አርዕስተ ዜና

የሁልጊዜም ተግባራችን ሊሆን የሚገባው መቻቻልና ደግነት

13 Jun 2017
4444 times

ሚስባህ አወል-ኢዜአ

በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ በአንዱ ጥግ ላይ ተቀምጠው የሃይማኖት ትምህርት ሲያስተምሩ ከ40 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡

ሀጂ ሰኢድ ሁሴን፡፡ ቀይ ቀጭን ናቸው፡፡ በትንሹ የፊት ገጽታቸው ላይ በአግባቡ ተከርክሞ የሚታየው ነጩ ጺማቸው ግርማ ሞገስ ሰጥቷቸዋል፡፡

አርባ አመት ሙሉ በታላቁ አንዋር መስጊድ በአንዲት የተለመደች ጥግ ላይ ተቀምጦ በርካቶችን የዕውቀት ባለቤት ማድረግ መቻል አስቡት ቀላል እንዳልሆነ፡፡

የአስር ሰኣቱ አስር ሰላት እንዳበቃ አገኘሁዋቸውና የነሱ ደረሶች /የቆሎ ተማሪዎች/ አስኪመጡ ድረስ ስለረመዳን ወር አንድ ሁለት ጥያቄዎችን አንስቼ አወጋን፡፡

ሀጂ ሰኢድ ረመዳን የጾም ወር ብቻ አይደለም ወሩ በሁሉም ዓለማዊ ነገሮች ቁጥብነት የሚታይበት በተቻለ አቅም ከማንኛውም ችግር ጥል መታገስን ያስቀደመ ሰላም የሚወርድበትና ሰዎች ካላቸው ነገር ሁሉ የሚቸሩበት ወቅት መሆኑን ነገሩኝ፡፡

በረመዳን ብቻ የሚገኙ በሌላ ጊዜያት የማይታሰቡ እንደ ቴምር ያሉ ምግቦች ለጻሚው የሚሰጡትን ጥቅም ጠቆም አደረጉኝ ቴምር ተክል ነው፡፡ ቴምር ሆድ በማለስለ ከምግብነት ያለፈ መድሀኒትነት እንዳለው በሀይማኖቱ መጸሀፍት ይገለጻል፡፡

የጾመ ሰው መጀመሪያ ጾሙን አንዲፈታ የሚመከረው በቴምር ነው ለዚህም ነው ከተማው ውስጥ የቴምር ምርት በረመዳን ወር በስፋት የሚታየው፡፡

ሌላው ማፍጠሪያ /ጾም መፈቻ / የገብስ ወይም የአጃ ሾርባ ነው፡፡ ይህም በጾም የዋለ ሰውነትን የሚያፍታታና በቀላሉ ሰውነታችን ሊቀበለው የሚችለው ስለሆነም ነው ይላሉ ሀጂ ሰኢድ፡፡

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎችም ሆነ በዓረቡ ዓለምም ከነዚህ ምግቦች በተጨማሪ የተለያዩ ጣፋጭ ብስኩቶችና ጥብሳ ጥብሶች ይቀርባሉ፡፡

የጾም ዋና አላማ ሰውነትን በምግብ ቆጥቦ የረሀብ ስሜት መፍጠር ነው የረሀብ ስሜት ምን እንደሆነ ሁሉም ማወቅ ስላለበት ይህ በችግር በእጦት የሚራቡ ወገኖች ምን ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል የሰው ልጅ እንዲገነዘብ  ከፈጣሪ የታዘዘ ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች ቀን ተጹሞ ለሊቱን በሙሉ እየተበላ የሚታደር ይመስላቸዋል አሉ ሀጂ ሰኢድ ሳቅ እያሉ ሳቅ ሲሉ የጥርሳቸው ንጻት በዚህ እድሜ ላይ ያስገርማል ተጨማሪ ውበት ያጎናጽፋቸዋል፡፡

ግን አይደለም አሉ አንድ ታሪክ አለ አሉ አሁንም እንደማስታወስ ጺማቸውን እያፍተለተሉ አንድ በጣም የተራበ ገበሬ ነው ለረሃቡ ማስታገሻ በሬውን ያርድና አንድ ከጥሱም ከቅቅሉም ከቀማመሰ በሁዋላ ያለው፡፡ “አልጠብ መስሎኝ በሬዬን አረድኩ” ያለው አባባል ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በማለት የሚያምረውን ሳቃቸውን ደገሙኝ፡፡

ሌላው በዚህ ወር የሚፈለገው ሰላም ነው “ቀኝህን ቢመታህ ግራህን ስጠው” የሚባለው ቅኔያዊ አባባል በዚህ ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው ታጋሽሁን ለማለት ነው አልፎ የሚመጣን እንኩዋን በትእግስት እለፈው እንደማለት ነው፡፡

በስራ አጋጣሚ ሊከሰቱ የሚችሉ ጥሎችን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ትእግስት ሊኖር ያስፈልጋል አልያ ጾሙ ይጠፋል ለዚሀ ነው ወሩ የሰላም ወር እንደሆነ የሚነገረው አሉኝ፡፡

በተለይ ማታ የአፍጥር/የፍቺ / ሰዓት ሲሆን የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ጎረቤቶቻችን መጥተው ያቺን ጣፋጭ ቴምርና ሾርባ በመቃመስ የምናሳልፋት ጊዜ የአብሮነታችንን የምናስታውስባት ወቅት በመሆኗ መቼም ቢሆን ከአእምሮ አትጠፋም፡፡ 

በረመዳን ወር ከጾሙ ጋር አብሮ የሚከወን ሌላ ተግባር አለ ወይ ስል ጠየቅኩዋቸው፡፡

አዎ ረመዳን ማለት እኮ የደግነት ዋናው ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወር ከምንም ነገር በላይ መስጠት መሰደቅ/መመጽወት/ የሚበዛበት ወቅት ከመሆኑም ባሻገር ልክ እንደ ጾሙ ግዴታ የሆኑት የዘካ /የመስጠት/ እና የሀጅ ማድረግ ወቅቶችም የተካተቱበት ወቅት ነው ሲሉ ገለጹልኝ፡፡

መስጠት ሲባል እስከምን ድረስ እንደሆነ ታውቃለህ? አሉኝ ሀጂ ሰኢድ የሌለው ዘካ /ምጽዋት/ተቀብሎ ከተሰጠው ምጽዋት ላይ ቀንሶ ከበታቹ ላሉት ሲሰጥ እንደማለት በመሆኑ ሰላም ፍቅርና ደግነት የሁልጊዜ ተግባራችን መሆን ይኖርበታል እንዳሉኝ ተማሪዎቻቸው መጡ እና ተሰነባበትን ከናንተም ጋር !! እንዲሁ!!

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን