አርዕስተ ዜና

የካምቦሎጆ ድምቀትና ሁከት

15 May 2017
4365 times

ነፃነት አብርሃም (ኢዜአ)

በዓለማችን ላይ አዝናኝ ከሚባሉ ስፖርታዊ ክንውኖች መካከል አንዱ እግር ኳስ ነው። ከዚህም በላይ በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ለመዝናኛነትም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይኸው የስፖርት ዘርፍ በተለይም በምዕራባዊያን ዘንድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የእድገት ግስጋሴው ዘላቂ በሚባል ሁኔታ ላይ መሆኑን ሁላችንም እንረዳዋለን። ይህንንም ተከትሎ በአውሮፓም ሆነ በሌሎች ክፍለ-ዓለማት አስደናቂና እጅግ አዝናኝ የሆኑ የእግር ኳስ ጥበቦችን የሚያሳዩ ተጫዋቾችና ቡድኖችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውም ሌላው የምናስተውለው ጉዳይ ነው። ስፖርት ወዳዱ ኅብረተሰብም እነዚህን የሜዳ ላይ ክስተቶች ለመመልከት ከያለበት ተነስቶ አንድም በስታዲየም አልያም ደግሞ በቴሌቭዥን መስኮት ለመከታተል ሲዋትት ማየት ልማድ ሆኗል።

በተለይም በሁለት ተቀናቃኝ የስፖርት ቡድኖች መካከል የሚካሄደውን የ"ደርቢ" የእግር ኳስ ግጥሚያ የብዙኃኑን የስፖርት ተመልካች ቀልብ የሚስብ መሆኑንም ልብ እንላለን። እንዲህ ያሉ የደርቢ ጨዋታዎች ተመልካቾችን ከማዝናናነት በተረፈ ለእግር ኳስ እድገት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የብዙዎች ግምት ነው፡፡ በተለይም በእግር ኳስ ወዳዱ ማኅበረሰብ መካከል ባለው ተፈላጊነት የተነሳ በእያንዳንዱ የእግር ኳስ የውድድር ዘመን የሚጠበቅ የጨዋታ መርኃ ግብር መሆኑንም ልብ እንላለን። የደርቢ ጨዋታዎች ሲካሄዱም፤ ስታዲየሞች ጢም ብለው ሲሞሉ፣ ከፍተኛ የትኬት ሽያጭ ሲመዘገብ፣ በማልያ ሽያጭና በቴሌቭዥን የአየር ሰዓት ስርጭትም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ መሆናቸው ይታወቃል። 

በዓለማችን ላይ በተለይም እግር ኳስ በመደበኛነት በሚዘወተርባቸው አገሮች ታላላቅ ደርቢዋች የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ደርቢዎች መካከል ለምሳሌ ያክል በእንግሊዝ ሜርሲሳይድ ደርቢ ሊቨርፑል ከኤቨርተን፣ በሰሜን ለንደን ደርቢ አርሴናል ከቶትንሃም ማንሳት እንችላለን። በሌላ በኩል በማንችስተር ከተማ ክለቦች ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ፣ በጣሊያን ሚላን ደርቢ(ሳንሲሮ ደርቢ) ኤሲ ሚላን ከ ኢንተር ሚላን፣ በስፔን ማድሪሊያኖ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ፣ በአርጀንቲና ሱፐርክላሲኮ ደርቢ ቦካ ጁኒዬርስን ከሪቨር ፕሌት፣ ፣ በቱርክ ፌነርባቺ ከጋላታሳራይ፣ በስኮትላንድ ሰልቲክ ከረንጀርስ፣ በጀርመን ቦርስያ ዶርትመንድ ከሻልካ 04፣ በፖርቱጋል ሊዝበን ቤነፊካ ከ ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ በጣሊያን የሮም ደርቢ ሮማ ከላዚዮ፣ በግሪክ የአቴና ደርቢ አቴንስ ኦሎምፒያኮስ ከፓነትኒያኮስ፣ በብራዚል ሳኦፓውሎ ደርቢ ኮረንቲያስ ከፓልሚሬስ እንዲሁም በሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ ፍላ ፍሉ ደርቢ የፍላሚንጎ ከየፍሉሚንዜ ክለቦች የደርቢ ጨዋታ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በሁለት የተለያዩ ከተሞች ተወካዮች የሚደረጉ ታላላቅ የደርቢ ጨዋታዎችንም ብንመለከት አንዱ በኤል ክላሲኮ ደርቢ የሪያል ማድሪድ እና የባርሴሎና ክለቦች ፍልሚያ መጥቀስ ይቻላል። የአፍሪካ አገራትን ደርቢዎች ብንመለከት በግብጽ የካይሮ ደርቢ አል አሃሊን ከዛማሌክ የሚያገናኘው በአፍሪካ ትልቁ የደርቢ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ ደርቢ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከካይዘር ቺፍ፣ በቱኒዚያ ቱኒዝ ደርቢ ክለብ አፍሪካን ከኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ዴስ ቱኒስ የመሳሰሉት ክለቦች ይገኙበታል። ወደ አገራችን “ኢትዮጵያ” ስንመለስ ደግሞ የበርካታ ዓመታት ታሪክና ዝና ካለቸው ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ወይንም "የሸገር ደርቢ" ሁነኛ ምሳሌዎች ናቸው።

በአገሪቷ ቀደምት ታሪክ ካላቸው የእግር ኳስ ክለቦች ተርታ የሚሰለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን ከምስረታው አንስቶ በፕሪሚየር ሊግ፣ በጥሎ ማለፍ፣ በሱፕር ካፕ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊና በሌሎችም ውድድሮች ከ50 በላይ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ገናና ለመሆን የቻለ ቡድን ነው። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ አንድ ጊዜ ዋንጫ ያገኘ ሲሆን፤ በጥሎ ማለፍ፣ በአሸናፊዎች አሸናፊና በሱፕር ካፕ ፣ በራን አዌይ ሊግ በርካታ ዋንጫዎችን በማግኘት በለስ ቀንቶታል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የደርቢ ጨዋታ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ካሉት 16 የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በተመልካች ዘንድ ትኩረትን ማግኘት ችሏል። በብዙዎች ግምትም በርካታ ደጋፊ ያላቸውና በከፍተኛ ደረጃ የፉክክር ስሜት ታጅቦ የሚካሄድ ደርቢ መሆኑንም የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችም ለጨዋታው የሚያገኙት ትኩረትም ላቅ ያለ መሆኑን እናስተውላለን።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በሚኖርበት ወቅት በየደረጃው ያሉ ህጻናትና ወጣቶች ሴቶችና ወንዶች፣ አዛውንቶች ሁሉ በጨዋታው ለመታደም በስታዲየሙ ይገኛሉ። እኔም የሁለቱን ክለቦች ጨዋታና የድጋፍ ሁኔታ ለመመልከት ወደ ስታዲየሙ ከሚያመሩት መካከል አንዷ በመሆኔ ጨዋታው በሚደረግበት ወቅት የሚኖረው ድባብ ትኩረቴን ስለሳበውና ስላስደመመኝ በጥቂቱ ላወጋችሁ ወደድኩ ።

ሁለቱም የአንድ ከተማ ክለቦቹ ለፕሪሚየር ሊጉ ድምቀት እያበረከቱ ያሉት አስተዋፅኦ የጎላ ነው። ጨዋታውን በስታዲየሙ ለመከታተል የሚጓጉ ፀሀይና ዝናብ የማይበግራቸው የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ጨዋታው በሚኖርበት ወቅት ከንጋት ጀምሮ ሰልፍ በመያዝ በስታዲዩሙ ዙሪያ የሚያገኟትን ሳምቡሳ ችብስና ብስኩት እየቀማመሱ የጨዋታውን ሰዓት በጉጉት የሚጠብቁ ደጋፊዎችን እግር ጥሎት ለሚመለከት ሰው የተለየ ስሜት ይሰማዋል። ጨዋታቸውን ውስጥ ገብቶ ለሚመለከት በስታዲየሙ የሚገኘው ተመልካች ብቻ ሳይሆን ከውጪ ሆኑ የድጋፉን ድምጽ ለሚሰማው እንኳን ምነው እኔም የዚህ ድባብ ታዳሚ በሆንኩኝ የሚያሰኝ ነው።

እነዚህ ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ የክለቦቹ ደጋፊዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ በወንበር 25 ሺ እንዲሁም ከወንበር ውጪ እስከ 35 ሺ ተመልካቾችን መያዝ እንደሚችል የሚነገርለት የአዲስ አበባ ስቴዲየም ከምን ጊዜውም በበለጠ ከሚችለው በላይ እንዲሞላ ይገደዳል። አያሌ ደጋፊዎች ደግሞ ቲኬት በማለቁ የተነሳ አስፋልቱ ላይ ሲተራመሱና ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ያለፉት ዓመታት የስታዲየም አካባቢ ትርክቶች ይመሰክራሉ፡፡

በዚህም በፕሪሚየር ሊግ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል የሸገር ደርቢ የካምቦሎጆ ድምቀት በመሆን "ቀዳሚ ናቸው" ብንልም የማያሻማና ብዙዎችን የሚያስማማ ይመስለኛል። የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎቹ በኅብረት፣ በሚያምርና በሚስብ መልኩ ተደርድረው ቆመው ተቃቅፈው እያዜሙ ሲንቀሳቀሱና ሲወዛወዙ እጅግ ቀልብ በሚስብ ትዕይንት ክለቦቻቸውን ሲያበረታቱ 90 ደቂቃ ያልቃል። ከዚህ ድምቀት ጀርባ በእስካሁኑም ሂደት፤ የአንድ ከተማ ክለቦቹ የደርቢ ትንቅንቅ ለ36ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ 20 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሰባት ጊዜ ረቶቷል፡፡ በዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ተለያይተዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን በተለያዩ ጊዜያት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንደኛው በአንዱ ላለመሸነፍ በሚያደርጉት ትንቅንቅ የተነሳ እንከን የማያጣው መሆኑን እዚህ ጋር ለመጥቀስ እወዳለሁ። በተለያዩ መድረኮች ላይ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነትና የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሥነ-ምግባር ቢነገርም አሁንም ድረስ ግን  አንዳንድ ነውጠኛ ደጋፊዎች በካምቦሎጆ ሜዳ ላይ አላስፈላጊ ተግባር ሲፈጽሙ ይስተዋላሉ። እንዲህ ያሉ ችግሮች በተለይም በእነዚህ ሁለት የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ክስተት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው። 

ለዚህ ችግር ግን በዋነኝነት የሚጠቀሰው ደግሞ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእግር ኳስ ፍቅር ከልብ ያልገባቸው ውስን ደጋፊዎች ያልተገባ ተግባራት ስለሚፈጽሙ እንደሆነ ይነሳል። ደጋፊዎቹ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ፣ የቡድኖችን ስም በአሉታዊ መልኩ በመጥቀስ ወይንም ደግሞ የተጫዎችን ስም በማጉደፍ አልፎም ተርፎ በተቃራኒ ተጫዋቾች ላይ ጉዳት ለማድረስ የተለያዩ ቁሶችን እንደሚወራወሩ ነው የሚስተዋለው። በዚህም አላስፈላጊ ክስተቶች እንዲከሰቱና ለጸብ የሚዳርጉ ድርጊቶችን በመፈጸም ሰላማዊውን የእግር ኳስ መድረክ ሲያውኩ ማየት የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በሶሻል ሚዲያ የሚናፈሱ ውሃ የማያነሱና ለብጥብጥ የሚጋብዙ ወሬዎችም በስታዲየሙ ለሚከሰተው ሁከት ሁነኛ ምክንያት ስለመሆናቸው አምናለሁ። በተጨማሪ ደግሞ አንድ ሁለት በማለት መጠጥ ጎንጨት እያሉ የሚገቡ ደጋፊዎችም አንዱ የጥፋቱ ሰለባ ናቸው።

ጥቂት ደጋፊዎች ደግሞ ሲበሻሻቁ፣ ሲሰዳደቡና ከዚያም ባለፈ ወንበር እየነቀሉ በመወራወር ነገ ትውልድ ሊገለገልባቸው የሚችሉ ግብዓቶችን በማጥፋት የክለቦቻቸውን ስም ሲያጎድፉና በርካታ ደጋፊዎችን ሲፈነከቱ እና አደጋ ሲደርስባቸው እየተመለከትን ነው፡፡ በዚህ ሁከትና ብጥብጥ ሳቢያ "ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ" ነውና የፖሊሶች ዱላ እንዳያርፍባቸው በሚመስል መልኩ በፍርሃት በተዋጠ መንፈስ ሲሯሯጡ ለሚመለከት እንኳን ለመደገፍ በስታዲየሙ የገባውን ቀርቶ መንገደኛውንም የሚያስደነግጥ ነው።

ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከመካሄዱ አስቀድሞና ከጨዋታውም በኋላ ስለ ስፖርታዊ  ጨዋነት በተደጋጋሚ የፌዴሬሽን አመራር አባላት፣ አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች፣ ተጨዋቾችና የክለብ ደጋፉዎች የሚነጋገሩ ቢሆንም እንኳን ችግሩ ሊቃለል ያልቻለ ተግባር እየሆነ መጥቷል። በተጨማሪም አንዳንድ የክለቦቹ ነውጠኛና ጸብ አጫሪ ደጋፊዎችም በሚፈጥሩት ስነ ምግባር የጎደለው ተግባር የተነሳ ክለቦቹ በተለየዩ ጊዜያት ቅጣት ሲጣልባቸው ይስተዋላል።  

ለአብነት ያህል በዚህ ዓመት በሚያዚያ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በተደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የተከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ ማንሳት ይቻላል። በፕሪሚየር ሊጉ 23ኛ ሳምንት መርኃ ግብር የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በወቅቱ ቡናማውን እና ቡርቱካናማውን ማሊያ ለብሰው ባሸበረቁ የሁለቱ ደጋፊዎች የደመቀው ጨዋታ በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የሚያምር ህብረ ዜማና ቀልብ በሚስብ የድጋፍ ድምጽ የደመቀና በሚያምር የድጋፍ ስሜት የዘለቀ ነበር። ይሁንና  ልዩ ስሙ ካታንጋ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ላይ በጥቂት ጸብ አጫሪ ደጋፊዎች አማካኝነት የእርስ በእርስ አለመግባባት የተነሳ ወደ አላስፈላጊ ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት ቡድናቸውን ከማበረታታት ይልቅ ለስድብና አልፎም ለድብድብ ሲጋበዙ ተመልክቻለሁ።

በዚህም የሁለቱም ክለብ በካታንጋ ቦታ ላይ የነበሩ ደጋፊዎች መቀመጫ ወንበሮችን በመስበርና በመወራወር ሰላማዊ የሆነው ደጋፊ ላይም ጭምር ጉዳት ሲደርስበትና ጨዋታውን አቋርጦ ሲወጣም ተመልክቻለሁ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በዕለቱ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ባሳዩት የስነምግባር ጉድለቶች በክለቦቹ ላይ የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል። ይሁንና ክለቦቹ በእነዚህ ጸብ አጫሪ ደጋፊዎች ምክንያት ክለቦቹ ሲቀጡ የመጀመሪያ አይደለም፤ ነገር ግን ቅጣቱ ምን ያህል አስተማሪና ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ስለመሆኑ እንዲሁም ደግሞ "ደጋፊዎችን ምን ያህል ያስተምራል?" ለሚለው ግን አሁንም ጥያቄ አለኝ።

ታዲያ እንደዚህ ያለው አላስፈላጊና ጸያፍ ተግባር መፈጸሙ የአገሪቷን ስፖርት እንዳያድግ ከማድረግና ስፖርቱን ከማቀጨጩም በላይ በርካታ ሰላም ወዳድና እግር ኳስ አፍቃሪ የስፖርት ቤተሰብን ከካምቦሎጆ እንዲርቅ ምክንያት ይሆናል። በስታዲየሙ ታድሞ በሰላማዊ መልኩ የሚከታተለው የእግር ኳስ ማኅበረሰብ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር በስታዲየሞች የሚከታተለውን የህዝብ ቁጥር እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሊሆን የሚችል ተግባር ነው። ይህም የአገራችንን እግር ኳስ ገጽታ ጥላሸት ከመቀባት በዘለለ እድገቱን ወደ ኋላ እንደሚጎትተው መገንዘብ እንችላለን።

ታዲያ ችግሩን ማቃለል ይቻል ዘንድ ምን ቢደርግ ይሻል ይሆን? እንደ እኔ ሃሳብ፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ማንኛውም የስፖርት ቤተሰብ ውድድሮችን በነጻነትና በሰላማዊ መንገድ ተመልክቶ ወደ ቤቱ የሚጓዝበት ሁኔታ መፍጠር ቀዳሚ መሆን የሚገባው ተግባር ነው። በተለይም ሁለቱም ቡድኖች የካምቦሎጆ ድምቀት እንደመሆናቸው መጠን ደጋፊዎች ባላቸው ውብ ቀለም የራሳቸውን ቡድን ብቻ መደገፍ፣ ጨዋታውን ስነ ምግባር በተላበሰ መልኩ መመልከትና የዳኛን ውሳኔ በጸጋ መቀበል አስፈላጊ ይመስለኛል። ሌሎች ለብጥብጥ መንስኤ የሚሆኑ ተግባራትን ለምሳሌ ተጫዋቾችን፣ ዳኞችንና ደጋፊውን የሚዘልፉ ቃላትን በማስወገድ በኩል የበኩላቸውን አሰተዋፅኦ ማድረግ መቻል ተገቢ ነው። በመሆኑም ካምቦሎጆ ሁሌም ደምቆ እንዲታይና ሁከት የራቀበት ይሆን ዘንድ ተጫዋቾች፣ ዳኞች፣ የክለብ አሰልጣኞች፣ አመራር አባላት እና የክለቦቹ ደጋፊዎች "የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል" የሚል ምክረ ሀሳብ አለኝ። ችግሮቹን ሊያቃልሉ በሚችል መልኩ ለችግሩ መንስኤ የሚሆኑትን ደጋፊዎች የተለያዩ መድረኮች በአባል ደጋፊዎቻቸው አማካኝነት በመፍጠርና ስፖርቱን የሰላም መንደር በማደረግ "ማስተማር ቢቻል ችግሩ ይቃለላል" የሚል ጽኑ እምነት አለኝ

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን