አርዕስተ ዜና

ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በትክክለኛው ጊዜ የመጣ ነው-በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ አምባሳደር

12 May 2017
3497 times

ከሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በትክክለኛው ጊዜ የመጣ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያያ አምባሳደር ተቀዳ አለሙ ኒው ዮርክ ላይ መቀመጫቸውን ላደረጉ የቻይና መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መናገራቸውን ቻይና ፕላስ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

የአለም ትኩረት ቤጂንግ ላይ በሚከናወነው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ላይ አርፏል፡፡  አለም የገጠማት  የኢኮኖሚ እድገት መቀዛቀዝ፣የሉላዊነት አስተሳሰብ በተዛባ መንገድ መታየት እና አለመረጋጋት እያቆጠቆጠ መሆኑን ተከትሎ ፕሮጀክቱ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ተቀዳ አለሙ ተናግረዋል፡፡

" የመጣው በትክክለኛው ጊዜ ነው፡፡ የዘር ጥላቻና በሰዎች መካከል የልዩነት መስፋት በታየበት በዚህ ወቅት ሰዎችን ማቀራረቡ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ኢኒሸቲቩ የተቀረጸው በአገራትና በህዝቦች መካከል ያለውን ትብብር በማሳደግ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው”፡፡

“አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢኒሼቲቩ ከፍ ያለ እውቅና እንደሚሰጠው አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም የተመሰረተው ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ እና ልማትን በፍትሐዊነት  በማዳረስ አለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት ነው” በማለት ዶክተር ተቀዳ አለሙ ተናግረዋል፡፡

"የኢኒሸቲቩ ጥሩው ክፍል የትኛውንም አገር አለማግለሉ ነው፡፡ የትኛውም አገር ሆነ ህዝብ ይሳተፍበታል፡፡በኢኒሼቲቩ ሂደት በንቃት የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው በሙሉ መቀላቀል ይችላሉ፡፡የሚተገበረው ይህንኑ መመሪያ መሰረት በማድረግ በመሆኑ ማንኛውም አገርም ሆነ ግለሰብ ከኢኒሼቲቩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ይህም ብዙዎችን ለመሳብ ያግዛል፡፡."

የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤና የጸጥታው ምክር ቤት የሮድ ኤንድ ኢኒሸቲቭን እንደሚደግፉት ዶክተር ተቀባ ተናግረው የተባበሩት መንግስታት ተቋማት ድጋፉን የሚያደርጉት ህዝቦችና አገራት አብረው እንዲሆኑ ለማበረታታት ነው ብለዋል፡፡

ኢኒሸቲቩ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታትን ቀጣይነት ያለው የልማት ግብ ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ዶክተር ተቀዳ መናገራቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

" ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ አጀንዳ 2030 ን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ይህንኑ አላማ ለማሳካት ብዙ ሐብት ያስፈልጋል፡፡ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገራት ያላቸውን እምቅ ሐብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ቁመና ላይ አልደረሱም፡፡ስለዚህ ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያንና መሰል አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እምቅ ሐብት ይዞ ነው የሚመጣው እናም እነዚህ አገራት በዚህ ሒደት ተሳታፊ ይሆናሉ." በማለት ዶክተር ተቀዳ መናገራቸውን ድረ ገጹ ጽፏል፡፡

ደካማ የመሰረተ ልማት አቅርቦት በኢትዮጵያና በመሰል አገራት የእድገት ጉዞ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት በመደቀን የህዝቦችን ግንኙነት፣ የገበያ መስፋፋትንና ቀጠናዊ ትስስርን እንደሚያዳክም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡በዚህ ምክንያት ኢኒሼቲቩ ልዩነት መፍጠር የሚያስችል እድል ያስገኛልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት የዚህ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 475 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው ፕሮጀክት የተደገፈው በቻይና መንግስት ሲሆን የተገነባውም በቻይና ተቋራጭ ነው፡፡ይህ ደግሞ ቻይና መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የምታደርገው ድጋፍ ማሳያ መሆኑን ዶክተር ተቀዳ አስታውቀዋል፡፡

"ኢኒሸቲቩ ልማትን በማፋጠን ኢትዮጵያንና ሌሎች የአፍሪካ አገራትን ተጠቃሚ በማድረግ ለአህጉሪቱ የማይተካ አሰተዋጽኦ ያበረክታል፡፡የቻይና የልማት እገዛ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ብቻ ሳይወሰን በኢኒሼቲቩ በመታገዝ እስያን ከአውሮፓና አፍሪካ ጋር ለማገናኘት ያለመ በመሆኑ አለም አቀፍ ጠቀሜታ አለው፡፡ጠቀሜታው እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ያላደጉ አገራት ጋር የግንኙነት  ገደብ ሳይኖረው  የአለም ህዝቦችን እንደሚያቀራርብ  "ዶክተር ተቀዳ ተናግረዋል፡፡ ኢኒሼቲቩ ከቻይና ቢነሳም ጥቅሙ አለምን እንደሚያዳርስ በመጥቀስ ድረ ገጹ ዘገባውን ደምድሟል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን