አርዕስተ ዜና

ኮማንድ ፖስቱና የቀጣይ አራት ወራት የቤት ሥራው

18 Apr 2017
3057 times

ከዓለም ለገሰ (ኢዜአ)


ከስድስት ወር በፊት እንዲህ ሆነ።

በዕለቱ ከቢሮዬ አምሽቼ አንድ ሰዓት ገደማ ነበር የወጣሁት። ጀምበሯ ብትጠልቅም አዲስ አበባ እንደወትሮው በመብራት ደምቃለች። ምሽቱ ሰላም የሰፈነበት ነው። የሕዝቡ እንቅስቃሴ የተረጋጋና ሰላማዊ ነው።

የእለት ስራችንን እንዳጠናቀቅን ከሥራ ባልደረባዬ ጋር ወጥተን “ከየአከራዮቻችን የተጣለብን የሰዓት እላፊ ገደብ” ሳይደርስ በጊዜ ቤት ለመግባት ተጣድፈናል።  

በአውቶቡስ ማቆሚያ ላይ ሆኜ ’ሸገር ባስ’ በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ ድንገት የተንቀሳቃሽ ስልኬ ጥሪ አሰማ። ከኪሴ አውጥቼ ስመለከተው የተደወለልኝ ከቅርብ ዘመድ ነው። ተደሰትኩ። ድምጹን ለመስማት ጓጉቼ በፍጥነት “ሄሎ” አልኩ። ከወዲኛው  ጫፍ የሚመጣው ድምጽ ግን እጅግ የደከመና ለቅሶ የተቀላቀለበት ነበር። አውቶቡስ በምጠብቅበት ስፍራ በድንጋጤ መንፈሴ ታወከ።

“ምን ሆነሽ ነው ጡባዬ?” ስል ጠየኳት፤ ሳግ እየተናነቃት “በከተማው ሁከት ተነስቶ ቤታችንን አቃጠሉት፣ አንድም ነገር አልቀረንም፣ ወድሟል። እኔም ዘመዶቼ ጋር ሄጃለሁ” ስትለኝ ድንጋጤዬ በእጥፍ ጨመረ። ግን ደግሞ የግድ ራሴን አረጋግቼ ስለሁኔታው መረጃ መለዋወጥ ነበረብኝ።

የሰው ህይወት ጠፍቶ እንደሆነ ጠየኳት። በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ያለመድረሱን ነገረችኝ። ''አይዞሽ፣ እንኳን የሰው ህይወት አልጠፋ፤ ሀብትና ንብረት ይተካል” ብዬ አጽናናኋት።

ጡባ ጥቃት የደረሰባት ተወልዳ ባደገችበት፣ ለወግ ለማዕረግ በበቃችበት፣ ቤተሰብ መስርታ የልጆች እናት በሆነችበት አካባቢ ነው። በአካባቢው ሁከትና ብጥብጥ በመነሳቱ ጥራ ግራ ያፈራችው ንብረት ወደመባት። ለእኔ አዳሬን ሰላም የነፈገኝ የስልክ መልዕክት የደረሰኝም በዚሁ ምክንያት ነው።

ወቅቱ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ሁከትና ብጥብጥ ተከስቶ የነበረበት ነው። በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ተከስቷል። ከውስጥም ከውጪም የፀረ ሰላም ኃይሎች ግንባር በመፍጠር መንግስት በወቅቱ ያልመለሳቸው የህዝብ ችግሮች በመጠቀም ወጣቱን ለዓመፅ አነሳስተዋል።  

የፀረ ሰላም ኃይሎች የዓመጹን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የብሔር መልክ ማስያዙን ዋነኛ የትግል ስልትነት ተጠቅመዋል። ይህም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል አይደለም። ሁኔታው እየተባባሰ እንዲሄድም ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል።

በሁለቱ ክልሎች ዓመጽ እየተስፋፋ በመሄዱ መንግስት በመደበኛ የህግ አሰራር ሰላምን ማረጋጋትና ማስከበር በማይችልበት ደረጃ መድረሱም የተረጋገጠው በዚሁ ወቅት ነው። በተለይ በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች በህዝብ ንብረት፣ በባለሀብቶች ተቋማት፣ በመንግስት ተቋማት እና በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ እጅግ አስከፊ ውድመት ተከስቷል። በሰው ህይወት ጉዳት ደርሷል።

በአማራም ብሔርን ለይቶ ማጥቃት፣ ሀብትና ንብረት ማውደም፣ ሰው መግደል፣ የመንግስት ተቋማት ሰንደቅ ዓላማን አውርዶ መቀየር፣ ህዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ ማገድ ሴራዎች ተደርገዋል። ሁኔታው ከክልሉ ቁጥጥር ውጪ መሆን ጀመረ። በሁለቱም ክልሎች መንገዶች እየተዘጉ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ማውደም በየእለቱ የሚሰማ እኩይ ተግባር ሆነ።

በመጨረሻም ጸረ ሰላም ሀይሎቹ ግንባር በመፍጠር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ በቅርቡ “አዲስ መንግስት ይቋቋማል” እያሉ በመላው አገሪቷ ትልቅ ፍርሀት እንዲነግስ አደረጉ። በወቅቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ መሰናክል ለመፍጠር የሚፈልጉትን ሃይሎች ጨምሮ የውጭ ጠላቶች የፀረ ሰላም ኃይሎችን እኩይ ተግባር በመደገፍ እንደተሰለፉ መንግስት “በቂ መረጃ አለኝ” ማለቱ የሚታወስ ነው።

አደጋው በዚሁ መልክ እየከፋ ሄደ። ድርጊቱን በመደበኛ ህግ ማስከበር ስራ ማስቆም እንደማይቻል የተረዳው መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገደደ። ከዚህ ጎን ለጎን ገዢው ፓርቲ እስከ መንግስት መዋቅርና ህዝቡ የዘለቀ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማጥራትና ለማደስ በይፋ መንቀሳቀስ ጀመረ።  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ሁሉንም ነገር ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ መቻሉ ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቷ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራዎቻቸውን የሚያከናውኑበት ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሯል። ተፈጥሮ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ እና በህዝቡ ላይ ፈጥሮት የነበረው የፍርሃት ድባብም ሙሉ በሙሉ ቀንሷል ማለት ይቻላል።

ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ የፀረ ሰላም ሃይሎች ዓመፁን የማስቀጠል ፍላጎት እንዳለ ምልክቶች ተስተውለዋል። በሁከቱና ብጥብጡ ተሳትፎው በህግ ተጠያቂ ላለመሆን በየጫካው የገቡ ጥቂት ግለሰቦች መኖራቸው እና በኦሮሚያ የአርሲ አካባቢን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም የቅስቀሳ ሙከራዎች እንደሚደረጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ በተጨማሪ በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት ለመፈፀም ሰርገው  የገቡ የፀረ ሰላም ኃይሎች በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በቁጥጥር ስር የዋሉትም በቅርብ ጊዜ ነው፣ ይሄም ሌላው ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

መከናወን ያለባቸው ተግባራት ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቃቸውና አሁንም አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች በመኖራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወያየ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቆይታ ለአራት ወራት እንዲራዘም ተደርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮማንድ ፖስቱ እና የአዋጁ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ በየፊናቸው በሰበሰቡት መረጃ ህዝቡ የአዋጁ መቆያ ጊዜ እንዲራዘም ፍላጎት እንዳለው መግለጹን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ለምክር ቤቱ በማቅረባቸው ለመራዘሙ ምክንያት ሆኗል።

አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በቅርቡ የአዋጁ የስድስት ወራት አፈጻጸምና የቀጣይ አራት ወራት ዕቅዶች ላይ ተወያይቷል። በዚሁ መሰረት ኮማንድ ፖስቱ በስድስት ወራት ተልእኮው የተገኙ ስኬቶች፣ ክፍተቶች እና በቀጣይ አራት ወራት የሚከናወኑ አቅጣጫዎችን ለይቶ ወደ ስምሪት ገብቷል።

ኮማንድ ፖስቱ በስድስት ወራት ባከናወናቸው ሥራዎች የተሻለ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠሩ በአዋጁ የማስፈፀሚያ መመሪያ ላይ መሻሻሎችን ማድረጉ ይታወሳል። ስለዚህ በመመሪያው ላይ የተነሱትንና ያልተነሱትን አንኳር አንኳር ጉዳዮች በቅድሚያ ማየቱ በአሁኑ ወቅት የኮማንድ ፖስቱ ሚና ላይ ግልፅነት ለመፍጠር ይረዳል።

አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት ሁከትና ብጥብጡን በመቀልበስ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ማድረጉ በግልጽ የሚስተዋል ሀቅ ነው። የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ወደ መደበኛ የህግ አሰራር ቀስ በቀስ ለመመለስ እንዲቻል ኮማንዱ ፖስቱ መጀመሪያ ላይ ያወጣውን የማስፈፀሚያ መመሪያ ሁለት ጊዜ አሻሽሎታል።

ማሻሻያው የሚያካትተው በዲፕሎማቶች ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ፣ ያልተፈቀዱ አልባሳት ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ፣ በመሰረተ ልማት አውታሮች የተጣለው የሰዓት እላፊ እና ተጠርጣሪዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የመበርበር እና መያዝ የሚሉት እንዲቀሩ ተደርገዋል። በማንኛውም ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጽሁፍ፣ ምስል፣ ፎቶግራፍ፣ ቲያትርና ፊልም የሚተላለፉ መዕልክቶችን ለመቆጣጠርና ለመገደብ የተሰጠው መብትም እንዲቀር ተደርጓል።

የጦር መሳሪያ ወይም ማንኛውንም የግልም ሆነ የመንግስት ንብረት ለዘረፈ፣ ለህገ ወጥ ተግባራት ድጋፍ ያደረገና አቅራቢያው ለሚገኝ የህግ አስከባሪ መመሪያ ቁጥር አንድ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ እንዲመልስና እጁን ለፖሊስ እንዲሰጥ የሚለው አንቀጽም ቀርቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ወረቀት በመበተን፣ አድማ በማድረግ ለተሳተፈ፣ ላነሳሳ፣ ሰው የገደለ፣ ማንኛውንም ንብረት ያቃጠለና ማንኛውንም ወንጀል ፈጽሞ እጁን ለሰጠ የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት የመልቀቅ እርምጃም ቀሪ ሆኗል።

ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ጉዳዮችን ጨምሮ የተነሱ ክልከላዎችና እርምጃዎች ኮማንድ ፖስቱ በመመሪያ ቁጥር ሦስት መሰረት አዋጁን ተግባራዊ በሚያደርግበት ተፈፃሚ አይሆኑም።

አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የአዋጅ ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር ሶስት የተለዩ የዋና ዋና ዞኖች፣ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ ከሽብርተኞች ግንኙነት ማድረግ፣ በትምህርት ተቋማት ረብሻ ከተፈፀመ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግና ከአቅም በላይ ከሆነ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ የሚፈቅደው አንቀፅ እንደቀጠለ ነው።

ራስን ለመከላከል በህግ አስከባሪዎች ስለሚወሰድ እርምጃ፣ በብርበራና በፍተሻ ወቅት ስለሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በመመሪያ ቁጥር አንድ ላይ የተመለከቱ ክልከላዎችና እርምጃዎች ተፈጻሚነት ይቀጥላል። ከዚህ በተጨማሪ ሽብርተኞችና ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል አሁንም የፍርድ ቤት ትእዛዝ ሳያስፈልግ መያዝ ይቻላል።

“ጉዳት ይደርስባቸዋል” ተብለው የተለዩ ዜጎች ካሉበት የማንሳት እና አፕሬሽን በሚሰራበት አካባቢ ያሉ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ስለማንሳት የሚፈቅደው አንቀፅም ባለበት እንደቀጠለ ነው።

ይሁን እንጂ በአዋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች በመደበኛ የህግ ማስከበር መሸፈን የሚቻል በመሆኑና የመመሪያው መሰረታዊ አንቀፆች የቀጠሉ በመሆናቸው የሚፈጥሩት ችግር አይኖርም።

በተነሱት ክልከላዎች ምክንያት ክፍተት ቢፈጠር ኮማንድ ፖስት የተነሱትን የመመለስና ሌላም የማንሳት መብት ያለው በመሆኑ ብዙም የሚፈጥረው ስጋት እንደሌለ ነው በግምገማው ወቅት የተለጸው። በአዋጁ አፈፃፀም መመሪያ ላይ ማሻሽያ መደረጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ትግበራ ሂደት ቀስ በቀስ ወደ መደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለማሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱንም የሚያሳይ ነው።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ማሻሻያ የተደረገው ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በመቀልበስ በመደበኛው የህግ ማስከበር አሰራር መፈፀም የሚቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱ ነው። የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት እና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እንዳመለከቱት፤ በአዋጁ ማስፈፀሚያ ላይ ማሻሻያዎች በመደረጉ ሶስት መሰረታዊ ጥቅሞች እያስገኘ ነው።

በመጀመሪያ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪዎች መያዝና ቤታቸው መበርበር የሚለው አንቀጽ መነሳቱ “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ቤታችን ተበረበረ፣ ንብረታችን ተዘረፈ እየተባለ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና አሉባልታዎች የሚከሰቱበት ዕድል ይዘጋል'' ይላሉ።

ሁለተኛ የፀጥታ አካላት አብዛኛው ሥራዎቻቸውን በህጋዊ አግባብ መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው። ሶስተኛው እና ዋናው ማሻሻያ መደረጋቸው በመደበኛው የህግ አሰራር ጉዳዮችን እያከናወኑ መሄድ በተቻለ ቁጥር ቀስ በቀስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሚና በሂደት እየቀነሰ ወደ መደበኛው የህግ አሰራር ለመግባት በር የሚከፍት ነው። ዋናው የኮማንድ ፖስት ዓላማም ይህ ነው ብለዋል።

ኮማንድ ፖስቱ የአገሪቷ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆንም የአዋጁ የስድስት ወራት አፈፃፀም ተገምግሟል። በግምገማው የተገኙ ስኬቶች፣ የነበሩ ክፍተቶች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ተለይተዋል። በዚሁ መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ የተከሰተውን ሁኔታ በማረጋጋትና ሰላም በማስፈን የሁከትና ብጥብጡን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ በስኬት ተገምግመዋል።

አቶ ሲራጅ እንዳሉት፤ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ህዝቡ በህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ መተማመን እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ ተሰርቷል።በተለይ የተዘረፉ ንብረቶችን በማስመለስ፣ የተረጋጋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር የተሰራው ሥራ ህዝቡ የተሻለ መረጋጋት እንዲያገኝ አድርጎታል።

ህዝቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆንና በመካከሉ መተማመን እንዲፈጠር የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ በጥንካሬ የተገመገመው ነጥብ እንደሆነም አቶ ሲራጅ ተናግረዋል። በሁከትና ብጥብጡ ወቅት በዝርፊያ፣ በሽብር ስራዎች እና መሰረተ ልማቶችና ኢንቨስትመንቶችን በማቃጠልና በማውደም የተሰማሩትን አብዛኛዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉም በስኬት ተገምግሟል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ተሃድሶ መውሰዳቸው እና በህግ መጠየቅ የሚገባቸው ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውለው በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ በመፍጠር የተሰራው ሥራ በተሻለ ደረጃ መፈጸሙ ነው የተገለጸው። በመሰረተ ልማቶች፣ በዋና ዋና መስመሮች፣ በኬላዎች እና ተቋማት ላይ በተሰሩ ሥራዎች በሁከትና ብጥብጡ የተከሰተው ውድመት እንዳይደገምና ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈፀም በማድረግ የተሰራው ስራም በስኬት እንደሚታይ ነው የተመለከተው።

ሁከትና ብጥብጥ በተፈጠረበት ወቅት በተለያየ መንገድ በትጥቅ ትግልም ጭምር ሁከቱን ለማቀጣጠልና ለማባባስ ይሰሩ የነበሩ አካላት አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ማዋላቸው ኮማንድ ፖስቱ ገምግሟል። በአገር ውስጥና በድንበር አካባቢ በተሰራ የተሻለ የቁጥጥርና ክትትል ስራ በተለይ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ግንባር በመፍጠር ሁከትና ብጥብጥ ለማስቀጠል የሞከሩት ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ይሄም “ፀረ ሰላምና የሽብር ኃይሎች የፈለጉትን ዓላማ ማሳካት እንዳይችሉ ከማድረግ ባለፈ አጠቃላይ መረጋጋት በተሻለ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለን በስኬት ገምግመናል'' ብለዋል አቶ ሲራጅ።

ባለፉት ስድስት ወራት በየደረጃው ያሉትን የፀጥታ አካላት የማጥራት፣ የማደራጀትና የማሰልጠን ሥራዎች ጎን ለጎን መከናወናቸውም እንዲሁ ተመልክቷል። በተለይ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሚሊሻና ከፖሊስ ጀምሮ የፀጥታ ኃይሉን የማጥራት፣ የማደራጀት እና የማሰልጠን ስራዎች ተሰርተዋል። ይሄም “ጥሩ ስራ” ተብሎ በኮማንድ ፖስቱ ተገምግሟል።

ኮማንድ ፖስቱ የስድስት ወር ሥራዎቹን በገመገመበት ወቅት በክፍተት የተለዩ ችግሮችንም ለይቶ ለመፍታትና የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ወስኗል። ኮማንድ ፖስቱ ተልዕኮውን በሚወጣበት ወቅት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ሥራዎችን ያለማከናወን ስህተት በተለያየ ደረጃ ላይ ባሉ አካላት ላይ መታየቱ እንደ አንድ ችግር ተለይቷል። አልፎ አልፎ በተለይ በአንዳንድ የፀጥታ አካላት ህጉ ከሚፈቅደው ውጭ አልፎ በመሄድ ህግን ለማስከበር የመሞከር ሁኔታም ማጋጠሙ ተጠቅሷል።

በፀጥታ አካላት ስም የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የሚፈፅሙ የጸጥታ አካላት ያልሆኑ አልፎ አልፎ መከሰታቸውም በችግር ተለይቷል። ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በቂ ክትትል በማድረግ ረገድም ክፍተት እንደነበር በግምገማው እንደ ችግር ታይቷል።

አቶ ሲራጅ እንዳብራሩት፤ በቀጣይ አራት ወራት ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች መታረም የሚችሉበትን አቅጣጫ ኮማንድ ፖስቱ አስቀምጧል። በመጀመሪያ የተቀመጠው አቅጣጫ የፀጥታ ኃይሎች የሥራ ክፍፍል አድርገው ተልዕኳቸውን እንዲፈፅሙ ማድረግ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ተልኳቸውን ሲያከናውኑ የቆዩት በአንድ የኮማንድ ፖስት ውስጥ ሆነው ነው። አሁን ግን የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ባይባልም እየቀነሰ መጥቷል።“የሚሊሻው አካል ሊሰራው የሚችለው ስራ ለሚሊሻው የመስጠት፣ በፖሊስ መሰራት ያለበት ሥራ ለፖሊስ የመስጠት በመከላከያ መሰራት ያለበት ሥራ ደግሞ መከላከያ በተመረጡት ጉዳዮች እንዲሳተፍ በማድረግ ሥራዎችን ተከፋፍሎ ለመስራት አቅጣጫ ተቀምጧል” ብለዋል አቶ ሲራጅ።

በተለይ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት በተመረጡ ቦታዎች ላይ ብቻ እንዲሳተፉ የትኩረት አቅጣጫ ተቀምጧል።  በዚህ የሥራ ክፍፍል መሰረት ከህዝብና ከመስተዳድር አካላት ጋር በመተባበር የተፈጠረው ሁኔታ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ ሥራዎች ለማከናወን አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጀመረው የፀጥታ አካላትን የማጥራት፣ የማሰልጠን፣ የማብቃትና መልሶ የማደራጀት ሥራዎች በተለይ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እስከመጨረሻ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በዋና ዋና የመሰረተ የልማት  አውታሮች እና ኢንቨስትመንቶች፣ በኬላዎች እና የመንግስት ተቋማትን ላይ የሚደረገውን ጥበቃ አጠናክሮ መስራት መሰረታዊ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል።

ከዚህ ቀደም ጥቆማ የቀረበባቸውና በሁከትና ብጥብጡ ላይ ተሳትፈው በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ህዝቡን በማሳተፍ ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራዎች ይሰራሉ። የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ህዝቡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱና በህገ መንግስቱ ላይ ያለውን እምነት እየጠነከረና እየጎለበት እንዲሄድ ለማድረግም በተደራጀ መልኩ ለመስራት አቅጣጫ ተቀምጧል።

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አራት ወራት ሁሉንም ነገር በመደበኛ የህግ ማስከበር አሰራር ማከናወን የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ይሰራል ተብሏል።

በመሰረቱ ኮማንድ ፖስቱ የሁከትና ብጥብጡን መንስኤዎች በዘላቂነት አይፈታም፤ ሃላፊነቱም አይደለም። ኮማንድ ፖስቱ በዋናነት የሁከትና ብጥብጡ መንስኤ ለመፍታት የሚያስችል የተረጋጋና የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ነው። የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ጨምሮ የሁከትና ብጥብጡ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን መፍታት የሚችለው በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ናቸው።

የኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳም “ለሁከትና ብጥብጡ መንስኤ የነበሩ መሰረታዊ ምክንያቶች በየደረጃው ያለው የአስተዳደር አካል ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሊፈታው የሚገባው ሥራ ነው” ያሉት ይህን ሃሳብ ያጠናክራል።

የአስተዳደር አካላት ችግሮችን ለመፍታት በሚያከናውኑት ሥራም ከማንድ ፖስቱ የማገዝ ሚናውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል። ስለዚህ በየደረጃው የሚመለከታቸው የአስተዳደር አካላት በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮች በመለየት፣ መላ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ አጠናክሮ እስከወዲያኛው በማድረስ ችግሮችን መፍታት አለበት። 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን