራ ልምድና ማስትሬት ዲግሪን የሚጠይቅስራ መደብ ላይ ከሚያምር ቢሮና ከምርጥ መኪና ጋር ሊቀመጥ የቻለበት ጉዳይ ሁላችንንም ሲከነክነን እንደነበር በማስታወስ ነው።

“ይሄን መጽሃፍ ካነበብኩት አመት ያህል ሆኖኛል። እናም የትምህርት ማስረጃውን በ ‘C’ ሞልቶ የተመረቀው ጓደኛችን በብርሃን ፍጥነት እዚህ ላይ እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ጥሩ ማሳያ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ነው።

ጓደኛችን አክስቱ አሜሪካ እንደምትኖርና የሆነ ትልቅ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳላት ደጋግሞ ሲነግረን እንደነበር ታስታወሳለህ መቼም

ያኔ የምርቃታችን ሰሞን ሴትየዋ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችበት ወቅት ነበር። አሁን ያለበት ድርጅት ውስጥ ካለው ሃላፊ ጋር ተጨባብጠው ተሳሳቁ ጓደኛችን ፈተናውን አለፈ ተባለና ስራ መያዙን ሰማን

በመሆኑም መጽሃፉን ብንሰጠውና ቢያነበው አንደኛ ራሱን ይመዝንበታል፤ ሁለተኛ ከሃገራችን አልፎ አህጉራችን አፍሪካንና የተቀረውን አለም ያይበታል ብዬ ስላሰብኩ ነውአለኝ

*****

ስኮትላንዳዊውን ጋዜጠኛ ግርሃም ሀንኩክን ኢትዮጰያውያን አንባቢዎች የሚያውቁት the Sign and the Sealታቦተ ጺዮንን ፍለጋ’ በሚል ባሳተመው መጽሃፍ ሲሆን Ethiopia: The Challenge of Hunger የሚል ሌላ መጽሃፍም አለው

ድህነትን ለመግለጽና ለማስረዳት ታላላቅ የአለማችን የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንዲሁም ድርጅቶች የራሳቸውን ትንታኔዎች የሰጡ ቢሆንም አሁንም ድህነትን ይሄ ነው የሚል አስማሚ ብያኔ ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ይነገራል

ሆኖም በግርድፉ ድህነት ሲነሳ ደግሞ ሃብታምና ድሃ፣ ሰጭና ተቀባይ፣ የበላይና የበታች መኖራቸው አይቀሬ ነው

አፍሪካ፣ የላቲንና የኤሺያ ሃገራት ስማቸው ከድህነት ጋር ተደጋግሞ ሲጠራ መስማት የተለመደ መሆኑን ሁላችንም የምናውቅ ሲሆን፤ በእነዚህ አህጉራት ያሉ ድሃ ህዝቦችን ለማገዝ በሚል ብዙ ነገሮች ይሰራሉ

በተጠቀሱት ሃገራትና አህጉራት ለሚገኙ ተረጂዎች ድጋፍ ማሰባሰቢያ በሚልም ታላላቅ የሙዚቃ ዝግጅቶች በአውሮፓና በአሜሪካ ከተሞች መዘጋጀት ከጀመሩ አመታትን አስቆጥረዋል

ለጋሽና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከለጋሾች በተሰበሰበው ገንዘብ  አከናወን የሚሏቸውን ልዩ ልዩ ስራዎች ሲያስመርቁና ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ  ማየትም ብዙም  አዲስ ነገር  አይደለም

ያለመታደል ሆኖ አህጉራችን አፍሪካም ሆነች ሃገራችን ኢትዮጵያ በታሪካቸው የበዙ አሳፋሪና አሰቃቂ የእርስ በእርስ እልቂቶችን፣ ድርቅና የረሃብ አደጋዎችን ደጋግመው ማስተናገዳቸውን ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ነው

እነዚህ ክስተቶች እንዳይኖሩ ወይም ጉዳታቸው ይቀንስ ዘንድም አፍሪካውያን የተማጽኖ  እጃቸውን ወደ ምእራባውያን መዘርጋታቸውን አሁንም አላቆሙም

ለትርፍ ያልተቋቋሙ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በመላው አለምና በአፍሪካ ቁጥራቸውም ሆነ ተግባራቸው እያደገ ስለመምጣቱ ዘገባውን ያስቀመጠው ኒውስ 24 እንደሚያመለክተው ከሆነ በደቡብ አፍሪካ 100 በላይ የተመዘገቡ ድርጅቶች ሲኖሩ፤ በኬንያ ደግሞ  1997-2006 ባሉት አስር አመታት 400 በመቶ ማደጋቸውን አስነብቧል

1980ዎቹ ከፍተኛ እዳ ውስጥ የተዘፈቁ የአፍሪካ ሃገራት ወጪያቸውን እንዲቀንሱና መንግስታቱ የማይሸፍኗቸውን ጉዳዮች መንግስታዊ ያልሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ለማስቻል የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ድርጅት ባስቀመጡት አስገዳጅ መመሪያ መሰረት ወደ አህጉሪቱ እንደገቡ ያሰፈረው ዘገባው ድርጅቶቹ ለደሃው ማህበረሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶች መሟላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አመልክቷል

የአስተዳደር ጣልቃ ገብነት

ለጋሽ ድርጅቶች የህብረተሰቡን ወቅታዊ ችግር በመቅረፍ ረገድ ድርሻቸው ትልቅ መሆኑ አከራካሪ  አይደለም። አስቸኳይ የምግብና የህክምና እርዳታ ለማድረግ የሚለገሱ ስጦታዎች ሰብኣዊ ከመሆናቸው አኳያ ችግር እንደሌለባቸው የሚናገሩት ባለሙያዎች የህብረተሰቡን የወደፊት ህይወት ታሳቢ በማድረግ የተረጂ ሃገራቱ መንግስታት በሚያወጧቸው የልማት እቅዶች መሰረት የሚለገሱ ስጦታዎች ትርጉም ያለው ለውጥ ስለማምጣታቸው በየሃገራቱ  የተሰሩ  ታላላቅ የጤናና የትምህርት ተቋማት ምስክር መሆናቸውን ይጠቅሳሉ

ዛምቢያዊት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዳምቢሳ ማዮ ዴድ ኤይድ /Dead Aid/ የተባለ በእርዳታ ድርጅቶች አጠቃላይ አደረጃጀትና አሰራር ዙሪያ ትኩረት ያደረገ መጽሃፍን ለንባብ አብቅታለች

የለጋሽ ድርጅቶቹ ተጠያቂነት የጎደለውና ገደብ ያልተበጀለት የገንዘበ አጠቃቀም አፍሪካውያን ተረጂዎች ላይ ስለሚያሳድረው ተፅእኖ ባለሙያዋ በመጽሃፉ እንደመከራከሪያ የምታቀርበው ሃሳብ ሲሆን፤ ድርጅቶቹ ለታላላቅ ስራ አስኪያጆቻቸውና ባለሙያዎቻቸው የሚከፍሉት ረብጣ ገንዘብ  የአፍሪካ ሃገራትን የእርዳታ ድርጅቶች መፈንጫ ከማድረጉም በላይ የአፍሪካ የፖለቲካና የህዝብ አስተዳደር ስርአት ለቀውስ እንዲዳረግ አድርጓል ባይ ነች

እንደ ጸሃፊዋ ገለጻ ከሆነ ለጋሽ ድርጅቶቹ በአፍሪካውያን ስም ከምእራባውያን ለምነው የሚያመጡትን ዶላር አስደንጋጭ ደሞዝ ስለሚከፍሉ በመንግስት ቢሮዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራውን የተማረ አፍሪካዊ ቢሮክራት ተስፋ እንዲቆርጥ በማድረግ ወደ ውጭ እንዲያማትር፣ ያሳደገውን ማህበረሰብ ለማገልገል መማለጃ እንዲቀበልና ተገቢ ያለሆነን ብልጽግና እንዲያስብ እያስገደዱት ነው ትላለች

የሃገራቱ ተሞክሮ

ባለፉት ወራት በግብጽ ያለፈቃድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና ራሳቸውን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ብለው የሚጠሩ ድርጅቶች እንዲስተካከሉ አልያም ግብጽን ለቀው እንዲወጡ የሚያስችል አሰራር ስለመዘርጋቱ የግብጽ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ያተተውአልጀዜራ ቴሌቪዥን ድርጅቶቹ 2011 የተጀመረውን የአረቡ አለም አብዮት እንዲባባስ ከማድረጋቸውም ባሻገር የትኛውም መንግስታዊ መዋቅር አቅም እንዳይኖረው ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን አትቷል

በሆስኒ ሙባረክ አስተዳደር የግብጽ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከፍተኛ አማካሪ / አብዱላህ አል አሻል እንደተናገሩት፤ ጥቂት የማይባሉ የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች ከምእራባውያን ሃገራት ቀጥተኛ ትእዛዝና ድጋፍ ያገኛሉ፣ አጀንዳ ይቀርጻሉ፣ አስፈጻሚዎቻቸውን መልምለው ስምሪት ይሰጣሉ ብለዋል

ለአላማቸው ማስፈጸሚያ የሚሆናቸውን ገንዘብ ያለ ችግር ስለሚያገኙ የሚፈልጉትን ጉዳይ ለማንሳትና ሰልፍ ለመጥራት ችግር የለባቸውም የሚሉት ዶክተሩ የመጨረሻ ግባቸው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት መሥራት እንዳይችል የህዝብ ቁጣን በመቀስቀስ ማወክ፤ ከፍ ሲልም እንዲወርድ ለማድረግ ሰፊ ትንታኔና  የሚድያ ሸፋኑን ማመቻቸት ነው ብለዋል

በሌላ በኩል የምርጫና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲጠብና ቭላዲሚር ፑቲን የፈለጉትን እንዲያደርጉ ምቹ መንገድ መፍጠራቸውን በማንሳት ውትወታውን የሚያቀርበው ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው ድርጅት ኦፕን ሩስያ የተባለው ተሟጋች ድርጅት እንዲዘጋ መወሰኑ የሩስያ መንግስት ለአለም የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ምን ያህል እንቅፋት እየሆነ መሆኑን ለማሳየት ሞክሯል

ጉዳዩን አስመልክቶ ምላሻቸን የሰጡት ፑቲን የሩሲያ ጉዳይ መወሰን ያለበት በሩሲያውያን በመሆኑ ለሩሲያ ህመም መፍትሄ የሚሆነው ሩሲያውያን የሚያመጧቸው መድሃኒቶች እንጂ በምራባውያን ባለመሆኑ እነሱ በሚልኳቸው አካላት ሩሲያ እንድትረበሽ እንዳማይፈቅዱ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል

ቻይና ከወትሮው በበለጠ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥሯን አጥብቃለች የሚለው የአሜሪካው ሲኤንኤን ዘገባሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ስራቸውን እንዳይሰሩ ህጉ አላንቀሳቅስ ስለማለቱ አስነብቧል። ጉዳዩ  ቻይና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ስላለት ግዴለሽነት አመላካች ሲልም ማብራሪያውን ሰጥቷል

ቻይና በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በአካባቢ ጥበቃና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን አሁንም እንደምትፈልግ የተናገሩት የቻይና ሠራተኞች ቡለቲን ሊቀመንበ ሃን ዶንግፋንግ አዲስ የወጣው ህግ ቻይና ልዩ ልዩ  ህግጋትና ደንቦችን አክብረው ለሚሰሩት ይህን ያህል ከባድ እንደማይሆንባቸው አስረድተዋል

ኢትዮጵያ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኦሞ ወንዝን ተከተሎ እየተገበረችው ባለው የመስኖ ልማትና የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ሳቢያ ሂውማን ራይትስ ዎችና ራሱን የወንዞችና የአካባቢ ተሟጋች ያደረገው ኢንተርናሽናል ሪቨርስ የተባለው ድርጅት ሰፊ ዘመቻ ከፍተው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን፤ የዘመቻው ማጠንጠኛም ወንዙ የአጎራባች ኬንያን የቱርካና ሃይቅ መጠን በመቀነስ ሃይቁን ጨዋማ ያደረገዋል የሚል ነበር። በአካባቢው ያሉ የሃመር፣ የበና እና የሙርሲ ብሄረሰቦችን የቀደመ የአኗኗር ዘይቤም እንዲረበሽ ያደረገዋል ሲሉ እንደነበር አይዘነጋም

የኢትዮጵያ ምርጫና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ሲነሳ የ1997 ምርጫ ወርቃማው ጊዜ መሆኑን የሚጠቅሱት የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች ሂደቱ እስከ ድምጽ መስጫው እለት ድረስ ነጻና ሰላማዊ የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ የምርጫ ውጤት ለህዝብ ሲገለጽ ሃገሪቱ ወደ አልፈለገችው አቅጣጫ እንድትሄድ የሚያደርጉ ሁነቶች የተፈጠሩት ራሳቸውን የመብት ተሟጋች ባደረጉ ቡድኖችና ድርጅቶች ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነት ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

ህጉ ለምን አስፈለገ?

የኢትዮጰያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት አንቀጽ 31 “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም አላማ በማህበር የመደራጀት መብት አለው፤ ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ  በመጣስ  ወይም ህገመንግስታዊ ስርአቱን  በህገ ወጥ መንገድ  ለማፍረስ  የተመሰረቱ  ወይም የተጠቀሱትን  ተግባራት  የሚያራምዱ  ድርጅቶች  የተከለከሉ ይሆናሉ”   ይላል።

በመሆኑም የአዋጅ ቁጥር 621/2001 ተብሎ የተሰየመው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማህበራትን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የወጣው ህግም ከሌሎቹ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነጻነት ስለመስጠቱ ማስረጃዎችን በማስቀመጥ የሚከራከሩ አካላት ቢኖሩም፤ ህጉ አፋኝና ምንም አይነት ነጻነት የማይሰጥ፤ የድርጅቶቹንና የማህበራቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ስለመሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን በሚሉ አካላት ተደጋግሞ ሲገለጽ ይሰማል።

አዋጁን የሚነቅፉት አካላት እንደሚሉት ከገንዘብ ምንጭና የአስተዳደር ጉዳዮች አንጻር ያሉት ጉዳዮች ስራ ለመስራት አስቸጋሪ እንደሆኑባቸውና መንቀሳቀሻ ገንዘብ ከሃገር ውስጥ ለማሰባሰብ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ለድርጅቶች ድጋፍ የማድረግ ባህላቸው እንደ ምእራባወያኑ ስላልሆነ በገንዘብ እጥረት እየተቸገሩ ስለመሆኑ ያነሳሉ

መንግስት በበኩሉ ህጉ የወጣው ድርጅቶቹ ከውጭ የሚያመጡትን ገንዘብ ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲያውሉት ለማስቻልና በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ሁሉ የሃገሪቱን ህጎችና ደንቦች አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ በመሆኑ የሀገሪቱ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያ መንግስትን ብቻ በመሆኑ የውጭ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ አለመሆኑን ደጋግሞ ይናገራል

የእርዳታ ድርጅቶቹ በሚንቀሳቀሱባቸው አንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ  የህብረተሰብ ክፍሎችም ሁሉንም አይነት ድጋፎች ከድርጅቶቹ ስለሚጠብቁ ሰርቶ የመለወጥና ራስን የመቻል አስተሳሰብን በህብረተሰቡ ላይ የማስረጽ ሂደቱን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ጥናቶች ያሰረዳሉ። 

ወደ መጽሀፉ

የግርሃም ሃንኩክ የድህነት ጌቶች /Lords of Poverty/ ተብሎ የተሰየመው መጽሃፍ እንደሚያትተው ታላላቆቹ የእርዳታና የግብረ ሰናይ ተቋማት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ለስራ ማስኬጃ፣ ለመስተንግዶ፣ ለስብሰባ፣ ለአውሮፕላን ጉዞ፣ ለሆቴል ቆይታ፣ ለስልጠናና ለደሞዝ የሚመድቡት በጀት የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች እንኳን ሊከፍሉት የማይችሉት መሆኑን አውስቷል

ለንጽጽር እንዲሆን አንድ አሜሪካዊ የመካከለኛ መደብ ሰራተኛ የጤና ሽፋን ለማግኘት በአማካይ አስራ ሶስት አመታት ያህል ማገልገል ያለበት ሲሆን፤  በተባበሩት መንግስታትና በሌሎች ተቋማት የተቀጠረ እድለኛ ሰራተኛ ግን የጤና ሽፋኑን ለማግኘት መጠበቅ ያለበት አንድ ወር ብቻ ነው

በመሆኑም በድሃ ሃገራት የተንሰራፋው ድህነት ለተቋማቱ ሰራተኞችና ሃላፊዎች ህይወት በፍስሃና በሽርሽር የተሞላች እንድትሆን ማስቻሉን የሚሞግቱ አካላት እንደሚሉት ከሆነ በየትኛውም የአለም ጥግ ድህነት በእርዳታ ስላለመጥፋቱ  ግርሃም ሃንኩክን አስረጂ አድርገው ያነሳሉ ።

በድሃ ሃገራት ያሉት አብዛኞቹ ግብረሰናይ ድርጅቶች ውስጣዊ የአስተዳደር ዘይቤ በራሱ ጥያቄ እንደሚያስነሳ የሚያወሱ ወገኖች እንደሚያስቀምጡት ከሆነ ድርጅቶቹ የቢሮ መዋቅር  በቤተሰብና በወዳጅ ዘመድ ስለመተብተቡና ትምህርትና የስራ ልምድን መሰረት አድርገው ቅጥርና ስንብት እንደማያደርጉ በርካታ አስረጂዎችን ይጠቅሳሉ

እንደዚህ አይነቶቹ አካሄዶች ታላላቆቹ ግብረሰናይ ድርጅቶች የራሳቸውን ተልእኮ የሚያስፈጽሙላቸውን ሌሎች አነስተኛ ተቋማት በልዩ ልዩ ስያሜዎች በድሃ ሃገራት እንዳስፋፉ  ያተተው የግርሃም ሃንኩክ መጽሃፍ ምእራባውያን ግብር ከፋዮችና በደሃ ሃገራት መንግስታት እየተሰራ ያለውን ነገር እንዲያጤኑት መነሻ  እንደሆነ ሃሳባቸውን የሚያነሱ  አካላት አሉ

ከላይ ለማሳያነት ያቀረብኩት የትምህርት ቤት ጓደኛዬ በአቋራጭ የድህነት ኑሮን ጤና ይስጥልኝ ብሎ ተሰናብቶ እሱም ከራሱ አልፎ ሌሎች ዘመዶቹን በተመሳሳይ መንገድ ጠቅሞ በግብረ ሰናይ ስም ግብረ ገብነት የጎደለው ተግባር በመፈፀም ኑሮውን እየገፋ ይገኛል። መሰል በርካታ የድህነት ባለፀጎችን በያሉበት ቤቱ ይቁጠራቸው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን