አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ግብርናው ካልዘመነ የምግብ ዋስትና አይታሰብም!

18 Apr 2017
3184 times

 

 ሰለሞን ደሳለኝ  /ኢዜአ ማይጨው/

በትግራይ ክልል ከፍተኛ  የሰብል ምርት ከሚመረትባቸው አከባቢዎች የራያ አዘቦ ወረዳ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል። በእንስሳት ሃብቱም ቢሆን አካባቢው ወደር የለውም። እንደውም የወረዳው ገበሬዎች  ከሰብል ልማቱ  ቀጥሎ የኑራቸው መሰረት  ከእንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ የሚያገኙት  የገቢ ምንጭ ነው።

ይሁንና የወረዳው አርሶአደሮች የሚያካሄዱትን  የግብርና ልማት በባለሙያና በግብዓት እጥረት ምክንያት ከዘርፉ  ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ  የሚናገሩት  በግብርና ልማት  አፈፃፀምና ችግሮች ዙሪያ  ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ልማት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር  ሰሞኑን የተወያዩ የአካባቢው ገበሬዎች ናቸው።

በመስኖ  ልማት  በአመት 3 ጊዜ እያመረትን  የምግብ ፍጆታችንን ከመሸፈን አልፈን የእንስሳት ቀለብ ችግርን በማስወገድ ድርቅን መቋቋም ብንችልም በተባይ መከላከያ መድሃኒት አቅርቦት ችግር ከልማቱ የምንፈልገውን  ጥቅም ማግኘት  አልቻልንም ሲሉ  የውይይቱ ተሳታፊ  አርሶአደር  ንግስቲ  ሃፍቱ ተናግረዋል።

በተለይ የአትክልት ተባይ መከላከያ መድሃኒቱን ከአቅራቢ ነጋዴዎች በውድ ዋጋ ገዝተው ለማልማት ጥረት ቢያደርጉም  ለኪሳራ እየተዳረጉ ትርፉ ድካም እንደሆነባቸው  ነው አርሶ አደሯ  የተናገሩት።

″ ለመስኖ  ልማቱ 10 ሺህ ብር አውጥተን  የምናገኘው የምርት ሽያጭ 3 ሺህ ብር  ነው ። የተባይ መድሃኒት ከነጋዴ ለኪሎ አንድ ሺህ ብር እየገዛን ለማልማት ተገደናል። ከአቅማችን በላይ ነው። የወረዳው ግብርናም  ሆነ የእርሻ ምርምር ሊያግዙን አልቻሉም። አትክልታችን  በተባይ ተበልቶ እየቀረ ተቸግረናል።″ብለዋል፡፡

የመስኖ ልማቱ ለልጆቻችን  ስራ በመፍጠሩ   ከስደት ጉዞ እየታደገ  ቢሆንም  የልማቱ ስራ ውጤታማ ባለመሆኑ  ጥቅም እንዳላገኙበት የሚገልፀው ደግሞ  የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት  አሰፋ አባይ  ነው።

መንግስት  የውሃ ጉድጓድና መሬት  ሰጥቶን  በመስኖ ማምረት ጀምረናል። ነገር ግን  ከነጋዴ በከፍተኛ ገንዘብ የምንገዛው  የተባይ መከላከያ  ኬሚካል  የአትክልት በሽታው መድሃኒቱን  ተላምዶት  ያለሙትን  ከጥፋት ማዳን እንዳልቻለ ነው ያስረዳው  - ወጣቱ ።

″ ከሁሉም በላይ ደግሞ የግብርና ባለሞያዎችም  የመስኖ ልማቱን  በእውቀት  ሰርተን ለማሻሻል በቴክኒክ  መደገፍ ሲገባቸው ተገቢው እገዛ ስለማይሰጡን  ልማቱ  ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል።″ ብሏል፡፡

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ  አርሶአደር ምህረት ረብሶ  እንዳሉት ደግሞ  በመስኖ ማልማት መጀመራቸው ከመንግስት ተረጂነት ያላቀቃቸው ቢሆንም  ምርታቸውን  የሚሸጡበት ገበያ እያጡ ለችግር ተዳርገዋል።

አሁን  በአካባቢው ገበያ  እንደ ሽንኩርት የመሳሰሉ የአትክልት ምርቶች  መሸጫ  ወጋ በኪሎ እስከ ሶስት ብር ድረስ በመውረዱ  የድካማቸውን ዋጋ ለማጣት እየተገደዱ መሆናቸውን  ነው አርሶአደር ምህረት  ያስረዱት ።

″መስኖ ብናለማም  የገበያ ትስስር  ድጋፍ  ማግኘት አልቻልንም  ። ገበሬው በተደጋጋሚ እየከሰረ ተስፋ  ቆርጧል። አሁን የሽንኩርት ዋጋ  ከመውረዱ በላይ  የቲማቲም  ምርታቸውን  ገዢ አጥተው ከማሳቸው ነቅለው የጣሉ በርካታ ገበሬዎች ናቸው።″ብለዋል፡፡

የመስኖ ልማቱ በምግብ እህል ምርት ራሳቸውን  ቢያስችላቸውም  ለልማቱ  የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን  የሚናገሩት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፉ አርሶአደር አሸናፈ ባበ ናቸው።

″ግልፅ  የሆነ የመብራት ክፍያ ተመን  የለም። የመብራት ሃይል ሰራተኞች እንዳሻቸው ያስከፍሉናል።በዚህ ወር 120 ሺህ ብር፤ እንደገና ቀጥሎ 50 ሺህ ብር ያስከፍሉናል።አቤት ስንል እኛ አናውቅም ከፌደራል ተሰርቶ ነው የመጣው ይሉናል።″ብለዋል፡፡

የውሃ  አማራጭ ገንብቶ የአነስተኛ መስኖ ልማት ተጠቃሚ እንድንሆን አቅጣጫ ቢቀመጥም የአካባቢው ገበሬዎች የውሃ አማራጭ መያዝ አለመቻላቸው  የአርሶአደሩ ድክመት መሆኑንም አልደበቁም ።

ገበሬው  ኩሬዎች በብዛት  ቆፍሮ የዝናብ ውሃን በማቆር አትክልት አልምተን መጠቀም ችለን ነበር ያሉት አርሶአደር ነገር ግን ልጆቻችን ተንሸራትተው ውስጥ እየገቡና የወባ ትንኞችም እየተራቡ ስለተቸገርን ለመድፈን ተገደናል ነበር ያሉት።

ከእርሻ ስራ ቀጥሎ እንስሳትን በማርባትና በማድለብ  ኑራቸውን እየመሩ ቢሆንም የዘርፉ ልማት ኋላቀር በመሆኑ የሚያገኙት ጥቅም ዝቅተኛ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህንኑ ሃሳብ አርሶአደር ባህፍታ መሃሪም ይጋሩታል። የብድር ገንዘብ ወስደው 16 ፍየሎችና በጎችን ገዝተው የማርባት ፤የማድለብና የዶሮ ርቢ በማካሄድ ኑራቸውን ለመለወጥ ቢጥሩም ከአካባቢው ባለሞያዎች የሙያ እገዛ  ማግኘት አልቻሉም ።በዚህም አስር ፍየሎቻቸው በበሽታ እንዳለቁባቸው ነው  ያስታወቁት።

″ከመንግስት ብድር በስተቀር ምንም አይነት ድጋፍ አላገኘሁም።አሁን በቅርቡ ግን ክትባት ተጀምሯል ጥሩ ነው።ነገር ግን በበሽታ ብዙ ፍየሎቼ ካለቁ ብኋላ ክትባት መጀመሩ ለኔ ትርጉም የለውም ″ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በግብርናው ዘርፍ ካነሱት ችግሮች መካከል በአካባቢ ጥበቃና ልማት ስራ የሚታዩ ጉድለቶች ናቸው። ካሁን በፊት የአፈር እቀባና ደን ልማት ጥቅሙን ሳይገነዘቡ ለምን ስሩ እያሉ ያደክሙናል በማለት ሲቃወሙ እንደነበር  የሚናገሩት አርሶአደር ግደይ መሃሪ ናቸው።

የኋላ ሃላ ግንዛቤ አግኝተው አፈርን በማቀብ ደን በማልማታቸው  ከደኑ ሳር አጭደው ለእንስሳት መኖና በእርከኖች የሚቋጠር የዝናብ ውሃን ለእንስሳት መጠጥነት በማዋል ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው  የተናገሩት ።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማቱ እንደ ወይራና ግራር የመሰሉ የተፈጥሮ ዛፎችን በብዛት እንዲበቅሉ እያደረገ ቢሆንም  ከልቅ ግጦሽ ባለመቆጠባችን  የዛፍ ችግኞች መብቀል እንዳልቻሉ ነው ያስረዱት ።

″አሁን ወደ ደኑ ብንሄድ እንስሳት ተሰማርተውበት እናገኛለን። ልቅ ግጦሽ ካለ ደግሞ ደናችን መልማትና ማደግ አይችልም። ይህ ድክመታችን ነው ።እንስሳቶቻችንን በመከልከልና የደን ይዞታውን አክብረን መጠበቅ ከቻልን በተሻለ ተጠቃሚ እንሆናለን ።″ብለዋል

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ማከናወናቸውም የእርሻ መሬታቸው በጎርፍ እንዳይታጠብ በመከላከል የአፈር ለምነትና እርጥበቱን  በመጠበቅ የሰብል ምርታቸው እያደገ መሆኑን አርሶአደር ግደይ ይናገራሉ።

ነገር ግን  የአከባቢያችን  አፈር ለሰው ሰራሽ ዛፎች አይሆንም ። ስለሆነም ለአከባቢው ተስማሚ የሚሆኑ አገር በቀል ችግኞችን መትከል ከተቻለ  በጥሩ ሁኔታ እንደሚለማ ነው አርሶአደሩ ያመከቱት።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው  በአከባቢው የተጀመረው የመስኖ ልማት  ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም  አርሶአደሮቹ መስኖን በማልማትና ከድህረ ምርት በኋላ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች መፍታት እንደሚገባ  ገልጸዋል።

በውይይቱ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ጎበና አባተ እንደገለጡት የአካባቢው አርሶአደሮች በመስኖ የሚያመርቱት አትክልት በቀላሉ የሚበላሽ በመሆኑ  በቀላሉ ወደ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የገበያ ትስስሩ በመፍጠር ሊደገፉ ይገባል።

ወደፊት አርሶአደሮቹ  የሚያመርቱት አትክልትን እሴት ጨምረው ወደ ገበያ ማቅረብ እንዲቻል የግብርና ምርቶችን የሚለውጡ ኢንዱስትሪዎች የማስፋፋቱ  ስራ ትኩረት ሊሰጠው ግድ ይላል ብለዋል ።

አርሶአደሩ የፀረ ተባይ መድሃኒቶችን ከመጠቀም ውጪ አትክልቶችን ማምረት አይችልም ያሉት አቶ ጎበና  በክልሉ  ካሉት የህብረት ስራ ማህበራት ጋር በማስተሳሰር መድሃኒቶቹን በተመጠጣነ ዋጋ የሚያገኙበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል ።

የመብራት  ተጠቃሚዎችን በቆጣሪና የታሪፍ  ተመን መሰረት የሚያስከፍልበት ስርዓት ያለው በመሆኑ ከዚህ ውጪ አርሶአደሮቹ የሚከፍሉበት መንግድ ተገቢነት እንደሌለው አስረድተዋል።

የአካባቢው  አርሶአደሮች ለመስኖ ልማት በሚገለገሉት መብራት የሚከፍሉት አግባብነት የሌለው ክፍያ በማጣራት እርምት እንዲወሰድ  በየደረጃው የሚገኝ አካል መስራት እንዳለበትም ነው ያስረዱት።

በህዝብ ተሳትፎ የሚካሄዱ የተፈጥሮ ሃብት ልማቶች በየጊዜው እያደጉ ቢመጡም መሬት አልባ ወጣቶችን የሚጠቅሙ ተጓዳኝ የልማት ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም አቶ ጎበና አሳስበዋል።

የወረዳው ህዝብ ያለ ተፈጥሮ ሃብት ኑሮን ማሻሻል እንደማይቻል ተገንዝቦ  በየአመቱ ሰፊ የደን ተከላና ልማት ስራ በማካሄድ  በአካባቢው ለኢኮ- ቱሪዝም  ልማት የሚያገለግል ሃብት መፍጠር  መቻሉን ተገንዘበናል  ነበር ያሉት።

ህዝቡ የተፈጥሮ ሃብት ልማቱ ስራ ማካሄዱ የዝናብ ስርጭትን በማስተካከል የመሬት እርጥበትና  የሰብል ምርታማነት  በማሻሻል የእንስሳት መኖ ለማምረትም አስተዋፀኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።  እናም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ።

በተለይ በተፈጥሮ ሃብቱ ዙሪያ  የንብ ማነብና ማር ማምረት ጨምሮ የበጎች፤ ፍየሎችና እርባታ ማድለብ  ፕሮግራሞችን  በማካሄድ  ወጣቶችንና ሴቶችን  ተጠቃሚ ማድረግ ሲገባ ትኩረት  አልተሰጠምና ሊስተካከል ይገባል ብለዋል  ።

በመሆኑም የተፍጥሮ ሃብትን ከሌሎች የገቢ ማስገኛ የልማት ስራዎች ጋር በማስተሳሰር የስራ እድል አማራጮችን  በማስፋፋት ረገድ የታየው ጉድለት ማስወገድ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

በውይይቱ የግብርና ቋሚ ኮሚቴው  ቡድን መሪ አቶ አረጋዊ አፅባሓ  በበኩላቸው እንዳሉት የአከባቢው አርሶአደር  ለረጅም አመታት በእንስሳት እርባታ ስራ የተሰማራ ቢሆንም የዘርፉ ልማት ለማዘመን የሚያስችለው ድጋፍ እያገኘ አለመሆኑን  መገንዘብ ችለዋል።

አርሶአደሩ በእርሻ ስራ ብቻ ኑሮውን ለመለወጥ አደጋች ነው ያሉት አቶ አረጋዊ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር መጠኖ በመያዝና የልማቱ ስራ በማሻሻል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።

ለዚህም አከባቢው የሚታየውን የእንስሳት ህክምና ባለሞያዎች እጥረት በማስወገድ አርሶአደሩ የሙያ እገዛ በስፋት በመስጠት ከእንስሳት ሃብቱ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ መሰራት እንዳለበት ነው ያስታወቁት።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የእንስሳት ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ አማረ መሃሪ በሰጡት መልስ አርሶአደሩ ያቀረበው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ገልጠው ችግሩ ለማስተካካል  የተጠናከረ  ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በውይይቱ ማብቂያ የራያ አዘቦ ወረዳ አስተዳደሪ ተወካይ አቶ ኢፃይ  ስዩም   በሰጡት መልስ የአካባቢው አርሶአደሮች በግብርና ልማቱ ዙሪያ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢነት እንዳለው ጠቁመው ችግሩን ለማስወገድ የተጠናከረ ስራ እንደሚከናወን አረጋገጠዋል።

አዎን የአካባቢው አረሶአደሮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ልማት ስራቸውን ማዘመን የግድ ይላል። ለዚህም የባለሞያ ደጋፍና የግብዓት አቅርቦት ማሟላት ወሳኝ ነው።ከዚህ ውጪ የምግብ እህል ተረጅነትን መመከት ፈፅሞ የሚቻል አይሆንም።

የአካባቢው አርሶአደሮች የውሃ አማራጭ ግንባታ ጠቀሜታን በማስረዳት  ለነገ ሳይባል መተግበር ይገባዋል።ምክንያቱም የውሃ አማራጭ መያዝ የዝናብ እጥረት ሲገጥም የጓሮ አትክልትን በማልማት ችግሩን ለመቋቋም ያስችላል። የውሃ አማራጭ ቢያንስ ቢያንስ የምግብ እህል እጥረት ሲገጥም በአነስተኛ መሬት ስኳር ድንችን በማምረት ቤተሰቡን በመመገብ ድርቅን ለመቋቋም የሚረዳ ብቸኛው አማራጭ መንገድ ነውና።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን