ከቅዳሜ ገጠመኝ የተፈለቀቀ እውነት

18 Jun 2017
3141 times

የፀዳወርቅ ታደለ (ኢዜአ)

መቼም ዕለተ ቅዳሜን ስናስባት፤ በአብዛኛው በተለይም በወጣቶች ዘንድ የምትወደድና የምትናፈቅ ዕለት እንደሆነች የማይታበል ሃቅ ነው። ከፍ ሲልም በሥራ፣ በትምህርትና በተለያዩ ጉዳዮች የተጨናነቀ ሳምንት ለሚያሳልፉ ሰዎችም እንደ ወጣቱ ሁሌ ቅዳሜ ተወዳጅ ናት፤ በዚህም ልዩ የሚያደርጋት ይመስለኛል። ይህችንም ቀን በጉጉት ከሚጠብቁና በዕለቱም “አሉኝ” ከምላቸው ጓደኞችና የቅርብ ሰዎች ጋር ዘና ማለት ከሚከጅላቸው መካከል አንዷ ነኝ ማለት እችላለሁ።

በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ መሃል፤ የጥንት የአራዶች (የአሪፎቹ) መናገሻ ወደ ምትባለው ፒያሳ ጎራ በማለት ነው ይህችው የእረፍት ቀኔን የማሳልፍው። ከእነዚህ ቀናት መካከል በአንዷ ቅዳሜ፤ በፒያሳ ከአንዱ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና እያልን፣ እያወጋሁ ባለሁበት ወቅት በዚህ ዘመን አንድ የማልጠብቀው ክስተት ገጠመኝ።

ነገሩ እንዲህ ነው፤ እኔና ጓደኛዬ ከተቀመጥንበት ወንበር አጠገብ አንድ ወጣት ልጅ ከጎናችን ተቀምጣ ለስላሳ እየጠጣች ወጪና ገቢውን በመመልከት ላይ ነበረች። የልጅቱ በር በር ማየትና ፊቷ ላይ የሚነበበው ሁኔታ አንድ የምትጠብቀው ሰው እንዳለ የፊቷ ገጽታ ያሳብቅባታል። በጊዜው ካፌው በሰው ተሞልቷል፤ አስተናጋጆቹ በቅጡ ለመታዘዝ እንኳን ጊዜ አጥተው ወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ። የሚገባውና የሚወጣው ሰውም ብዛት ዓለው፤ እንዲያው ካፌው ተጨናንቋል ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በዚህ መሃል፤ ደጅ ደጁን እያየች የነበረችው ይህች ወጣት ድንገት ፊቷ በፈገግታ በርቶ ከተቀመጠችበት ብድግ አለች። እንዳጋጣሚ ልጅቷን እያየኋት ስለነበር እኔም አብሬያት ወደምትመለከትበት አቅጣጫ አንገቴን መለስ ሳደርግ አንድ ዘመናዊ ወጣት በእጁ ምልክት እያሳያት ወዳለችበት ሲመጣ ተመለከትኩኝ።

ወጣቱ ከመጣ ደቂቃዎችን ያህል በጨዋታ ካሳለፉ በኋላ ከልጅቷ ጋር በነገር ያልተግባቡ የሚመስል ጭቅጭቅ የሚመስል ድምጽ ሰማሁኝ። አተኩሮ ለተመለከታቸው ሰላማዊ ወሬ እያወሩ እንዳልሆነ ለማወቅ አያዳግትም። ብቻ በቅጽፈት፤ ከልጅቷ ጋር የነበረው ወጣት ከመቀመጫው ተስፈንጥሮ በመነሳት በጠረጴዛው ላይ የነበሩትን ብርጭቆዎች በንዴት እያነሳ ከሸከሻቸው። ልጅቷም ላይ እያፈጠጠ ድምጹን ከፍ አድርጎ የስድብ ናዳ አወረደባት፤ እንደውም “አለቅሽም” በሚል እያስፈራራትና እየዛተባት በማን አለብኝ ስሜት ትከሻውን እየሰበቀ ወጣ። ልጅቷ ከድንጋጤ የተነሳ በዝምታ ተዋጠች፤ በደቂቃ ውስጥ የሰው ሁሉ ዓይን ማረፊያና መነጋገሪያ ሆነች። የካፌው ድባብ ከሁካታና ከግርግር ላፍታ ተግ በማለት በተፈጠረው ኩነት ላይ አትኩሮቱን አድርጓል።

እኔም፤ ኩነቱ የእውነት ክስተት ሳይሆን ቁንጽል የድራማ ክፍል የሚመስል አኳኃን የተላበሰ በመሆኑ በጊዜው አግራሞትም፤ ድንጋጤም ጭሮብኛል። ያውም ይህ ክስተት የሴትና የወንድ ልጅ እኩልነት “እውን ሆኗል” በተባለበት፤ ያውም የዚህ ዘመን ትውልድ “የውጪውን ባህልና የአኗኗር ስልት ተከትሏል” እየተባለ በሚነገርላት  በመዲናችን ‘አዲስ አበባ’ መከሰቱ ነው የሚያስደንቀው። ይሁንና ከምናብ ባለፈ በገሃዱ ዓለም እንዲህ ያለ እውነታ ሳይ ለመጀመሪያዬ ቢሆንም የሴት ልጅ ክብሯ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሲራቆት መመልከት እንደ አንድ ዜጋ አሳፍሮኛል። ከዚያም ባለፈ የሴትና የወንድ ልጅ እኩልነት እስከ ምን ድረስ ነው? ብዬ እራሴን እንድጠይቅ ምክንያት ሆኖኛል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሶስት ሴቶች አንዷ ከሥነ-ልቦና ባለፈ የአካል ወይንም ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባት ያሳያል። እነዚህ ጥቃቶች ደግሞ የሚፈጸሙት በአብዛኛው ለሴቶቹ ቅርብ በሆኑ ጓደኞች ወይንም የትዳር አጋሮች መሆኑም ተገልጿል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በሚለው ጉዳይ “ይህ ነው” የሚባል ምክንያት የተጠቀሰ ባይኖርም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሁንም ዘርፈ ብዙና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን ሪፖርቱ አጽንዖት ሰጥቶ የሚያሳየው። ከእነዚህ መካከል በሴቶች ሥነ-ልቦና ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተጠቃሽ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ያወጣው ድንጋጌ እንደሚያመለክተው፤ በሴቶች ስሜት ላይ የሚደርስ ማንኛውንም ዓይነት ጉዳት “በሴቶች ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብሎ መውሰድ ይቻላል። በዚህም መሠረት ሴቶችን በማወክ፣ ማዋረድ ወይንም የሚገባቸውን ክብር አለመስጠት፤ ስሜታቸውን እንዳይገልጹ ጫና ማሳደር፣ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፤ መስደብና ማስፈራራት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።  

በኢትዮጵያ በማኅበረሰብ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑት በመኖሪያ ቤታቸው አልያም ደግሞ በቅርብ ሰዎች ጥቃት ይደርስባቸዋል። የችግሩን ግዝፈት ለማሳየትም ለዚህ ጽሁፍ የተጠቀምኩት ጥናት በአገሪቷ በአንዳንድ አካባቢዎች 'ባሌ ካልመታኝ የሚወደኝ አይመስለኝም' የሚል አመለካከት መኖሩ በራሱ ችግሩ ስር እንዲሰድና አሁን ላይ የተለመደ እንዲሆን እንዳደረገው ነው የሚጠቅሰው።

ይሁንና በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በቅርብ ጓደኞቻቸውና የትዳር አጋሮቻቸው እንዲሆን ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን ሁኔታ ስናጤን የተለያዩ ችግሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ።  ከእነዚህ መካከል የአልኮል ተጠቃሚ ወንዶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱና ያላቸው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ችግሩን እንዳባባሰው መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህም ጎን ለጎን ራሳቸውን ያልቻሉ ወንዶች ከሴቶች ጋር ጓደኝነት በሚመሰርቱበት ወቅትም እንዲህ ያሉ ችግሮች እንደሚያጋጥም ነው የሚነገረው። በኢትዮጵያ በአብዛኛው ወንዶች ቤተሰብ ስለሚያስተዳድሩና ትዳርን በተመለከተ ውሳኔ ሰጪ መሆናቸው ከሴቶች ጋር በማኅበራዊ ህይወት ውስጥ ያላቸው እኩልነት የተዛባ መሆኑ ለዚሁ ችግር ሌላኛው ምክንያት ነው። በአንጻሩ ሴቶች አሁንም ድረስ በቤት ውስጥ ካላቸው አነስተኛ ዓቅም በቤታቸው ውሳኔ አለመስጠታቸውም እንዲሁ የችግሮች ገፈት ቀማሽ እንዳደረጋቸው ማወቅ ይቻላል።

ወንዶች በሴቶች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ የሚያጋጥማቸው ሰዎች ጉዳዩን በቸልታ ማየታቸውና መታገሳቸው፣ ጥፋተኛው ተይዞ ለፍትሀ ሲቀርብም የሚወሰዱ እርምጃዎች አስተማሪ አለመሆናቸው እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳሉ። ህግና ደንቦች በሚያስፈጽሙ አካላት ዘንድ ያለው የተሳሳተ አመለካከትም ሌላው የሚነሳ ምክንያት ነው። ይህም በአፈጻጸም ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለመገመት አያስቸግርም። ይህን ስል ሥራዎች አልተሰሩም ሳይሆን በተለይም ሴቶች በቤታቸው የሚደርስባቸውን ጥቃቶች በማስቆም ረገድ አሁንም ቢሆን በሚፈለገው ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስለኝም። ከላይ ለማቅረብ እንደሞከርኩት ሴቶች የሥነ-ልቦና ጥቃት ብቻ ሳይሆን የጾታና የአካል ጉዳትም እንደሚደርስባቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ይገለጻል፡፡

በመሆኑም እንደ መፍትሄ ተብለው የሚቀርቡ ጉዳዮች የሥነ-ልቦና ጥቃትን ብቻ ሳይሆን የሴቶችን ሁለንተናዊ ችግሮች ሊያስቀሩ በሚችሉ መልኩ የተቃኙ መሆን አለባቸው። በዚህም መሠረት “ሴት እናት፣ እህት፣ ሚስት እንዲሁም ልጅ ናት” የሚለውን የአገራችን ብሂል ከግምት በማስገባት ሁሉም በየፊናው የሚጠበቅበትን በማድረግ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውን ጥቃት ማስቆም ተገቢ ነው። በተለይም የግንዛቤ ችግር በሥፋት በሚታይበት አገር መንግሥትና በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ አካላቶች በኅብረተሰቡ ዘንድ መሠረታዊ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊካሄዱ ይገባል።

ይህንን ሥራ በተለይም የእምነት ተቋማት ከኃይማኖታዊ አስተሳሰብ ጋር በማያያዝ ተከታዮቻቸውን በማስተማር የብሔራዊ ጥረቱ ዋነኛ አካል ሊሆኑ ይገባቸዋል። የምርምር ተቋማትም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ሊያስቆሙ የሚያስችሉ የቅድመ ሁኔታ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችሉ ጥናቶችን በማካሄድና መጪውን የማመላከት ሥራ ሊሰሩ የግድ ይላቸዋል። ይህንንም በማድረግ በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ችግሮች ከመፈጸማቸው በፊት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ጥፋቱን ከወዲሁ ማስቀረት እንደሚቻል ሙሉ እምነት አለኝ። ፖለሲ አውጪዎችና አስፈጻሚ አካላቶችም የሚወጡ ሕጎችና ደንቦች ተፈጻሚ መሆናቸውን የዳሰሳ ጥናት ጭምር በማካሄድ ተግባራዊነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል። በተለይም የሴቶችን ምጣኔ ሃብታዊ ዓቅም ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች መተግበራቸውን በመቆጣጠር ሴቶች ከዚህ ቀደም ኢኮኖሚያዊ ዓቅም በማጣቸው የሚደርስባቸውን ችግር እንዲያቃልሉ መደረግ አለበት።

የሴቶች ጉዳይ ማለት የሁሉም ጉዳይ ነው። በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ አካላት መተባበርና መቀናጀት እንዳለባቸው ሁሉ ኅብረተሰቡም የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ሁላችንንም የሚያስማማን ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ‘‘ ሴቶችን የማብቃት እና ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ግዴታ ነው" ያሉት። በአገሪቷ ካለው አጠቃላይ ህዝብ ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው የአገሪቷን መፃዒ እድል የሴቶችን ዓቅምና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያማከለ መሆኑ በሴቶች ላይ ትኩረት ማድረጉ የውዴታ ግዴታ የሚያደርገው ይመስለኛል። በመጨረሻም ሴቶች ራሳቸውንና መብታቸውን ለማስከበር በመታገልና ምጣኔ ሃብታዊ ዓቅማቸውን ለማጎልበት አንድም በትምህርት አልያም ደግሞ በሙያቸው ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ቀዳሚውን ሥፍራ ሊይዙ ይገባል ባይ ነኝ።

ሴቶች ባልታገሉበትና ንቁ ተሳትፎ ባላደረጉበት ሁኔታ የሴቶች ጥያቄ መፍትሄ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነ ለሁሉም እሙን ነው። የሴቶች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ በሁሉም ሴቶች ዘንድ ብቁ ግንዛቤ እንዲያዝ ማድረግና ሴቶች በራሳቸው ጥረት ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዳይችሉ የሚያደናቅፉ ጉዳዮችን ማቃለል ላይ መረባረብ ይገባል። በተለይም ሴቶች ከበታችነት አስተሳሰብ እንዲላቀቁና በማንኛውም የሥራ መስክ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ በመስራት “እንችላለን” የሚል እምነት እንዲያሳድሩ ማድረግ እንዲሚገባም የብዙዎች እምነት ነው። የሚዘጋጁ መድረኮች የሴቶችን የተለያዩ ጉዳዮች ከግምት ያስገቡና ውጤታማ ምክክርና አቋም የሚያዝባቸው እንዲሆኑ ማስቻል በተለይም በአመራርነት ላይ ያሉ ሴቶች ቀዳሚ ሚናውን መውሰድ እንዳለባቸውም ያስማማል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን