አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ሊቀ ሊቃውንቱ አርሶ አደር

18 Apr 2017
4608 times

                               መብራህቱ ይባልህ (መቀሌ ኢዜአ)

አርሶ አደር ተካ ገብረ ኪዳን ተግባር ተኮር ትምህርት ከመውሰዳቸው  በቀር  መደበኛ ትምህርት ቤት ገብተው ፈደል ለመቁጠር አልበቁም ፡፡ በልጅነት ጊዜያቸው ጎበዝ አርሶ አደር እንጂ ጎበዝ ተመራማሪ ለመሆን ህልምም ሆነ ውጥን አልነበራቸውም፡፡

አሁን ግን ምሁራን የሚጠቀሙበት ተመራማሪ የሚለውን ቃል አርሶ አደር ተካ ገብረ ኪዳንም  በጥረታቸው ተጋርተውታል ፡፡ ተመራማሪ አርሶ አደር ተካ የሚል ስያሜ ተጎናፅፈዋል ፡፡

ስራዎቻቸውንና ታታሪነታቸውን ተከትሎ ከአካባቢው ማህበረሰብ  ሊቀ ሊቃውንት የሚል ስያሜ ተለግሶአቸዋል ፡፡ ጥበባቸው፣ክህሎታቸውና ብልህነታቸው መሰረት ተደርጎ የተሰጣቸው ስያሜ ነው ።

አርሶ አደሩ ውልደታቸውና እድገታቸው በትግራይ ክልል ደጉዓ ቴምቤን ወረዳ ’’አይንንብረከክን’’ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  ነው፡፡’’አይንብርከክን’’ የሚለው የቀበሌው ስያሜ ወደ አማርኛ ሲመለስ ’’አንንበረከክም’’ ማለት ነው፡፡

የቀበሌው ስያሜ ታሪካዊ ዳራ የያዘ ነው ፡፡ የደርግ ሰራዊት በ1980 ዓ.ም በትግራይ ከተሞች ባጋጠመው ሽንፈት  ነፍሰጡሮች ፣ህፃናት፣ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ሳይቀር በሳንጃና በጥይት ደብድቧቸዋል ፡፡ ማህበረሰቡም በድርጊቱ ’’አንንበረከክም ’’ በሚል መንፈስ ያሳየውን ፅናት ለማስታወስ ቀበሌውን በዚሁ እንዲጠራ አድርጓል ።

አርሶ አደር ተካ  ለድህነት አልንበረከክም በማለት ሙሉ ጊዜያቸውን  ለምርምርና ለፈጠራ ስራ የሰጡ ናቸው ። በእርሻ መሳሪያ፣በምርታማነትና ቴክኖሎጂን በማፍለቅ ስራ ውጤታማ ሆነዋል ።

ከእንጨት  ውጤቶች የሚሰሩ የእርሻ መሳሪያዎች ምንም ለውጥ ሳይደረግባቸው አብረውን ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ አሁንም ምንም ፈጠራ ሳይታከልባቸውና ለውጥ ሳይደረግባቸው  ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ ቀጥለዋል ፡፡

አርሶ አደር ተካ ግን ዛፍ መቁረጥ ሳያስፈልግ ከእንጨት የተሰራ ባህላዊ የእርሻ መሳሪያ ሙሉ በሙሉ በብረት በመተካት ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡

ሞፈር፣ ቀንበር ፣ እርፍ ፣ ድግርና  ሌሎች ተጓዳኝ የእርሻ መሳሪያዎችን በብረት ተክተው የማስተዋወቅ ስራ በማካሄድ ላይ ናቸው ፡፡  እስከ አሁን ድረስ 150 ለሚሆኑ አርሶ አደሮች በሽያጭ እንዲዳረስ አድርገዋል።

ባለ ሁለትና ባለ ሶስት ቀንድ መንሽም የአርሶ አደር ተካ  አንዱ የፈጠራ ውጤት ነው ፡፡ ሶስት መቶ የሚሆኑ መንሾችን በሽያጭ አሰራጭተዋል ፡፡ በክልሉ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ቢስፋፋ ምን ያህል ደን ከጭፍጨፋ መታደግ እንደሚቻል መገመት አያዳግትም፡፡

ለምን ሁልጊዜ ደን እየጨፈጨፍን እንኖራለን የሚል ቁጭት ስላደረባቸው እንጨቱን በብረት እንደተኩት ይናገራሉ ።

የአርሶ አደሩ የፈጠራ ውጤቶች ክብደታቸው ከልማዳዊው  የእርሻ መሳሪያዎች ጋር ሲነፃፀሩ   በአምስት ኪሎ ግራም የቀለሉ   በአገልግሎት  ዘመናቸው  ደግሞ  የላቁ መሆናቸውን በትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሳይቀር ተረጋግጧል ይላሉ ፡፡ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችም  እንዲሁ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በእጅ የሚሰራ የስንዴ መውቅያም ለገበያ ለማቅረብ ጫፍ ላይ ደርሰዋል ፡፡ ምንም ነዳጅና የኤሌክትሪክ ሀይል ሳያስፈልገው  በሰው ጉልበት በቀን አምስት ኩንታል ስንዴ ለመውቃት እንደሚቻል ሞክረው አረጋግጠውታል፡፡

’’ያላለቁ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለማስገምገም ወደ ክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የገጠር ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ማእከል አቀርበዋለሁ’’ ይላሉ - አርሶ አደር ተካ ገብረኪዳን ፡፡

የስንዴ ዘርና  ማዳበሪያ በየራሳቸው መያዣ ቦታ ተቀምጠው በዘር ወቅት ግን  አንድ ላይ  በማዋሃድ  የሚዘራ ቴክኖሎጂም ሰርተው  በማጠናቀቅ  ላይ ናቸው ፡፡

ለብቻው ሳይሆን ከእርሻ መሳሪያው ተገጥሞ የሚሰራ በመሆኑ ስንዴና ማዳበሪያ የሚዘራ ተጨማሪ የሰው ሀይል ሳያስፈልግ ሁሉንም ስራዎች በአንድ ሰው የሚከውን ቴክኖሎጂ ነው ።

ሊቀ ሊቃውንት አርሶ አደር ተካ ሌላ የምርምር ስራ ለማከናወንም  ወጥነዋል ፡፡ ምስር፣ባቄላና ተልባ የመሳሰሉ ’’ ከተወሰኑ አመታት ወዲህ በአከባቢያችን ለምንድን ነው ምርታማነታቸው እየቀነሰ የመጣው’’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተዘጋጅተዋል ።

አርሶ አደሩ ለዚሁ የሚሆን መልስ አለኝ ይላሉ ፡፡ የግብርና ባለሙያዎች ቢያንስ ከሶስት አመታት  ሙኮራ በኋላ ነው መልሱን መናገር የምትችለው ስላሉኝ እያጠናከርኩት  ነው ባይ ናቸው  ፡፡

አርሶ አደር ጣሰው ገብረ ዮሀንስ   በሊቀ ሊቃውንቱ አርሶ አደር ተሻሸለው የቀረቡ የእርሻ መሳሪያዎችን ገዝተው ከተጠቀሙ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

የተሻሻለው የእርሻ መሳሪያ ክብደቱ ቀላል፣ ሳር በበዛበትና ጭቃማ በሆነ ማሳ ላይ ሰርስሮ የመግባት ጉልበት ያለው በመሆኑ በዘልማድ ከሚጠቀሙበት የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ይመሰክራሉ፡፡

ልጃቸውን ጨምሮ ሌሎች አምስት አርሶ አደሮችም አገልግሎቱ የተሻለ መሆኑን በማስረዳት  ገዝተው እንዲጠቀሙ አድርገዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር ገብረ ህይወት ፍሰሀ  በአርሶ አደር ተካ ገብረ ኪዳን  ከብረት የተሰራውን  የእርሻ መሳሪያ ገዝተው ስራ ላይ በማዋል ከነባሩ በተሻለ እያገለገላቸው መሆኑን በመግለፅ መስክረዋል ፡፡ 

በክልሉ  ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእርሻ መካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ አስገዶም በበኩላቸው "የደን ውድመትን ለመከላከል አርሶ አደሩ ያቀረቡት አማራጭ የሚደነቅና የሚበረታታ  ነው" ብለዋል፡፡

የስንዴ መውቂያ መሳሪያም  ወደ ኢንዱስትሪ የሚቀርብ የስንዴ ምርት ከእንስሳ እበት ንክኪ ነፃ መሆን ስለሚገባው ስሪቱ የሚበረታታ ሀሳብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ምርምር ከማካሄድ ባለፈ እውቅና የመስጠት ስልጣን የሌለው በመሆኑ የአርሶ አደሩን ስሪቶች መመዝገብ እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡

ኢንስቲትዩቱ የአርሶ አደሩን ክህሎት ከፍ ለማድረግ የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት ድጋፍ እንዳደረገላቸውም ተናግረዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን