አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

"የጎዳና ላይ ባላንጣዎቹ’’

20 Apr 2017
4930 times

ነጻነት አብርሃም (ኢዜአ)

የሰው ልጅ ከጥንት የጋርዮሽ አኗኗር ዘዬ ተላቆ ወደ ተሻለው የማኅበራዊ መዋቅር እንዲሸጋገር ካደረጉት ወሳኝ ታሪካዊ ክስተቶች መካከል አንዱ የንግድ ሥራ ነው። በተጓዳኝም የሰውን መሰረታዊ ሕይወት እንዲሻሻል፣ በተዘዋዋሪ የሀብት ክፍፍል እንዲረጋገጥና ዓለማችንም በገበያ አማካኝነት የባህልና ሌሎች ተያያዥ የአኗኗር ሥርዓትን በማወራረስ "ሉላዊነት" መልክ እድትቀዳጅም አስችሏታል።
በርግጥ ንግድ ለአገራዊ እድገት ያለው ፋይዳ የጎላ እንደሆነና በአግባቡ ካልተያዘም የሚያሳድረው አሉታዊ ጫና ቀላል ባለመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች አበክረው ይመክራሉ። ይሁንና በበርካታ አገሮች ላይ ዘርፉ በተለይም ኋላ ቀር በሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ከመረጃ አያያዝ ጋር በተገናኘ የሚፈለገውን ያክል እድገት እያስመዘገበ እንዳልሆነ ይጠቀሳል። 

ለዚህም ደግሞ አብዛኞቹ የንግድ ተዋናዮች በሕገ-ወጥ መንገድ ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በአፍሪካ ያለው የንግድ ሥርዓት ከ50 በመቶ በላይ የሚፈጸመው በሕገ-ወጥ መልኩ ወይንም ኢ- መደበኛ መሆኑን ልብ ይሏል።

ይህም በአንድ በኩል መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ በታክስና በቀረጥ መልኩ እንዳያገኝ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ የምርቶችን ጥራት፣ ፍትኃዊ ክፍፍል እንዳይኖር እንዲሁም ዋጋ ላይ ቁጥጥር እንዳይደረግ ሸማቹ ኅብረተሰብ ተጎጂ እንዲሆን ያደርጋል። ከእነዚህ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ኢ-መደበኛ ያልሆነ የንግድ ሥራ በተለይም በከተሞች አካባቢ ይስተዋልባታል።

ሕገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ስናስብ አዲስ አበባ በአሉታዊ ከምትታወቅበት መስክ አንዱ ይመስለኛል። ይህም በዋና ዋና መንገዶች ላይ ከሚዘወተሩ ድርጊቶች መካከል በቃዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ይህ የጎዳና ላይ ትዕይንት በአብዛኛው የመዲናዋ ክፍሎች በተለይም በፒያሳ፣ በአራት ኪሎ፣ በስድስት ኪሎ፣ በሜክሲኮ፣ በቄራ፣ በሳሪስ፣ በመገናኛና በሌሎችም ዋና ዋና መንገዶች ላይ ይዘወተራሉ።

ቋሚ መሥሪያ ቦታ ሳይኖራቸው ሕዝብና ተሽከርካሪ በሚንቀሳቀስባቸው ጎዳናዎች የተለያዩ የግብይት እቃዎችን ይዘው ከአላፊና ከአግዳሚው ጋር ሲገበያዩ ማየት ልማድ ሆኗል።

የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በአብዛኛው ለሽያጭ የሚያቀርቧቸው ሸቀጦች ዘመናዊና ባህላዊ  አዳዲስ አልባሳት ሲሆኑ፤ ልክ እንደ ልብስ መደብር፣ የሕጻናት፣ የአዋቂዎች/የሴትና የወንድ/ ማግኘት አይከብድም። ከሸቀጦችም ኤሌክትሮኒክስ ፣ ሻንጣዎች ፣ የሴት ቦርሳዎች፣ ጌጣጌጦች፣ የቤት ውስጥ የምግብ ማብሰያ እቃዎች፣ መጫሚያዎች፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የሕጻናት መጫወቻዎችና ሌሎችም በርካታ እቃዎች ጎዳናው ላይ በሽበሽ ናቸው።

እነዚህ ነጋዴዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር በጎዳና ላይ ሙጥኝ ካሉ ውለው አድረዋል። ይሁን እንጂ ነጋዴዎች በጎዳና ላይ የንግድ ሥራቸውን የሚያካሂዱት ከሚመለከተው አካል ሕጋዊ ፍቃድ ያላገኙ ናቸው። ሁነኛ አድራሻ የሌላቸው በመሆናቸውም ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እሰጥ አገባ  ውስጥ ሲገቡ ማየት አይደንቅ ይሆናል። በተለይ የሁለቱ ወገኖች የድብብቆሽ ጨዋታን አመሻሹ ላይ መመልከት አይደንቅም። እንደውም  መዲናችን ምሽትን ጠብቃ ጀባ ከምትለን የጎዳና ላይ ድራማዎች አንዱ ክፍል ነው ማለት ይቀላል።

የሚገርመው ግን፤ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር የሚገጥሟቸው የድብብቆሽ ጨዋታ አልፎ አልፎ ፍጻሜው እንደ ልጅነት ዘመን ድብብቆሽ ጨዋታ ጋር መመሳሰሉ ነው። ይህን ስል ይህንን ትዕይንት አይተን "እረ መኪና በላቸው አሊያም ደግሞ ሰው ገፍተው መኪና ውስጥ ከተቱት ብለን" ስንሳቀቅ፤ ከዚሁ ሁሉ ተርፈው በንጋታውም እንዲሁ ዳግም መገናኘታችን የሚያተዛዝብ ነው።

የጎዳና ላይ ንግድ በመዲናዋ ላይ ከሚያደርሰው ተጽዕኖ መካከል በዋነኝነት የትራፊክ አደጋ ተጠቃሽ ነው። በአሁኑ ወቅት ለትራፊክ አደጋ መነሻ ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንዱ የመንገድ መሰረተ ልማት አለመሟላት ይህም በቂ የሆነ የእግረኛ መንገድ አለመኖር ነው። ይሁንና አሁን ላይ እንደምንታዘበው ከሆነ የእግረኛ መንገድ ባላቸውም ሆነ በሌላቸው አውራ ጎዳናዎች ላይ የንግድ እንቅስቃሴ በመኖሩ የተነሳ እግረኞች በተሽከርካሪ መንገዶች ላይ  እንዲጓዙ እየተዳረጉ ነው።

ይህ የትራፊክ እንቅስቃሴን ከመግታት ባለፈ እግረኞችን ለአደጋ ተጋላጭ እያደረጋቸው ይገኛል። ይህ ብቻ ሳይሆን፤ በጎዳና ላይ ባላንጣዎቹ ማለትም በደንብ አስከባሪና በነጋዴዎቹ መካከል ባለው ትርምስ ለእግረኛ ተብሎ በተፈቀዱ መንገዶች ላይ የዜጎችን ነጻ እንቅስቃሴ ከመግታት ባሻገር ለስርቆት መዳረጉም ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ነው።

በተጨማሪም በሚፈጠረው ግፊያና ትርምስ አቅመ ደካሞች፣ ሕጻናት እንዲሁም ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲስተጓጎሉና ሲደናገጡ ማየት ሌላው የምሽት አግራሞት ይሆናል። እንደውም በአንድ ቀን ከምሽቱ 12 ሰዓት ገደማ፤ ከመሥሪያ ቤት ወደ መኖሪያ ቤቴ በማመራበት ወቅት፣ ፒያሳ በተለምዶ አራዳ ህንጻ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ ነጋዴዎቹ ከደንብ አስከባሪ ለመሸሽ በሚያደርጉት ትንቅንቅ በእድሜ የጠኑ አዛውንትን ገፍትረው መሬት ላይ ጥለዋቸው አይቻለሁ።

ይህም ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመላክቶኛል ማለት እችላለሁ። ከዚህም ባለፈ፤ መዲናችን “የአፍሪካ ከተማ ናት” ተብላ በምተጠራበት ወቅት እንዲህ ያሉ የጎዳና ላይ ንግዶች በከተማዋ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ማዋቅ ተገቢ ይመስለኛል። ይህንን ስል አንድም ከላይ ለመጥቀስ የሞከርኳቸው ጉዳዮች በውጭ ዜጎች እይታም ሆነ በእነርሱ ላይ ተፈጽሞ ማየት ከተማዋ ሥርዓት የጎደላት ያክል እንዲሰማቸው ያደርጋል ባይ ነኝ። በአንጻሩ፤ ነጋዴዎቹ የሚጠቀሙባቸው ፌስታሎች፣ ካርቶኖችና ሌሎች እቃ የሚያጓጉዙበት መሳሪያዎች እዛው አካባቢ ላይ በነጋዴውም ሆነ በሸማቹ የሚጣሉ በመሆናቸው የከተማዋን ውበት አደጋ ላይ የሚጥለው ይመስለኛል።

ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ ችግሩን ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?

የጎዳና ላይ ንግድ ለማስቆምም ሆነ ለመከላከል እጅግ በጣም አዳጋች ይመስለኛል።  ይሁን እንጂ “ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ነው” ብዬ የማስበው በሚመለከተው አካል የመሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። ይህ ከተደረገ በኋላ በትክክለኛው መሥመር ለመሥራት ፍላጎትና አቅም ያላቸውን መርጦ ወደ ሥራ ማስገባት ሊከተል ይገባል ባይ ነኝ።

ይህም በተለይም ነጋዴዎችን በማደረጃት ተግባራዊ ቢሆንና ወደ መደበኛው የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ የሚያስችላቸው ይመስለኛል። በአንጻሩ፤ ለምሳሌ ያህል ልክ እንደ ቅዳሜና እሁድ ገበያ (Sunday market)  አልያም ደግሞ እግረኛና ተሽከርሻሪ በማይበዛባቸው ሥፍራዎች በሳምንት ውስጥ ባሉ በተወሰኑ ቀናት እንዲሸጡ ቢፈቀድላቸው አግባብ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች ተደርጎ እንደሚታየው ማለት ነው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ሕገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድንና ኩነቱን ተከትሎ የሚመጡ ችግሮቹን መከላከል ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን