አርዕስተ ዜና

የኃላፊነት ቅርጫ

15 Apr 2017
3170 times

አየለ ያረጋል -ኢዜአ

ዛሬ ላይ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ነው። በዚህ በሉዓላዊነት ዘመን ላይ ግን ዓለም እንጂ የግለሰቦች አብሮነት ወደ ብዙ ተናጠላዊ መንደሮች የተበታተነ ነው። አስተሳሰቡ፣ ሥነ ልቦናውና አጠቃላይ የህይወት ዑደቱ ከአንድ መንደር ነዋሪዎች መካከል ለብቻው መነጠል።

በርግጥ ውጥንቅጡ በወጣና የተናጠል ኑባሬ (individual culture) በነገሰበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን ያላቸው የአብሮነት ኑባሬ (collectivism culture) እንደተጠበቀ ነው። ለምሳሌ እኔ ባደኩበት ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ሰው ከልደቱ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በማህበረሰቡ ጥላ ስር ነው የሚኖረው። የልደቱ ቀን ከመወለዱ አስቀድሞ መንደርተኛው እናቱን ከብቦ ይሰበሰባል። እናቱ ከተገላገለች በኋላም ገንፎ ተገንፍቶ፤ ጭብጦ ተጨብጦ ጠላም ተጠምቆ ዓለምን ይቀላቀላል። ለአቅመ ስራ ሲደርስም በደቦ ይሰራል። ትዳር ሲመሰርትም ዘመድ ጎረቤት ተጠርቶ በፌስታ ሶስት ጉልቻው ይጎለትለታል። የዓለም “የኪራይ ዘመኑን” ሲያጠናቅቅም አገሬው ተሰብስቦ አዝኖ ተላቅሶ ይሸኘዋል። እንዲህ ነው። እንዲህ ነው የአንድ ግለሰብ የኑሮ ዑደቱ። በማህበረሰቡ መካከል ተወልዶ ከማህበረሰቡ መካከል ያልፋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በማህበራዊ መስተጋብሩ ከእርሱነቱ ጋር ጎልተው የሚወጡ ክዋኔዎች አሉ። ለአብነት ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በርካታ የአብሮነት ማህበረሰባዊ ክንዋኔዎችም ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል ጾሙን ለመፈሰክ  በሬ ገዝቶ  በ“ቅርጫ” ስርዓት መከፋፈል የተለመደ ነው።

ዛሬ ላይ ያለው የቅርጫ ክንዋኔ ምን እንደሚመስልም ፋይዳው ለመዳሰስ ሞከርኩ። በተለይ የተለያየ የህብረተሰብ ስብጥር ባለባት አዲስ አበባ።

ቅርጫ - በአዲስ አበባ

ጋሽ ስንታዬሁ አዳፋ ኮፍያቸውን አድርገው በጥዋት ጸሃይ ይሞቃሉ። ከእኛ ሰፈር "ደመቅ" ያለች ሱቅ ባለቤት ናቸው። ምናልባትም ከሱቁ ውጭ ያሉ ሸራ መሰል ነገሮችን ይሸጣሉ እንጂ፤ ከሱቃቸው ሽያጭ ላይ ብዙም አይደሉ። ሌሎች ወጣቶች ናቸው ሱቅ ውስጥ የሚቀመጡት። ያም ሆነ ይህ ጠዋት ማታ በዚያ ስናልፍ (ወደ ተከራየንበት ግቢ)ና ከሱቃቸው አንዳንድ ነገሮችን ስንሸምት ሠላምታ እንለዋወጣለን። ዛሬ ለዕለቱ ጉዳይ እፈልጋቸዋለሁና ሞቅ ያለ ሠላምታ አቅርቤ ተጠጋኋቸው።

'ጋሽ ስንታየሁ ሠላም ነዎት?' ብዬ እጄን ዘረጋሁላቸው።

"እግዚአብሔር ይመስገን ደህናህን አድርክ? በዚህ ሰሞን ሠላም ይባላል ብለህ ነው?" አሉኝ። ዘወትር ከዘራቸውን ጨብጠው ከሚቀመጡባት ከሱቃቸው ፊት ለፊት ካለችው ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ከጎናቸው ተቀምጨ ወግ ጀመርን።

'ጋሽ ስንቴ የዘንድሮ ቅርጫ ሁኔታ እንዴት ነው?'

"ምንም አይልም ዘንድሮ ትንሽ በሬ ተወደደብን እንጂ" በፈገግታ ነው የመለሱልኝ።

እንደ ጋሽ ስንቴ አባባል ዘንድሮ ለቅርጫ የሚገዛ በሬ ከፍተኛው እስከ 30 ሺ ብር ይደርሳል። በርግጥ እንደየአቅሙ እንጂ ከ14 እስከ 15 ሺ ብር ጀምሮ በሬ ይገኛል። "እኛ ለምሳሌ ትናንትና (ጸሎተ ሃሙስ ዕለት) ወደ ሱልልታ ሰው ልከን በ30 ሺ ብር ነው ያስገዛነው" አሉኝ።

'ቆይ ግን ጋሽ ስንቴ የቅርጫ ሥርዓት ምን ይመስላል? ማለቴ አንድ በሬ ለስንት መደብ ነው የሚከፋፈለው? ስንት አባላት ነው ያሉት? የአንድ መደብ ዋጋ ስንት ገባ' የሚለውን ጥያቄ አስከተልኩ።

ያጣመሩትን እግራቸውን እየለያዩ "ብዙ ጊዜ ቅርጫ በአንድ ሰፈር ያሉ ሰዎች ናቸው የሚገቡት። ብዙ ጊዜ ስድስት፣ ስምንት ወይም አስር አባላት ይኖሩታል። በስራቸው ደግሞ ሌላ አባወራ ሊያስገቡ ይችላሉ። ወትሮ ሁሉ ነገር በቅጡ ነበር። የዘንድሮ የቅርጫ ዋጋማ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው። አምና ለምሳሌ የአንድ መደብ ዋጋ እስከ ሁለት ሺ ነበር ዘንድሮ ግን ይሄው በአምስት መቶ ብር ጨምሯል" ጨዋታቸውን ቀጠሉ።

'በበዓል ዕለት ከቅርጫ ወይ ከልኳንዳ የትኛውን መጠቀም ደግ ነው?'

"ቅርጫ የተሻለ ነው እንጂ። ዛሬ ምን ይሁን ምን ይሁን በሚያስጠረጥር ጊዜ ቅርጫን የመሰለ የለም። አንደኛ ዋጋው ውድ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ጨጓራ ነገሮችን ከልኳንዳ አታገኝም። ቅርጫ ደሞ ሰብሰብ ብለህ በደስታ እየተጫወትክ ስለሆነ ጨዋታውስ ቢሆን ማን ይሆነዋል?" ነበር ያሉኝ።

'ጋሽ ስንቴ ስርዓቱ ከእርድ ስነ ስርዓት በኋላ መለያየት ነው? ማለቴ እንዴት ነው የሚበላ የሚጠጣ እንደ ጠላ ወይም አረቄ ነገርስ አለ?'

"እንዴታ! በደንብ ነው እንጂ። ጠላ ግን አዲስ አበባ ያው አታገኝም። አረቄና ቢራ ግን አለ። ምላስ ሰንበርና ለምለም ጉበት ተቋድሰን ነው የምንለያየው። ይሄ ግን አሁን የፋሲካ፣ እርዱ የሚፈፀመው ሌሊት አጠባብ ላይ ስለሆነ ዖም ስለሆነ እህል ውሃውን ሲነጋ ነው የምንቋደሰው..."

ጋሽ ስንቴ የቅርጫ ገንዘብ ሰብሳቢ መሆናቸውንም አጫወቱኝ። እናም ስለ ቅርጫ የተሻለ ልምድ እንዳላቸው ገመትኩኝና ብዙ አወራኋቸው። እንደ ጋሽ ስንቴ አባባል ቅርጫ ብዙ ጊዜ ለገናና ለበዓለ ትንሳኤ ነው የሚከወነው። ከነጋሽ ስንቴ አብዛኛው የቅርጫ አባላት ከቤተሰብ የተወረሰ ነው። ይህ የአብሮነት እሴታቸውና ማህበራዊ ትስስራቸው ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ መሆኑ ነው እንግዲህ። እኔም አመስግኜ ተሰናበትኳቸው።

ቅርጫ በተለይም በከተሞች አካባቢ ካለው የማህበረሰብ የዳራ ታሪክና ባህል፣ ከብዝሃነቱ አኳያ "በቀላሉ ለማከናወን" በሚል በውስጤ ሲመላለስ የነበረ ጥያቄ ነው። አንድ የስራ ባልደረባዬ ተከራይታ በምትኖርበት ግቢ ውስጥ አከራዩ ተከራይዎችን አስተባብሮ ቅርጫ እንዲገቡ እንደሚያደርግ ቀደም ብላ ነግራኝ ነበር። ይህ ነገር እንዴት ይሆን?

አቶ ግርማ አሰፋ በቅርጫ ጉዳይ የተሻለ ልምድ እንዳላቸው ሰማሁ። እኔ ከምሰራበት መስሪያ ቤት የካሜራ ባለሙያ ናቸው። እናም ስለ ነገረ ቅርጫ እባክዎ ያጫውቱኝ ማለቴ አልቀረም። ከሰዎች ጋር ቆመው ስለነበር ‘ይቅርታ አቶ ግርማ! ስለ ቅርጫ ላዋራዎት ፈልጌ ነበር’ አልኳቸው በለሆሳስ መጠየቅ።

“ውይ እርሱም እየጠየቀኝ ነበር” ከፊት ለፊታችን የቆመውን ሾፌር እየጠቆሙ።"ሞልቷል። ቀደም ብለህ ብትነግረኝ ኖሮ…" አቋረጥኳቸው።

'እኔ ቅርጫ ልገባ ሳይሆን ስለቅርጫ መረጃ ለመጠየቅ' መሆኑን ነገርኳቸው። ተሳሳቅንና ወደ ጉዳያችን ገባን።

"አሁን እኔ ለአዲስ አበባ ከተማ እንግዳ ነኝ። ሌሎችም ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ወደ ከተማ የሚፈልሱ ነዋሪዎች ቅርጫ ለመግባት አያስቸግራቸውም?" አልኳቸው።

"ቅርጫ የሚከናወነው'ኮ በቆዩ ጎረቤታሞችና ዘመዳሞች ብቻ አይደለም። ብዙ ጊዜ በአስተባባሪነት ሰርቻለሁ። እኛ ለምሳሌ ከመስሪያ ቤት አምስት አባላት አሉን። አሁን አንተ አዲስ ተከራይ ከሆንክ በተከራየህበት ግቢ ውስጥ የሚከናወን ቅርጫ አለ። እና ቅርጫ በመስሪያ ቤት፣ በንግድ ተቋማት፣ በጉርብትና ቅርበት ነው ብዙውን ጊዜ የሚደረገው" አሉኝ።

'የቅርጫ ማህበራዊ ፋይዳው ምንድን ነው?'

"እንዴ! በዓል'ኮ በዓልነቱ ዋናው ሳቅ ጨዋታው ነው። ባህላዊ ገጽታው ራሱ ለይት ያለ ነው። በቅርጫ ጊዜ እንዳልኩህ ትተዋወቅበታለህ። ከተማ ላይ በሬው የሚታረደው ባለሙያ ተፈልጎ ነው። አራት መቶ ወይም አምስት መቶ ይከፈላል። አባላቱ ግን ቅርጫውን በዓይነት በዓይነት እየመደብክ ቁጭ ብለህ መጨዋወት ነው። በዚያ ሠዓት ከጓዳ እስከ አደባባይ ያሉ ወሬዎች ይወራሉ። እርስ በርስ እየተቀላለዱ መጨዋወቱም እንደዚያው። በጎዳና ላይ ያሉ ወገኖችን ሰብስበን የምንመግብበት ሁኔታም አለ። በቅርጫ ወቅት ብዙ ገጠመኞችም ይከሰታሉ" ሲሉ አቶ ግርማ መለሱ።

'ለምሳሌ ምን ምን ገጠመኞች ያስታውሳሉ?'

"በሬ ሲገዛ ከደላሎች ጋር አለመግባባት ሊከሰት ይችላል። እና አንዳንድ ደላሎች ሰንጋውን ወስፌ ወይም መርፌ ነገር ይወጉታል። ያኔ በሬው ሲይዙት ይጎፋል። እኛንም ይህ ነገር ገጥሞን ያውቃል። ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ በቅርጫ ላይ የሚቀርቡ እንደ ጠጅና አረቄ ነገሮችም አሉ። እና አንዳንዴ የሞቅታ ስሜትም ይኖራል። በዚያው ልክ በስራ ተጠምደህ ከርመህ ለበዓል ስትገናኝ ጨዋታው ይጣፍጥሃል። እና ብዙ ጊዜ ጨዋታችንን ስንል የቤተሰብን ጉዳይ እየረሳን በጣም አርፍደን እንሄዳለን" እየሳቁ።

እርዱ የት እንደሚፈጸምም ጠየኳቸው። ቅርጫው በስራ ባልደረባነት ከሆነ እርዱም በመስሪያ ቤት፤ ካልሆነ ግን በየተራ በአባላቱ ቅጥር ግቢ እንደሚፈፀም አጫወቱኝ። እርዱ ከተፈጸመ በኋላ የራስን መደብ ለማስወሰድ ቤተሰብ ይጠራል። ያኔም ልጆች የመተዋወቅ እድሉን እንደሚያገኙ አቶ ግርማ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ የቅርጫ ሁኔታ በወፍ በረር ቢሆንም ከላይ ተመልክተናል። ከጋሽ ስንቴና ከአቶ ግርማ ምናልባትም እኔ የገጠር ልጅ ስለሆንኩኝ በገጠር አካባቢ ስለሚከናወነው ቅርጫ (በአደኩበት አካባቢ) ጥቂት ልበል። በእኛ ሰፈር ቅርጫ ለበዓላት ብቻ አይደለም። አንድ ሰው አንድ በሬ ወይም ላም በገደል፤ በዋጅማ በሌላም እክል ከተጎዱና የመትረፍ እድል የላቸውም ተብሎ ከታመነ እርድ ይከናወንና የአካባቢው ማህበረሰብ ስጋውን በመደብ ይካፈለዋል። እያንዳንዱ አባወራ/እማወራ ማህበረሰባዊ ግዴታ ስላለበት ባይፈልግም ይቃረጠዋል። ምናልባት በቀጥታ (ገንዘብ) አይከፍልም። አዝመራው ሲደርስለት 'ገበያ ውዬ እመልሳለሁ' ብሎ ድርሻውን ይወስዳል። ይህ በዋናነት ለስጋው ተብሎ ሳይሆን ከብቱ ቢጎዳበት ኪሳራ የሚገባውን ግለሰብ ለመደገፍ የሚደረግ ነው።

ከዚህ ባለፈ በገና፣ በመስቀል (ክብከባ ይባላል)፣ በትንሳኤና በመሳሰሉ በዓላት ቅርጫ የግድ ነው። በጉርብትና፣ በእድር አልያም በማህበራት ተሰባስቦ። በግ ወይም ፍየል ገዝቶ ለብቻው በዓሉን ለመዋል ያልቻለ ሰው ቅርጫ ገብቶ በዓሉን በደስታ ያሳልፋል። እኔ እንኳን የእኛን ድርሻ 'የቅርጫ መደብ' ለማምጣት እሄድ ስለነበር ለበዓላት ወቅት ከሚናፍቁኝ ትዕይንቶች ልጆች ተሰባስበን የምናደርገው ጨዋታ ነው። የአካባቢው አባቶች የሚያደርጉት ለዛ ያለው ባህላዊ ጨዋታ ነው። ቅርጫ የፋሲካ ሌሊት ላይ ስለሚከናወን ብዙም ባይሆንም ለገና በዓል ግን ቅርጫ ትልቅ ማህበረሰባዊ ትርጉም አለው። በሰፈሩ በተለያዩ ምክንያቶች የተቀያየሙ ግለሰቦች ካሉ ለዚህ ቀን ሲባል ሽማግሌ ተፈልጎ ይታረቃሉ። ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ የቅርጫ ተሳታፊ እንዲሆንም እንደየአቅሙ እንዲደራጅ እድሎች ይመቻችለታል። ዛሬም በዚህ መልኩ የቀጠለ ይመስለኛል።

እንግዲህ ከሁለቱ የመረጃ ምንጮቸ መገንዘብ እንደሚቻለው ቅርጫ የማይናቅ ማህበረሰባዊ ትውውቅን የመፍጠር እድሉ ሰፊ ነው። በቅርጫ የተጀመረ ግንኙነት ወደ እቁብና ማህበር መሰል የኅብረት ትስስሮች እንደሚያድግም ከጋሽ ስንቴም ሆነ ከአቶ ግርማ ንግግር ተገንዝቤያለሁ። በጥቅሉ ቅርጫ ያለው ባህላዊ የአብሮነትና የመተጋገዝ እሴትነቱ የጎላ ነው። ነገር ግን የሰንጋውን ጤንነት ከማስመርመርና ጤናማ የእርድ ሁኔታ ከማከናወን አኳያ ሊሰራ እንደሚገባ አምናለሁ። ቅርጫ ከጊዜ ጊዜ ያለው ሉዓላዊነት የህብረተሰቡ ባህል በምዕራባዊያኑ ባህል መፈተኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ ያላቸውን የአብሮነትና የመረዳዳት ኑባሬ መሸርሸሩና ወደ ተናጠላዊ አኗኗር መምራቱ አይቀርም። ከጊዜ ጊዜ የአጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ለእንደዚህ ዓይነት ጠቃሚ ባህሎች መዳከም የራሱን አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድርም አስባለሁ።

አዋጁም ያትታል። ከ17 ዓመታት በፊት የወጣው የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ። አዋጅ ቁጥር 209/92 አንቀጽ 3 ነጥብ 5 ላይ ስለ እነርሱ ያወራል። የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች (Intangible Heritages) በዓይን ሊታዩና በጆሮ ሊሰሙ ቢችሉም ግን አይዳሰሱም፣ አይጨበጡም፣ አይነኩም። ለአብነትም ማህበራዊ ክንዋኔዎች፣ ሥነ-ስርዓቶችና ፌስቲቫሎች ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ማህበራዊ ክንዋኔዎች መካከል ክብረ በዓላት፣ ሠርግና ሞት ጋር የተያያዙ ሥነ-ስርዓቶች ባህላዊ የዳኝነትና የዕርቅ ስርዓቶች፣ ደቦና ዕድር የመሳሰሉ ነባር የሕብረት ሥራ ባህሎችና መረዳጃዎች ወግና ልማዶችን ይጠቅሳል።

ከማንነት ስሜት ጋር ያለመጻረር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ከሰው ልጅ ፈጠራ ክብር ጋር፣ ከህዝቦች የእርስ በርስ ባህል ጋር የማይቃረኑ ከሆኑ እንደ ማይዳሰሱ ቅርሶች እንደሚቆጠሩም በዩኔስኮ የተቀመጡ ‘የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ኮንቬንሽን” መስፈርቶች ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ የድርጅቱን  የጠቅላላ ጉባኤ ስምምነት አሜን ብላ ተቀብላለች። እንደ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አካባቢያዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ነባራዊ ሁኔታ ቢለያይም በበዓል ወቅት ኢትዮጵያዊያንን አንድ የሚያደርጓቸው ባህላዊ ክዋኔዎች ሞልተዋል። ለአብነትም ከላይ የተመለከትነው የቅርጫ ስርዓት።

በኑሯችን ውስጥ የሚገጥሙንን የክፉ ቀናትም ሆነ የደስታ ጊዜያት በጋራ "እየተቃረጥን" ስናሳልፋቸው በባህላዊና በማህበራዊ ልማት ረገድ ብዙ እናተርፋልን። ካተረፍን ደግሞ ጸጸት የለብንም። ትርፋችንን እያጠነከርን እንጂ ኪሳራ አያጋጥመንም። 'ብሔራዊ መግባባትስ ከሰፈር  ይጀምራል' የሚል አባባል ቢተረትስ? ሕብረተሰቡ ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቆ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የራሱ ፈንታ ነው። ጎልተው የወጡትን ማህበራዊ ክዋኔዎቻችንን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን ለአብሮነታችን ምሰሶ የሆኑ ባህላዊ እሴቶቻችንን በስነ ልቦናችን ማተም ያሻናል እላለሁ። ለእያንዳንዱ የማህበረሰብ ባህላዊ እሴቶችና የአብሮነት መገለጫዎች የሆኑ የማይዳሰሱ ቅርሶችን መጠበቅ “የኃላፊነት ቅርጫ” አለብን።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን