አርዕስተ ዜና

የህብረቱ ቀጣይ ፈተና

4446 times

ምንይችል ዓለማየሁ (ኢዜአ)

አህጉረ አፍሪካ ግራ በሚጋቡ የተለያዩ ቀውሶች በተደጋጋሚ ትጠቀሳለች፡፡ ተፈጥሮ ለአፍሪካ የሚያዳላ እስኪመስል የተለያዩ ሃብቶችን ቢቸራትም፤ በርካታ አፍሪካውያን የዚህ ገፀ-በረከት ተመልካች እንጂ ተጠቃሚ አይደሉም ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ባወጣው የሰው ልጆች የልማት ልኬት (ኢንዴክስ) መሰረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን አሁንም ከድህነት ወለል በታች ይገኛሉ፡፡

በአፍሪካ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት የሰው ልጆች ትኩስ የሥራ ጉልበት በሚገለጥበት የወጣትነት እድሜ  ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ይኸው ልኬት አሳይቷል። አህጉሪቷ በርካታ ትኩስ ኃይል ይዛ  በድህነት ቀንበር መንገላታቷ ደግሞ ጉዳዩን እንቆቅልሽ  አድርጎታል። ለአፍሪካ ድህነት በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች  በምክንያትነት ሲጠቀሱ ኖረዋል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች  በግንባር ቀደምትነት እንደሚቀመጡ በርካታ ምሁራን ይስማማሉ፡፡

ሙስና አፍሪካን ከየትኛውም የዓለማችን አህጉሮች በበለጠ እየተፈታተናት የሚገኝ እንቅፋት መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ይፋ የሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ 'ትራንስፓረንት ኢንተርናሽናል' የተባለ ድርጅት እ.አ.አ. በ2016 ይፋ ባደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ በ2015 ብቻ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 75 ሚሊዮን የሚሆኑት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መሰረታዊ አገልግሎት ለማግኘት ጉቦ ከፍለዋል፡፡

ይህ ጥናት ከሰሃራ በታች ባሉ 28 አገሮች የሚኖሩ 43 ሺ 143 ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን፤ በአገራቱ  የሚገኙ የህግ ማስፈፀሚያ ተቋማት ደግሞ በሙስና በመዘፈቅ ቀዳሚውን ደረጃ መያዛቸውን አትቷል፡፡ የፍትህ አካላት በሙስና እጃቸው መቆሸሹ ደግሞ የችግሩን ውስብስብነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ጥናቱን ያደረገው ድርጅት ሊቀ መንበር ጆዜ ኡጋዝ "ሙስና በአህጉሪቷ ድህነትና ከልማት የተገለለ ማህበረሰብ እየፈጠረ ነው፡፡ ሙሰኞች በቅንጦት ኑሮ ሲንደላቀቁ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን  እንደ ምግብ፣ ንፁህ ውሃና ትምህርት የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች ማግኘት አልቻሉም" ሲሉ ሙስና  ምን ያህል በአህጉሪቷ ኢ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንደፈጠረ አፅኖት ሰጥተዋል፡፡

ለዚህም ይመስላል አዲስ አበባ በተካሄደው 30ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ  ሙስና አንኳር  የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ. በ2063 በአህጉሪቷ ሁሉን አቀፍ እድገትና ቀጣይነት ያለው እድገትን እውን ለማድረግ አጀንዳ ቀርፆ መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ለዚህ አጀንዳ ተፈጻሚነት የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስና ለአጀንዳው  እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን በመለየት በህብረቱ ጥላ ስር በየጊዜው ይወያያሉ፤ ችግሮችን ይኮንናሉ፤ አቅጣጫም ያስቀምጣሉ፡፡ የአቅጣጫው ተግባራዊነት ሌላ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፡፡

የህብረቱ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት፤ በአፍሪካ በየዓመቱ 148 ቢሊዮን ዶላር  በሙስና ይመዘበራል፡፡ ይህም 25 በመቶ ከሚሆነው የአህጉሪቷ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ጋር የሚስተካከል ነው፡፡

የህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት 30ኛውን የህብረቱን መሪዎች ጉባኤ በከፈቱበት ወቅት "የአፍሪካ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ በተባበረ ክንድ ሙስና ላይ ድል መጎናጸፍ ያስፈልጋል" ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡

ሙስና በአህጉሪቷ በፍጥነት መጨመሩን አመላካቾች

ሙስና በአፍሪካ እጅግ እየጨመረ መምጣቱን አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ 58 በመቶ የሚሆኑ የአህጉሪቷ ዜጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሙስና እጅግ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ "ሙስና ጨምሯል ወይ? ብዬ ከጠየኳቸው ደቡብ አፍሪካውያን መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት አወንታዊ ምላሽ ሰጥተውኛል" በማለት ትራንስፓረነት ኢንተርናሽናል በቅርቡ ሪፖርት አድርጓል፡፡

ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያና ላይቤሪያ በሙስና ስማቸው በክፉ የሚነሱ አገሮች መሆናቸውን ያመለከተው ጥናቱ፤ ሞሪሺየስ፣ ቦትስዋና እና ሴኔጋል ደግሞ ሙስናን በመዋጋት አበረታች ስራ መስራታቸውን አስታውቋል፡፡ በተለይ ሴኔጋል እ.አ.አ. ከሚያዝያ 2014 ጀምሮ የመንግስት ባለስልጣኖቿ  ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ማድረግ ለትግሉ እገዛ እንዳደረገላት ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአህጉሪቷ በተለያዩ አገሮች የሚደረግ ምርጫ ሙስና በአህጉሪቷ መንሰራፋቱን አመላካች ነው፡፡ በምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች "ሙስናን እዋጋለሁ" የሚል  እቅድ በማስቀደም ከህዝብ ይሁንታ ለማግኘት ሲሯሯጡ መመልከት የተለመደ ሂደት እየሆነ መጥቷል፡፡

ከወር በፊት የተደረገውና እውቁን የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃን ወደ መንበረ ስልጣን ያመጣው የላይቤሪያ ምርጫ እንዲሁም በ2016 የተደረገውና አክፎ አዳን ወደ ፕሬዝዳንት ያመጣውን የጋና ምርጫን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ አሸናፊዎች ቃላቸውን ያከብራሉን? የሚለው ጥያቄ ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ቢሆንም፤ የሙስና ትግል በምርጫው  የልዩነት  አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል፡፡

ሙስና የደቡብ አፍሪካውን ፓርቲ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረንስን( ኤ.ኤን.ሲ) ፓርቲን በከፍተኛ ሁኔታ እየናጠው መሆኑንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ ችግር ፓርቲው በቅርቡ  በአገሪቷ በተደረገው አካባቢያዊ ምርጫ ላይ በርካታ ወንበሮችን እንዲነጠቅ ማድረጉን  በርካታ መገናኛ ብዙሃን በስፋት አስተጋብተውታል፡፡ ኢትዮጵያን የሚመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) በቅርቡ በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ግርግሮችና ሁከቶች ምክንያት በኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር መሆኑን ማስታወቁ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

የህብረቱ ሙስና ትግል ምን ይመስላል?

የአፍረካ ህብረት ሙስናን ለመዋጋት ይጠቅሙኛል ብሎ የነደፋቸው በርካታ የህግ ማዕቀፎች አሉት፡፡ እነዚህን የህግ ማዕቀፎች እንዲያስፈፅሙ ያዋቀራቸው ተቋማትም እንዲሁ፡፡ የተወሰኑ የህግ ማዕቀፎችን ለመጥቀስ ያህል:- እ.አ.አ. በ2003 የረቀቀውና የ38 አገሮችን ተቀባይነት ያገኘው የህብረቱ የሙስና መከላከያና መታገያ ኮንቬክሽን፣ የአፍሪካ ዴሞክራሲ፣ ምርጫና አስተዳደር ቻርተር እንዲሁም ያልተማከለ አካባቢያዊ አስተዳደርና ልማት ቻርተር  ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁሉ የህግ ማዕቀፎች በአህጉሪቷ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት በማስፈን ለሙሰና ትግሉ መልካም መደላድል እንደሚፈጥሩ ታምኖባቸው የጸደቁ ናቸው፤ ምንም እንኳ መሬት ላይ ያለው ሃቅ ሌላ ቢሆንም፡፡ ከማዕቀፎቹ በተጨማሪም አገሮች የራሳቸው የሆነ የሙስና መታገያ ተቋማት  እንዳሏቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ምንም እንኳ ህብረቱ ሙስናን መዋጋት የሚያስችሉ መሰል ሰርዓቶች ቢኖሩትም  ችግሩ አሁንም የአህጉሪቷ ፈተና መሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይባስ ብሎ ችግሩ በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱ ከአህጉሪቷ መሪዎች አፍ ተደምጧል።

በሌላ በኩል ህብረቱ በተለያዩ ጊዜያት በሙስናና ብልሹ አሰራር ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሱ መንግስታትን ከማውገዝ በዘለለ ተጠያቂ ሲያደርግ አይታይም፡፡ ከዚህ ይልቅ  ድምጹ የማይሰማበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ ማውገዙንም ቢሆን በተጠቀሰው ችግር በሚታመስ መንግስት የሚመሩ ህዝቦች ቁጣቸው ገንፍሎ ወደ አደባባይ ከወጡ በኋላ መሆኑ በርካታ ጊዜያት ታይቷል፡፡

ህብረቱ የጋምቢያ ህዝቦች የቀድሞ መሪያቸው የያያ ጃሜ በሙስና የተጨማለቀ አስተዳደር በቃን ብለው አደባባይ ከወጡ በኋላ አለሁ ብሎ ድምጹን ማሰማቱን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ታዲያ ምን ይሻላል?

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚኖሩ ሁሉም አባል አገሮች የሙስና ትግሉ ፍሬ አፍርቶ የአህጉሪቷ ህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልባዊ ፍላጎት ካላቸው፤ ለሚከተሉት ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡

በተጨባጭ የሙስና ትግሉ ባለቤት ህዝብ መሆን አለበት፡፡ ዜጎች ማናቸውንም ዓይነት  የሙስና ተግባር የሚጠቀሙበትና ይህን በማድረጋቸው ደግሞ ምንም ዓይነት የደህንነት ስጋት እንዳይገጥማቸው ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት ከማናቸውም የመንግስት ጣልቃ ገብነት  ነፃ ሆነው ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት  ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ የበጎ አድራጎት ማህበራትን የትግሉ ማሳተፍ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት።

ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት በሙስና የተዘፈቁ መንግስታትን ተጠያቂ የሚያደርግ ህጋዊ ተቋም ማዋቀር አለበት፡፡ ምን አልባት በሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ የሚመራውና ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው የህብረቱ ሪፎርም ተግባር ይህን የሚታገል ተቋም ይዞ ይመጣ ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን