አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

“ሰላም ለትምህርት - ትምህርት ለሰላም! “

17 Jun 2017
1546 times

አዳም ካሳሁን (ሀረር ኢዜአ)

  ለአንድ አገር ልማትና እድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ አለው ። ሰላም  በዋጋ አይሰላም ። ተመንም ሆነ መስፈርያ የለውም። ከግለሰብ የነገ  የመለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ የቱንም ዓይነት ራዕይና ግብ ማሳከት አይቻልም።

 በአንድ ወቅት በተገኘሁበት የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የቀረበው ጽሁፍ ሰላምን ሲገልጸው  "ሰላም ማለት በግለሰቦች፣ በቤተሠብ፣ በቡድን፣ በማሕበረሰብ እንዲሁም በሀገር ደረጃ  አነስተኛ ያለመግባባቶች የሚታዩበት ሁኔታና የሕብረተሰቡ ግንኙነት በጋራ ስምምነትና መግባባት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ነው።

 የሰላም ፅንሠ ሀሳብ “ከግጭት (ያለመግባባት) ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆን ማለት ሳይሆን፣ በማንኛውም መልኩ ከሁከት ነፃ በሆነ አኳኋን ያለመግባባቶችን በመቻቻል የሚፈቱበት መንገድ ነው፡፡" ይላል ።

 ሰላም ለአንድ ሀገር የልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለው አስተዋጽዎም የጎላ ነው። በአንድ አካባቢ ወይም ስፍራ የሰላም እጦት ከተከሰተ ህብረተሰቡ  ወደ አልተፈለገ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ይገደዳል።  ይህም   የማህበረሰቡ ህይወትና አኗኗር ከመናጋት ባለፈ አካባቢው ለእርስ በርስ ጦርነት ይጋለጣል ።

 የሰው ልጅም ላልተፈለገ ስደት ፣ረሀብና በሽታ ይዳረጋል ።ይህንን መቋቋም ሲያቅተው     ህይወት እንደዋዛ ይጠፋል። ሠላም ለማንኛውም ኀብረተሰብም ሆነ አካባቢ እጅግ በጣም አስፈላጊና ውድ ስጦታ  ነው፡፡

 ታላላቅ የነበሩት እንደ ሶማሊያ፣ሶርያና ሌሎች  ሀገራት በሰላም እጦት በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት በርካታ ዜጎቻቸውን ከማጣታቸው ባለፈ እስካሁን ድረስ መንግስት አልባ ኑሮን ሳይወዱት በግዳቸው እንዲገፉ አድርጓቸዋል። ሠላም ህይወት ላለው ነገር ሁሉ ተፈላጊ ነው ።

 በሃገራችን በብዙ መልኩ የሚገለጽ የሰላም መሰረት አለን፡፡ የቆየ ወርቃማ የመቻቻል፤ መከባበር፤ እንግዳ ተቀባይነት፤ ህገ-መንግስታችን፤ ፓሊሲዎቻችን በማክበር ማህሰረሰባችንን ከግጭት ተጋላጭነት የመጠበቅ ሃለፊነት የሁሉም መሆን የሚገባው አጀንዳ ነው ።

  መንግሥትም የዚህ ግዴታና ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ አስተማማኝ ሰላም በሃገራችን ለማስፈን ቁርጠኝነት እና ተቋማዊ ዝግጁነት አለው ። ታላላቅ የአለም መንግስታት፣ አርቲስቶች ፣ በበጎ አድራጎት የተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ፣ሙህራን ፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ስመጥር ግለሰቦች ስለ ሰላም አስተምረዋል ። አዚመዋል ።  ሰብከዋልም።

  በተለይ ሰላም በአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ፋይዳው የጎላ ነው ። በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሰላም ከሌለ የመማር ማስተማር ስራውን ከማወክ ባለፈ ተማሪዎች በተሳሳተ መረጃ በመጓዝ ለግጭት ይዳረጋሉ ። የአካባቢው ማህበረሰብም የሁከቱ ተጋላጭ ይሆናል ።

 የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲም “ሰላም ለትምህርት - ትምህርት ለሰላም! “ በሚል መሪ ቃል የሰላም ቀንን ሰሞኑን አክብራል።

 የዩኒቨርሲቲው የሰላም ክበብ መስራችና የዘንድሮ የሰላም ክብር ተሸላሚ መምህር ንጉሴ አንጋሳ እንደሚገልጹት በአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሰላም ክበብ /ፎረም/ መቋቋም ተማሪዎች ሰላምን የማስጠበቅ ጉዳይን የተቋሙ ወይንም የማኔጅመንቱ ሳይሆን የእኛ ድርሻ ነው ብለው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል ። የመማር ማስተማር ስራን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ያስችላል።

 በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚገኙ ተማሪዎች ከተለያዩ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የእምነት ተከታይና ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ህብረተሰብ እንደመምጣታቸው መጠን በሰላም እጦት የመማር ማስተማሩ ስራ ህልም ሆና እንዳይቀር የሰላም ፎረም የተማሪዎችን የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያበረክታል።

 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ክበብ በሚል መጠሪያ በ2001 ዓም የተቋቋመውና ከ2006 ጀምሮ የሰላም ፎረም ተብሎ የተሰየመው በተማሪዎች መካከል ይከሰት የነበረውን የእርስ በርስ አለመግባባቶችና ግጭቶችን በአቻ ለአቻ ትምህርትና ውይይት የማስወገድ ስራ በማከናወን የተቋሙ የመማር ማስተማር ስራ ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

 በተለያዩ አለመግባባቶች ወደ ዲሲፒሊን የሚያመሩ ምክንያቶችን ፎረሙ በኮሚቴ አባላት አማካኝነት በመነጋገርና በመግባባት እንዲፈቱ  ያደርጋል  ።

 ይህን ተሞክሮ ለባህርዳር፣ ጎንደርና አምቦ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከውጭ አገር ወደ ተቋሙ ለመጡ የኬኒያና የሱዳን መምህራን ማስፋፋትና ማካፈል መቻሉን የጠቆሙት መምህር ንጉሴ አንጋሳ  በቀጣይም በአገር ውስጥ ለሚገኙ አምስት  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማስፋፋት መታቀዱን አስረድተዋል።

 የፎረሙ ፕሬዚዳንት ተማሪ አንድነት አድነው ፎረሙ ከምስረታው ጀምሮ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስጠበቅ መጠነ ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ለዩኒቨርሲቲው ሰላም የበኩሉን አስተዋጽዎ ከማበርከቱ ባሻገር ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላም ፎረሞች አብነት መሆን ችሏል።

 ከዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ተማሪዎች፣ አስተዳደር ሰራተኞችና አጋር የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፎረሙ በሚያከናውነው ስራ ተማሪዎች ልዩነታቸውን እንደ ታላቅ ጸጋ ተቀብለው ለተቋሙ ሰላም በአንድነት እንዲሰሩና በተማሪዎች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በጠረጴዛ ዙርያ ውይይት በማድረግ  እንዲፈቱ እያደረገ ይገኛል።

 በተቋሙ ላይ የአገልግሎት መጓደል ሲያጋጥም ከተማሪዎች ህብረት ጋር በመቀናጀትና ለሚመለከተው አካል በማቅረብ በጋራ ችግሩን የመፍታት ስራም ፎረሙ በማከናወን ለዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መጎልበት ሰፊውን ድርሻ  እየተወጣ ነው ይላል ።

 በአካባቢው ከሚገኙ የሁለተኛና መሰናዶ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር የሰላም ክበብ በመመስረት ተግባራዊ ስራ ከማከናወን ባለፈ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን በማስተባበር ለአካባቢው ትምህርት ቤቶች የማጣቀሻ መጽሀፍት ልገሳ ስራ ያካሂዳል ።

 “ዓምና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ወቅት በተቋሙ ያለመረጋጋት ሁኔታ ተከስቶ ነበር ። የተከሰተውን አለመረጋጋት ተማሪዎችን በማወያየት ተቋሙ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲመለስ ፎረሙ ከፍተኛ አስተዋጽዎ አበርክቷል” ያለው  የሶስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ አሸናፊ ወንደሰን ነው።

 የመጀመሪያ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ሜላት አስፋው በበኩሏ በአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚቋቋሙ የሰላም ክበብና ፎረሞች ተማሪዎች በመከባበር ፣ በመቻቻልና በመረዳዳት ፣ በሰላምና በነጻነት እንዲኖሩና ትምህርታቸውን  እንዲከታተሉ ገንቢ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው ።

 የዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም ኮሚቴዎችና አባላት ከሁሉም ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተውጣጡ መሆናቸውና  በየጊዜውም ከተማሪዎች ጋር በሚያከናውነው ስራ የግቢው ሰላም በፊት ከሚታወቅበት  በተለየ ሁኔታ ሰላማዊ አየር መተንፈስ ተችሏል ትላለች ።

 “በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የፎረሙ ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ለመወዳደር ተዘጋጅቻለሁ። ምርጫውን ካሸነፍኩኝ ደግሞ በመጪዎቹ ሁለት ዓመት የተለየ ስራ ለማከናወን አቅጃለው “ የሚል አስተያየት ሰጥታለች ።

 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ሲገልጹ ሰላምና ልማት ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። ሰላም ባልተረጋገጠበት ማህበረሰብ ልማትና ዴሞክራሲን ማስቀጠል የማይታሰብ ነው።

 የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተጣለበትን የመማር ማስተማር፣ የምርምር ስራና የማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮዎችን በሚያከናውንበት ወቅት ጥቂት ሰላምን የሚያደፍርሱ እንቅስቃሴዎች አልፎ አልፎ ቢከሰቱም በአሁኑ ወቅት ግን ሰላምን በማስረጽ በኩል አመርቂ ተግባር እየታየ  የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት መስክረዋል ።

 ለዚህም የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና አመራሩ የመሰረቱት የሰላም ፎረም ለተመዘገበው ውጤት በቀዳሚነት ይጠቀሳል ።

 በስነስርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲተሪው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ የአጎራባች ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በኦሮምያ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ተወካይዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 አቶ ሸምሸዲን መሀመድ ይባላሉ ። የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረምን በመወከል ነው በእለቱ የተገኙት ። በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚመሰረቱ የሰላም ፎረሞችን በተመለከተ ሲገልጹ “የተማሪዎችን የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር  የመማር ማስተማሩ ስራው ሳይስተጓጎል ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን የሰላም ፎረም ድርሻ የላቀ ነው “ ብለዋል ።

 “በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የሰላም ፎረም ተማሪዎች ያላቸውን ልዩነቶች በማጥበብ ፍቅርና ሰላምን በመፍጠር የመማር ማስተማሩ ስራን ሲያግዙ ተመልክተናል “ ያሉት አቶ ሸምሸዲን ይህን አበረታች ተግባር ወደ ዩኒቨርሲቲያቸው በመውሰድ የማስፋፋት  ተግባር  እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

የሰላም  ፎረም ዋና ዓላማ የመማር ማስተማሩ ሂደት ያለምንም የሰላም እጦት እንዲከናወንና ሴኩላሪዝም በተቋሙ እንዲተገበር በማድረግ ብዝሃነትና መቻቻልን በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙበት ወሳኝ ሚና የሚያበረክት ነው ያሉት ደግሞ የኦሮምያ ክልል ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ሐላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ ናቸው።

 በዲስፒሊን የታነጸና ምርታማ ዜጋ ለማፍራት የሰላም ፎረም  በከፍተኛ ትምህርት ተቋም መቋቋም አስተዋጽዎው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው የተቋሙ ተማሪዎች ፣መምህራን፣ አመራሮችና የተቋሙ ማህበረሰብ በሙሉ የጀመሩትን ሰላምን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጦውላቸዋል ።

 ለአገራችን እና  ለህዝባችን ሰላም ይበዛ ዘንድ ሁላችንም  ለሰላም ዘብ  እንቁም !  እያልኩኝ መጪው ጊዜ የሰላም እንዲሆን እመኛለሁ ።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን