×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

“ዱላ ለአህያ ! ለምን ?”

19 Jun 2017
2752 times

 ገብረህይወት ካህሳይ (ኢዜአ )

የቢሾፍቱ ከተማ ምርጡ ገጠመኜ ነው ። በትዝታ ከ7 ዓመታት በላይ የኋሊዮሽ ይዞኝ ነጎደ ። “እንኳን ማርያም ማረችሽ “ ያለ አልነበረም ። አራሷ ግን ወፍራም የስፖንጅ ፍራሽ በተነጠፈበት ክፍል ውስጥ ተንጋልላ ተኝታለች ። ሁሉም በአግራሞት ይመለከታታል ።በአገራችን ከሚገኙ እኩዮቿ ጋር ስትነፃፀር የመጨረሻዋ እድለኛ ሳትሆን አትቀርም ።

የአራስ ጥሪ ሳንይዝ ድንገት የጎበኘናት እንግዶች መደናገር ይሁን መደናበር በውል ባናውቀውም  እንደገና  “ ማርያም በሽልም ታውጣሽ “ ሳንል ተለየናት ።

አራሷ ዕድሜዋ ለግብረስጋ ግንኝነት ሳይደርስ ፣ አካሏ ሳይጠነክርና ማህፀኗ ሳይሰፋ የወሲብ ጥቃት ስለተፈፀመባት ለእርግዝና ተጋልጣለች ። እርግዝናው ስለከበዳት ደግሞ በቀዶ ጥገና ህክምና እንድትገላገል ተደርጓል ። የወለደችው ግን ህፃን ሳይሆን ውርንጭላ ነው ። እናትየዋም ሰው ሳትሆን - አህያ ። የችግሩ ምንጮች ደግሞ እንድትወልድላቸው ያለ ዕድሜዋ ያስጠቁዋት ጌቶቿ ወይም ባለቤቶቿ ናቸው ።

ብዙም ሳንርቅ አሸዋ ተሸክማ በማመላለስ የተጎሳቆለች አህያ ግሉኮስ ተተክሎላት ተመለከትን ። አጃኢብ ነው ። ፊቷ አብጧል ። የመተንፈሻ አካል ችግር ስላጋጠማት ምግብ መውሰድ ባለመቻልዋ ነበር ግልኮስ በመርፌ የተሰጣት ።

በሌላኛው ክፍል ደግሞ ከጭኗ ሙዳ ስጋ በጅብ የተነጠቀች አንዲት አህያ ቆማለች ። ቁስሏ ተጠርጎ መድሃኒት ተደርጎላታል ። ቶሎ እንድታገግም ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ቀርቦላት ትበላለች ።ተመሳሳይ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ሌሎች አህዮችም በቦታው አሉ ።

ለአገራችን አህዮች ተገቢውን እንክብካቤ የሚያደርገው የጋማ ከብቶች ደህንነትና እንክብካቤ ፕሮጀክት ነው ።ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ  ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል ። በአማራና በትግራይም ተመሳሳይ አገልግሎት  የሚሰጡ  ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ለመክፈት በመንቀሳቀስ ላይ ነበር ።

የፕሮጀክቱ ዓመታዊ በጀት 60 ሺህ ዶላር ሲሆን የገንዘብ ምንጩ ደግሞ  The donkey sanctuary የተባለ አንድ የእንግሊዝ ድርጅት ነው ።

በወቅቱ የፕሮጀክቱ አማካሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ፍስሃ ገብረአብ  ሰነፍ ሰው ለምን “አህያ “ ተብሎ  እንደሚሰደብ በአግራሞት ይጠይቃሉ ። “ አህያ በጦርነት ወቅት ስንቅና ትጥቅ በማጓጓዝ ለአገር ሉአላዊነት ድርሻዋን የምታበረክት ፣ በድርቅ ወቅት የእርዳታ እህልን በማመላለስ ውድ የሰው ህይወትን የምትታደግና በሰላም ጊዜ እህልና  ማገዶን በማቅረብ ኑሮአችን እንዲቃና እገዛ የምታደርግ የታታሪዎች አርአያ እንጂ የስንፍና መገለጫ አይደለችም “ በማለት ለጥያቄአቸው መልስ የሰጡት ራሳቸው ነበሩ ።

እንዲያውም አሉ  ፕሮፌሰሩ  በአማራ ክልል አህያ የሌለው ገበሬ ሁሉንም ስራ በጉልበቱ ለማከናወን ስለሚገደድ “ አህያ የሌለው ገበሬ እራሱ አህያ ነው “  የሚል ብሂል አለ ። ታዲያ ! ስድቡ አልበቃ ብሎ ለምን ዱላውም ጭምር ለአህያ ተባለ ?።

እንግሊዝ የአህያ ሃብቷ ቁጥር ከሶስት ሺህ አይበልጥም ።ኢትዮጵያ ግን 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአህያ ቁጥር እንዳላት ወቅታዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። የእንግሊዝ አህዮች በእንክብካቤ ስለሚያዙ  በህይወት የመኖር እድሜአቸው 35 ዓመት ይደርሳል ። የኢትዮጵያ  አህዮች አማካይ እድሜ ግን  ከ9 ዓመት እንደማይበልጥ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል ።

የአገራችን አህዮች በአያያዝና በአመጋገብ ጉድለት ሙሉ በሙሉ ኮሶና ወስፋት በመሳሰሉት ጥገኛ ተህዋስያን የተጠቁ ናቸው ።በርካታዎቹም በቂ መጠለያ ስለማይዘጋጅላቸው በጅብ ይበላሉ ። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀጨጩ የሚሄዱ ፣ ጉልበታቸው ደካማና በቀላሉ ለሞት የተጋለጡ ናቸው ።

ለምሳሌ አንዲት የእስራኤል ላም በቀን የምትሰጠውን የወተት መጠን ለማግኘት 33 የአገራችን ላሞችን መያዝ ይጠይቃል ። ይህ ማለት እስራኤላዊያን በሚያገኙት የወተት መጠን 33 በመቶ ከኛ በላይ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ። በጉዳት ደግሞ 33 በመቶ እኛ እንበልጣቸዋለን ። ምክንያቱም አንዲት ላም መያዝና 33 ላሞች መንከባከብ ልዩነቱ ሰፊ ነው ።

ዋናው ነገር ከዚህ ምን እንማራለን ? የሚለው ነው ። እንስሳት በአግባቡ ካልተያዙ ተገቢው ምርትና አገልግሎት  አይሰጡም ። ጤንነታቸው በደንብ ካልተያዘ ደግሞ በሽታው ከእንስሳት አልፎ ለሰው ልጆችም  ይተርፋል ።

 የዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገፅ Zoonoses diseases Oie;WHO from animal to human (infectious diseases ) በሚል ርእስ  የለቀቀው መረጃ የእንሰሳት በሽታ ወደ ሰው የሚተላለፍና ጉዳቱ ሰፊ መሆኑን ያብራራል ። በእንስሳት ላይ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል 75 በመቶ ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው ።

በአገራችን የእንሰሳት አያያዝ ቅጥ ያጣ ነው ። በተለይ በከተሞች  ዕድሜ  ልካቸውን በታማኝነት  ያገለገሉንን  የጋማ ከብቶች ከቤት አስወጥተን  ጎዳና ላይ እንጥላቸዋለን ።  ስጋቸው አለመበላቱ ብቻ አገልግሎታቸው  ከውለታ ሳይገባ  እንደ አሉባሌ ዕቃ ይወረወራሉ ።

በአንዳንድ ከተሞች  አውራ መንገዶች ላይ የሚርመሰመሱ  ፈረሶችና አህዮች የዚህ ዕጣ ፈንታ ሰለባዎች ናቸው ።  አስፋልት መንገድ ላይ መቆም የሚመርጡት  ደግሞ በአገልግሎት ብዛት የተላላጠውንና  የቆሰለውን ጀርባቸው በዝንብ ስለሚወረርና ተሽከርካሪዎች በአጠገባቸው በፍጥነት ሲያልፉ  በንፋስ ሽውታ ዝንቡን ስለሚያባርሩላቸው መሆኑን የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ ።

በከተሞች ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚልከሰከሱ ባለቤት አልባ ውሾችም ቢሆኑ የህዝቡ የእንስሳት አያያዝ ችግር  ውጤቶች ናቸው ።  ህዝቡ ለታማኝ አገልግሎታቸው  የሚሰጣቸው ምላሽ በእጅጉ አሳዛኝ ነው ።  ውሾቹ ለእብድ ውሻ በሽታ ይጋለጡና ተመልሰው ለሰው ልጅ ስጋት ሲሆኑ ይስተዋላሉ ።

ከጤናው  ስጋት ባሻገር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውና የአገር ገፅታም  ክፉኛ እንደሚጎዱት ዶክተር ሀድጉ ይገልፃሉ ። ከአደጉት አገራት  ለጉብኝት የሚመጡ ዜጎች  በእንስሳት  አያያዝና መብት አከባበር  ላይ  ርቀው የተጓዙ ናቸው ። እንስሳት ሲጎዳ ከተመለከቱ  መንፈሳቸውም  ወዲያውኑ ይጎዳል ። 

ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገር ተመልክተው እያለ  ያልተገባ  ጭነት  የተሸከመ እንስሳ ሲያጋጥማቸው ፣ እንስሳት ሲገረፉ  ከተመለከቱና  አለአግባብ የተጣሉ ሲኖሩ  መልካሙን ሳይሆን መጥፎውን  ይገነዘባሉ ።

ይህ ድርጊታችን ቱሪስቶች  የቆይታ ጊዜአቸው እንዳያስረዝሙና ዳግም ተመልሰው እንዳይመጡ  ተፅእኖ ይፈጥርባቸዋል ። በመሆኑም ከመስኩ የሚገኘው ገቢ እንዲያሽቆለቁል አሉታዊ ድርሻ ይጫወታል ።

እውነታው ይህ ከሆነ አገራችን ከእንስሳት ሃብቷ ምን ያክል ተጠቅማለች ? በሽታውስ ምን ደረጃ ላይ ነው ? የሚለውም ማየቱ አይከፋም ።

የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ሀብት ልማት ኢንዱስትሪ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃይለስላሴ ወረስ ያካፈሉኝ መረጃ እንደሚያመለክተው  አገራችን 56 ሚሊዮን ከብት ፣ 29 ነጥብ 3ሚሊዮን በጎች ፣ 29 ነጥብ 1 ሚሊዮን ፍየሎች ፣ 2ሚሊዮን ፈረስ ፣ 1ነጥብ 1 ሚሊዮን ግመልና 56 ነጥብ 8 ሚሊዮን የዶሮ ሃብት ባለቤት ናት ።

ይህ የእንስሳት መጠን በአጠቃላይ ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም ደግም 9ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠናል ። እንዲያውም በከብት ብዛት ከዓለም 5ኛ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር የእንስሳት ልየታ ፣ ክትትልና ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ሀድጉ ማንደፍሮ አጫውተውኛል ።

ይሁን እንጂ የእንስሳት አረባብ ልምዳችን ፣ የመኖ አቅርቦትና አጠቃቀማችን ፣ የእንስሳት ጤናና ደህንነት ጥበቃ ስርአታችንና  የግብይት ሂደቱ ደካማ መሆን  አገራችን ከእንስሳት ሃብቷ የሚፈለገውን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓት ቆይቷል ይላሉ ።

በተለይ የእንስሳት በሽታ በአግባቡ ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገበት በሰው ጤና ፣ በእንስሳት ተዋፅኦና በአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ሰፊ ነው ባይ ናቸው ።

የህዝቦቿ አኗኗር ከእንስሳት ንኪኪ ጋር ቀጥተኛ ግንኝነት ያለው በመሆኑ ከእንስሳት ወደ ሰውና ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር  ስራ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ።

የችግሩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት  የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና ፣ የማህበረሰብ ጤናና የእንስሳት ደህንነትን  አካትቶ የያዘ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በየደረጃው እያስተቸ ይገኛል ። 

አዋጁ በእንሰሳት ጤና ፣ በህብረተሰብ ጤናና በእንስሳት ደህንነት ላይ ያተኮረ ሲሆን በስሩ አምስት ደንቦችን አካትቷል ።

አዋጁ የእንስሳት ሃብታችንን ከእርባታ እስከ ኤክስፖርት ድረስ ያለውን የእሴት ሰንሰለት ተከትሎ የክትትል ስርዓት በመዘርጋት አገራችን ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ የሚረዳ ነው ብለዋል ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእንስሳት ልየታ ምዝገባና ክትትል ባለሙያ ወይዘሮ አስቴር እሼቴ እንዳሉት ከሆነ ደግሞ እንስሳት በህግ ማእቀፍ የተደገፈ ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገላቸው ከኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ባሻገር በህብረተሰቡ ጤንነት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ነው ።

በዓለማችን ከሚገኙ 10 ተላላፊ በሽታዎች መካከል 6ቱ ፣ ብቅ ብቅ እያሉ የሚገኙ 4 ተዛማች በሽታዎች  ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ናቸው ። በአገራችንም ቢሆን ስጋቱም ሆነ ተጨባጭ ችግሩ እንዳለ ነው ይላሉ ።

በተለይም ጥሬ ስጋና ጥሬ ወተት በመመገብ ሳንባ ነቀርሳና ውርጃን ጨምሮ በርካታ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው ይተላለፋሉ  ባይ ናቸው  

አዋጁ  በአገራችን እየተስፋፉ የመጡትን  የእንስሳት በሽታዎች ለመከላከል ፣ ለመቆጣጠርና ደረጃ በደረጃ ለማጥፋት ፣ ባህላዊ የእንስሳት አያያዝን ዘመናዊ ለማድረግና የእንስሳትና የእንስሳት ምርቶች ተቀባይ አገሮች ፍላጎት በማስፋት የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑንም ያምኑበታል ።

የእንስሳት ህክምናና የህብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ወንድወሰን በቀለ በበኩላቸው  የእብድ  ውሻ በሽታን ጨምሮ ለህብረተሰቡ አስጊ የሆኑና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችንና  ለህዘቡ የሚቀርበው ስጋ የእርድ ጥራት ለመቆጣጠር አዋጁ አመቺ የህግ ድጋፍ የሚሰጥ  ነው ።

እዚህ ላይ የእንሰሳት ሀብትን ከበሽታ መጠበቅ ፣ አመጋገባቸውን በማስተካከል ምርታማ ማድረግና የግብይት ሰንሰለቱን ፈር ማስያዝ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በህይወት ጤናማ ሆኖ የመቆየት ጉዳይ መሆኑ ነው ። 

በአንድ በኩል  እኛው ንፅህናውንና ጤንነቱን የተጠበቀ ስጋና ወተት እንድንመገብ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በገበያው ተወዳዳሪ ሆነን አገራችንም ሆነ እራሳችንን ለመጥቀም  የእንስሳት ሀብታችንን መንከባከብና መጠበቅ ግድ የሚለን ወቅት ላይ እንገኛለን ።

መንግስትም የእንስሳት ሃብታችንን ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ለማዋል እየተጋ ይገኛል ። ረቂቅ አዋጁ በየደረጃው በውይይት ዳብሮ ከፀደቀ ደግሞ በዘርፉ የነበሩት ክፍተቶች ይሞላሉና ሃላፊነቱን የወሰደው አካል ይበርታልን እንላለን ።

 

 

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን