አርዕስተ ዜና

የአይጥና ድመት ጨዋታ

15 Apr 2017
2419 times

መስፍን አራጌ- ኢዜአ

ከሰሞኑ እኔ በምኖርበት ደሴ አካባቢየደረሰው ሁኔታ የመነጋገሪያ ርዕስነቱ ሳምንታት አልፈው እንኳ አልቀዘቀዘም፡፡ ከከንፈር መጣጩ  የባስ አታምጣ እስከሚለው ሁሉም ጉዳዩን ከአፉ አላወጣውም ።

ሰላማዊት አንዳርጌ (እውነተኛ ስሟን ለማኅበራዊ ደህንነቷ ስንል ቀይረነዋል) የ29 ዓመት ወጣት ነጋዴ ናት፡፡ ኑሮዋን በደሴ 011 ቀበሌ ያደረገች፡፡

ጥር19/2009 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤልን ወርሃዊ በዓል በጧት ተነስታ መሳለም ባለመቻሏ ወደ ቅጽር ግቢው ያመራችው ፀሃይ መጥለቂያዋ አካባቢ ነበር፡፡ ግቢውን ጸጥታ ወርሶታል፡፡ በጸጥታው ውስጥ ለአምላኳ መልእክቷን ታደርሳለች፡፡ በተመስጦ ጸሎት ስታደርስ የነበረችው ሰላማዊት ግቢው ውስጥ ቀይ ቀለም ያላት የቤት መኪና መግባቷን ያወቀችው ዘግይታ ነበር፡፡

ድንገት አንድ የወንድ ድምጽ ፀጥታውን አደፈረሰው ፡፡ የመኪናው ሾፌር ነው፡፡

"እንዴት ዋላችሁ?"አለ ሰውዬው በትህትና፡፡

ሰላማዊት ሰውዬውን ባታውቀውም የእግዚአብሔር ቤት ሆና የእግዜሩን ሰላምታ አልነፈገችውም "እግዚአብሔር ይመስገን" አለች፡፡

ሰውየው ከጎኗ ለመቀመጥ ፈቃዷን አልጠየቀም ቤተክርስቲያን አይደል፡፡ ቁጭ እያለ ጥያቄ ቢጤ ወረወረ፡፡"ይሄ ቤተክርስቲያን ማን ይባላል?"

"ለአካባቢው እንግዳ ነህ?"

"አዎ ከአዲስ አበባ ነው የመጣሁት፡፡" አለ ሰውዬው ተረጋግቶ፡፡

"ቅዱሥ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡"

ጥያቄና መልሱ መለስተኛ መግባባት ፈጠረ፡፡ ስም ለስም ተዋወቁ፡፡ ሰላማዊት አለችው፡፡ አክሊሉ አላት- አክሊሉ ግሩም፡፡

አክሊሉ መኪና መያዙን ገልጾ ለመሸኘት ቢጠይቃትም ጥያቄውን አልተቀበለችውም፡፡ በእግሯ መሄድን እንደምትመርጥ ነገረችው፡፡ ተስፋ አልቆረጠም፡፡

"እሽ ስልክ ቁጥርሽን ስጭኝ" አላት፡፡ ሰጠችው፡፡

በዚህ መልክ የተጀመረው ትውውቅ በስልክ ልውውጥ ተጠናከረ፡፡ ይደውልላታል ። ብዙ ነገር ያጫውታታል፡፡

አክሊሉ በትዳር ተሳስሮ በአንድ ታዛ ስር መኖር እንደሚፈልግ ነገራት፡፡ የአወንታም የአሉታም ምላሽ አልሰጠችውም፡፡ እሱ ግን ጥያቄውን አላቋረጠም፡፡ ጓደኛዋ እንድታማልደው ለመነ፡፡ ወንድሞቿን ወተወተ፡፡ ቤተሰቦቸዋን ተማጸነ፡፡ ለትዳር የተጠማ መሆኑን የ49 ዓመቱ አክሊሉ በተሰበረ አንደበት ገለጸ፡፡ በመጨረሻም ጥያቄው ተቀባይነት አገኘ፡፡

በከተማው የተከበሩ የኃይማኖት አባቶችን ሽምግልና ላከ፡፡ ሽማግሌዎቹም የደስደሱን አበሰሩት፡፡ ጋብቻው የካቲት 11/2009ዓ.ም እንዲሆን ቀን ተቆረጠ፡፡

ጋብቻው ታላላቅ ሽማግሌዎች፤ የኃይማኖት አባቶችና እንግዶች ባሉበት ተካሄደ፡፡ አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤትና ንብረት እንዳለው የሚናገረው አክሊሉ ከሁለት ግራም የጣት ወርቅ ውጭ ሌላ መስጠት አልቻለም፡፡ ሃብቴና ንብረቴ ባለበት አዲስ አበባ ፈታ ያለ ድግስ እደግሳለሁ ሲል ቃል ገባ፡፡

በሰርጉ እለት ዶፍ ዝናብ ይጥል ነበር፡፡ አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ድንገት አንዳች ነገር ያሳሰበው ሙሽራው አክሊሉ ወደ ሙሽሪት ሰላማዊት ጠጋ ብሎ የሆነ ነገር ሹክ አላት፡፡

"ወደ ባንክ መሄድ ነበረብኝ፡፡ በዚህ ዶፍ ዝናብ መሄድ ግን አልችልም፡፡ ሰዎች ደግሞ እየደወሉልኝ ነው፡፡ አስር ሽህ ብር ካለሽ ባክሽ ስጭኝ" አላት፡፡ ሰላማዊት አላመነታችም፤ የትዳር አጋሯ ግማሽ አካሏ ለመሆን የህይወት ጉዞ ጀምሮ የለ፡፡ ሰዎቹ ለምን እንደሚደውሉለት አታውቅም፡፡ ገንዘቡን ለምን እንደሚፈልገውም አልጠየቀችውም፡፡ የጠየቃትን ብቻ ሰጠችው፡፡

አክሊሉ ገንዘቡን ተቀብሎ አመሻሽቶ ተመለሰ፡፡ በሰርጉ ጊዜ አምሽቶ ቢመለስም በሙሽራ ወግ ተስተናገደ፡፡

ጧት አራት ሰዓት ገደማ ሙሽራው አክሊሉ ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡፡ የሚሄድበት ጉዳይ እንዳለው ነገራት፡፡ እሱን ያህል ሰው ግን አንገቱ ላይ ሃብል ሳያስር ጣቱ ላይ ቀለበት ሳያጠልቅ ሌጣውን ቢሄድ እንደማይመጥነው አስረዳት፡፡ እናም ወርቋን እንድታወሰው ጠየቃት፡፡ ሰላማዊት 16 ግራም የሚመዝን  የአንገትና ሀብልና የጣት ቀለበቷን ሰጠችው፡፡

አክሊሉ አነስተኛ ሻንጣውን አንጠልጥሎ በሰርጋቸው እለት የተለገሳትን ስጦታዎችና አምስት ብልኮ ሰብስቦ መጠቅጠቅ ጀመረ፡፡ ሁኔታው ያላማራት ሰላማዊት በድንጋጤ ታስተውለዋለች፡፡ ደርሶ የሚመጣበት ቦታ እንዳለ ነግሯት ከቤት ወጣ፡፡

እመጣለሁ ብሎ የወጣው አክሊሉ ደብዛው ጠፋ፡፡ የት እንዳለ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ ስልክ መደወሉን ግን አላቋረጠም፡፡ አስቸኳይ ስራ ስላጋጠመው መምጣት አለመቻሉን ይነግራታል፡፡

የካቲት 12 በጋብቻው ማግስት ከቤት የወጣው አክሊሉ የውሃ ሽታ እንደሆነ መጋቢት ደረሰ፡፡

መጋቢት 5/2009ዓ.ም ደሴ ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጉዳይ የነበራት ሰላማዊት ጉዳይዋን ጨርሳ ስትመለስ ፒያሳ አካባቢ አንድ መኪና አየች፡፡ ዓይኗን አላመነችም፡፡ ለአንድ ቀን አብሯት ያደረው ባለቤቷ የአክሊሉ መኪና ናት፡፡ አንዲት ትራፊክ የመኪናዋን ታርጋ እየፈታች ነው፡፡ የሆነች ሴት ደግሞ ሁኔታውን በሞባይሏ ትቀርጻለች፡፡ አንዳች ነገር እንዳለ ውስጧ ነገራት፡፡

ሰላማዊት ሞባይል ወደምትቀርጸው ሴት ጠጋ ብላ "አንችም እንደኔ ተዘርፈሽ ይሆን?" አለቻት፡፡

"አዎ የተዘረፍኩ ነኝ" አለች በእልህ ራሷን በመነቅነቅ፡፡

ሰላማዊት የአክሊሉ መኪና ሰው በመግጨቷ ባለችበት እንድትቆም መደረጓን አወቀች፡፡ ስልኳን አውጥታ ወደ አክሊሉ ደወለች፡፡ የውስጧን በውስጧ ይዛ አናገረችው፡፡ ተረጋግቶ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰብ እንዲያሳክም ከነገረችው በኋላ እዚያው እንደምትጠብቀው ነገረችው፡፡ አክሊሉ መኪናው የቆመችበት ቦታ ሲመለስ ተዘርፈናል የሚሉ ሁለት ሴቶች ብቻ አልነበረም የጠበቁት ፖሊስ ጭምር እንጅ፡፡

የአክሊሉን መኪና በሞባይል ስትቀርጽ የነበረችውና ተዘርፊያለሁ ስትል የነበረችው ሴትስ ማን ናት?

የ38 ዓመቷ ምህረት ሲሳይ (እውነተኛ ስሟን ለማኅበራዊ ደህንነቷ ስንል ቀይረነዋል) በደሴ ከተማ በቀበሌ 10 የምትኖር የመንግሥት ሰራተኛ ናት፡፡ የካቲት 10 የመብራት ወርሃዊ ክፍያ ለመክፈል በጉዞ ላይ ሳለች ኪዳነምህረት አካባቢ አንድ መኪና ውስጥ የተቀመጠ ሰው በምልክት ይጠራታል፡፡ ወደ ጠራት ሰው ሄደች፡፡

"ለአገሩ እንግዳ ነኝ፡፡ ባክሽን እዚህ አካባቢ የኮምፒውተር ታይፕ የሚያደርጉ ወይም ፎቶ ኮፒ አገልግሎት የሚሰጡ ካሉ ብታሳይኝ" አላት፡፡

ሳታመነታ አሳየችው፡፡ ሰውየው ግን በቀላሉ የሚላቀቃት አልሆነም፡፡ ወደ ምትሄድበት ሊሸኛት እንደሚችል ጠየቃት፡፡ አልተቀበለችውም፡፡  ቅርብ ስለሆነ መሸኘት እንደማያስፈልጋት ነገረችው፡፡ በክርስትና እምነት ቅዱሳን የተባሉትን ሁሉ በስማቸው እየጠራ ተማጸናት፡፡ ምህረት ልመናውን መቃወም አልቻለችም፡፡ "ጻድቃኑን ረግጨ የምሄድ ያህል ተሰማኝ" የምትለው ምህረት መኪናው ውስጥ ገባች፡፡

አክሊሉ እንደሚባል ነገራት፡፡ በትዳር የተጎዳ፣ በብቸኝነት የተሰቃዬ መሆኑን አንጀት በሚበላ ትካዜ ገለጸላት፡፡ ለእምነቷ የምታድር እንደ እሷ ዓይነት ሴት እንደሚፈልግ ጠቆማት፡፡

"ፈጣሪ ልመናየን ሰምቶ አንችን የመሰለ የእምነት ሰው ሰጥቶኛል፡፡ ባክሽን እንጋባ" አላት አክሊሉ፡፡

"እንዴት ትዳርን ያህል ተቋም በጥድፊያ እንገነባለን፡፡ ባይሆን ፈጣሪ እንዲያሳካው በጸሎት እንለምን" ስትል ምላሽ ሰጠችው፡፡ እስከ ምጽአት ሊጠብቃት ዝግጁ መሆኑን አረጋገጠላት፡፡

አክሊሉ ምህረት ወደምትሰራበት ቢሮ ካደረሳት በኋላ በስራ መውጫ ሰዓት እንደሚመለስ ነግሯት ተሰናበታት፡፡ አክሊሉ እንዳለው አስር ሰዓት ገደማ ምህረት ወደምትሰራበት ቢሮ መጣ፡፡ ከስራ ሰዓት ስትወጣ ያልጠበቀችውን ስጦታ አበረከተላት - የአንገት ሃብልና የጣት ቀለበት፡፡  ምህረት ግን አልተቀበለችውም፡፡ የእሷ ሃቅ አለመሆኑን ገልጻ መለሰችለት፡፡ የትዳር ጥያቄውን ከማቅረብ ያልተቆጠበው አክሊሉ ያለውን የሃብት መጠን በመዘርዘር ለማማለል ሞከረ፡፡

"አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ 480 ሄክታር ላይ የተንጣለለ ቪላ ቤት ከነሰርቪሱ፣ ሲኖ ትራክና ገልባጭ መኪና አለኝ፡፡" አላት፡፡

የምህረትን ልብ ለማሸነፍ አክሊሉ ወደ ስራ ቦታዋ በመምጣት አገኛት፤ ጓደኞቿንም ጋበዘ፡፡

በተዋወቁ በማግስቱ ሻይ ቡና ካሉ በኋላ እንደዘበት የባንክ አካውንት እንዳላትና እንደሌላት ጠየቃት፡፡ የጥያቄው ዓላማ ባይገባትም በቅንነት መለሰችለት፡፡

"ውጭ አገር የምትኖር እህቴ በስሜ ካስቀመጠችው 57 ሺህ ብር ውጭ የኔ የምለው የባንክ ሂሳብ የለኝም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ የምተዳደር የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፡፡" አለችው፡፡ ለአክሊሉ ይሄ በቂ ነበር፡፡ የባንክ ቡኩን እንድታሳየው ጠየቃት፡፡

ከሁለት ቀናት በኋላ ተገናኝተው ምሳ ተገባበዙ፡፡ ምህረት የጊዜ ጉዳይ እንጅ አንድ ቀን እንደምታገባው አምናለች፡፡ አክሊሉ ደግሞ ይሄንን ተረድቷል፡፡ 

ግብዣው ሲጠናቀቅ በአክሊሉ ጥያቄ መሰረት የባንክ ደብተሯን አሳየችው፡፡ አክሊሉ ደብተሩን በአጽንኦት ከመረመረ በኋላ "ደብተርሽ ወጭ ገቢ እንዳለው ታውቂያለሽ? ወጭ አድርገሽ ነበር?" አላት፡፡

"ለእህቴ ቦታ ለመግዛት ለወንድሜ የተወሰነ ገንዘብ አውጥቼ ሰጥቼው ስለነበር ነው" ስትል መለሰች፡፡

አክሊሉ የራሱን ሁለት የባንክ ደብተሮቹን አውጥቶ አሳያት፤ አንዱ የንግድ ባንክ ሌላው የዳሸን ባንክ ነው፡፡ በደብተሮቹ ላይ ያለውን የገንዘብ መጠን ግን አላየችውም፡፡ የማየትም ፍላጎት አልነበራትም፡፡ ከሁለት የባንክ ደብተሮቹ ለስራ የሚያስፈልገውን አስቀርቶ ቀሪውን ገንዘቡን በእሷ ስም ከተቀመጠውን 57ሺህ ብር ጋር በመቀላቀል የጋራ አካውንት መክፈት እንዳለባቸው አሳሰባት፡፡ ማሳሰቢያው አሳብ የሆነባት ምህረት "ገንዘቡ የእህቴ እንዴት ሆኖ በጋራ አካውንት መክፈት እንችላለን?" ስትል ጭንቀቷን ገለጸች፡፡

"ምን መሆንሽ ነው ፍቅሬ እንኳንስ ገንዘባችን እኛ አንድ አካል አንድ አምሳል ልንሆን አይደል እንዴ?"

ምህረት በፍጹም ልቧ አመነችው፡፡ ዳሸን ባንክ በስሟ የተቀመጠውን 57ሽህ ብር አውጥታ ቆጥራ ሰጠችው፡፡ አካውንቱን በጋራ ለመክፈት መታወቂያ ስለሚያስፈልግ መታወቂያዋን እንድትስጠው ጠየቃት እሱንም አስረከበችው፡፡

የምህረት ስጋት ወንድሟ የእህቷን ቤት እያሰራ ስለሆነ ድንገት ገንዘብ ቢያጥረው እንዴት ይሆናል የሚል ነው፡፡ አክሊሉ ደግሞ ለዚህ ጥሩ ምላሽ አዘጋጅቷል፡፡ ብሩን በፈለገው ሰዓት ለወንድሟ እንደሚሰጡት አረጋገጠላት፡፡ ምህረት ስጋትም ፍርሃትም እየናጣት ይቅርብኝ አለች፡፡ በመሃላ ሊያረጋጋት ሞከረ፡፡

በየሰዓቱ ካላገኘሁሽ እያለ ፋታ ይነሳት የነበረው አክሊሉ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ደብዛው ጠፋ፡፡ ወትሮም ጥርጣሬ ውስጧን ሲያነጥረው የነበረው ምህረት ሰማይ ምድሩ ዞረባት፡፡ ደጋግማ ብትደውልለትም ስልኩ ጥሪ መቀበል አልቻለም፡፡

እምባና ጭንቀት፣ ፀፀትና ብስጭት እያብሰለሰሏት ሳለ መጋቢት አምስት የምትሰራበት ቢሮ አካባቢ ፒያሳ ላይ የአክሊሉን መኪና ታያታለች፡፡ ጊዜ አላጠፋችም፡፡ ቦርሳዋን ቢሮዋ ወርውራ ወደ ቆመችው መኪና ተንደርድራ ሄደች፡፡ አክሊሉ የለም፡፡ ባይኖርም ግድ አልሰጣትም፡፡ እንኳንም መኪናውን ያገኘቻት፡፡ ቢያንስ መኪናን ያህል ነገር ጥሎ አይሰወርም፡፡

ሞባይሏን አውጥታ መኪናዋን መቅረጽ ጀመረች፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር ከሰላማዊት አንዳርጌ ጋር የተገናኙት፡፡

አክሊሉ ወደ መኪናው ሲመለስ ምህረትና ሰላማዊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውል አደረጉ፡፡ በአቅራቢያቸው ወዳለውም አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ተያይዘው አመሩ፡፡ ጉዳያቸውን ዘርዝረው አስረዱ፡፡ በዚህ መሃል ነበር ተጠርጣሪ ወደ ጊዜያዊ ማረፊያ ሲላክ ከኪሱ  የወጣ የአንዲት ሴት ፎቶና መታወቂያ የተመለከቱት፡፡ ሁለቱም ከሳሾች በመታወቂያ ላይ ያለችውን ሴት ያውቋታል፡፡ ምናልባትም የእነሱ እጣፈንታ የደረሰባት እንደሆነችስ ማን ያውቃል?... እውነቱን ለማረጋገጥ ባለመታወቂያዋ ጋር ስልክ ተደወለ፡፡

"ሃሎ" አለች ስልክ የተደወለላት ሴት

"እንግዳወርቅ ማስረሻ  ነሽ?" አለ ከወዲያኛው መስመር የሚሰማው ድምጽ፡፡ (እውነተኛ ስሟን ለማኅበራዊ ደህንነቷ ስንል ቀይረነዋል)

"አዎ ነኝ"

"አክሊሉ ግሩም የሚባል ሰው ታወቂያለሽ?" ተጠየቀች፡፡

አክሊሉ ግሩምን ታውቀዋለች እንጂ ፡፡ የእንግዳወርቅ ልብ ደረቷን ጥሶ ይወጣ ይመስል በድንጋጤ ይመታል፡፡ አዎ በእርግጥም አክሊሉን ታውቀዋለች፡፡ ያ ጊዜ እንዴት ይረሳል?!

በመንግሥት ስራ የምትደዳረው የ55 ዓመቷ እንግዳወርቅ ጎንደር በር አካባቢ ታክሲ እየጠበቀች ነበር፡፡ ቀኑ ደግሞ የካቲት 27/2009ዓ.ም፡፡

ታክሲዎች ከመነሻቸው ተሳፋሪ እየሞሉ ስለሚመጡ  መንገድ ዳር ላይ የትራስፖርት አገልግሎት ማግኘት ይከብዳል፡፡ በርካታ ታክሲ ጠባቂ የአስፋልቱን ዳር ይዞ ተደርድሯል፡፡

ድንገት አንዲት የቤት መኪና ቆመችና ሾፌሩ እንግዳወርቅን እንድትገባ ምልክት ሰጣት፡፡ በታክሲ እጥረት የተጉላላቸውና በድካም የዛለችው እንግዳወርቅ ትብብሩን አመስግና መኪናው ውስጥ ገባች፡፡ በጉዞው መሃል የሆድ የሆዳቸውን ተጨዋወቱ ከአክሊሉ ጋር፡፡ ነዋሪነቱ አዲስ አበባ መሆኑንና ቱርቦ የጭነት መኪናው ሃይቅ አካባቢ ተገልብጦበት እሱን ለማስነሳት መምጣቱን ነገራት፡፡ እንግዳወርቅ ለአገሩ እንግዳ ሆኖ ላደረገላት ትብብር አመስገነችው፡፡ እንግዳ ነውና ቤቷ ሻይ ቡና እንዲል ጋበዘችው፡፡ አላንገራገረም - ግብዣውን ተቀበለ፡፡

ቤተቦሰቿ የክብር እንግዳቸውን በአክብሮት ለማስተናገድ ሽርጉድ አሉ፡፡ መብራት ባለመኖሩ ከሰል ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የተመለከተው አክሊሉ "መኪናዬ ላይ ከሰል ስላለ ኋላ አመጣልሻለሁ" አላት፡፡ እንግዳወርቅ ውለታው በዛባት፡፡ መልካምነቱ ከበዳት፡፡

ቤት ያፈራውን ቀማምሶ የተደረገለትን መስተንግዶ አመስግኖ ከቤት ሲወጣ የሞባይል ቁጥሯን ተቀበለ፡፡

ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ የእንግዳወርቅ ስልክ ጥሪ አሰማ፡፡ አንስታ አነጋገረች - አክሊሉ ነበር፡፡ የት እንደሆነች ጠየቃት፡፡ ወደ ቤት ለመግባት መንገድ ላይ መሆኗን ነገረችው፡፡ ከሰሉን ይዞ እየመጣ መሆኑን ጠቁሞ "ጠብቂኝ" አላት፡፡ ጠበቀችው፡፡ ስጦታውንም ይዘው ወደ ቤት ገቡ፡፡ የእንግዳወርቅ እናት በአንድ ቀን ትውውቅ ይሄን ያህል ቸርነት ላሳያቸው እንግዳ ምስጋናቸውን አቀረቡ፡፡

አክሊሉ አንዳንድ ግለሰባዊ ጥያቄዎችን ጠየቃት፡፡ እንግዳወርቅ በምትችለው መጠን መለሰችለት፡፡ እምነትሽ ምንድን ነው አላት፡፡ ፕሮቴስታንት መሆኗን ነገረችው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ የጠበቀ ቅርርብ መፍጠር የቻለው አክሊሉ ወደ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንዲሄዱ ለእንግዳወርቅ ጥያቄ አቀረበ፡፡ በእምነቷ ፕሮቴስታንት ብትሆንም እንግዳወርቅ ጥያቄውን ለመግፋት አልደፈረችም፡፡ አብራው ሄደች፡፡ በጉዟቸው ላይ ስለ ግል ህይወቱ አንድ ሁለት አላት፡፡

"እኔ በሚስት የተጎዳሁ ሰው ነኝ፡፡ 250ሺህ ብርና አንድ ሚኒባስ ለሚስቴ ሰጥቼ ተፋትቻለሁ፡፡ አሁን በሃዘን የተጎዳውን ጎኔን የምትጠግንልኝ ሴት እፈልጋለሁ፡፡ ያች ሴት ደግሞ አንች ነሽ፡፡ ታገቢኛለሽ?"አላት፡፡

ጥያቄው ዱብዳ ቢሆንባትም ተረጋግታ ለመመለስ አልተቸገረችም፡፡ "ትዳር ጥሩ ነበር ግን እንዴት ሁለት የተለያዬ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች በአንድ ጣራ ሊኖሩ ይችላሉ? አይከብድም?" ስትል መለሰችለት፡፡

"ምንም የሚከብድ ነገር የለውም፡፡ ከፈለግሽ እኔ ሃይማኖቴን እቀይራለሁ፡፡ የምፈልገው ትዳር ብቻ ነው" ሲል ወተወተ፡፡

የእንግዳወርቅን ልብ በተወሰነ ደረጃ ማሸነፍ የቻለው አክሊሉ የተገለበጠብኝን መኪና ተሳቢ ላሳይሽ በማለት ወደ አንድ ጋራዥ ወስዶ የሆነ ተሳቢ አሳያት፡፡  አመነችው፡፡

ከጋራዥ መልስ የእንግዳወርቅን እጅ በእጆቹ አጥብቆ ያዘ፡፡ እንግዳወርቅ ምንም አላለችም፡፡ በጣቷ ላይ ያለውን የወርቅ ቀለበት አውጥቶ እሱ ጣት ላይ አደረገው፡፡ እንግዳወርቅ ድርጊቱን እንደ መድረክ ተውኔት በትኩረት ትከታተላለች፡፡ ከዚያም የእሱን ቀለበት አውጥቶ እሷ ጣቶች ላይ ሰካው፡፡ አንገቱ ላይ ያለውንም ሃብል አውጥቶ በስጦታ ዘረጋላት፡፡

በማግስቱም ተቀጣጥረው ተገናኙ፡፡ አሁንም የጋብቻ ጥያቄውን አቀረበላት፡፡

"በሃብት ደረጃ ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ እኔ ካንች የምፈልገው 70 በ30 ነው"አላት

"እንዴት?" ጠየቀች እንግዳወርቅ፡፡

"ሰባ በመቶ እንደ እናት የት ገባህ የት ወጣህ ብላ የምትቆረቆርልኝ ሰላሳ በመቶ እንደ ሚስት አካሌ ብላ የምታስብልኝን ሴት ነው የምፈልገው፡፡ እኔ ባለኝ ሃብት የተንደላቀቀ ኑሮ መምራት እንችላለን፡፡ አንች ጋር ስንት ብር ይኖራል?"ሲል እንደዘበት ጥያቄውን

ወረወረ፡፡

"አንድ ሰላሳ ሺህ ብር አላጣም" አለች በለሆሳስ እሱ አለኝ ካለው ብር ጋር ስታነጻጽረው የእሷ መጠኑ አንሶባት፡፡አክሊሉ በፍጥነት የጋራ አካውንት መክፈት እንዳለባቸው አሳሰባት፡፡ እናም መታወቂያና ፎቶዋን እንድትሰጠው አግባባት፡፡

የእሷ ሚስትነት የእሱ ባልነት የሚረጋገጠው የጋራ ሃብታችው መገለጫ የሆነ የጋራ አካውንት ሲከፍቱ እንደሆነ አስረዳት፡፡

እንግዳወርቅ ቆም ብላ ለማሰብ እንኳን ፋታ አላገኘችም፡፡ መታወቂያና ሁለት ጉርድ ፎቶ ግራፍ ከቤቷ አፈላለጋ ሰጠችው፡፡

10 ሺህ ብር ከብርሃን ባንክ 20 ሽህ 900 ብር ደግሞ ከንግድ ባንክ አውጥታ ታስረክበዋለች፡፡ የጋራ ሃብት በጋራ አካውንት ሊከፈት ያለ የሌለ ጥሪት ተሟጥጦ ተሰጠው፡፡

አክሊሉ ታማኝነቱንና ለእንግዳወርቅ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ግማሽ ኩንታል ጤፍ ገዝቶ ለቤተሰቡ አስረከበ፡፡ አንድ ጆንያ ከሰል ለእህቷ በመለገስ  በልቧ ውስጥ ማህተሙን አሳረፈ፡፡

በጋራ አካውንት እንከፍታለን ብሎ 30 ሺህ 900 ብር ከወስደ በኋላ መታወቂያና ፎቶ ሰብስቦ ፎርም መሙላቱን ነገራት፡፡

"እኔ በሌለሁበት የጣምራ ፊርማ እንዴት ሊፈረም ይችላል?" የሚል ጥያቄ አነሳችለት፡፡

ችግር እንደሌለው በመግለጽ ጥያቄዋን ያጣጣለው አክሊሉ ብሩ እንዳይባክን በእሱ አካውንት ውስጥ እንዲገባ ማድረጉንና ነገሮች ሲመቻቹ የጋራ አካውንቱን ባንክ ድረስ በመሄድ እንደሚከፍቱ ያብራራላታል፡፡ ውስጧ  ቢጠረጥርም ማመኗ ሚዛን ደፋና የተናገረውን ተቀበለችው፡፡

ገንዘቡን እጁ ውስጥ ያስገባው አክሊሉ በቀን ሁለትና ሶስቴ የሚያያትን ሴት ዘነጋት፡፡ ዱካው ተሰወረ፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ለስራ ከከተማ ውጭ እንደሆነ በአፍታ የስልክ መልእክት ያስተላልፍላታል፡፡

በዚህ ወቅት ነበር ከአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ተደውሎ አክሊሉ የሚባል ሰው ታውቅ እንደሆነ የተጠየቀችው፡፡ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ስትገሰግስ ሄደች፡፡ ምህረትና ሰላማዊት አዚያው ጠበቋት፡፡

እንግዳወርቅ ከአክሊሉ በስጦታ የተበረከተላትን የአንገት ሃብልና የጣት ወርቅ አውጥታ ለፖሊስ አስረከበች፡፡ በጋብቻዋ ማግስት የአንገትና የጣት ቀለበቷን በአስገራሚ ሁኔታ ተነጥቃ የነበረችው ሰላማዊት  ንብረቷን አገኘች፡፡ የትዳር ፈላጊው አስገራሚ የፈጠራ ድርጊትና የማጭበርበር ጉዞ በአስገራሚ ቅጽበት ተገታ፡፡

ፖሊስ ባደረገው ማጣራትም ግለሰቡ ሁለት መኪኖችን ከአዲስ አበባ በመከራየት ለዚሁ ስራ ሲጠቀምባቸው እንደነበር ደርሶበታል፡፡

አከሊሉ ግሩም የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በ1996 የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ ቁጥር 6921/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በቀረበበት የማታለል ክስ ድርጊቱን መፈጸሙ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋገጠበት፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየውም የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎ ውሳኔ አሳለፈበት፡፡

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 13 በዋለው ችሎት ተከሳሹን ጥፋተኛ በማለት እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የሰባት ዓመት ጽኑ እስራት አሳልፎበታል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን