አርዕስተ ዜና

ያልተገለጡ የታሪክ ምስክሮች

16 May 2017
4507 times

 መኳንንት ካሳ /አሶሳ ኢዜአ/

ጠና ያለ የእድሜ ስብስብ አላቸው ፡፡ ከስብስቦቹ መካከል  ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የተሻገሩም ይገኙበታል፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ከዘጠና እስከ ሰማኒያ አመት በላይ የሚሆን እድሜ አስቆጥረዋል፡፡ ስብስቦቹ ሸሯማ መልክ ያላቸው፤ ወፈር ባለ ወረቀት የተፃፉና ጫፋቸው የሳሳ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡

ደብዳቤዎቹ በወቅቱ የአሶሳና የተወሰኑ አጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎችን ሲያስተዳድሩ ለነበሩት ሼህ ሆጀሌ አልሃሰን የተፃፉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ደብዳቤዎች ውስጥ ዳግማዊ ምኒሊክ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅትና ከነገሱም በኋላ የፃፉዋቸው  ይገኙበታል፡፡ ልጅ እያሱ፣ እቴጌ መነን እና ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ የፃፏቸው የደብዳቤ መልእክቶችም ከስብስቡ መካከል ተጠቃሾች ናቸው ።

ደብዳቤዎቹ በሼህ ሆጀሌ ቤተሰቦች እጅ የሚገኙ ሲሆን ብዛታቸው 24 ነው፡፡ ከደብዳቤዎቹ በተጨማሪም ሼህ ሆጀሌ በወቅቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የነበሯቸው ይዞታዎችን የሚያሳዩ ካርታዎችም ይገኛሉ፡ 

አብዛኛዎቹ ደብዳቤዎች ሼህ ሆጀሌ ቀድመው በደብዳቤ ለላኩት መልእክት የተሰጡ ምላሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች በወቅቱ የአካባቢው ገዢዎች ከሌሎች የአካባቢ ገዢዎች ጋርና  ከማአከላዊው መንግስት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ምን እንደሚመስል ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በተጫማሪ በአካባቢው የነበረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችሉ የታሪክ ሰነዶችም ናቸው፡፡

ሼህ ሆጀሌ በአገራዊ ጉዳይ ያደረጉትን አስተዋጽኦም ያመላክታሉ፡፡ ከአፄ ኃይለ ስላሴ በ1923 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ‹‹ የባንኩ እዳ ላገራችን ክፉ ስም የሚያሰጥ በመሆኑ ትልቅ ጉዳት የሚያመጣ ስለሆነ የዘውዱን በዓል እንኳ ሳታይ የሰደድሁህ ነገሩ በጣም ስለከበደን ነው፡፡›› የሚል ሃሳብ ይገኝበታል፡፡ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ሼህ ሆጀሌ የላኩት 240 ወቄት ወርቅ እንደደረሳቸውና በቀጣይም ተጨማሪ ወርቅ እንዲልኩ በአደራ ጭምር የገለፁበት ነው፡፡

በዳግማዊ ምንሊክ ዘመነ መንግስት በሼህ ሆጀሌና ሌሎች አጎራባች የአካባቢው ገዢዎች መካከል በሚፈጠረው የግዛት ይገባኛል አለመስማመት የተፃፉ ደብዳቤዎችም የወቅቱን አካባቢያዊ ፖለቲካ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

በተለይ ከደጅአዝማች ጆቴ ቱሉ ጋር በተደጋጋሚ በቤጊ አካባቢ በተፈጠረ የግዛት ይገባኛል አለመግባባት ሌሎቹ በአካባቢው እንዳይደርሱ የተገለፀበትና በመጨረሻም ለሼህ ሆጀሌ መወሰኑን የሚገልፁ ደብዳቤዎች አሉ፡፡

ሌሎቹ ደብዳቤዎችም ሼህ ሆጀሌ ከማዕከላዊው መንግስትና ከሌሎች አገር ገዢዎች ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ግንዛቤ የሚሰጡ ናቸው፡፡

የአሶሳ ሙዚየምና የቤተ መጽሐፍት ማዕከል ከእነዚህ ደብዳቤዎች መካከል የሁለቱ ደብዳቤዎች ቅጂ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ከላይ ብዛታቸው የተገለፀው ደብዳቤዎች ዋናውን የያዙት የሼህ ሆጀሌ ቤተሰብ የሆኑ ግለሰብ ናቸው፡፡

ደብዳቤዎቹን በተመለከተ ባገኘሁት መረጃ ያነጋገርኳቸው አቶ አብዱራሂም መሃመድ እንደነገሩኝ ሼህ ሆጀሌ ቅድመ አያታቸው ናቸው፡፡ አቶ አብዱራሂም በአያታቸው በአሻፊ ሆጀሌ ቤት በማደጋቸው ደብዳቤዎቹን የማግኘት እድል እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡

ያሰባሰቡዋቸው ደብዳቤዎች 60 ይሞሉ እንደነበር በመግለፅ ደርግ ስልጣን ሲይዝ በወቅቱ የነበሩትን የሼህ ሆጀሌ ልጆች አስሮ ነበር፡፡ እሳቸውም ወደ ሱዳን አገር ኮብልለው ሲመለሱ አብዛኛዎቹ ደብዳቤዎች ጠፍተው እንደጠበቁዋቸው ተናግረዋል፡፡

ደብዳቤዎቹ ከሚናገሩት ዋናውና ትልቁ ነገር ሼህ ሆጀሌ በኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት የነበራቸውን ሚና ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሼህ ሆጀሌና በማዕከላዊው መንግስት መካከል ያለው ግንኙነት ቤተሰባዊ መልክ እንዳለው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ድንበርን በሚመለከት የሚፈጠሩ አለመግባበቶች እንዴት ሲፈቱ እንደነበር የሚያሳዩ እንደሆኑም አቶ አብዱራሂም ገልፀዋል፡፡

ተጨማሪ ደብዳቤዎች በሌሎች የቤተሰቡ አባላት እጅም ሊኖር እንደሚችል የገለፁት አቶ አብዱራሂም ሼህ ሆጀሌ በህይወት እያሉ በተለየ ሁኔታ የሚያቀርቡዋቸው ከነበሩ ልጆቻቸው  ዘንድ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎች ይኖራል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ከዚህ ቀደም በመንግስት በኩል ሼህ ሆጀሌ የተመለከቱ ቅርሶችን ለማሰባሰብና ለመጠበቅ የተወሰኑ ሙከራዎች ተደርገው እንደነበር በማስታወስ በአሁኑ ወቅት ግን የተሻለ ትኩረት መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

በመፍረስ ላይ የነበረው የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽ እድሳት የተደረገለት መሆኑን እንዲሁም ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መገልገያዎችን የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡

ደብዳቤዎቹን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የጠየቃቸው አካል ስለሌለ መኖሩ አይታወቅም  የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀው ፤ ደብዳቤዎቹም ሆኑ ሌሎች ቅርሶች የሼህ ሆጀሌ ቤተሰቦች ሃብት ብቻ ሳይሆኑ ከክልሉም ባለፈ የአገር ሃብቶች ናቸው ያሉት አቶ አብዱራሂም በቅርስ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ አሁንም የሚቀረው ነገር ስላለ ቅጂውን እንጂ ዋናዎቹን ደብዳቤዎች እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ቁጥጥርና ደረጃ ምደባ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፋንታሁን ደጀን በክልል ደረጃ እና በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የተመዘገቡ ቅርሶች በክልሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽ፣ የሼህ ሆጀሌ መካነ መቃብር፣ የመሃመድ ባንጃው ቤተ መንግስት፣ የጣሊያን ምሽግ እና በመተከል ዞን የሚገኘው ደቀመሃሪ ገዳም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ነገር ግን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከተደራጀ ወዲህ ቋሚ ቅርሶችን የመመዝገብና ችግራቸውን የመለየትና የማጥናት ስራ ተጀምሯል፡፡ ቅርሶቹ የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ጽዳት የተጠበቀ እንዲሆን፣ ይዞታ የማስከበር፣ ለህዝብ የማስተዋወቅ እና የመሳሰሉ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም አሁንም በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ እየተሰራ ባለው ስራ የሚቀሩ ጉዳዮች አሉት ባይ ናቸው ።

ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን በመመዝገብና ጥበቃ በማድረግ ረገድ ቆየት ያለ ልምድ መኖሩን የገለፁት አቶ ፋንታሁን አሶሳ አካባቢ በወለጋ ክፍለ ሃገር ስር በነበረበት ወቅት ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል፡፡ በወለጋ ሙዚየም የበርታና የጉሙዝ ብሔረሰቦችን ባህል የሚገልፁ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

ክልሉ ዘጠነኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ባሰናዳበት ወቅት የክልሉን አምስት ነባር ብሔረሰቦች የሚወክሉ ቅርሶችን አሰባስቦና አደራጅቶ በሙዚየም እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ የብሔረሰብ ምክር ቤቶች መቋቋማቸው የነባር ብሔረሰቦችን ባህል፣ ቋንቋና ታሪክን ለማልማት በሚደረገው እንቅስቃሴ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የክልሉን ነባር ብሔረሰቦችን ባህል የሚገልፁ ቅርሶች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በቅርብ ጊዜ እንዲካተቱ መደረጉንም ባለሙያው አቶ ፋንታሁን ደጀን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሼህ ሆጀሌና መሃመድ ባንጃውን የመሳሰሉ የቀደምት አስተዳዳሪዎች ሲገለገሉባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎች በግለሰቦች እጅ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለቋሚ ቅርሶች የሚደረገው ጥበቃና እንክብካቤ አናሳ መሆኑን እያየ በእጁ ያለውን ቅርስ ለመስጠት ፍቃደኛ ላይሆን ይችላል፤ ከሼህ ሆጀሌ የችሎት አዳራሽ እድሳት የተገኘው ልምድ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው ብለዋል፡፡

ቋሚ ቅርሱ ላይ በማተኮር ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ መንግስት ሲያደርግ ማህበረሱ ከዛ ጋር የተገናኙ ሌሎች ቅርሶችን ለመስጠት ፍቃደኛ እየሆነ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የሼህ ሆጀሌ የችሎት እድሳት ሲደረግለት ሼህ ሆጀሌ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መገልገያዎችን ቤተሰቦቻቸው አሰባስበው በአደራ መስጠታቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ደብዳቤዎቹ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች በሚፈልጉት ሁኔታ ተመቻችተው ባለመቀመጣቸው ተገቢ መረጃና እውቀት እንዳያገኙ አድርጓል፡፡

ደብዳቤዎቹ መታወቃቸውና መጠናታቸው ደግሞ የማህበረሰቡን ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቁ በመሆናቸው ጥቅሙ መልሶ የማህበረሰቡ መሆኑን የቅርስ ቁጥጥና ደረጃ ምደባ ባለሙያው አቶ ፋንታሁን ተናግረዋል፡፡

ደብዳቤዎቹን አሰባስቦ ለመያዝ ቢሮው እስከመጨረሻው ኃላፊነት ወስዶ መስራት ስለሚገባው ክፍተቱን በማረም በቀጣይ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት መስራት ይጠበቅበታል፡፡

በአብዛኛው የክልሉን ነባር ብሔረሰቦች የባህል መገለጫዎች የያዘው የአሶሳ ሙዚየምና ቤተ መፅሐፍት ማዕከል ከደብዳቤዎች መካከል የተወሰኑት ቅጂዎችን ይዟል፡፡ እነዚህ ቅጂዎች ከስፔን አገር የመጡ ባለሙያዎች በ1998 ዓ.ም ሙዚየሙን አደራጅተው ስራ ሲያስጀምሩ ገቢ የደረጉ   መሆናቸውን የሙዚየሙ አስጎብኚ የሆኑት አቶ ሱሌማን አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

ደብዳቤዎቹ በሙዚየሙ አለመግባታቸው ቅርስን የማሰባሰብ ስራ በሚገባ ባለመከናወኑ ነው የሚሉት አቶ ሱሌማን ከዚህ ቀደም ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ2003 ዓ.ም ራሱን ችሎ በቢሮ ደረጃ እስኪዋቀር ድረስ በተለያዩ ቢሮዎች ስር በመምሪያና በጽህፈት ቤት ደረጃ መቆየቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል ፡፡

ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት ከተፃፈው የአፄ ምኒሊክ ደብዳቤ አንስቶ አብዛኛዎቹ ደብዳቤዎች የተፃፉበት ጊዜ ከዘጠና ዓመት በፊት ነው፡፡ ደብዳቤዎቹ የተፃፉባቸው ወረቀቶች ወፍር የሚሉ ሲሆን እድሜያቸው የጠና በመሆኑ ወደ ጫፍ አካባቢ ሳሳ ያሉ ናቸው፡፡ ወረቀቶቹ ሽሯማ መልክም አላቸው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን