አርዕስተ ዜና

በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው እየታየ ያለው እምርታዊ ለውጥና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት

12 May 2017
5343 times

ከገዛኸኝ ደገፉ /ኢዜአ/

የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ዘርፍ የአለማችንን አጠቃላይ አመታዊ ምርት ወይም ጂዲፒ ሁለት በመቶ በመያዝ 3 ትሪሊየን  የአሜሪካን ዶላር በማንቀሳቀስና ለበርካታ ሚሊዮኖችም መተዳደሪያ መሆን ችሏል፡፡

ሁሉም የዘርፉ ተሳታፊዎች ድርሻቸውን ለማሳደግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያደርጉት ፉክክርም እየጨመረ መምጣቱን በአልባሳትና በጨርቃጨርቅ ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ላለፉት 100 እና ከዛ በላይ አመታት ታዋቂዎቹ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በአለማችን ተንሰራፍተው በመቆየታቸው የሌሎች ሃገራት የምርት ውጤቶች ራሳቸውን አስተዋውቀው ወደ ገበያው እንዳይገቡ ትልቅ ተጽእኖ ሲፈጥሩ እንደነበረ አውስቷል፡፡

ፋይበር ቱ ፋሽን ድረ ገጽ እንዳለው ግሎባላይዜሽን የምርትና የሽያጭ ውድድሩን እጅግ ከባድ ከማድረጉም በላይ የዘርፉ ተዋናዮች ሁሌም አርቀው እንዲመለከቱና ለምርቶቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገድዷል።

አፍሪካም ሆነች ሃገራችን ኢትዮጵያ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከአገር ውስጥ ፍላጎት ባሻገር ወደ አለምአቀፉ ገበያ ለመግባት የሚያስችሏቸውን የፖሊሲና የአሰራር መንገዶች አዘጋጅተው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ጎልተው የሚታዩ  በርካታ እርምጃዎችም ተወስደዋል።

ኢትዮጵያ የምታሰፋፋቸው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለአውሮፓና አሜሪካ ማሽነሪና መለዋወጫ አምራቾች የገበያ ሲሳይ ይዘው መምጣታቸውን የጣሊያን የጨርቃጨርቅ ማሽኖች አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ራፋኤል ካሩቤሊ ዉልን ኒውስ ኔት ለተባለው ድረገጽ ነግረውታል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ከሆነ ኢትዮጵያ የምትከፍታቸው ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ማእከላትን የሚያካትቱ በመሆናቸው ማእከላቱ የሚፈልጓቸውን የመሸመኛ፣ የማቅለሚያ፣ የስፌትና የመሳሰሉትን ማሽኖች ለማቅረብና ለመትከል ዝግጁ ሆነው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቂ የግብአት አቅርቦት

አፍሪካ ለጥጥ ማምረቻ የሚሆን ሰፊ መሬትና የውሃ ሃብት እንዲሁም በቀላሉ ሰልጥኖ ወደስራ ሊገባ የሚችል ወጣት የሰው ሃይል ያላት ሲሆን ይህንን ምቹ የተፈጥሮ ሃብትና ሰፊ የሰው ሃይል ወደ ስራ ለማሰማራት እንዲረዳም የአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያም ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለጥጥ አምራቾች ምቹ ማድረጓን ያወሳው ፊውቸር ቴክስታይል ድረ ገጽ ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከ30-40 ሺህ የሚሆን ሄክታር ብቻ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይሄም ሃገሪቱ ምን ያህል ለጥጥ፣ ለጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ምቹ የስራ ቦታ እንደሆነች አመላካች ነው ብሏል ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያደረጋቸው የአሰራር ማሻሻያዎች መንግስት ለጨርቃጨርቃና አልባሳት ልዩ ትኩረት እንዳለው ያመላክታል ያለው ዩሮ ሞኒተሪንግ ዋቢ ያደረገው ጀስት ስታይል ድረ ገጽ በ2016 የምርት ዘመንም አገሪቱ አንድ ቢሊየን ዶላር ለማግኘት በርትታ መስራቷን አስነብቧል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በተለያዩ ምእራፎች ከፋፍላ ባስቀመጠቻቸው የእድገትና የሽግግር መረሃግብር አመታት ለዘርፉ በሰጠችው ልዩ ትኩረት ካልቪን ከሌይን እና ቶሚ ሂልፊገር የተባሉ የንግድ ምልክቶች ባለቤት የሆነው  ፒቪኤች ኮርፕ የመሳሰሉ ታዋቂ ኩባንያዎችን ባስገነባበቻቸው ታላላቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሰሩ ማድረጓ ለሌሎች ታዳጊ ሃገራት ምሳሌ ያደርጋታል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቴክኖሎጂን ወደ አፍሪካ ለሚያመጡና እንደ ጨርቃጨርቅ ብዙ የሰው ሃይል ለሚያሰማሩ የአፍሪካ ሃገራትና ድርጅቶች ድጋፉን እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የገበያ አቅም

አንድ ቢሊየን የተጠጋ ህዝብ ያላት አፍሪካ ለዜጎችዋ የምታቀርበው ምርት በአብዛኛው መሰረቱን ያደረገው ከአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ከህንድና ከቻይና በሚመጡ አልባሳት ላይ በመሆኑ አፍሪካ ለራሷ ዜጎች ራሷ ያመረተቻቸውን አልባሳት ብታቀርብ ወደውጭ የምታወጣውን ገንዘብ ከማስቀረቷም በተጨማሪ ለዜጎቹዋ አስተማማኝ የሰራ እድል ልትፈጥር እንደምትችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

ምጣኔ ሃብቷና የህዝብ ቁጥሯ በፍጥነት በሚያድገው  አፍሪካ የህጻናትንና ወጣቶችን ቀልብ መሳብ የሚችሉ አልባሳትን ማምረት የሚችሉ አፍሪካውያን ኩባንያዎች ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል።

ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦች እየታዩባት ባለችው አፍሪካ ዘመናዊ አኗኗር እየተለመደና እያደገ ካለው የከተሜነት የህይወት ዘይቤ ጋር በተገናኘ ሁሉንም ማእከል ያደረጉ አልባሳት መመረትና ለገበያ መቅረብ መቻላቸው እንዲሁም ምርቶቹን በማከፋፈልና በመቸርቸር የተሰማሩ  አካላት ውጤታማ መሆናቸው  አፍሪካን የቻይናና የህንድ ምርቶች መጣያ እንድትሆን አደርጓታል የሚሉ ዘገባዎች ተደጋግመው ሲሰሙ እንደነበር ይታወቃል።

ብዝሃነትና ፈጠራ

አፍሪካ ያሏትን እምቅ ባህሎችና የአለባበስ ዘይቤዎች ዘመኑን በሚመጥኑ ንድፎች አምረው እንዲቀርቡ ማድረግ ብትችል አህጉሪቱን ከማስተዋወቃቸውም ባሻገር የወጣት የአልባሳትና የፋሽን ንድፍ ባለሙያዎችን አቅም ለመጠቀም እንደሚያስችላት ፋይናንሺያል ታይምስ ጋዜጣ አስነብቧል ።

እንደጋዜጣው ከሆነ አፍሪካውያን ለረጅም ዘመናት ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ራሳቸው እያመረቱ የተጠቀሙባቸው አልባሳት ራሳቸውን ከማሰተዋወቃቸውም ባሻገር ሌሎች አይተው ቢገዟቸው የበለጠ ተጠቃሚ ሊሆኑና አፍሪካ የራስዋ የሆኑ መታወቂያዎች እንዳላት የምታሳይበት  መሆኑንም አመላክቷል።

ብዙ አይነት የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤ ካሏቸው ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች የገለጸው አይፒ ኤስ ኔውስ በበኩሉ ኢትዮጵያውያን ሙሉ በሙሉ  የሃገራቸው የሆኑና ባህላዊ የአመራረት መንገዶችን ተከተለው ከተፈጥሮ ግብአቶች የተመረቱ አልባሳት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ገበያዎች እየደረሱ ቢሆንም ተገቢው የማስተዋወቅ ስራ ስላልተሰራባቸው አምራቾቹ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እያገኙ አለመሆኑን አትቷል።

ያልተነካው እድል

ኢትዮጵያ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች ትርጉም ያለው ገቢ ማስገኘት የተለያዩ ፖሊሲዎችን አውጥታ ተግባራዊ ማድረጓንና ለዘርፉ ቀጥተኛ ግብአት የሚሆኑ ወጣት ምሁራንን በልዩ ትኩረት በመመልመል በሃገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በጨርቃጨርቅ  አልባሳትና ንድፍ ምህንድስና ዘርፍ እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት ይፋዊ ድረገጽ አስነብቧል፡፡

አሜሪካ ለአፍሪካ ምርቶች የሰጠችውን እድል / AGOA / ለመጠቀም ኢትዮጵያም በርትታ እየሰራች እንደሆነ አስፍሯል። አጎዋ የአፍሪካ ምርቶች ግብኣቶቻቸውን ከአፍሪካ እንዲያገኙ የሚያስገድድ በመሆኑ ሁሉንም ነገሮች ለማሟላት ጥረቶች እየተደረጉና አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑንም ድረ ገጹ አመላክቷል።

ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ባይችልም የሚታዩት እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውንና የኢትዮጵያ ምርቶችም ትኩረት ቢሰጣቸው አለምአቀፍ ተወዳደሪ መሆን እንደሚችሉ አለምአቀፍ የሚድያ አውታሮች ከሚያወጣቸው  ዘገባዎች መረዳት ይቻላል።

ባሳለፍነው ሳምንት ጃካርታ ፖስት የተባለው ድረ ገጽ እንዳስነበበው ከሆነ ኢትዮጵያ የምታመርታቸው የጨርቃጨርቅና የአልባሳት ውጤቶች ለኢንዶኔዥያ የአልባሳት ኩባንያዎች ፈተና እየሆኑ መምጣታቸው እንዳሳሰበው የኢንዶኔዥያ የጨርቃጨርቅ አምራቾች ማሀበራት ሊቀመንበርን ጠቅሶ አሰነበቧል ።

ብዛትና ጥራት

ሃብታሞቹ የአውሮፓና የአሜሪካ ሃገራት ለሚያመርቷቸው ምርቶችና ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የጥራትና የደረጃ መስፈርቶችን አዘጋጅተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ከ50 አመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ሃገራቱ ስለጥራትና ደረጃዎች የሚያወጡዋቸውን መረጃዎች መመለከቱ በቂ ነው።

ያደጉት ሃገራት የከባቢ አየር መበከልና የአለም ሙቀት መጨመር እያስከተለባቸው ያለውን ተጽእኖ መቋቋም እንዲያስችላቸው ወደ አህጉራቸው የሚገቡ ምርቶችም ከአካባቢ ጋር የተስማሙና ተመልሰውም ጥቅም ላይ ሊውሉ ከሚችሉ ጥሬ እቃዎች የተመረቱ ሊሆኑ  እንደሚገባ ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ ይሰማል።

በመሆኑም ሃገራቱ ይህንን አላማቸውን የሚያስተገብሩባቸው ህግጋትን በማውጣት ወደስራ የገቡ ሲሆን አካባቢያቸው እንዳይበከል ሲባል የተገለገሉባቸውን አልባሳት በመሰብሰብ ወደ አፍሪካ ሃገራት እንደሚልኩና ትንሽ የማይባል ገንዘብ እንደሚያገኙ ሃፊንግተን ፓስት ድረ ገጽ አፍሪካ የአውሮፓ ልባሽ ጨርቆችን አትፈልግም ሲል ባወጣው ጽሁፍ አስነብቧል።

እ.ኤ.አ 2014 ብቻ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ በማውጣት ልባሽ ጨርቆችን እንዳስመጡ ያተተው ጋዜጣው ልባሽ ጨርቆችን መጠቀም ከሚያስከትለው የጤና እክል ባለፈም የአፍሪካ ታዳጊ የዘርፉ አንቀሳቃሾችን አቅም እየተፈታተነ መሆኑንና አፍሪካ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንዳስቀረባት አመልክቷል።

በመጪው አዲስ አመት መስከረም ወር ማብቂያ በመዲናችን አዲስ አበባ ከ25 ሃገራት የሚመጡ ከ250 በላይ አለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾችን የመዋቢያ ቁሰቁሶች አቅራቢዎችንና ልዩ ልዩ የዘርፉ አንቀሳቃሾችን የሚያካትት ግዙፍ አውደ ርእይና ባዛር ይካሄዳል፡፡ ይህም አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ ለዘርፉ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠችው አመላካች መሆኑን ኒቲንግ ኢንዱስትሪ ዶት ኮም አውስቷል፡፡

በአውደ ርእዩ ኢትዮጵያ ያላትን አቅምና ዝግጁነት ለተሳታፊ አካላት የምታሳይበትና ልምድ የምትወስድበት መሆኑንም ጠቅሷል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን