አርዕስተ ዜና

አመልድ - ህዝባዊነቱን እንዳስመሰከረ የዘለቀው ተቋም

19 May 2017
4224 times

 ብሩህ ኮኮብ -ባህርዳር ኢዜአ

የአሁኑ የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት /አመልድ/  በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል ሲካሔድ በነበረው የትጥቅ ትግል ምክንያት በጦርነት ለችግር ተዳርጎ ለነበረው ህዝብ የእለት እርዳታ ለማድረስ  የዛሬ 32 ዓመት እንደተቋቋመ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ኗሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ተብሎ ይጠራ ነበር ።

የትጥቅ ትግሉ በድል ከተጠናቀቀ በኋላም  ድርጅቱ እንደገና ራሱን በማደራጀት የእለት እርዳታ ከማድረስ ጎን ለጎን በጦርነቱና በሌሎች ምክንያቶች የተጎዳውን የተፈጥሮ ሃብት ወደነበረበት ለመመለስ ትኩረቱን ወደ ምስራቅ አማራ በማድረግ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ መጀመሩን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አምላኩ አስረስ ይገልፃሉ።

ከዕለት እርዳታ እስከ መልሶ ማቋቋም፤ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ክልላዊ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባትም ጉልህ አሻራውን እያሳረፈ፤ ፋና ወጊ የልማት ድርጅት በመሆን ህዝባዊ አጋርነቱን  አጠናክሮ ቀጠለ።

የአመራር ስርዓቱን፤ ድርጅታዊ መዋቅሩን፤ የስራ መሳሪያዎቹንና የአሰራር ስርዓቱንም ዓለም አቀፋዊ፤ አህጉራዊና ክልላዊ ለውጦችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መስራት መጀመሩ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና አካባቢያዊ ልማት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዲመጣ አስችሎቷል።

በአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የጀመረው ስራም በመስኖ፤ በመጠጥ ውሃና ስነ-ንጽህና፤ በግብርናና በአደጋ ስጋት ቅነሳና በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ አስፋፍቶ መቀጠል መቻሉ ህዝባዊ የልማት ድርጅት መሆኑን  በተግባር ማስመስከር ችሏል።

ባለፉት ዓመታትም ድርጅቱ ካከናወናቸውና ካስመዘገባቸው የልማት ስኬቶች መካከል የደን ልማት ስራ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ባለፉት ዓመታት ባከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራም ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ የተጎዳና የተራቆተ መሬት በደን በመሸፈንና በመንከባከብ አገግሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ አድርጓል። ይህም ለክልሉ የደን ሽፋን የአራት ነጥብ ሁለት በመቶ ድርሻን እንዲያበረክት አስችሎታል።

በብዝሃ ህይወት እንክብካቤና ጥበቃ ስራም ከ1 ሺህ 700 በላይ አባል አርሶ አደሮችን በአሳታፊ የደን አስተዳደር ቡድኖች እንዲቋቋሙ በማድረግ ከ65 ሺህ 800 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የተፈጥሮ ደንን በመጠበቅ ከጥፋት እየታደገ ይገኛል።

በለሙ ተፋሰሶችም የአካባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች በንብ ማነብ፤ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፤ በወተት ልማት፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎች ስራዎች በመግባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።

የንጹህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረትም ባለፉት ዓመታት ድርጅቱ አምስት ሺህ የሚጠጉ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።

በዚህም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህም ለክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን የ12 ነጥብ 7 በመቶ  በማበርከት ለክልሉ ልማት የድርሻውን እንዲወጣ አስችሎታል።

አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በዘላቂነት እንዲላቀቅ ለማድረግ በጀመረው የአነስተኛ መስኖ ልማት ግንባታ ስራም ከ22ሺህ 600 በላይ ሄክታር ማልማት የሚችሉ 244 ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን ገንብቶ ወደልማት እንዲገቡ ማድረግ ችሏል።

ይህም በዘመናዊ መስኖ ልማት ግንባታ ዘርፍ ባደረገው አስተዋፅኦ የ27 በመቶ ክልላዊ ድርሻ እንዲይዝ አድርጎታል። በርካታ የክልሉ አርሶ አደሮችም በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በመስኖ አልምተው በሚያገኙት የሰብል ምርት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ተጨማሪ ጥሪት እንዲያፈሩ ዋስትና ሆኗቸዋል ይላሉ።

ድርጅቱ በመደበኛነት ከሚያከናውነው የልማት ስራ በተጨማሪ በ2008 ኤሊኒኖ አስከትሎት በነበረው የአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተውን አስከፊ ድርቅ ለመቋቋም በክልሉ በድርቁ ተጎጂ ለነበሩ ወገኖች እንደወትሮው ሁሉ የዕለት ዕርዳታን በማቅረብ ወገናዊነቱን አስመስክሯል።

ድርቁ ክፉኛ ባጠቃቸው 33 ወረዳዎች ኤሊኖ ያስከተለውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ከ43 ሺህ ኩንታል በላይ ተተኪ ዘር  በማቅረብም ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮች ድርቁ ካስከተለባቸው ችግር ፈጥነው በመውጣት ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል።

በክልሉ የሚታዩ የልማት ክፍተቶችን ዘወትር እየለየ በመግባትም ጥራትንና የህዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ሁለገብ የልማት ስራዎችን ድርጅቱ ያከናውናል። ይህም የክልሉን የልማት ተጠቃሚ ቤተሰቦች የምግብ ዋስትናና የአኗኗር ዘይቤያቸው እየተሻሻለና እየተቀየረ እንዲመጣ አድርጓል ይላሉ።

በስኬታማ የአመራር ብቃቱ፤ በሰራተኞቹ ታታሪነትና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ እያከናወናቸው በሚገኙ ውጤታማ የልማት ስራዎች በሀገር አቀፍና በአውሮፓ ድርጅቱ ከተለያዩ አቻ ተቋማት ጋር በተለያየ ጊዜ ተወዳድሮ በማሸነፍ የጥራት አዋርድ አሸናፊ በመሆን ተሸላሚ እስከ መሆን ደርሷል።

በቀጣይም ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር የተፈጠረውን ጠንካራ አጋርነትና ምቹ ሁኔታን በመጠቀም የክልሉን ህዝብ በዘላቂነት ከድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ ሁሉን አቀፍ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም ህዝባዊ ኃላፊነቱን እንደወትሮው ሁሉ በብቃት ለመወጣት ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል።

ከድርጅቱ ሰራተኞች መካከል ወይዘሮ መሰረት አለባቸው አንዷ ናቸው። ድርጅቱ ከውጭ ሀገር ጠቃሚ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን እያመጣ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ሰራተኛው የተሻለ አፈፃፀም በየጊዜው እያስመዘገበ እንዲመጣ አስችሎታል ይላሉ ።

“እኔም በድርጅቱ በተመደብኩበት የሙያ ዘርፍ ጠንክሬ በመንቀሳቀስ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ስራዎችን ግንባር ቀደም ሆኜ በመስራት የተጣለብኝን ኃላፊነት በአግባቡ እንድወጣ አስችሎኛል” ባይ ናቸው ።

ይህንን አስተሳሰብም ሌላኛው የድርጅቱ ሰራተኛ አቶ ድረስ ምህረቴ ይጋራሉ። ያለሰራተኛው ሙሉ ተሳትፎ ድርጅቱ ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም።ድርጅቱ የሚተገብራቸውን አዳዲስ አሰራሮች ሰራተኛው ፈጥኖ በመቀበል ወደተግባር በመቀየሩም ለውጤት አብቅቶታል ባይ ናቸው።

በቀጣይም ህዝቡን የልማቱ ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም የነቃ ተሳታፊ በመሆን ለክልሉ ልማትና ዕድገት መጠናከር ሁሌም ዝግጁ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

አርሶ አደር ብርሃኑ መኩሪያ በምስራቅ ጎጃም ዞን በማቻክል ወረዳ የላይ ዳሞት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በአካባቢያቸው “ቃሰተች” ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ላይ አመልድ ዘመናዊ መስኖ ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃቱ ባለፈው የበጋ ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ የዘመናዊ መስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።

በዓመት አንድ ጊዜ የክረምትን ዝናብ ብቻ ጠብቀው ከማልማት በመላቀቅም ያላቸውን አንድ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መስኖ ድንችና በቆሎ ዘርተው በማልማት ከ70 ኩንታል በላይ ተጨማሪ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሎአቸዋል።

“በዚህ ዓመት የጀመሩትን የመስኖ ልማት ስራም በመጭው ዓመት የበጋ ወራት ፈጥነው የሚደርሱና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎችን ለይተው እስከ ሁለት ጊዜ በማልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ማቀዳቸውን ነው አርሶ አደሩ  የሚያስረዱት።

“አመልድ በቀበሌያችን ገንብቶ ለአካባቢው ህብረተሰብ ያስረከበን የንፁህ መጠጥ ውሃ ከነቤተሰባችን ከውሃ ወለድ በሽታ እንድንጠበቅ አስችሎናል” የሚሉት ደግሞ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የላታ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ታለማ አቤ ናቸው።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ከመሆናችን በፊት ሰውና እንስሳት በጋራ ከሚጠቀሙበት ምንጭ ቀድተን ለመጠቀም ደርሶ መልስ አንድ ሰዓት ተኩል መጓዝ ግድ ይለን ነበር። ለመጠጥ ቀድተን የምንጠቀመው የምንጭ ውሃ ንፅህናው ያልተጠበቀ በመሆኑም ከነቤተሰባችን ለከፋ የጤና ዕክል ተዳርገን ቆይተናል ይላሉ።

አመልድ የንፁህ መጠጥ ውሃ በደጃቸው ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃቱም የቤተሰባቸው ጤንነት በተሟላ መልኩ እንዲጠበቅ አስችሎታል። ቀደም ሲል ውሃ ለመቅዳት ከአንድ ሰዓት ተኩል ያላነሰ ጊዜ ይወስድባቸው የነበረው አሁን ከአስር ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ቀድተው በመመለስ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው፤ ሌሎች ደግሞ የልማት ስራቸውን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ድርጅቱ ቀደም ሲል በደን ልማት፤ በመጠጥ ውሃና በዘመናዊ መስኖ ግንባታ፤ በግብርናና አደጋ ስጋት ቅነሳ፤ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ… እያከናወነ ያለውን የልማት ስራ በቀጣይም አጠናክሮ በመቀጠል የክልሉን ህዝብ በልማቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም እንደወትሮው ሁሉ ጠንክሮ ይሰራል የሚም እምነት አሳድሯል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን