አርዕስተ ዜና

የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፌዴሬሽን ምስረታ በ'የዓለም ውሃ ቀን' ዋዜማ

5106 times

አየለ ያረጋል/ኢዜአ

 የኢትዮጵያ ከተሞች በዓለም ውሃ ቀን ዋዜማ (ትናንት) በመሰረቱት 'የኢትዮጵያ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፌዴሬሽን' ለሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ለሆነው የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዘርፍ መሻሻል ተስፋ ይዘው መጥተዋል።

ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም የ'ዓለም የውሃ ቀን' ነው። ውሃ ለሕይወታዊያን ፍጥረታት ስሪት ትልቁ ግብዓት ብቻ አይደለም፤ ለህልውናቸው ብርቅዬ ስጦታ ጭምር እንጂ፤ በተለይ ለሰው ልጆች (70 በመቶ የውሃ ስሪቶች) ለመጠጣችን፣ ለውበታችን፣ ለጤናችን፣ ለተዝናኖታችን ዋስትና ነው። የምድራችን የውሃ ሀብት ክምችት የተትረፈረፈ ቢሆንም አብዛኛው ለመጠጥነት የማይውልና የብክለት ሰለባ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ፣ የአካባቢ ብክለት፣ በከተሞችና ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የሕዝብ ብዛት በሰው ልጆች ውድ ስጦታ 'ውሃ ሀብት' ላይ ትልቅ ስጋት መደቀኑ አልቀረም። እናም የቅርብ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ ቢሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ይጠማሉ።

የ'ውሀ ማማ' በምትባለው የምድረ ቀደምቷ አገር ኢትዮጵያም የንጹህ መጠጥ ውሃ ነፍስ ወከፍ ድርሻቸው ከሚፈለገው በታች የሆነባቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። በኢትዮጵያ 30 በመቶ ህዝብ ለንፁህ መጠጥ ውሃ፣ 70 በመቶ ደግሞ ለፍሳሽ አገልግሎት ተደራሽ አይደለም። ከገጠሩ ይልቅ የተሻለ ንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ባለባቸው ከተሞች አካባቢ እንኳን የውሃ አቅርቦት ሰፊ የሕዝብ ቅሬታ ምንጭና የማኅበራዊ ቀውስ መንስኤ ሆኗል። እናም አብዛኛዎቹ የአገሪቷ ከተሞች የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የጥራትና የተደራሽነት ማነቆ ተጋርጦባቸዋል። አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም 'ለችግሩ መፍትሔነት ማኅበር መስርተን እንስራ' በሚል በትናንትናው ዕለት በክልሎች የሚገኙ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ማኅበራት የተውጣጡ 55 ከተሞች 'የኢትዮጵያ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፌዴሬሽን' የተሰኘ ማኅበር መስርተዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አባል ከተሞችም ለሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ለሆነው የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎትን "ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ዘላቂና አስተማማኝ አገልግሎት ለመዘርጋት ያግዘናል" የሚል ተስፋ ጥለውበታል።

በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመስኖ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ገርባ ''የከተሞች ህዝብ ጨምሯል፣ ኢንዱስትሪ ተስፋፍቷል፣ ይህም የኅብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ፍላጎቱ አንሮታል፤ ከአቅርቦቱ ጋር አልተጣጣመም። እናም የውሃ ሀብትን መለየት፣ ማልማትና መንከባከብ የማይቆም ቀጣይ ስራ ነው'' ይላሉ።

ፌዴሬሽን መመስረቱ ሁሉንም ነገር ባይሰራም በዘርፉ ወደሚፈለገው ደረጃ ለመድረስ ከተናጠል ይልቅ በቡድን መስራቱ ይበልጣል፤ ለአብነትም ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት በተደራጀ መልኩ ለመስራት ያግዛል ባይ ናቸው። ተቋማቱ በተናጠል የውድድር ስሜት እንዲፈጥሩ የራሱን እገዛ እንደሚያደርግ ነው የሚገልጹት።

'ሌላውና ዋናው የፌዴሬሽኑ ዓላማ ግን ወዲህ ነው' ይላሉ። የፌዴሬሽኑ አንዱ ዓላማ አቅርቦትና ፍላጎቱ ላልተጣጣመው የውሃ አገልግሎት ዘርፍ ችግርን መፍትሄ ለማምጣት ትልቅ ካፒታል ይጠይቃል። መንግስት ለውሃ ልማት የሚያደርገው የኢንቨስትመንት ወጪ እያደገ ቢመጣም የህብረተሰቡን ፍላጎት መመለስ አልቻለም። ስለዚህም ከፌዴሬሽኑ መመስረቻ ዓላማዎች መካከል አንዱ "የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታን መፍጠር" የሚል ነው።

የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦች ቢቀመጡም "እስካሁን ግን በከተማ በውሃ ልማት ዘርፍ በጥናት፣ በተቋራጭና ዲዛይን ስራዎች ከነበረው አገልግሎት በዘለለ የውሃ ልማት አልምቶ ለህብረተሰቡ ወይም ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመሸጥ ስራ አልነበረውም" ይላሉ። ስለሆነም መንግስት በገጠርና በከተማ ብቻውን ያለውን ፍላጎት ማርካት ስላልቻለ የግሉን ዘርፍ እምቅ አቅም ለመጠቀም ማሳተፍና ማጎልበት ማስፈለጉን ያስረዳሉ። እናም በቀጣይ፤ የግሉ ዘርፍ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሮ ለአንድ መንደር አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል። በቀጥታ ለተጠቃሚው ባያከፋፍልም እንኳን የውሃ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለከተሞች የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ተቋማት የሚሸጥበት እድል ይኖራል። ከታሸገ ውሃ አቅርቦት በተጨማሪ በቧንቧና ሌሎች ግብዓት አቅርቦቶች አቅምን በማሳደግ በትላልቅ የውሃ ጋኖች ማቅረብ ይችላል። "መንግስትም አሰራሩን የህግ ማዕቀፍ በማውጣት፣ ልምድ በማምጣትና ቴክኖሎጂ በማሰባሰብ ያግዛል" ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የዱከም ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ እስኪያጅ አቶ አህመድ አብዱልጀሊል ማህበሩ" በጣም ብዙ ተስፋ አለው" ይላሉ። ትልቁ ተስፋ መንግስት በውሃ ዘርፍ አሰራሮች ላይ ፖሊሲ ሲቀርጽ ፌዴሬሽኑ ስለሚሳተፍ እንደየአካባቢውና ወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ የተጣጣሙ የፖሊሲ ሃሳቦችን ለማመንጨት እድል ይፈጥራል። በውሃ ሀብት ላይ ከተመሰረቱ የተፋሰስ ባለስልጣኖች ጋር በቅንጅት ለመስራት አጋጣሚ ይፈጥራል። "የውሃ አጠቃቀምን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን፣ የውሃ ብክለትን እነዚህ ሁሉ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለመውሰድ የተመሰረተ ነው" ብለዋል።

በትግራይ ክልል የአክሱም ከተማ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሥራ እሰኪያጅ አቶ መስፍን ብሩ ፌዴሬሽኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ የሚሰሩትን በጥራትና በአቅርቦት በተለይ አሁን ባለው በቴክኖሎጂ በተደራጀ አኳሃን ያለባቸውን ችግር ለመፍታት፣ በግላቸው የሚሰሩትን የተደራጀ አቅም ፈጥሮ ለማከናወን፣ ውሃ አገልግሎቶችም እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ።

ከሃረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የተወከሉት አቶ ቡሽራ መሃመድ ፌዴሬሽኑን ለመመስረት ከ10 ዓመታት በፊት መወሰኑን ያስታውሳሉ። በፎረም ደረጃ ቆይቶ ከረጅም ጊዜ በኋላ ዘንድሮ መመስረቱን ይበል አሰኝቷቸዋል። ፌዴሬሽኑም ለተቋማቱ የአገልግሎት ልህቀት ማዕከልነት፣ አገልግሎታቸው እንዲዘምንና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ፣ የተቀላጠፈና ደንበኛን የሚያረካ ለማድረግ ያስችላል የሚል ተስፋ አላቸው። "የውሃ ዘርፍ ለመልካም አስተዳደር፣ ለማህበራዊ ቀውሶች፣ ለጤና፣ ለልማት መሰረት ነው" የሚሉት አቶ ቡሽራ፤ ለዕለታዊ ቁልፍ ሚና ለሚጫወተው ውሃ ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ለመገኘት የተበጣጠሰውን አሰራር በቅንጅት ለመምራት፣ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋት ሚናው የጎላ ነው።

በአዲስ ለተመሰረተው ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት የመቀሌ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጊደና አበበ "የፌዴሬሽኑ መመስረት አብይ መነሻ ጉዳይ በህዝባችን ላይ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተለይ ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የጥራት፣ የግልጽነትና የተነሳሽነት ችግር ያለበት በመሆኑ ነው። ይህን አገልግሎት ግልጽና ፈጣን ከማድረግ አኳያ ጥረቶች አሉ። ስለሆነም አቅም ለማደራጀትና ተግባር ላይ ለማዋል ፌዴሬሽኑ ይረዳል" ብለዋል። ውሃ ከምንጩ ጀምሮ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ ቴክኒካዊ፣ መልካም አስተዳደራዊና ህጋዊ ችግሮች እንደሚያጋጥሙት ያብራራሉ። በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውም የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማውጣት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ይገልጻሉ። በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለው ችግር በአጭር ጊዜ መፈታት እንዳለበት ያምናሉ።

መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ፣ አቅምን ማጠናከርና መደገፍ፣ ከህግም አኳያ የተሻለ ማዕቀፍ እንዲኖር በርግጠኝነት የተሻለ ስራ እንዲሰራ እንደሚያግዝ አብራርተዋል። ተቋማቱ ተናበው በመስራትም የወጪ ብክነትን ለመቀነስ እገዛ እንደሚያደርግ ነው አጽንኦት የሰጡት።

የዓለም የውሃ ቀን 'ተፈጥሮ ለውሃ' ወይም 'ተፈጥሮን በመንከባከብ የውሃ ተግዳሮትን መፍታት' በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ተከብሯ። ሚኒስትር ዴኤታው ከበደ ገርባ የውሃ ቀን በተለያዩ ውይይቶች ሲከበር ተፈጥሮን መንከባከብ፣ ውሃን በቁጠባ በመጠቀም ከብክነት የመከላከልና የመጠበቅ ስራዎች በስፋት መሰራት እንዳለባቸው "ግንዛቤ በመፍጠር ነው" ብለዋል።

Last modified on Friday, 23 March 2018 00:35
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን