አርዕስተ ዜና

ለፍትህ ትኩረት.....

ሚስባህ አወል /ኢዜአ/

ግንቦት 2/2009 ዓመተ ምህረት በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አንድ የክሰ መዝገብ የቅጣት ውሳኔ ስለሚሰጥ ገና በጠዋቱ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ተገኝቻለሁ፡፡

ሁሉም ችሎቶች ጠዋት በመሆኑ ገና አልተሰየሙም፡፡ በቅጥር ግቢው በስተቀኝ በኩል ተለቅ ያለና ግርማ ሞገስ ያለው ዘመናዊ ድንኩዋን ተጥሏል፡፡

ድባቡ የሆነ የበዓል ዝግጅት መኖሩን ያሳብቃል ፤ በመግቢያው በር ዙሪያ የተለያዩ መፈክሮችና የተወጠሩ ባሉኖች በየጥጋጥጉ ተሰቅለው ይታያሉ፡፡

ቀረብ ብዬ ስረዳ ከሚዝያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት የሚከበረው የፍትህ ሳምንት በከፍተኛው ፍርድ ቤት በመከበር ላይ መሆኑን ተረዳሁ፡፡

የፍትህ ሳምንት በተለይ ህብረተሰቡ የህግ ግንዛቤ የሚያዳብርበት ሰሞን እንደመሆኑ በርካታ ዝግጅቶች ቀርበው ይታያሉ፡፡

ከቀረቡት ዝግጅቶች መካከል የፎቶ ኤግዚቢሽን፣ የተለያዩ የግንዛቤ መስጫ ትምህርቶችና በርካታ የፍርድ ቤቱን የተሻሻሉ አገልግሎት አሰጣጦችን  የሚያሳዩ መግለጫዎች ተለጣጥፈው ይስተዋላሉ፡፡

በዚሁ አጋጣሚም በፍርድ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መግለጫ ለመስጠት አንድ የጋዜጠኞች ቡድን መኖሩን አስተዋልኩ፡፡

በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህዝብ ግንኘነት እየተመሩ በጊቢው ውስጥ የተዘረጋውን የፍትህ አካላቱን የፎቶ ግራፍ ኢግዚቢሽን ከታደሙ በሁዋላ በባለሙያዎች ገለጻ ይደረግላቸው ገባ፡፡

የመጀመሪያው ገለጻ በዚሁ ፍርድ ቤት ሬጅስትራር ወይዘሮ ህይወት ማሞ አማካይነት የተሰጠ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ በተያዘው ዓመት የተዘረጋውን  ዲጂታል የአገልግሎት መስጫ ማእከልንና ሌሎች የአይ ሲቲ አገልግሎቶችን ነበር የሚያስተዋውቁት፡፡

ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ተገልጋዮች እንደአመጣጣቸው ከዲጂታል ማሽኑ በአሻራ ቁጥር በመውሰድ አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናገሩ፡፡ ይህም ተገልጋዩ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስቻለው መሆኑን አብራሩ፡፡

በዚሁ አገልግሎት ሲጠቀሙ ያገኘሁዋቸው ባለጉዳይ አቶ ተሰፋዬ ስለሺ  ፍርድ ቤቱ አሰራሩን ለማዘመን የሚያደርገው ጥረት ጥሩ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡

ይሁንና በአሻራ ቁጥር ከመውሰድ ጀምሮ የመረጃ መረብን በመጠቀም የጊዜ ቀጠሮ የመለየትና መቼ እንደሆነ የማወቅ ጉዳይ የቴክኖሎጂ እውቀት የሚጠይቅ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በመሆኑም ይላሉ አስተያየት ሰጪው በቴክኖሎጂው መጠቀም ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በየችሎቱ አካባቢ የፅሁፍ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ከአንዱ ወደ ሌላው ተፍ ተፍ እያለ የመረጃ ቋቱን ለመሙላት የሚጣደፈው የጋዜጠኞቹ ቡድን የፍትህ ሳምንትን የማጠቃለያ ፕሮግራም ለመስራት የፌደራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው አንሺሶን ከበው መቅረፀ-ድምጽ እና የካሜራ መሳሪያዎቻቸውን ደቅነው በማስታወሻዎቻቸው ላይ የሚባለውን እየከተቡ ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ አቶ በላቸው የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመንና የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄዎች ለመመለስ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉን ያብራራሉ፡፡

በተለይ በመላ ሀገሪቱ የተዘረጋው የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከመሆን ባሻገር በፍትህ ስርዓቱ ላይ የመብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡

ዜጎች በሚያውቁት ቋንቋ እንዲዳኙ ከማድረግ ጀምሮ ህግ አውጪውና አስፈጻሚው ያለ ጣልቃ ገብነት፣ ህግ ተርጉዋሚውም በነጻነት ስራቸውን የሚያከናውኑበት ሥርዓት መኖሩን ይናገራሉ፡፡

በያዝነው ዓመትም በከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚገኙ ባለሙያዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ በማሰብ መንግሰት የደመወዝ መዋቅር ማሻሻያ ፈቅዶ ተግባራዊ መደረጉን ነው አቶ በላቸው ያብራሩት፡፡

በአሁኑ ወቅት የፈዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በየክልሉ ቅርንጫፎችን በመክፈት ህብረተሰቡ የፍትህ አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ በላቸው በአሶሳና አፋር ሰመራ አካባቢዎችም ተዘዋዋሪ ችሎቶችን በማዘጋጀት አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የህብረተሰቡ ተሳታፊነት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ በመግለጽ የፍትህ ስርዓቱ የበለጠ ሊጠናከር የሚችለው የሁሉም ተሳትፎ ሲታከልበት ብቻ ነው በማለት አቶ በላቸው ገለፃቸውን አጠቃለዋል፡፡

በዚሁ ፍርድ ቤት ባለጉዳይ የሆኑትንና ስሜን ተወው ያሉኝ አንድ ግለሰብ የፍትህ ስርዓቱ መሻሻል ይታይበታል እየተባለ ቢወራም የሚወራውን ያህል አይደለም ባይ ናቸው፡፡

ለአብነት ወደ ፍርድ ቤቱ የሚያመላልሳቸው ጉዳይ በገቢ ግብር ማጭበርበር ወንጀል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ክስ ከተመሰረተባቸው ከሰባት ወር በላይ እንደሆነውና  አንዴ ዳኞች አልተሟሉም ቀጠሮ ነው! ሌላ ጊዜ የአቃቤ ህግ ምስክር የሉም ቀጠሮ ነው! እየተባለ መጉላላት ደርሶብኛል ባይ ናቸው፡፡

የፍትህ ተቋማት በበቂ የሰው ሀይል፣ በማቴሪያልና በፋይናንስ ካልተደራጁ በየአካባቢው የሚገነቡና የሚቋቋሙ የፍትህ ተቋማት ፍትህን ከማጉዋተት አያልፉም ነው ያሉት ባለ ጉዳዩ፡፡

ባለፈው ወር የፍትህ ሳምንቱን አስመልክቶ የፈዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት ከፍተኛ አቃቤ ህግ የሆኑትን አቶ ዋለልኝ ምትኩና አቶ ተመስገን ላጲሶ አነጋግረናቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ከአቃቢያነ ህጎቹ እንደተሰማው ደግሞ  ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ እየሆነ ቢመጣም በአሰራር ችግሮችና በአንዳንድ የራስ ጥቅም ፈላጊዎች መካከል በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ   የሚፈለገውን ያህል እርካታ ሊያገኝ አለመቻሉን ጠቁመው ነበር፡፡

በሰው ሀይል  እጥረትና በግብዓት ችግሮች ሳቢያም ህብረተሰቡ ተገቢውንና ፈጣን አገልግሎት የማያገኝበት ሁኔታዎችን መቀየር እንደሚገባ በመግለጽ ለዚህም ሁሉም ህብረተሰብ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በፍትህ ተቋማት አካባቢ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮች በተገቢው መንገድ ለማጥራት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረኮች መካሄድ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን የሰጡት አቃቢያኑ በየአመቱ የሚከበሩ የፍትህ ሳምንቶች  ለህብረተሰቡ ግብዓት የሚቀርቡባቸው ሳምንታት በመሆናቸው ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

የፍትህ ሳምንቶቹ የህብረተሰቡ የህግ ግንዛቤ ከማጎልበት ባለፈ የፍትህ ስርዓቱ ዲሞክራሲያዊና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲከናወን  ያስችላልም ብለዋል፡፡

በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተዘጋጀውን ኢግዚቢሽንና ባዛር ሲመለከቱ ያገኘሁዋቸው አቶ ጌትነት ግሩም አምስቱ የፍትህ ተቋማት ራሳቸውን ለመግለጽ ያዘጋጁት በምስል የተደገፈ ኢግዚቢሽን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም በአመት አንድ ጊዜ ብቻ በማዘጋጀት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ  የፍትህ ተቋማት ህብረት የተዘጋጀ ሲሆን የፌደራሉ  ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የፌደራሉ ዓቃቤ ህግ ፤ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም የፌደራል ማረሚያ ተቋም ናቸው ያዘጋጁት፡፡

የፍትህ ሳምንቱ ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት ስድስት ይሁን እንጂ በሚያዝያ ወር በርካታ የህዝብ መድረኮች ተዘጋጅተው በፍትህ ተቋማቱ ዙሪያ ስላሉ ችግሮች ውይይት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ 

                                             

                                                                                                                                                                                 ቸር እንሰንብት !!

Last modified on Wednesday, 17 May 2017 16:38
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን