አርዕስተ ዜና

ለጤና ቁጥጥር ሁሉም ዘብ ይቁም ‼

19 May 2017
4093 times

በወንድማገኝ ሲሳይ (ኢዜአ)

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ መድኃኒትን ለማምረት እስከ 10 ዓመት ድረስ የሚወስድ ጊዜና እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል።ዘርፉ ከጦር መሳርያ ቀጥሎ ቤ፤መቱ በአማካየ 380  ቢሊዮን   የአሜሪካን  ዶላር   የሚንቀሳቀስበት  ንግድ  ነው።

የምርመር  ሂደቱ  በጣም  አስቸጋሪ፣ውስብስብና ብዙ  ውጣ  ውረድ  የሚጠይቀው ይኸው ዘርፍ ታዲያ አሁን አሁን የህገወጥ መድኃኒት ንግድ ሰለባ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን  የመደኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደሚሉት የህገ ወጥ  መድኃኒት  ንግድ  መገለጫዎች ተብለው የተለዩት የጥራት፤ ደህንነትና ፈዋሽነት ደረጃቸውን  ባልጠበቁ  ጥሬ  ዕቃዎች የሚመረቱ  መሆኑንና የመድኃኒት  ይዘት  የሌላቸውን ንጥረ  ነገር  መጠቀምን ይጠቅሳሉ።

የመድኃኒት ይዘት  ቢኖራቸውም  የተፈለገውን  መጠን ያልያዙ ፣ደረጃውን  ያልጠበቀ  ማሸጊያ፤ የአገልግሎት  ማብቂያቸው የማይታወቅ  የጽህፈት  መሳሪያ እና  ቀለም መጠቀም” እንዲሁ ።

በህጋዊ  መንገድ  የማይመረቱ፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፣ እንዲከፋፈሉና እንዲከማቹ ያልተፈቀደላቸውና ህጋዊ ሰነድ  የሌላቸው ደግሞ  ሌላው የህገ ወጥ መድኃኒት ንግድ መገለጫ መሆናቸውን ነው ዳይሬክተሩ የሚያብራሩት።

ከ1997-2003 እ.ኤ.አ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በተጠና ጥናት መሰረት ከአፍሪካ ዘጠኝ፣ ከኤስያ 11፣ ከአውሮፓ አገራትና ከላቲን አሜሪካ ሰባት አገሮች ተመሳስለው የተመረቱ መድኃኒቶች መገኘታቸው ሪፖርት አድርጓል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም እስከ 2ሺህ 500 የሚደርሱ ሰዎች በናይጄሪያ ተመሳስለው በተሰሩ መድሃኒቶች ምክንያት ለሞት ተዳርገዋል።

በኢትዮጵያ በ2016 በተካሄደው ተመሳሳይ ጥናት ሁለት መድኃኒቶች ተመሳስለው መመረታቸውን ባለሥልጣኑ አረጋግጧል።

በ2008 ዓ.ም በባለሥልጣኑ ከተሰበሰቡ 501 ናሙናዎች ውስጥ 8 መድሃኒቶች  የተቀመጠውን መስፈርት ያላሟሉ ሆነው በመገኘታቸው  ከገበያ እንዲሰበሰብ ተደርጓል ባይ ናቸው። 

ከማታለያ መንገዶች መካከል  ጥራትና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ጥሬ ዕቃ ተጠቅሞ ማምረት፤የታወቀ አምራች ኩባንያ ስም፣ አድራሻና ሌሎች ምልክቶች መለጠፍና በስሙ መነገድ፣በህገ ወጥ መንገድ ተመርቶ  ሀገር ውስጥ የገባ ምርትን ከህጋዊ ምርት ጋር በመቀላቀል ህጋዊ ማስመሰል ዋንኞቹ ናቸው።

ለችግሩ መስፋፋት በመንሰዔነት የሚጠቀሱት ደግሞ በአቋሯጭ   የመበልፀግ አባዜ ፣የአቅርቦትና   ፍላጎት    አለመመጣጠን፣በቁጥጥሩ  ሂደት  ቀልጣፋ አገልግሎት   አለመስጠት፣ከህግ  አስፈፃሚ  አካላት ጋር   ተቀናጅቶ   አለመሥራትና ሌሎችም መሆናቸውን አቶ ገዛኸኝ ይናገራሉ።

የታዳጊ   ሀገሮች   የመድኃኒት   አቅርቦት   በውጭ  ሀገር   ተመርተው   በሚገቡ መድኃኒቶች    ላይ   የተመሰረተ   መሆኑ፣ በህገወጥ   የመድኃኒት  ንግድ  ላይ  የህብረተሰቡ ግንዛቤ   በሚፈለገው ደረጃ አለመሆንም ሌላው የችግሩ መንስዔ ነው።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ  ”ሀገሪቱን የመልካም አስተዳደርና የልማት ለውጦች ከሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ  ነው”።

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ በማቀጨጭና በማዳከም በውጭ ምንዛሪ ልናከናውናቸው የሚገቡ ልማቶች፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎቻችንን በማስተጓጎል፣አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳረፍ ረገድ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነም  ተረጋግጧል ይላሉ።

በኪራይ ሰብሳቢነት ጥቅም የሚያገኙ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም በህገ ወጥ መንገድ የሚያገኙትን ጥቅም ለማስፋፋት የሚያደርጉት እንቅሰቃሴ ትግሉን ውስብስብ እንዲሆን ማደረጉን ይገልጻሉ።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚሉት ከሆነ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ፣ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ለህብረሰቡ ጤናና ደህንነት አስጊ የሆኑ፣የምግብ፣የመድኃኒት፣የመዋቢያ ምርቶች እንዲሁም ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ምንም ዓይነት የጤና ደረጃ ሳያሟሉ፣ግብርና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ።

ህገ ወጦች እየተበራከቱና  ተጠቃሚ እየሆኑ መጥተዋል ያሉት ዳይሬክተሯ የህግ የበላይነትና አስተማማኝ ዴሞክራሲ የተረጋገጠባት ሀገር ለመገንባት የተጀመረውን ሂደት የሚያውክ ሁኔታም በተግባር እየታየ ነው ብለዋል።

ጤናማና ህጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዳይኖር ከማድረግ አንፃርም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ያነሳሉ።

ዘርፉ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳረፉም ባለፈ የፀረ ሰላም ኃይሎች እድሜ ማራዘሚያም እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ።

በመላ ሀገሪቱ በተደረገ ርብርብ ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ የሆነ መድኃኒት ተይዞ እንዲወገድ መደረጉን ያስታወቁት ደግሞ በባለስልጣኑ የፕሮጀክት ዝግጅትና ማስተባበሪያ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ልሳነወርቅ ዓለሙ ናቸው።

ባለሥልጣኑ የሶስተኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ግምገማ በቅርቡ በአዳማ ከተማ በካሄደበት ወቅት አስተባባሪው እንዳስታወቁት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ የሆነ መድኃኒት እንዲወገድ የተደረገው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ነው።

የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መደኃኒቶች የተያዙት በ17 በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻና በመደበኛ የቁጥጥር ስራዎች መሆኑን በመጥቀስ።

ባለስልጣኑ ከአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር በመተባበር በቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ ቃሊቲ፣ መተማና ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ድንገተኛ ፍተሻ ማድረጉን ለአብነት አንስተዋል።

የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ውጤታማነትን ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴም በ129 የጁስ ናሙናዎች ላይ በተካሄደው የላብራቶሪ ምርመራ 20ዎቹ መስፈርቱን ሳያማሉ በመቅረታቸው ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ተደርጓል።

ለድህረ ገበያ ጥናት የተሰበሰቡ 215 የማንጎ ጁሶች ናሙናዎች የጥራት ምርመራ የተሰራላቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 103 ናሙናዎች መስፈርቱን ሳያማሉ ቀርተዋል፡፡

ከ28 የጨቅላ ህጻናት ወተት ናሙናዎች ውስጥ 22ቱ መስፈርቱን ባለማሟሏታቸው፣ ከ94 የዘይት ናሙናዎች ውስጥ ደግሞ 19ኙ መስፈርቱን ሳያማሉ በመቅረታቸው እንዲወገዱ ተደርጓል።

ባለ 20 ሊትር 7 ሺህ 500 ጀሪካን ዘይት የአምራች ስምና አገር " ባች ቁጥር " የተመረተበት ጊዜና መጠቀሚያ ጊዜ እንዲሁም የምርቱ ይዘት ስለማይገልፅ ወደ መጣበት አገር እንዲመለስ ተደርጓል።

የጥራት መስፈርትን አሟልተው ያልተገኙ መድሀኒቶች እና የኮንዶም ምርቶች እንዳይመዘገቡ፣ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እና ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ የማድረግ ስራም ተከናውኗል።

ከ5 ሺህ 600 በላይ የሆነ የተለያየ መጠን ያላቸው አገልግሎት ዘመን አልፎባቸው እንደገና ሌብል ተደርገው እየተሸጡ የነበሩ ኮስሞቲክሶችም ተይዘዋል፡፡

በሻሻመኔ ከተማ ከሕብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሠረት  በ102 የጤና ድርጅቶች ላይ ድንገተኛ አስሳ በማካሄድ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው ህገ ወጥ ሥራ ሲስሩ የተገኙ 47 የመድሀኒት ችርቻሮ ድርጅቶችና የግል ጤና ክሊኒኮች ላይ ክስ በመመስረት የድርጅቶቹ ባለቤቶች ከ2 ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጥተዋል።

በባለሥልጣኑ የምግብ አምራቾች ኢንስፔክሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ ገረመው ጣሰው በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 127 ቶን የሚጠጋ ምግብ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተደረገ ሲሆን 836 ነጥብ 6 ቶን የሚሆን ምግብና የምግብ ግብዓቶች ደግሞ ወደ ሐገር እንዳይገባ ተደርጓል ይላሉ።

አቶ ገረመው እንዳሉት የሀገሪቱን ህዝብ ከሚያጠቁ በሽታዎች ውስጥ ከ92 በመቶ በላይ የሚሆኑ በሽታዎች የሚከሰቱት ከምንመገበው ምግብ፣ ከምንኖርበት አከባቢ ንፅህና ጉድለት መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።

በመላ ሀገሪቱ  የጤና ቁጥጥር ሰራዊት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ በባለሥልጣኑ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አምዴ ናችው።

ይህን እውን ለማድረግ የጤና ቁጥጥር ልማት ሰራዊት ማቀጣጠያ ሰነድና የመልካም አስተዳደር እቅድ ተዘጋጅቶ እንቅስቃሴ ውሰጥ ተገብቷል።

ይህም ህብረተሰቡን የቁጥጥሩ አካል ከማድረግ ባለፈ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትና ግብዓት ለሁሉም  ዜጎች ለማዳረስ ያስችላል ነው የሚሉት።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ አከባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማዘጋጀት ለወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ ለጤና ልማት ሰራዊት መሪዎች ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ፍትህና አመራር አካላት በህገ ወጥ ምግብ፣መድኃኒትና ጤና አገልግሎት እንዲሁም አደገኛ መድኃኒቶችና በትምባሆ ኮንቬንሽን ዙሪያ ስልጠና ተስጥቷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በመድኃኒቶች ፣ ጥራቱ ያልተጠበቀ አገልግሎት አስጣጥ እና ህገ-ወጥ ንግድ ላይ ውይይት በማካሄድ ሁሉም በዞኑና በወረዳው ውስጥ የጤና ቁጥጥር ሥራን ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ህብረተሰቡ በ8482 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማውን የማቅረቡ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው እስከ ሶስተኛው ሩብ ዓመት 18 ሺህ 763 ጥቆማዎች ለባለስልጣኑ ደርሰዋል።

የሞባይል ኢንተርኔት በመጠቀም ህብረተሰቡ የተመዘገቡና ያልተመዘገቡ መድሃኒቶችንና ጊዜያቸው ያለፈባቸውን በቀላሉ እንዲያውቅ የሚያስችል  የሙከራ ስራ እየተሰራ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ  ለህብረተሰቡ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የጤና ባለሙያዎች ምዝገባና  ፍቃድ ዳታ ቤዝ ዝርጋታ በአዲስ አበባ፣ ደቡብ፣  ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ድሬዳዋ እና ሐረሪ  ክልል የተጠናቀቀ  ሲሆን በሌሎች ክልሎች በቅርብ ቀናት የመዘርጋቱ ስራ እንደሚጀመር አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።

ህገ ወጥ የምግብና የመድሃኒት ንግድ ዝውውር፣ ጥራት የጎደላቸውና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶችን ከማምረትና ከማከፋፈል አንጻር ያሉ ችግሮችንም ለማስወገድ ባለስልጣኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ከስራ ኃላፊዎቹ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

ህገ ወጥ የመድኃኒት ንግድ ለመከላከል መወሰድ ካለበቸው እርምጃዎች ውስጥ  ህብረተሰቡ  በባለቤትነት ተቆጣጣሪ   እንዲሆን   ማድረግና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ግድ ይላል።

በመሆኑም የጤና ቁጥጥር ስራን በአንድ ተቋም ብቻ ማሳካት አዳገች ስለሚሆን  ሁሉም ለጤና ቁጥጥር ስራ ዘብ ይቁም ‼ ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን