×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ፌዴራሊዝም የብዝሃነት ማገር!

17 Jun 2017
3008 times

ተካ ጉግሳ መቐለ ኢዜአ

አገራችን የፌዴራሊዝም ስርዓት መከተል ከጀመረች 26 ዓመታት አስቆጥራለች። በእነዚሁ አመታት በአብዛኛው የአገራችን ህዝቦች ማንነታቸው አውቀው፣ የሌላውን ማንነት ተቀብለውና አክብረው በአንድነት እንዲዘልቁ እድል ፈጥሯል ።

በአገራችን የብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ተከብሮ ለጋራ እድገት በአንድነት መንፈስ እንዲተጉ ያደረጋቸው ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የተገነባው ፌዴራላዊ ስርዓት መሆኑን ምሁራን ያብራሩታል ።

ልዩነታችን ውበታችን መሆኑን በማመን ብዝሃነታችን የማጠናከር ስራ በስፋት ከሚያከናውኑ ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንና የሰንደቅ አላማ  በዓላትም ይህንኑ የማጠናከር ተልእኮ ሰንቀው የሚከበሩ ናቸው።

በዚሁና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የመቐለ ዩንቨርስቲ በቅርቡ አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።  በዚሁ ዙሪያ ምሁራንን አነጋግረናል።

" የኢትዮጵያ የፌደሬሽን ትርጓሜና የብዝሃነት እይታ"  በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ሃብተጽዮን  ነበሩ፡፡

በዚሁ ጥናታዊ ጽሁፋቸው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች በማንነታቸው ኮርተው ለአገራቸው እድገት በጋራ እንዲሰሩ እንዳስቻላቸው አመልክተዋል፡፡

መንግስት የህዝቦችን ማንነትና አንድነት ለማጠናከር የሚያግዙ  የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ብዝሃነትና ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያስገኙት ጥቅም "  በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር  ዶክተር አሰፋ ፍስሃ በበኩላቸው "ለብዝሀነት የተሰጠው እውቅና  በህዝቦች መካከል ያለውን የባህልና የአኗኗር ሁኔታ አጠናክሯል" ይላሉ ።

በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያላቸው ግንኙነት እንዲጎለብትና በሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር አሰፋ ገለፃ በአንድ አገር  ለዘመናት የማይተዋወቁ ህዝቦች በፌዴራል ስርዓቱ ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መጥቷል ።

የህዝቦች የማንነትና የብዝሀነት መገለጫ የሆኑ ባህሎችና ቋንቋዎች እውቅና ማግኘታቸው በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማምጣት የጎላ ሚና መጫወቱን የገለጹት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስነ- ዜጋና ስነ -ምግባር መምህርት ብርነሽ አፅብሃ ናቸው፡፡

"እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች  ባህሎቻችንን ለአገራዊ እድገት በሚጠቅም መልኩ ማጎልበት ይኖርብናል " ባይ ናቸው ።

አገራችን እየተከተለችው ያለውን የፌዴራሊዝም ስርዓት ህዝቦች ራሳቸው በራሳቸው ከማስተዳደር አልፈው ማንነታቸውና ባህላቸው እንዲከበር ማስቻሉንም ምሁራኖቹ አብራርተዋል ።

በመቐለ ዩኒቨርስቲ የህግና ስነ-መንግስት ኮሌጅ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር በላይ አብርሃ እንደገለፁት  ለብዙ ዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የነበረው ራስን በራስ የማስተዳደርና በቋንቋ የመናገር መብት ጥያቄ የመለሰው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ነው ።

ከዚህ በፊት የነበረው አሃዳዊ ስርዓት ያልመለሳቸው በቋንቋ የመጠቀምና የማንነት መገለጫ የሆኑት ባህልና ወግ የማጎልበት ጥያቄዎች የተመለሰው በዚሁ ስርዓት ነው ሲሉ አስምረውበታል ።

መምህር ገብሩ ገብረህይወት የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው “ ብዝሃነትን በምታስተናግድ አገር   ፌዴራሊዝም እጅግ ተመራጭ ስርዓት ነው “ ብለዋል ።

በተለያዩ  አካባቢዎች  የሚታዩ አንዳንድ ግጭቶች ከፌዴራሊዝምና ከአከላለል ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰቱ ሳይሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የፈጠሩዋቸው እንደሆኑ መምህሩ ያምናሉ።

በደርግ ጊዜና በንጉሱ ስርዓት በየደረጃው ይመደቡ የነበሩ አስተዳዳሪዎች ከማእከል ይላኩ እንደነበርና ይህም የህዝቡን ባህልና ቋንቋ  ስለማያውቁ በአግባቡ ለማስተዳደር ሳይችሉ መቆየታቸውን የገለፁት ደግሞ መምህር ብርሃነ ግደይ ይባላሉ ።

የህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሳይመስ ለዘመናት መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ መምህር ብርሃነ ግደይ  የተባሉ ናቸው።

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በማረጋገጥ ፣ በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም  እንዲሰፍንና ዲሞክራሲ እንዲጎለብት ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተጫወተው ሚና መተኪያ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።

የፌዴራል ስርዓቱ የአገራችን ህዝቦች አካባቢያቸውን የማልማትና የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑንም መምህር ብርሃነ ይናገራሉ ።

የፌዴራሊዝም አወቃቀሩ ጎሳን መሰረት ያደረገ በመሆኑ አገሪቷ ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጋትና የህዝቡ አንድነት እየተዳከመ ነው የሚሉት ወገኖች የፌዴራል ፅንሰ ሃሳብ ካለማወቅና የተገኙት ለውጦች ለመቀበል ባለመፈለግ  ምክንያት የሚደረድሩ ሃይሎች  ናቸው ብዋል።

ካለው ነባራዊ ሁኔታና ህዝቡ ካገኛቸው መብቶች አንፃር አገራችን ዳግም ወደ አሃዳዊ ስርዓት የምትመለስበት ምክንያት አይኖርም ሲሉም አክለውበታል ።

መንግስት የፌዴራሊዝም ስርዓት አስፈላጊነትና ያስገኘው ጠቀሜታ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል የተፈለገውን ያህል አለመሰራቱም ምሁራኑ እንደ ክፍተት ያነሱት ነጥብ ነው ።

ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁ አሁን እየተሰራ ካለው በላይ ሊሰራ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ሃሳቦች ሰንዝረዋል ።

አልፎ አልፎ በተለያዩ ቦታዎች በሃላፊነት የሚመደቡ ሰዎች በብቃት ሳይሆን የአካባቢ ተወላጅ እየተፈለገና ትምህርትና ብቃት መሰረት ያላደረገ መሆኑ እንዲሁም ጥፋት ፈፅመዋል የሚባሉ ግለሰቦች ለማስተማሪያነት የሚሆን ቅጣት ሳያገኙ ደመወዝና ሃላፊነት ጨምሮ ወደ ሌላ ቦታ መቀየር ስለሚታይ ለስርዓቱ አደጋ ነው ብለዋል።

ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግስት በቅርቡ ቁርጠኛ አቋም መያዙ ለዲሞክራሲ መጎልበትና ለስርዓቱ መጠናከር ወሳኝ ነው ያሉት ምሁራኑ እርምጃው ህዝብና መንግስት በሚፈልጉት መሰረት ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል ።

የህዝቡን ግንዛቤ ለማዳበርም የተለያዩ መድረኮች ሊፈጠሩ ይገባል የሚል አስተሳሰብ አላቸው።

በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ መድረኮች ስለ ዲሞክራሲና የማንነት አስፈላጊት እንዲሁም በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ለዘላቂ ልማት ያለው ጠቀሜታ ለማስረዳት ሰፊ ስራ መስራት ያስፈልጋል  ሲሉም ምሁራኑ አስረድተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን