"ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ"

04 Jun 2017
4438 times

መንበረ ገበየሁ (ኢዜአ) 

በቀን አምስቴና ከዚያ በላይ ለሬዲዮ ጣቢያ ደውሎ ሄሎ የማለት ልምዱን ያዳበረው ገና በልጅነት እድሜው በትውልድ መንደሩ አለታ ወንዶ ነው፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ደውሎ ሃሳቡን የሚያጋራው ወጣት አብዝቶ ግን ስለ ትራፊክ ጉዳይ ያወራል፡፡

ከዛሬ ሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት በደቡብ ድምጽ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 100.9 ስለማውቀው ወጣት ነው የማወራችሁ፡፡

ትናንት ቢሆን የሚለውን ሃሳቡን የሚያጋራን ይሄው ወጣት ዛሬ ህይወቱን የሚመራበት ስራው ሆኗል የትራፊክ ጉዳይ፡፡

ኑሮዬ ብሎ ከከተመባት ሃዋሳ በትራፊክ ማስታወቂያ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ መደወሉን አላቆመም ። የአለታ ወንዶው ነኝ ከሃዋሳ ብሎ የሚጀምረው ሃሳቡ ማጠቃለያ "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ" የሚለው መልእክቱ ነው፡፡

አደራጅ ዘርይሁን ይባላል ። ተወልዶ ባደገባት አለታ ወንዶ ከ2001 ዓም ጀምሮ በትራፊክ ላይ የሚሰሩ ክበባትን በመመስረት ወደ ሃዋሳ አስፋፍቶታል ።

49 የሚሆኑ ጓደኞቹ ዓላማውን ተጋርተው በትምህርት ቤቶች፣ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አደባባዮችና በተለያዩ ስፍራዎች በትራፊክ ጉዳይ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡

በባለ ሁለት እግር ተሸከርካሪው እየተንቀሳቀሰም መፈክሮቹን ያሰማል "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ ! ፍጥነት እድሜን እንጂ ኪሎ ሜትርን አይቀንስም ! " በቅስቀሳ ወቅት የሚጠቀምበት መለያው ነው፡፡

በቅርቡ ይደውልበት የነበረው ሬዲዮ ጣቢያ የምስረታ በዓሉን ሲያከብር እሱና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በሬዲዮ ጣቢያው ላይ የሚሳተፉ የዘወትር አድማጮች እንዲታደሙ አድርጓል ።

እኔና ጓደኖቼም ከመስራች ጋዘጤኞች ስም ዝርዝር ውስጥ ነበርንና ተሰባስበናል ፡፡ የሬዲዮ ጣቢያውን የ12 ዓመታት ጉዞ የሚያሳይ ጽሁፍ ቀርቦ ለውይይት መድረኩ ክፍት ሲሆን መድረኩን ይመሩ የነበሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መለሰ አለሙ እድል ሰጡ፡፡

እድሉ እጁን ላነሳ ሁሉ የተሰጠ አልነበረም በዘወትር አድማጮች፣በተባባሪ አዘጋጆች፣ በመስራች ጋዜጠኞችና በሌሎችም የተከፋፈለና አጭር ነው፡፡

ይሄው ሁሌም ደውሎ ስለትራፊክ ጉዳይ የሚያወራው ወጣት ከጥቂቶቹ ተናጋሪዎች አንዱ ሆኖ ተከታዮቹ የሚጋሩትን የትራፊክ ጉዳይ አንስቷል፡፡

ቤተሰቦቻቸውን፣ጓደኞቻቸውና የሚያውቋቸውን በትራፊክ አደጋ ያጡ ሁሉ በማስታወስ ሬዲዮ ጣቢያውና ጋዜጠኞቹ   በትራፊክ ጉዳይ ላይ የበለጠ መሰራት እንዳለባቸው  ለክልሉ መንግስት ጭምር አደራ ብሏል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ድርሻ ስላለቸው  የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያዳብሩ ፕሮግራሞችን ሊቀርጹ እንደሚገባም ጭምር፡፡

ወጣት አደራጅ የተሰጠውን እድል ተጠቅሞ የትራፊክ አደጋው አሳሳቢነት እስከ ቤት እየገባ ነው ሲል የቅርብ ጊዜ ትዝታውንና በበጀት ዓመቱ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ክፍለ ከተማ መኖሪያ ቤት የገባው ተሸከርካሪ የአንዲት  ሴት ህይወት መቅጠፉን አንስቷል፡፡

በሃላባ ልዩ  ወረዳም መኖሪያ ቤት ድረስ ገብቶ ከስድስት በላይ ቤተሰቦችን ህይወት በአንድ ጊዜ ያጠፋበትን የዚሁ ዓመት ተመሳሳይ አደጋ አንስቶ ሲያበቃ "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ" የሚለውን መልዕክቱን አስተላልፎ ንግግሩን ቋጭቷል፡፡

በዚህ መልዕክቱ በመገናኛ ብዙሃን የሚያውቁት የመድረኩ መሪና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በአካል ስላዩት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ስንጓዝ በግራ ስንሻገር ደግሞ በዜብራ የምትለው መልእክት ተገቢና በሃገር ደረጃ አስከፊ የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ቁልፍ ናት ብለዋል፡፡

ከክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው  በአሁኑ ወቅት አለማችንን ክፉኛ እያሳሰቧት ከሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች  ውስጥ የመንገድ ትራፊክ  አንዱ ሆኗል፡፡

ጥንቃቄ በማድረግ ልንከላከለው በምንችለው የትራፊክ አደጋ ሳቢያ ቤተሰብ እየተበተነ፣ብዙዎች ለአካል ጉዳት እየተዳረጉ፣ንብረት እየወደመና ሃገራትም ከድህነት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጥረት እየተጎተተ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በ2015 ባወጣው ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከ1ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎች በትራንፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ህይወታቸውን ሲያጡ ከ20 እስከ 50 ሚሊየን የሚደርሱት ደግሞ ለከባድና ቀላል የአደጋ ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

አደጋው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት በጣም የከፋ መሆኑን የገለጸው መረጃው 90 ከመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡

የትራፊክ አደጋ ከ15 እስከ 29 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶችን በመግደልም ቀዳሚ ከሆኑ 10 ችግሮች  አንዱ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ለሃገሪቱ ወሳኝ የሆኑ ወጣቶችን፣ የተማሩና አምራች የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመቅጠፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያደረሰ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መመዘኛና መለኪያ ሆኖ እየተሰራበት ባለው በ10ሺህ ተሸከርካሪዎች በሚደርሰው አደጋ ሞቱ ሲሰላ በ2008 በጀት ዓመት 61 ነጥብ 4 ከመቶ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይሄው ቁጥር ግን የመከላከሉን ስራ በከፍተኛ ሁኔታ በሰሩ ሃገራት ከ10 በታች ሲሆን በአፍሪካ እስከ 30 በመቶ ተመዝግቧል፡፡

ይህንን አሳሳቢ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ10 ዓመት የተግባር እቅድ የተዘጋጀ ሲሆን ሃገራችንም ከ2004 እስከ 2013 የሚዘልቅ የ10 ዓመት ስትራቴጅካዊ እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናት፡፡

በመጀመሪያው አምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኗም በ10ሺህ ተሸከርካሪ የሚደርሰውን አደጋ ወደ 27 ዝቅ ለማድረግ ብትንቀሳቀስም ቁጥሩ 61 ነጥብ 4 ከመቶ ላይ ነው ፡፡ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ  ዘመን  ወደ 27 በመቶ ዝቅ ማድረግ መታሰቡን መረጃው ያመላክታል ።

ሆኖም የ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ ሁለት ዓመታት ሪፖርት አዝማሚያ አስደንጋጭ በመሆኑ በተያዠው ዓመት ስራውን በንቅናቄ መምራት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

በመሆኑም መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን የመዘርጋት፣የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል፣ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የማገዝና ሌሎችን ተግባራትን እከናወነ ነው፡፡

በደቡብ ክልልም የመንገድ ትራፊክ አደጋ በክልሉ ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመከላከል በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም አደጋው ከመቀነስ ይልቅ ከፍ ማለቱን መረጃች ያሳያሉ፡፡

በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ስራ ሂደት ባለቤት አቶ መርከቡ ታደሰ እንደተናገሩ ከ2006 እስከ 2009 አጋማሽ በክልሉ የደረሰው የትራፊክ አደጋ የ1ሺ643 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡

አደጋውን በማድረስ  የጭነት ተሸከርካሪ 35 ነጥብ 1 በመቶውን ሲይዝ የህዝብ 22 ነጥብ 8፣ሞተር ብስክሌት ደግሞ 19 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ አለው፡፡

በእነዚህ ዓመታት በተመዘገበው ሞት ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት በአደጋው ጊዜ ተሸከርካሪ ያልተጠቀሙ እግረኞች ናቸው፡፡

በ2009 ግማሽ ዓመት ጉራጌ፣ሲዳማ፣ጋሞጎፋ፣ወላይታ ስልጤ፣ጌዲኦ፣ሃዲያ ዞኖችና ሃዋሳ ከተማ ደግሞ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባቸው የክልሉ አካባቢዎች ናቸው፡:

የአሽከርካሪው ስነ ባህሪይና ክህሎት ማነስ፣ የተሸከርካሪው ብቃት ማነስና የእግረኛው የመንገድ አጠቃቀም፣ ከመንገድ ጋር የተያያዙ የዲዛይንና ተገቢ ምልክት አለማድረግም በክልሉ ለተከሰቱ አደጋዎች ቀዳሚ መንስኤዎች መሆናቸውን አቶ መርከቡ ተናግረዋል፡፡

እንደ ክልል ችግሩን ለመቅረፍ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ሲለዩም በመንገድ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን የግንዛቤ እጥረት መቅረፍ ቀዳሚው ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም በገጠርና በከተማ አድረጃጀቶችን በመጠቀም፣ የአመራሩን ግንዛቤ በማሳደግ፣ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መታገዝና የሃይማኖት ተቋማት መደበኛ የስራቸው አካል እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት ነው፡፡

በተጨማሪም ለእግረኛ ተብለው የተገነቡ መንገዶችን ከተለያዩ ሸቀጦች መሸጫነት መከላከል ትኩረት ተሰጥቶበታል ብለዋል፡፡

የተሸከርካሪ ባለንብረቶችም የተሸከርካሪውን አካላዊና ቴክኒካዊ ደህንነት በመጠበቅ ተገቢውን መንጃ ፈቃድ ለያዙ አሽከርካሪዎች ብቻ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመስጠት አደጋውን የመቀነስ ሃላፊነታቸው እንዲወጡ በቅንጅት እየሰሩ ነው፡፡

በክልሉ ማዕከላዊ ዞኖች አካባቢ የሚዘወተረው የሞተር ብስክሌት እያደረሰ ያለው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ትርፍ በሚጭኑ፣ ያለሰሌዳና መንጃ ፈቃድ በሚያሽከርክሩና እድሜያቸው ለማሽከርከር ያልደረሱ ህጻናት ላይ ቁጥጥር በማድረግ አደጋውን የመቀነስ ስራው ተጀምራል፡፡

በዚህም ከ14ሺ በላይ ሞተር ሳይክሎችን ህጋዊ የማድረግና ትርፍ ጭኖ በሚንቀሳቀሱ ባለሁለት እግር ተሸከርካሪዎች ላይ ህብረተሰቡ ህግ አውጥቶ የመቅጣት እርምጃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በመንገድ ጠርዝ ግራና ቀኝ ሶስት ሜትር ክፍት በማድረግ በመንገድ ዳር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማራቅና በየትምህርት ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክበባትን ማጠናከር ትኩረት ከተሰጠባቸው ስራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በመንገድ ላይ የሚደረገውን የትራንስፖርት ቁጥጥር በአደጋ ቦታ፣ጊዜ፣መንስኤና ምክንያት ላይ ያተኮረ በማድረግ መስቀለኛ መንገዶች አደባባዮችና ለፍጥነት ምቹ የሆኑ መንገዶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ትኩረት ይደረግበታል፡፡

በንቅናቄውም ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር በመነጋገር በክልሉ ወላይታ፣ ጉራጌና ስልጤ ዞኖች ለአደጋ አስጊ የሆኑ ቦታዎች ተለይለው የማስተካከያ ስራ እየተሰራባቸው ነው፡፡

በቅርቡም የትራንስፖርት ስርዓቱን ሰላማዊና ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ጸድቋል፡፡

በዚህ ደንብ ላይ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት  በቢሮው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብርሃም ዳካ ናቸው፡፡

ባለሙያው እንዳሉት ደንቡ የትራንስፖርት ስርዓቱን ሰላማዊና ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ቢሆንም በህዝብ ንቅናቄ ችግሩን መፍታት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

ደንቡ በማንኛውም ትራፊክ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ ክልሎች የተለያዩ ደንቦችን ከመተግበራቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ነው፡፡

94 የጥፋት ዝርዝሮችንና የሚወሰደውን እርምጃ አካቶ የያዘው ደንቡ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የእግረኞችና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን የጥፋት ዝርዝሮችና የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያካተተ ነው፡፡

አሽከርካሪዎች ተደጋጋሚ የደንብ ጥሰት እንዳይፈጽሙ ለመከላከል፣ህገ ወጥነትን ለመቀነስና እግረኞች ለአደጋ መከሰት አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ የሚረዳ ደንብ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው አደጋውን ለመቀነስ መጋቢት 19 በተጀመረው ክልል አቀፍ የትራፊክ ንቅናቄ መድረክ አምስት ሚሊየን የሚደርሱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመድረስ የግንዛቤ ስራ ተሰርቷል፡፡

በዚህም ግንዛቤው ያደገ ህብረተሰብና አመራር መፍጠር፣ የሕግ ማስከበር  ክፍተቱንም ማረም የሚያስችል ግብ ተጥሎ በተሰሩ ስራዎች አመላካች ለውጦች ቢታዩም ውጤቱ በሃገር ደረጃ የሚገመገም ነው ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት ስርዓቱን መሰረታዊ ጉዳዮች ለማሳወቅ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እንደሚሰራና በጤና ኤክስቴንቴሽን ፕሮግራሙም ገዳይ ከሚባሉት በሽታዎች ተርታ በመሆኑ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታትና እስከ ያዝነው ዓመት አጋማሽ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ከደረሰው 1ሺ643 የሞት አደጋ 1ሺ ስምንቱ ተሸከርካሪ ያልተጠቀሙ እግረኞች መሆናቸውን ያሳያል፡፡

እናም "ሲጓዙ በግራ ሲሻገሩ በዜብራ" የሚለው የወጣቱ መፈክር የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት መስራት እንደሚያፈልግ አመላካች ነው፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን