አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

አፉርታማን በወፍ በረር

16 May 2017
2088 times

                                              ሚፍታህ አህመድ /ጅማ ኢዜአ/

ጥንታዊው የአባጅፋር ቤተመንግስት ወደሚገኝበት ጅሬን ስንጓዝ ታሪካዊው የአፉርታማ መስጊድን እናገኛለን፡፡ መስጊዱን ታሪካዊ የሚያደረገው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የእስልምና፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የመቻቻል አስተምህሮት ማዕከል ከመሆኑም በላይ የሩቅ ተጓዥ ነጋዴዎች በስፋት የሚያርፉበት፤ በጥንት ጊዜ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ መንደራ ተብሎ የሚጠራበት አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ጥንታዊና ህብራዊ  መስጊድ አፉርታማ በመባል ይታወቃል፡፡ አፉርታማ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጎሚውም አርባዎቹ እንደማለት ነው፡፡

 40ዎቹ እነማን ናቸው?

ከመስጊዱ አጠገብ ታሪክን የሚናገር  ጥንታዊ የመካነ-መቃብር ስፍራ ይገኛል፡፡ በስፍራውም ንጉስ አባቦቃ አሊይ፣ ንጉስ አባጉቡልና ንጉስ አባ ጅፋር፣ የአባ ጅፋር ቤተሰቦች ፣የአባጅፋር አገልጋዮች እንዲሁም ከሃረር፣ ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌና፣  ከተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች በሚከተሉት ሃይማኖት ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ላይ በመውደቁ የተነሳ የሰላም አየር ወደሚነፍስበት የአባጅፍር አገር አርባ  ኡለማዎች(የእስልምና ሃይማኖት ልሂቃን) ይሰደዳሉ፡፡

ኡለማዎችም ያገኙትን ሰላም በመጠቀም ኃይማኖታቸውን በተሰደዱበት አገር ጅማ ማስተማር፣  ማስፋፋትና ማሳደግ የቻሉ መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡

ስለአፉርታማ ስያሜ

ስለ አፉርታማ ስያሜ የሚቀራረቡ ግን የተለያዩ አስተያየቶች በአከባቢው እድሜ ጠገብ አዛውቶች ይነገራል፡፡ አርባዎች ኡለማዎች በህልፈታቸው ጊዜ ግበአተ መሬታቸው የሚፈጸመው በአንድ አከባቢ ሲሆን ቦታውም አፉርተማ መቃብር በመባል ይታወቃል፡፡ በመካነ መቃብሩ ስፍራ አጠገብ የሚገኘውን ታሪካዊው መስጊድ ደግሞ የአከባቢው ነዋሪዎች  አፉርተማ መስጊድ በማለት ይጠሩታል፡፡

በሂርማታ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አብዱልሰመድ የሱፍ የአፉርታማ መሰጊድ ስያሜ ንጉስ አባጅፋር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የእስልምና ሃይማኖት አዋቂዎችን በማሰባሰብ በጅሬን ባሰሩት መስጊድ ውስጥ በሳምንት አንድ ቀን  የጁመዓ ሶላት ሲሰገድ ከአርባ ሰው በታች እንዳይሆን በማሳብ ለኡለማዎቹ ሁሉን ነገር አሟልተውላቸው በመስጊዱ ውስጥ ሀይማኖታዊ ስርዓታቸውን እየፈጸሙ እንዲኖሩ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ የተሰጠ ስያሚ ነው ይላሉ፡፡

በጣሊያን ወረራ ጊዜ ብስክሌት በመጋለብ አብዛኛውን ጊዜዬን አሳልፍ ነበር ያሉት አቶ አባፊራ አባዋሪ በወቅቱ የነበሩትን ኡለማዎችን ያስታውሱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ የነበሩት ሰዎች የጅማ ንጉስ አባጅፋር ያደረጉላቸው እንክብካቤ እንዳስደሳታቸውና በደል የማይፈጽሙ ፍትህ አዋቂ እንደነበሩ ከእንግዳዎች አንደበት እሰማ ነበር ይላሉ፡፡ ኡለማዎቹ በስደት ሳይሆን በአባጅፋር ጥሪ የመጡ ናቸው ፡፡

ከሁለት ሜትር በላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አባጅፋር፣ የንግስና ካባቸው  ግርማ ሞገስ ያለው፣ የንግስና ክብር የተሰጣቸው፣  የንግስና አርማቸው ደማቅ፣  እንግዳ አክባሪ፣ ቃላቸው አስታሪቂ፣ እንደሆነ በብላቴና እድሜቸው በእንግድነት ከመጡ ኡለማዎች  ይሰሙ እንደነበር ይናገራሉ እድሜ ጠገቡ አዛውንት፡፡

በአሁኑ ሰአት የመስጊዱ አዛን አውጪ (ሙአዚን) ጀማል አባተማም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ አርባ ኡለማዎች በመስጊዱ ውስጥ በመሆን ቁርአን ይቀሩ ዱዓ(ጸሎት) ያደርሱ ስለነብር ነው አፉርታማ የተባለው ሲሉ የሌሎችን ሃሳብ ያጠናክሉ፡፡

አቶ ጀማል መከነ-መቃብሩና መስጊዱ ከውጭ አገር ጭምር በሚመጡ ሰዎች በመጎብኘት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡  የአፉርታማ መስጊድ ኮሚቴ አባላት መስጊዱንና የመካነመቃብር ስፍራውን የሚቆጣጠሩ መሆኑን ሙአዚን ጀማል እየነገሩኝ ባሉበት ሰዓት በርካታ ከብቶች ወደ መከነ-መቃብሩ ስፍራ ገብተው በቀብሩ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ተመልክቻለሁ፡፡ በመካነመቃብሩ  አጠገብ በሚገኘው ለምለም ሜዳ ላይ ቁጭ ብላው በቀዝቃዛ አየር እየተዝናኑ ቁልቁል ጅማ ከተማን በመመልከት ላይ የነበሩ ወጣቶች  ወደመካነ-መቃብሩ  ዘልቀው የገቡትን ከብቶች ሲያባርሩም ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ የአፉርታማ መስጊዲ አልፎ አልፎ የተተከሉ የቅንጭብ አጥር ሲኖረው መካነመቅብሩ ግን ያለምንም አጥር በሰማይ ጠቀስ ጽዶች ተከቦ ይገኛል፡፡

 

የመካነ-መቃብሩ ስፍራ ከአፉርታማ መስጊድ ኮሚቴ አባላት በተጨማሪም የአባጅፍር ቤተሰቦች እየተንከባከቡትና እየጠበቁት ይገኛሉ፡፡ ከአባጅፋር ቤተሰቦች አንዱ የሆኑት የጅማ አባቡና እግር ኳስ ክለብ መስራች አቶ አብዱልከሪም አባገሮ ሲሆኑ አፉርታማ በመባል የሚታወቁት ኡለማዎች ወደ ጅማ ለመሰደድ የመረጡት የተረጋጋ ሰላም የሰፈነበት፣ ንጉሱ ፍትህን የማያጓድሉ፣ በንጉሱ ግዛት ውስጥ በኃይማኖት፣ በዘር፣በሃብትና በመሳሰሉት ልዩነቶች የሰብአዊ መብቶች የማይጣሱበት መሆኑን በማወቃቸው ነው ይላሉ፡፡

ኡለማዎች  በጊዜው በነበሩ ነገስታት ይደርስባቸው የነበረውን የሀይማኖት ተጽዕኖ ምክንያት ከትውልድ  ቀያቸው ሰላም በማጣታቸው ምክንያት ወደ ጅማ ግዛት እንደተሰደዱ ይናገራሉ፡፡

በወቅቱም ለስደት የተዳረጉ ኡለማዎችም "ተብሎ ተብሎ ካልሆነ ነገሩ፣ ጅማ አባ ጅፋር ነው የሰው ልጅ አገሩ" በማለት መግጠማቸው ይነገራል፡፡

ንጉስ አባጅፋር ከተለያዩ አካባቢዎች በስደትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግዛታቸው የሚገቡ ዜጎችን ወንጀለኛ አለመሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ በተገቢው መንገድ ተቀብለው በሰላም እንዲኖሩ ሁኔታዎችን ያመቻቹላቸው እንደ ነበር አቶ አብድልከሪም ይገልጻሉ፡፡

አበጅፍር በግብጽ አሌክሳንድሪያ ዩኒቭርሲቲ አጠገብ ለኢትዮጵውያን ተማሪዎች እደዚሁም በሳወዲ አረቢያ ደግሞ ለሃጃጅ እንግዶች ማረፊያ እዲሆን በማሰብ ህንጻ ያሰሩ ሲሆን ሳወዲ አረቢያው የሚገኘው ህንጻ እስካሁን ድረሰ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር ከተቦ አብዲዮ በጅማ ዩኒቭርሲቲ ባሳተሙት የጥናት መጸሃፋቸው ላይ እንደገለጹት አሁን የአባጅፋር ቤተመንግስት የሚገኝበት የጅሬን አከባቢ የደቡብ ምዕራብ የእስልምና አስተምህሮት ማዕከል እንደነበር  ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይ በአጼ ዮሃንስ 4ኛ እና በአጼ ሚሊኒክ 2ኛ ዘመን ከወሎ አካባቢ የእስልምና ሊቃውንት በሚደርስባቸው በደል ምክንያት ወደ አባጅፋር ግዛት ይሰደዱ እንደነበር  በመጸሃፋቸው ላይ አመላክተዋል፡፡

አባ ጅፍር በግዛታቸው 60 የቅዱስ ቁርዓንና የአረብኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ማዕከላትን የሰሩ ሲሆን በስደት ወደ ግዛታቸው የመጡ በርካታ የእስልምና ሊቃውንት  ያስተምሩ እንደነበር በጥናት መጸሃፉ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የጅማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዊዳድ አባፊጣ  ጥንታዊ የጊቤ ግዛት አካባቢዎች የገዳ ስርዓትና የዋቄፈታ ኃይማኖትን ይከተሉ ነበር በሂደትም የእስልምና ኃይማኖት ከተጠናከረባቸው ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከይፋት፣ ከደዌይ፣ አካባቢ የእስልምና ኃይማኖት ወደ ጅማ ግዛት ሊስፋፍ በመቻሉ ምክንያት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሊያድግ እንደቻለ ያስረዳሉ፡፡

 በተለይ በ1830 ዓ.ም አካባቢ ከጎንድር የመጡት ሼህ አበዱልሃኪም በጎንደርና በጅማ የእስልምና ሀይማኖት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፈሮ ይገኛል ፡፡

ጅማ በ18ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ የሩቅ ተጓዝ ነጋዴዎች ማዕከል ነበረች፡፡ ነጋዴዎች ከጅማ ሂርማታ ገበያ እንደወርቅ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድ፣ ቡና፣ ብረት የመሳሰሉ ተፈላጊ ምርቶችን ያገኙ ስለነበር የውጭ አገር ነጋዴዎች ጭምር ወደ ሂርማታ ገበያ በስፋት ይመጡ ነብር፡፡

የአፉርታማ መስጊድ የተሰራውም በዚሁ ዘመን በአባጅፋር አባት በአባቦቃ 7ኛ የንግስና ጊዜ በ1862 ዓ.ም ነው፡፡ አፉርታማ የጥንታዊ ጅማ ማሳያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መጠበቅ ባለበት ልክ አለመጠበቁ የኛ ድክመት ነው ብለዋል፡፡

በመስጊዱ አጠገብ የሚገኘው ሰፊ ነፋሻማ ቦታ  በጅማ ዩኒቨርሲቲ አጠገብ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ በርካታ ተማሪዎች ለማንበቢያና ለመዝናኛ አገልግሎት እይተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች አካባቢውን ይጎበኙታል፡፡

የቱሪስት መደራሻው በጅማ ከተማ ውስጥ እንደመገኘቱ መሰረተ ልማት ችግር አይሆንበትም፡፡ የአካባቢ ነዋሪዎችን በተለይ ወጣቶችን በማስተባበር መዳረሻውን ማልማት ይቻላል፡፡

የጅማ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊም የቱሪስት መዳረሻውን አሁን ባለበት ደረጃ እንዲገኝ ያደረገነው ለማልማት ከባድ ሆኖ ሳይሆን ተዘናግተን ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም በአካባቢው ሀብት ብቻ መዳረሻውን ለማልማት እንሰራለን፡፡

በጅማ ዞንና ከተማ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው 78 የቱሪስት መዳረሻ ካርታ ሲዘጋጅ በዩኒቨርሲቲው አፍንጫ ስር የሚገኘውን የአፉርታማ መሰጊድና መካነ መቃብር ስፍራ ያለማካተቱ እና ያለመጠናቱ ለቅርሱ መረሳት ማሳያ አይሆንም ትላላችህ?

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን